1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረመሉ የተለወጠ ዘርና የኢትዮጵያ ዳርዳርታ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2010

ኢትዮጵያ በሳይንሳዊ አጠራሩ ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም የሚሏቸውን ዘሮች አጥብቆ የሚከላከል ሕግ ኖሯት ቆይታለች። ከጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም ወዲህ ደግሞ በሕጉ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ የትብብር እና ምርምር ፈቃድ ለቀቅ ማለቱ ይነገራል። ከሰሞኑም ዘረመሉ የተለወጠ«ህያው የጥጥ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ መመረት እንዲችል መፈቀዱ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/30lOO
Baumwollernte Elfenbeinküste
ምስል AFP/Getty Images/I. Sanogo

«ዘረመሉ የተለወጠ ጥጥ እንዲመረት ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል»

ቡርኪናፋሶ በጥጥ ምርቷ ብዛት እና ጥራት ባለነጭ ወርቋ አፍሪቃዊት ሀገር የሚል ዝና ነበራት። ዓይን የበዛበት ጥጧ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ90ዎቹ ማለቂያ ግድም በድርቅ እና በጥጥ አምካኝ ተምች ሲመታ መላ ታፈላልግ ገባች። ዘረመላቸው የተለወጠ የተለያዩ ዘሮችን በሞኖፖል በመያዝ የሚወቀሰው ሞንሳንቶ በተባለው ድርጅት ለቡርኪናፋሶ መንግሥት የራሱን ምክር አቀረበ። ዘረመሉ የተለወጠው ጥጥ ድርቅንም ሆነ ተባይን መቋቋም እንደሚችል ያመነው የቡርኪና መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2003ዓ,ም ከሞንሳንቶ ጋር ውል ተፈራረመ።  የሞንሳንቶን ዘር ሊጠቀም። ኩርኪናፋሶ የጥጥ አምራች ገበሬዎቿ ዘረመሉ የተለወጠ ጥጥ እንዲያመርቱ  ስታደርግ ምርት ማፈሷ ላይ ብቻ አተኩራ ነበር። ሆኖም ግን ዉሎ አድሮ ችግር ተከተለ። ያ ነጭ ወርቋ የገበያውን ቀልብ የሚስብበት አቅም አጣ። ሀገሪቱም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 እስከ 2016ዓም ባሉት ጊዜያትም ከሦስት አምራቾች ከጥጥ ብቻ ልታገኝ የሚገባትን 82 ሚሊየን ዶላር አጣች። የጥጥ አምራች ገበሬዎቿም ከመንግሥታቸው ጋር ተፋጠጡ። የቡርኪናፋሶ መንግሥት ደግሞ ከሞንሳንቶ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በጄኔቲክ ምህንድስና የተለወጠ ጥጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት በጥንቃቄ በተከለለ ስፍራ የመስክ ምርመራ ሲካሄድበት እንደቆየ፤ በሂደቱም በአካባቢም ሆነ በሰው ጤና እና በስነምህዳሩ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ በመጣራቱ ከስምምነት የመነጨ ፈቃድ እንደተሰጠው ለመረዳት ችለናል። ይህ ምን ማለት ይሆን? ፈቃዱስ ማን ምንዲያደርግበት ተሰጠ? የፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት  አቶ አሰፋ ጉዲና በአካባቢ ደን እና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር የደህንነተ ሕይወት እና መጤ ወራሪ ዝርያዎች ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።

«አመልካቹ ይህንን ሙከራ ለማድረግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ነው። የመስክ ላይ የዝግ ሙከራ ማካሄድን እና ወደአካባቢ ልቀትን ነው የሚጠይቀው በዚህ በጄኔቲክ ምህንድስና ወይ ደግሞ በጄነቲካል ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም ዙሪያ፤ ስለዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንደኛ ልዩ ፈቃድ ነው የሚሰጠው ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከስምምነት የመነጨ ፈቃድ ነው የሚሰጠው። ልዩ ፈቃድ የመስክ ላይ የዝግ ሙከራ ለማካሄድ የሚሰጥ ፈቃድ ሲሆን፤ ከስምምነት የመነጨ ፈቃድ ደግሞ ወደአካባቢ ቢለቀቅ በሰው ጤና ላይ በእንስሳት ላይ ወይ ደግሞ በብዝሃ ሕይወት ላይ ምንም ችግር የለውም የሚል ፈቃድ ነው የሚሰጠው ማለት ነው።»

Baumwollernte Elfenbeinküste
ምስል AFP/Getty Images/I. Sanogo

ምርምሩ በጥጥ ብቻ አላበቃም፤ በቆሎ ሌላው ተረኛ ነው። አሁንም አቶ አሰፋ፤

«በቆሎን በተመለከተ ደግሞ የአምስት ዓመት የዝግ ሙከራ ልዩ ፈቃድ ነው የሰጠነው። እና የዝግ ሙከራውን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ግርብና ምርምር ኢንስቲትዩት በተለያዩ የበቆሎ አብቃይ ቦታዎች ነው ማለት ነው። ለዚህም የባኮ እርሻ ምርምር እና የመልካሳ እርሻ ምርምር ግቢ ውስጥ ነው የሚያካሂደው ማለት ነው።»

ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ስብጥር ከታደሉት ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗን በዘርፉ አንቱ የተሰኙት ኢትዮጵያዊዉ የዘረመል እና የአዝርዕት ተመራማሪ ዶክተር መላኩ ወረደ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። የኩርኪናፋሶ ጥጥ ያጋጠመውን አደጋ በማስመልከት ከአንድ ዓመት በፊት ያነጋገርኳቸው ዶክተር መላኩ ዘረመሉ የተወጠ ጥጥ የገጠመውን ጣጣ ጠንቅቀው ያውቁታል። በጄኔቲክ ምህድንስና ዘረመሉ የተለወጠ ዘር ያሉትን አዎንታዊ እና አሉታዊ ገጽታዎችም ገልፀውታል።

ምርምሩ የተሻሻሉ ዘሮችን ድርቅም ሆነ ሌላውን ችግር ለመቋቋም እንደሚጠቅም የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፤ የእነሱ ማሳሰቢያ አንድ ነው፤ የተፈጥሮው ዘር እየተለወጠ ከሄደ ነባሩ ዘር ይጠፋል። ያኔ ዘሮችን በጄኔቲክ ምህንድስና እየለወጡ ለሚቸበችቡ የተፈጥሮ ዘር ቀበኞች መጋለጥ ይመጣል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ