1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የቋንቋ ማስተማሪያው “ቻትቦት” ውድድሮችን እያሸነፈ ነው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 10 2009

አዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ዓለም አቀፍ ሁነት አስተናግዳ ነበር፡፡ በመላው ዓለም ባሉ የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ሁነት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እና የኮምፒውተር ፕሮግራም ጸሐፊዎች የሚወዳደሩበት ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2iMiP
Äthiopien Addis Abeba Challenge Cup
ምስል Iceaddis

የቋንቋ ማስተማሪያው “ቻትቦት” ውድድሮችን እያሸነፈ ነው

የጎርጎሮሳዊው 1776 ዓ.ም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ያኔ በብሪታንያ ስር ያሉ 13 የአሜሪካ ግዛቶች ነጻነታቸውን ያወጁበት እና አንድ ሀገር የመሰረቱበት ጊዜ ነበር፡፡ አሜሪካውያን በዚያው ዓመት ሐምሌ 4 የጸደቀውን የነጻነት ውል ለማስታወስ ብሔራዊ በዓል አድርገው ሰይመውታል፡፡ በየዓመቱም ሰማይን የሚያንቆጠቁጡ ርችቶች በመተኮስ ዕለቱን ያከብሩታል፡፡ የዛሬ አራት ዓመት በአሜሪካ የተቋቋመ አንድ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ደጋፊ ኮርፖሬሽን ታዲያ 1776ን በመውሰድ የድርጅቱ መለያ አድርጎታል፡፡  

ድርጅቱ በአሰያየሙ ብቻ አይደለም ያልተለመደ አካሄድን የመረጠው፡፡ ለመስሪያ ቤቱ ዋና መቀመጫ የመረጠውም ከተማ በቴክኖሎጂ ድርጅቶች ከሚዘወተረው ለየት ያለ ሆኗል፡፡ ድርጅቱ ከፌስቡክ እስከ ጉግል፣ ከያሆ እስከ አፕል ያሉበትን የሳንፍራንሲስኮውን ሲልከን ቫሊ ትቶ ፖለቲከኞች በሚተራመሱባት የአሜሪካዋን መዲና ዋሽንግተን ላይ ከትሟል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba Challenge Cup
ምስል Iceaddis

የ1776 ዓላማ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ናቸው በሚባሉት እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ፣ ኃይል፣ መጓጓዣ እና የመሳሰሉ ዘርፎች ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሄ የሚያፈላልጉ ጀማሪ ድርጅቶችን መደገፍ፣ ከፍ ሲልም መነሻ ገንዘብ ማቅረብ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ እነዚህ ድርጅቶች በሩን እስኪያንኳኩ አልጠበቀም፡፡ በተመሰረተ በዓመቱ በስሙ የተሰየመ የቴክኖሎጂ ውድድር አዘጋጀ፡፡ ውድድሩ ችግር ፈቺ፣ ተስፋ ሰጪ እና በትልቅ ደረጃ ሊስፋፉ የሚችሉ ጅምር ሥራዎችን ለይቶ ሽልማት ማበርከት ነው፡፡ 

ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በ16 ከተሞች ተወስኖ የቆየው ይህ ውድድር ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም ባሉ 50 ከተሞች ተካሄዷል፡፡ ውድድሩን ከድርጅቱ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁ ከተሞች ቁጥር ዘንድሮ 75 ደርሷል፡፡ አዲስ አበባም ወጉ ደርሷት ከእነ ኒውዮርክ፣ ዱባይ፣ ቶኪዮ፣ ለንደን እና ቴል-አቪቭ ጋር ተሰልፋለች፡፡ የእዚህን ዓመት ውድድርም ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም አካሄዳለች፡፡ ማርቆስ ለማ ከ1776 ጋር ውድድሩን በመተባበር ያዘጋጀው የአይስ አዲስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ 

“የ1776 ውድድርን ኢትዮጵያ ውስጥ ስናዘጋጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜያችን ነው፡፡ የባለፈው ዓመት የነበረው ቀጠናዊ ነበር፡፡ ሶስት ተወዳዳሪዎች ኬንያ ላይ ለመወዳደር ከኢትዮጵያ አልፈው ነበር፡፡ እዚያ በነበረው ዝግጅት አፍሪካ ውስጥ ተወዳድረው ያሸነፉ ሰዎች አሜሪካ ውስጥ ያለው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ነበር፡፡ በእዚህኛው ዓመት ግን የአገር ውስጥ አዘጋጅ የሆነው እና አይስ አዲሶች [የምንመርጣቸው] አሸናፊዎች ቀጥታ ወደ ኒው ዮርክ ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ የ1776ን ውድድር እኛ የምናደርግበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለሚጀምሩ እና ስራ ፈጣሪ ለሆኑ ልጆች እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ልምድ በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሄዶ በማየት እና ሌላ ዓለምአቀፍ ውድድሮች ላይ በመወዳደር የተለያየ መዋዕለ ንዋይን መሳብ ይቻላል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ ልምዶች እና ክህሎቶች ማዳበር ይቻላል” ይላል ማርቆስ፡፡     

በእዚህ ዓመቱ ውድድር ለመሳተፍ ማመልከቻውን ያስገቡ ተወዳዳሪዎች ብዛት 54 ቢሆኑም ለመጨረሻው ዙር ያለፉት ግን 10 ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ ሥራዎቻቸዉን ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡ በተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲሁም በኢንተርኔት አማካኝት ለሚፈጸሙ ክፍያዎች የራሳቸውን የቴክኖሎጂ መፍትሄዎች ይዘው የቀረቡ ነበሩ፡፡ ለአርሶ አደሮች የሚሆን የገበያ ስርዓት እና ሸማቾች በአቅራቢያቸው ያሉትን ነገሮች መገብየት የሚያስችላቸውን የሞባይል አፕልኬሽኖች ይዘው የተወዳደሩም አሉ፡፡ ሰነዶችን በዲጂታል መልክ ለማሰባሰብ የሚረዳ እና የታክሲ አገልግሎትን ዝርዝር (በመጻጻፍ ) በቻት ለማግኘት የሚያስችል የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ይዘው የመጡም ነበሩ፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba Challenge Cup
ምስል Iceaddis

ሀገርኛ ሀሳብን ተውሰው ወደ አፕልኬሽን የቀየሩ ተወዳዳሪዎች የታዳሚዎችን ቀልብ ስበዋል፡፡ ከአፕልኬሽኑ ፈጣሪዎች አንዱ በሞሪሸስ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘዉ ኢዮሲአስ ወርቄ ምትኩ ነው፡፡ በሙከራ ደረጃ ስላለው አፕልኬሽን አጭር ገለጻ አለው፡፡ 

“መስራት የፈለግነው እቁብ የሚባለውን ባህላዊ ጽንሰ ሀሳብ ይዞ አሁን ለወጣቱ ገንዘብ የመቆጠብ ልማድ እንዲያስጀምር የሚያስችል አፕልኬሽን ነው፡፡ ተግባራዊ የሚሆነው በስራም አካባቢ ሊሆን ይችላል በዩኒቨርስቲም ካሉ ጓደኞችህ ጋር አንድ ላይ ሆናችሁ ገንዘብ በኦንላይ መቆጠብ የሚያስችል ነው፡፡ ቀን ትመርጡና በዚያ ሰዓት ላይ ታወጣላችሁ፡፡ የኦንላይን ስርዓቱ ለማን ማድረስ እንዳለበት ወዲያውኑ ያመለክታል፡፡ ከዚያ በኋላ የደረሰው ሰው እቁቡን መሰብሰብ ይችላል፡፡ እንደዚያው እየተደረገ እንደሰው ብዛት እና እንደ ብሩ መጠን ጊዜው  እየተቀያየረ ገንዘቡ እንዲዟዟር እንዲያስችል ነው ያሰብነው፡፡ ገንዘብ መሰብሰቡን አይደለም፡፡ ገንዘብ የሚሰበስቡ ድርጅቶች አሉ ለምሳሌ የኔፔይ፣ ኤም ብር፣ ሄሎ ካሽ፡፡ እነርሱ ከሚሰጡት አገልግሎት ላይ በተጨማሪ ምንድነው መስራት የሚቻለው? ገንዘብ ከመሰብሰብ ባሻገር ያ ገንዘብ እንዴት ይጠቅማል የሚለውን ነገር ነው ለመስራት ያሰብነው” ሲል ለውድድር ስላቀረቡት አፕልኬሽን ይገልጻል፡፡  

እነ ኢዮሲአስ ይህን ሀሳባቸውን በውድድሩ ላይ በዝርዝር ቢያቀርቡም አላሸነፉም፡፡ የእዚህ ዓመት አሸናፊው ቋንቋን በቀላሉ ለመማር የሚያስችል “ላንግቦት” የተባለ የሶፍትዌር ፕሮግራም ሆኗል፡፡ የእዚህ ፕሮግራም ሰሪ ናትናኤል ጎሳዬ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቁ ናትናኤል የ26 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የሶፍትዌር ፕሮግራም መጻፍ (coding) የጀመረው ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ እንደነበር ይናገራል፡፡ ከዩኒቨርስቲ ከወጣ በኋላ ላለፉት አራት አመታት በተለያዩ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በሶፍትዌር ፕሮግራም ሰሪነት አገልግሏል፡፡ ለሽልማት ስላበቃው ሥራ እንዲህ ያስረዳል፡፡

“ቻትቦት (chatbot) ነው የሚባለው፡፡ የምታወርደው (download) አፕልኬሽን ሳይሆን አሁን ለምሳሌ ፌስ ቡክ ሜሰንጀር ውስጥ ቻት ታደርገዋለህ እና የሚመልስልህ የኮምፒውተር ፕሮግራም ነው፡፡ እንደ ሰው ሆኖ ይነጋግራሃል አይነት ነገር ማለት ነው፡፡ ፌስ ቡክ  ሜሴንጄር ላይ ልክ ከጓደኞቻችን ጋር እንደምናደርገው ከቻት ቦቶችም ጋር ቻት ማድረግ እንችላለን፡፡ ፌስ ቡክ ሜሴንጀር ላይ አሉ እንደዚህ አይነት ቻትቦቶች፡፡  የአየር ሁኔታ የሚናገሩ አሉ፡፡ ዜና የሚያወሩ አሉ፡፡ የኩባንያዎች የደንበኞች አገልግሎትቻት ቦቶችም አሉ፡፡ እንደዚያ ሆኖ ቫይበር፤ ቴሌግራም፣ ስካይፕም ላይ አለ፡፡ ሁሉም ላይ እንደዚህ ቻትቦቶችን ማገናኘት ይቻላል፡፡ ቋንቋን የመረጥኩት እነዚህ ቻትቦቶች እንደአፕልኬሽን እየተጫንክ አይነት ነገር ሳይሆን እያነጋገርካቸው ነው የምትጠቀመው፡፡ ይሄ የንግግር አካሉ ቋንቋን ለማስተማር በጣም አሪፍ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ነው ቋንቋን የሚያስተምር ቻትቦት ለውድድሩ ለመስራት የመረጥኩት” ይላል ናትናኤል፡፡

የናትናኤል የቋንቋ ማስተማሪያ አሁን የሚያገለግለው ለፈረንሳይኛ ብቻ ነው፡፡ “ፈረንሳይኛ ለራሴም እየተማርኩ ስለነበር እና በመጠኑ ስለምችል በእርሱ ልጀምር ብዬ ነው” ይላል ቋንቋውን የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ፡፡ ፈረንሳይኛ ለብዙዎች ኢትዮጵያውያን ባዳ ቢሆንም የአዲስ አበባው ውድድር ዳኞች ግን ለዓለም አቀፍ መድረክ ይመጥናል በሚል የቋንቋ ማስተማሪያውን አሸናፊ አድርገውታል፡፡ 

Telegram Messenger
ምስል Imago/TASS/K. Kuhkmar

ወጣቱ ፕሮግራም ሰሪ የአዲስ አበባውን ውድድር “አሸንፋለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር” ነዉ የሚለዉ፡፡ ይህን ይበል እንጂ በዚሁ ሥራው በፌስ ቡክ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ ሆኗል፡፡ ውድድሩ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች መልዕክት ለመላላኪያ ለሚጠቀሙበት ሜሴንጀር ለተሰኘው አፕልኬሽን የሚሆን ቻትቦት መሥራት ነበር፡፡ በክፍለ አህጉራት እና በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍሎ በተካሄደው በዚህ ውድድር አንድ ሺህ አመልካቾች መሳተፋቸውን ፌስ ቡክ አሳውቋል፡፡ ናትናኤል ያሸነፈው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በ“Utility and Productivity” ምድብ ነው ናትናኤል፡፡   ለፌስቡክ ውድድር የሠራውን ቻትቦት ሲልክ ከተለመዱት ለየት በማለቱ ጥሩ ተወዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ገምቶ ነበር፡፡  

“ፌስቡክ ሜሴንጀር ላይ ቻትቦት ከጀመሩ ገና አመታቸው ነው፡፡ ያን ያህልም ቻት ቦቶች የሉም፡፡ ልክ AppStore የቦቶችም ስቶር አለ፡፡ ቋንቋ የሚያስተምሩ አንድ ሁለት አይቻለሁ፡፡ ግን ያን ያህል አሪፍ መስለው አልታዩኝም፡፡ በጣም አሪፍ የሆኑ ቋንቋ የሚስተምሩ ድረ ገጾች፣ አፕልኬሽኖች አሉ፡፡ ግን በቦት መልክ ምንም አላገኘሁም ነበር” ይላል ናትናኤል፡፡

ለናትናኤል በውድድሮች ማሸነፍ እና መሸለም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ገና የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ ዓለም አቀፉ የጉግል ኩባንያ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው አንድ ውድድር ላይ አሸንፎ የሞባይል ሽልማት አግኝቷል፡፡ የጉግል የተማሪ አምባሳደር በመባልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አብሮት ይማር ከነበረ ሌላ ወጣት ጋር ወደ ናይሮቢ በመሄድ ስልጠና ወስዶ ተመልሷል፡፡ የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኖ በአዲስ አበባ በተካሄደ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ውድድር ላይ ባቀረበው የሞባይል አፕልኬሽን ሦስተኛ በመውጣት 50 ሺህ ብር ተሸልሟል፡፡ ባለፈው ሳምንት ያሸነፈው ውድድርም በ1776 ወደሚዘጋጅ ዓለም አቀፍ የማጠቃለያ ውድድር በቀጥታ እንዲያልፍ አድርጎታል፡፡ 

በመጪው ኅዳር ወር በአሜሪካ የሚካሄደው ይህ ውድድር በ1776 የየሀገራቱ ተባባሪዎች በተዘጋጁ ውድድሮች ያሸነፉ የሚፎካከሩበት ነው፡፡ የእዚህ ውድድር አሸናፊዎች ከሚከፋፈሉት 175 ሺህ ዶላር ባሻገር 1776 በተመራጭ ጀማሪ ድርጅቶች ለማፍሰስ ካዘጋጀው አንድ ሚሊዮን ዶላር ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በእንዲህ አይነት ውድድሮች ጠቀሜታው ቀጥታ ከሚገኘው ገንዘብም በላይ የሚሻገር ነው ይላል ሃምሳ ሎሚ የተሰኘ አፕልኬሽን ሰርተው ለአገልግሎት ካበቁት ወጣቶች አንዱ የሆነው ተመስገን ፍስሀ፤ ውድድሮቹ ስላላቸው ጠቀሜታ ይዘረዝራል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba Challenge Cup
ምስል Iceaddis

“አንደኛ ትስስር ለመፍጠር፣ ከሌላ ሰው ጋር ለመስራት እና የተሻለ ነገር ለመፍጠር ዕድሉን ይሰጠሃል፡፡ እንደዚሁ ሀሳብን ብቻ አቅርበህ ሳይሆን ውድድሩ ከተደረገ በኋላ ተገናኝተህ የምታወራው እና የምታቅደው ነገር ጥሩ መነሻ ይሆናል ለወደፊት ስራዎች፡፡ ስለዚህ ሰዎችን የማግኛ ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ሁለተኛ እዚያ ላይ መወዳደርህ እና ማሸነፍህ ባለሀብቶች እና በዚያ ዘርፍ ያሉ ሰዎች [ለአንተ] ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ከዚያ በተረፈ ውድድሮቹ ከተካሄዱ በኋላ የሚደረጉት ውይይቶች ለተወዳዳሪዎቹ ጥሩ ግብረ መልስ ወይም ማጠናከሪያ አስተያቶች ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ ከመማሪያ፣ ከመገናኛ እና ከማስተዋወቂያ አንጻር የእነዚህ ውድድሮች ዋነኛዎቹ ጥቅሞች ይመስሉኛል”ብሏል ተመስገን፡፡ 

ናትናኤልም ውድድሮችን ሥራውን ለመፈተሺያነት እና ወደፊት ለሚሠራቸው እንደመንደርደሪያ እንደሚጠቀምባቸው ይናገራል፡፡ ፈታኝ ውድድር ከፊቱ የሚጠብቀው ናትናኤል በአሜሪካው ውድድር በሚያገኘው ዕድል በትንሹ የጀመረውን ሥራ ለማሳደግ ያስባል፡፡ አሁን ከጀመረው ፈረንሳይኛ ቋንቋ ሌላ አማርኛን እና ሌሎች ቋንቋዎችንም መጨመር ይፈልጋል፡፡ 

“አንዴ ዋና ዋና ነገሮቹ ከተሰሩ እና ሰው የሚፈልገው ነገር መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ይዘት መጨመር ነው የሚሆነው፡፡ አማርኛ መጨመር ካስፈለገ አማርኛ መጨመር ቀላል ነው የሚሆነው፡፡ ያው ለማደግ ቋንቋዎች መጨመር [ወደፊት] የሚመጣ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ግን የመጀመሪያ ትኩረቱ ለዓለም አቀፍ ገበያ ይሄ ነገር ይሆናል፣ አይሆንም የሚለውን ለማየት ነው፡፡ አሁን ፌስቡክ ሜሴንጀር ላይ ብቻ ስለሆነ ያለው ሌላ አፕልኬሽኖችም ላይ እንዲኖር ማድረግ ነው አላማው፡፡ ቀጣዩ እርምጃ ቴሌግራም፣ ቫይበርም ሆነ እንደዚያ አይነቶቹ ላይ እንዲኖር ማድረግ ነው” ሲል የወደፊት እቅዱን ያጋራል፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ