1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በ100 ዘመን

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2011

እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ1919 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ለማኅበራዊ ፍትሕ እንደታገለ ነው። ዛሬም ድረስ ግን በአፍሪቃ ገና በርካታ የሚሠሩ ተግባራት አሉ። የወጣቶች ሥራ አጥነት እና ፍልሰት ለዓለም አቀፉ ድርጅት አዳዲስ ተግዳሮቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3GVfB
ILO Konferenz in London 1920
ምስል Getty Images/Topical Press Agency

ሐሙስ፤ ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2011 ዓ.ም  ልክ 100ኛ ዓመቱ

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1917 ዓም በሩስያ አብዮት ተቀጣጥሎ መላ ዓለምን ባዳረሰው ንቅናቄ ጥላ ሥር የተመሠረተው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO)  አንድ ክፍለ-ዘመን አስቆጥሯል። ከተመሠረተ ሐሙስ፤ ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2011 ዓ.ም  ልክ 100ኛ ዓመቱ። 

ለሠራተኞች መብት ቅድሚያ ሰጥቶ የተቋቋመው ድርጅት ከአንድ ክፍለ-ዘመን ወዲህ ሠራተኞች በዓለም ዙሪያ ሲጨቆኑ፤ ወጣቶች ሥራ አጥ ኾነው ሲቸገሩ ከገቡበት የሕይወት ውጥንቅጥ ለማውጣት ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል። በተለይ ደግሞ በአፍሪቃ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና ፍልሰት ዋነኛ ተግዳሮት ከኾነ ሰነባብቷል። ፔተር ቫን ሮይጅ የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት የምዕራብ አፍሪቃ ቅርንጫፍ ኃላፊ ናቸው፤ ሐሳባቸው ተመሳሳይ ነው። «አንዱ ትልቁ ተግዳሮት ወጣቶች ሥራ በማግኘቱ ረገድ የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው መጣሩ ነው» ይላሉ።.

የማኅበረሰብ ፍትሕን ለማስጠበቅ የተቋቋመው ዓለም አቀፉ ድርጅት ሥራ ፍለጋ በገፍ የሚፈልሱ ምንዱባን ጉዳይ በራሱ ከማሳሰብ አልፎ ተግዳሮት ኾኖበታል። በኢትዮጵያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2008 እስከ 2013 ባሉት ጥቂት ዓመታት ብቻ 460.000 ዜጎች ወደ ሣዑዲ ዓረቢያ፤ ኲዌት እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መፍለሳቸውን ይጠቅሳል። ከፈላሲያኑ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች ሲኾኑ፤ በየዓረብ ሃገራቱ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሠራሉ። የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት የምዕራብ አፍሪቃ ቅርንጫፍ ኃላፊው፦ «ሌላው ብርቱ ተግዳሮት» ሲሉ ያብራራሉ። «መደበኛ ባልኾነው የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው በዝቅተኛ ገቢ ሕይወታቸውን ለመቀየር የሚታትሩ ሰዎችን መርዳቱ ነው። ችግሩ ሥራ-አጥነት ብቻ ሳይኾን፤ ዝቅተኛ ገቢ ማግኘቱ እና የስራ ዕድሉ አናሳ መኾኑ ነው» በማለት ተግዳሮቱ ጠንካራ መኾኑን ይገልጣሉ።

Äthiopische Hausangestellte im Libanon
ኢትዮጵያዊት የቤት ሠራተኛ ሊባኖስ ውስጥ የታጠቡ ልብሶችን ባልኮኒ ላይ ስታሰጣምስል picture-alliance/AP Photo/G. Kassab

ሥራ አጥነቱ እና የማኅበራዊ ፍትሕ እጦቱ በምሥራቊ አለያም በምዕራቡ የአፍሪቃ ክፍል ብቻ የሚወሰን አይደለም። ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሮዛ ሉግዘምበርግ ተቋም ባልደረባ የኾኑት ቤንጃሚን ሉዊግ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዛሬም ድረስ የሠራተኞች ብዝበዛ እጅግ ሥር መስደዱን ይናገራሉ። የዘር መድልዎ ከደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ባከተመበት ማግስት ሠራተኞች መብቶቻቸው ግልጽ በኾነ መልኩ ሊጠበቅ በተገባ ነበርም ይላሉ። 

ከዚያ ይልቅ ግን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የፊውዳል የሚመስል ብዝበዛ ተንሰራፍቷል እንደ ቤንጃሚን ሉዊግ። እርሳቸው ጉብኝት ባደረጉበት የሎሚ እርሻ ላይ እንኳን ብዝበዛው ለከት የለውም። አንዲት የደረሰች ነፍሰ-ጡር በሎሚ እርሻው ውስጥ እረፍት ተነፍጋ እጅግ ስታማርር ሰምተዋታል። ለሠራተኞቹ መጠለያ የተሰደሩት ዛኒጋባዎች ከሎሚ እርሻው ሦስት እና አራት ሜትር አይርቊም። ታዲያ ከእርሻው የሚነሳው እጅግ መርዛማ ጸረ ተባይ ንጥር እንደዘበት ደሳሳ ጎጆዎቻቸውን ያጥናል። ቤንጃሚን ሉዊግ፦ ሠራተኞች ሲበደሉ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ሚና ምን መምሰል እንደነበረበት በዚህ መልኩ አብነት ነቅሰው ያብራራሉ።

Hoodia Kaktus Plantage in Witdraai, Südafrika
በደቡብ አፍሪቃ እሾሃማው ካክተስ ተክል የእርሻ ማሳ ምስል AP

«ለአብነት ያኽል ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሀገሪቱ የተሠማሩ የተቆጣጣሪዎች እጥረት አለ። በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የግብርናው ዘርፍ ዘላቂ እንዲኾን ወሳኝ ሚና በተጫወተ ነበር።»

በእርግጥ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በቀደሙት ዘመኖቹ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች መለስ ብሎ ሊቃኝ እንደሚገባ ቤንጃሚን ሉዊግ ያሳስባሉ። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1921 የመሰብሰብ መብት እንዲጎናጸፉ የማብቃቱን ስኬት ያስታውሳሉ። ኾኖም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ እና አጠቃላይ የሠራተኞች የሥራ ኹኔታ ሊስተካከል እንደሚገባው ያሰምሩበታል። በፍልሰት የተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ሠራተኞች የጤና ዋስትና እንደ ሀገሬው ተወላጆች ሊከበር ይገባልም ባይ ናቸው። ያን ለማድረግ ደግሞ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ፖለቲከኞች ላይ ጫና ማሳደር አለበት ባይ ናቸው። ያም ብቻ አይደለም የሠራተኞችን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻል ዒላማቸውን የማይስቱ ጥረቶች ወሳኝ እንደኾኑም አበክረው ይናገራሉ።  

ከ100 ዓመት ወዲህም የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የተቋቋመበት መሠረትን ለማሳካት እጅግ ጉጉነቱ ይታያል። ኾኖም በድርጅቱ ፍላጎት እና ይኽን ፍላጎቱን ሃገራት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያሳዩት ዳተኝነት መካከል ያለው እውነታ ሰፊ ክፍተት ይስተዋልበታል። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ በራሱ በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም ገና መሻሻል የሚገባቸው ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩ አይክድም።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ