1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም ዓቀፉ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ በጀርመን

ሰኞ፣ ሰኔ 4 2010

በዓለም ዙሪያ በሚታዩ የእኩልነትና የፍትህ ችግሮች ላይ የሚያተኩር  የመገናኛ ብዙሃን መድረክ  በዛሬዉ ዕለት በቦን ከተማ ተጀምሯል። በዶቼ ቬለ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለዉ ይህ ዓለም ዓቀፍ የዉይይት መድረክ ኢፍትሃዊነትን ለመዋጋት መገናኛ ብዙሃን ያላቸዉን አስተዋፅኦ የሚዳስስ ሲሆን ከ100 በላይ የአዳጊ ሀገራት ጋዜጠኞች ይሳተፉበታል።

https://p.dw.com/p/2zJhp
Opening ceremony | Welcome Address: Armin Laschet (German State of North Rhine-Westphalia (NRW), Minister President, Germany)
ምስል DW/F. Görner

Global Media Forum - MP3-Stereo


በጀርመኗ ቦን ከተማ «ዓለም ዓቀፍ ኢ-ፍትሃዊነት»በሚል መሪ ቃል በዛሬዉ ዕለት የተጀመረዉ ይህ የዉይይት መድረክ ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን በዓለም ላይ የሚታዩ የፍትሃዊነትና የእኩልነት ችግሮች ዋና ርዕሰ ጉዳይ ያደረገ ነዉ።
ዶቼ ቬለ የሚያዘጋጀዉ ዓለም ዓቀፉ የመገናኛ ብዙሃን  የዉይይት መድረክ፤  ዉሳኔ ሰጭወች ፣ ፖለቲከኞች፣የንግድ ሰዎች ፣ሳይንቲስቶች ፣ጋዜጠኞች ፣የሚገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች የሚታደሙበት ዓመታዊ የዉይይት መድረክ ነዉ።
ይህ የዉይይት መድረክ ባለፉት አስር ዓመታት  በጀርመን ትልቁ  ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ጉባኤ እየሆነ እንደመጣ ብዙዎች ይናገራሉ ። በጎርጎሮሳዊዉ  ከ ሐምሌ 11 እስከ 13 በሚቆየዉ የዘንድሮዉ መድረክም ከ120 ሀገራት የተዉጣጡ 2 ሺህ እንግዶች ይሳተፉበታል።በዚህ የሦስት ቀን ቆይታ በተለይ ከተሳታፊዎች የመገኘዉ የልምድ ልዉዉጥ ለዶቼ ቬለ ቀላል እንዳልሆነ ዋና ስራ አስኪያጁ ፒተር ሊምቡርግ ይገልጻሉ።
«ዓለም ዐቀፉ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ  የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎች ጋዜጠኞች፤ ለዶቼ ቬለ ፍላጎት ያላቸዉ ሰዎችና የዓለም ዓቀፉን የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መከበር ከሚደግፉ ሰዎች ጋር የልምድ ልዉዉጥ የሚደረግበት ልዩ የሆነ መድረክ ነዉ።ይህ  የሦስት ቀን ዉይይት ለኔ ዶይቼ ቬለ ግልፅ ሚዲያ መሆኑን ለዓለም የምናሳይበት መድረክም ነዉ። ከአጋሮቻችንም ብዙ መማር እንችላላን ብዬ አስባለሁ።እናም የሚደረገዉ የልምድ ልዉዉጥና ዉይይት በጣም አስፈላጊ ነዉ።»
የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ስልክ ዘገባ በመድረኩ ዉይይት ከሚደረግባቸዉ ጉዳዮች መካከል ሲሆኑ በዚህ የዘገባ ስልት የዶቼ ቬለዉ የዓረብኛ ክፍል ባልደረባ ዩሱፍ ዑመር  ልምድ ያለዉ ጋዜጠኛ በመሆኑ ለታዳሚዉ ልምዱን ያካፍላል። «ብዕር ከሰይፍ የበለጠ ሀይል ዓለዉ» የሚለዉ የሱፍ  ለእኩልነትና ለፍትሃዊነት መስፈን የተንቀሳቃሽ ስልክ ዘገባን በለዉጥ መሳሪያነት ማዋል ይቻላል የሚል እምነት አለዉ ።
የዶቼ ቬለዉ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊምቡርግም ፤በመድረኩ የሚካሄደዉ ሰፊ ዉይይት ከሁሉም በላይ  ለሰዉ ልጆች መሰረታዊ መብት መከበር አጋዥ መሆኑን ያስምሩበታል።

Opening ceremony | Welcome Address: Armin Laschet (German State of North Rhine-Westphalia (NRW), Minister President, Germany)
ምስል DW/F. Görner

«እንደማስበዉ በዓለም ላይ የፍትህ መጓደልና የእኩልነት አለመኖር እንደዘወትራዊ ህይወት ተደርጎ በሚታይበት ሁኔታ  እነዚህን ችግሮች እንዴት መቋቋም ይቻላል በሚለዉ ዙሪያ ጥልቅ ዉይይት ይደረጋል።ምንም እንኳ በዓለም ላይ ፍፁም የሆነ እኩልነትን ማስፈን ባይቻልም።ለመሰረታዊ የሰዉ ልጆች መብት መከበር  በዘገባዎቻችን  ጥረት ማድረግ አለብን።ግልፅ በሆነ ሁኔታ ይህ ጥያቄ  በምንሰራቸዉ ዘገባዎች ምን ማለት እንደሆነ ማሳየት አለብን።»

Opening ceremony | Welcome Address: Armin Laschet (German State of North Rhine-Westphalia (NRW), Minister President, Germany)
ምስል DW/F. Görner

የዘንድሮዉ የዉይይቱ መርሃ ግብር ሀላፊ  ቬሮኒካ ስፓስቪካ እንደሚሉት በዚህ ዓመት ከፓኪስታን ከባንግላዲሽ እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች ይበዛሉ ።ያም ሆኖ ግን አንድ መቶ የአዳጊ ሀገራት ጋዜጠኞች በዉይይቱ ተሳታፊዎች ናቸዉ። አዉሮጳ ህብረት የፖለቲካና የማህበረሰብ ኮሚሽነር ማሪያማ ገብርኤልና የቀድሞዉ የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ሀሚዲ ካርዛይም  የዉይይቱ አካል  መሆናቸዉ ታዉቋል።
ዓለም ዓቀፍ ኢፍትሃዊነት የሚለዉን የዉይይቱን መሪ ሀሳብ በሚገባ ለማስተላለፍም 60 የሚሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ የመርሃ ግብሩ ሀላፊ ቬሮኒካ ስፓስቪካ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።


ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ