1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘርፈ ብዙዉ ኢትዮጵያዊ ሲታወሱ

ሐሙስ፣ ሰኔ 21 2010

ጣልያን ኢትዮጵያን ሊወር ሲል የጋሽ ዐብይ አባት ታመዉ ነበር። እናትየዉን በመሞቻ አልጋቸዉ ላይ ቃል ያስገቧቸዉ፤ ዐብይና ወንድሙን ጦርነት ፍራቻ፤ ከኢትዮጵያ ይዘዉ እንዳይወጡ ነዉ። ልጆቹን ኢትዮጵያ ዉስጥ እንድታሳድግ፤ እንደዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ የመጣነዉ ልንሞትም ልንንኖርም ነዉ ሲሉ ቃል አስገብተዉ ይህን ዓለም የተሰናበቱት።

https://p.dw.com/p/30UZa
Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

«ጋሽ ዐብይ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የኮራ ስሜት የነበረዉ ነዉ»

«ለኔ ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ነገር ነዉ ቀላል ነገር አይደለም፤ በቀላሉም አልመለከተዉም። ለኔ ኢትዮጵያዊነት በጣም ሰፊ ዓለም አቀፍዊ ነዉ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ጀርባ የሚሰጠኝ ነገር በመሆኑ በጠባብ የምመለከተዉ አይደለም። »

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

በቅርቡ በ 83 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድ፤ ከሃገር ዉስጥ መገናኛ ጋር ካደረጉት ቃለ-ምልልስ የተወሰደ ነበር። ፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድ፤የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምኒኬሽን የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን፤ የዩኒቨርስቲው ፐሬዚዳንት ጽ/ቤት ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርስቲው የሥነ-ጥበባት እና ፊልም ት/ቤት ልዩ አማካሪ እና በዩኒቨርስቲው የፊልም ጥናት ክፍል ለመጀመር የተደራጀው ግብረ ኃይል አማካሪም ሆነዉ ሰርተዋል። በሃገር ዉስጥ ሙዚቃ፤ በፊልም ሥራም ተሳትፎአቸዉ ይታወቃሉ። ቤተሰቦቻቸዉ ኒዮርክ ዩናትድ ስቴትስ ሃርለም ፓን አፍሪካን ንቅናቄ አራማጅ ሆነዉ ኢትዮጵያን ፈልገዉ ወደ ኢትዮጵያ በ 1920ዎቹ መጀመርያ ላይ መጥተዉ ቋሚ መኖርያቸዉን እዝያዉ አድርገዉ በርካታ ሥራዎችን ለኢትዮጵያ አበርክተዋል።

የፕሮፌሰር ዐብይ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያና ሙዚቃን አፍቃሪ ብሎም የተለያዩ የሙዚቃ መሳርያን ተጫዋች ናቸዉ። እንደዉም ሙዚቃን ከአባታቸዉ የወረሱት ሳይሆን እንዳልቀረ ነዉ የሚነገርላቸዉ። አብዛኞች ፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድን ጋሽ ዐብይ ሲሉ ነዉ የሚጠሩዋቸዉ። በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑት እና የኢትዮጵያን ብሎም የሌሎች አፍሪቃ ሃገራትን ባህል በማስተዋወቃቸዉ የሚታወቁት አቶ ጥበቡ አሰፋ፤ ከፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድ ጋር ላለፉት 30 ዓመታት በቅርብ ባልንጀራነት ያቋቸዋል። በተለያዩ ባህላዊ ጉዳዮች ላይም አብረዉ ሰርተዋል።

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

«ፕሮፊሰር ዐብይ አስተማሪዬ ፤ ከዚያም ለጥቆ በአሜሪካ ዉስጥ ሃገርን በማስተዋወቅ በምሰራቸዉ ሥራዎች ላይ አማካሪዬ፤ በስተመጨረሻም ደግሞ ጓደኛዬም ሆኖ፤ ከዝያም አልፎ የእናቱን ሥራ በቀጣይነት ለመስራት በአቋቋመዉ ድርጅት ዉስጥ የቦርድ አባል በመሆን፤ በማገልገል ላይ ነኝ። አጋሽ ዐብይን ለአለፉት 30 ዓመታቶች አዉቀዋለሁ። የጋሽ ዐብይ ታሪክ ከእናት እና አባቱ ይጀምራል፤ የአባት እና እናቱ ነፀብራቅ ነዉ። ሥራዉ ግዙፍ ነዉ። ልቡ በጣም ትልቅ ነዉ። ኢትዮጵያዊነቱ የሰከነ ነዉ። ሰዎችን ለመርዳት በሞያም በግለሰቦችም ደረጃ በተለይ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ብዙ ሥራዎችን ሰርቶአል። በአጠቃላይ ስለ ጋሽ ዐብይ በትንሽ ለማዉራት ይከብዳል።»    

ዓለም አቀፍ አፍሪቃዊነትን ለማጠናከር  ሰሜን አሜሪካን ጥለዉ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የፕሮፌሰር ዐብይ ቤተሰቦች ያበረከቷቸዉ ሥራዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉ አቶ ጥበቡ አሰፋ ተናግረዋል። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በ1923 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው ቡድን ጋር የመጡት አባቱ ራባይ አነርሆልድ ፎርድ እና እናታቸዉ ሚኒዮን ፎርድ፤ ኒዮርክ ዉስጥ አፍሪቃን ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ ኒዮርክ ሃርለም በነበረዉ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነበሩ።  ካሪቢክ ደሴት ሃገር ከሆነዉ ከባርቤዶስ የሚመጡት ሁለቱ የፓን አፍሪቃ አራማጆች ኢትዮጵያ ሲኖሩ ትዳር መስርተው ዐብይ ፎርድን እና ዮሴፍ ኃይለስላሴ ፎርድን ወልደዉ ቋሚ መኖርያቸዉን ኢትዮጵያ አደረጉ። ፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እናታቸው ሚሲስ ፎርድ በአቋቋሙት ቤተ-ኡራኤል በኋላም ልዕልት ዘነበወርቅ በተባለው የአፀደ ህፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፤ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሊሴይ ገ/ማሪያም አጠናቀዋል። በኃላም ለከፍተኛ ደረጃት ትምህርት ስኮላር ሽፕ አግኝተዉ ወደ ሰሜን አሜሪካ አቀኑ።   

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

«ጋሽ ዐብይ የተወለደዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ። መወለድ ብቻ ሳይሆን አባቱ ራንባ አኖልድ ፎርድ ኢትዮጵያ ሄደዉ እናቱን ሚስ ሚኒዮን ሎሬን ፎርድን፤ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ጋብዘዉ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከተጋቡ በኋላ ሁለት ልጆችን ወልደዉ ጣልያን ኢትዮጵያን ሊወር ሲል የጋሽ ዐብይ አባት ታመዉ ነበር። እናትየዉን በመሞቻ አልጋቸዉ ላይ ቃል ያስገቧቸዉ፤ ዐብይና ወንድሙን ጦርነት ፍራቻ፤ ከኢትዮጵያ ይዘዉ እንዳይወጡ ነበር። ልጆቹን ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲያሳድጉ እንደዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ የመጣነዉ ልንሞትም ልንኖርም ነዉ ፤ ሲሉ ነዉ ቃል አስገብተዉ ይህን ዓለም የተሰናበቱት። ይህን አደራ እባክሽ ብለዉ ሚሲስ ፎርድን በጦርነት ምክንያት ልጆቹን ከኢትዮጵያ ይዘዉ እንዳይወጡ ለምነዉዋቸዋል። ሚሲስ ፎርድም ይህን ቃል በመጠበቅ በአቋቋሙት ት/ቤት ዉስጥ ጋሽ ዐብይ ተምሮ፤ እዚያዉ አድጎ ከእናቱና ከአባቱ በወሰደዉ በጣም ጥልቀት ያለዉ ኢትዮጵያዊነት ያደገ ፤ ከወጣም በኋላ ያንን ያልረሳ ሁልጊዜ ሕይወቱ በዝያ ዙርያ የሆነ የባህል አርበኛ ነበር። »

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

ፕሮፊሰር ዐብይ ፍሮድ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸዉ በፊት እዝያዉ በሰሜን አሜሪካ በሃዋርድ ዩንቨርስቲ በመምህርነት አገልግለዋል። 

«ጋሽ ዐብይ በሥራዉ ፊልም፤ ሬድዮ ኮሚኒዬኬሽን ዉስጥ የጠለቀ እዉቀት ያለዉና ለብዙ ዓመታት በሃዋርድ ዩቨርስቲ ያስተማረ ከዚያም በሃዋርድ ዩንቨርስቲ ግልጋሎቱን ሲጨርስ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ፤ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዉስጥ የፊልም የሬድዮ ኮሚኒዩኬሽን ስልጠናን በመስጠት ያገለገለ ምሁር ነዉ። በግለሰብነት ጋሽ ዐብይ በሙዚቃ ይጠቀሳል። የጋሽ ዐብይ አባት እንደሚታወቀዉ ራባይ ፎርድ የማርክስ ጋርቬይ ንቅናቄ ዉስጥ በጎርጎረሳዊዉ 1920ዎቹ ጥቁሮችን ነፃ ለማዉጣት አሜሪካን ዉስጥ በነበረዉ እንቅስቃሴ እዛ ዉስጥ የተሳተፉ እና ያገለገሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሚባል በአሁኑ የዓለም ጥቁሮች የሚያዳምጡትን ዜማ የደረሱ ናቸዉ። ጋሽ ዐብይም እንደ አባቱ የጠለቀ የሙዚቃ ፍቅር ያለዉ የሙዚቃ ችሎታም ያለዉ ነዉ። ፕያኖ ከበሮ ይጫወታል።  አቶ ጥበቡ እንደሚሉት ከሆነ፤ ፕሮፊሰር ዐብይ ፎርድ ከእናታቸዉ ከሚሲስ ፎርድ የወረሱት ለየት ያለዉ ነገር ቢኖር፤ ሁሉን ማኅበረሰብ በአንድ ዓይን በፍቅር ማቀፍ ወንድም እህት ማድረግ ነዉ።

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

«ጋሽ ዐብይ ለየት የሚያደርገዉ ነገር ከእናቱ የወረሰዉ ባህሪ ነዉ። እናቱ መጀመርያ ቤተ- ኡራኤል በኋላ ደሞ ልዕልት ዘነብ ወርቅ የተባለዉን ት/ቤትን ከፍተዉ በዘመናዊ የትምህርት አሰጣጥ ብዙ ሰዎችን አስተምረዋል። ከዝያም አልፎ ከፍሎ ለመማር አቅም ያልነበራቸዉን በነፃ በማስተማር ቤተሰብ የሌላቸዉን ደግሞ እናት በመሆን በማሳደግ እና በመከባከብ በጣም ትልቅ ቤተሰብን ያፈሩ ናቸዉ። ሚሲስ ፎርድ ያሳደግዋቸዉ የጋሽ ዐብይ ወንድም እና እህቶቹ ከሦስት መቶ ይበልጣሉ። ጋሽ ዐብይ ላይም ለየት ያለ ነገር ያየሁበት አንድ ነገር አለ። ሁላችንም ቤተሰብ አለን። ቤተሰብን የምንገነባዉ በደም ትስስር ነዉ። የጋሽ ዐብይ እህት ወንድሞች ግን ከሁሉ ብሔር ብሔረሰቦች የመጡ ሃይማኖት የማይለያያቸዉ በፍቅር ላይ የተመሰረቱ ቤተሰቦች ናቸዉ። እናትዬዉ ይህን ገንብተዉ ነዉ ያለፉት። ጋሽ ዐብይም ይህን ከእናቱ በወረሰዉ፤ በፍቅር ቤተሰብን የመሰረት ሁሉን  በእኩል እንደወንድም እህቱ የሚያይ በኢትዮጵያዊነቱ የኮራ ስሜት የነበረዉ ነዉ» ፕሮፊሰር ስርዓተ ቀብር ላይ ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ አሉ አቶ ጥበቡ አሰፋ በመቀጠል፤ «በፕሮፊሰር ዐብይ ሥርዓተ ቀብር ላይ ከ ሦስት መቶ የሚበልጡ የሚሲስ ፎርድ ልጆችን አይቼአለሁ። ስለ ሚሲስ ፎርድ ባነሱ ቁጥር ፊታቸዉ እንደመብራት ሲበራና ደስታ ሲቃ ይዞአቸዉ አይቻለሁ። ይኸዉ ዓይነት ስሜት ስለ ጋሽ ዐብይም ሲያነሱ አይቼባቸዋለሁ። በተደረፈ ። ፕሮፌሰር ዐብይ ፎርድ እናት የተሰራው እና የተለያዩ ስሞች የተሰጡት ት/ቤት አዲስ አበባ ከካዛንችስ ወደ አቧሪ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ በሚሲስ ፎርድ ድጋፍ ትምህርት ቤቱ ተምረዉ ታዋቂ ባለሞያዎች ከሆኑት መካከል፤ታዋቂዉን ደራሲ በዓሉ ግርማን ጨምሮ፤ እታበዛሁ ማናዜ፤ አልማዝ በየነ፤ አቻምየለሽ፤ ታደሰ ኃይሌ፤ በርሄ አፍሮም የመሳሰሉ ሰዎችን አፍርቶአል። ትምህርት ቤቱ አሁን የሚስስ ፎርድ መታሰቢያ ሆኖ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

Professor Abiyi Ford
ምስል Tebebu Assefa

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ