1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዜናን በሙዚቃ- የሴናጋላውያኑ መንገድ 

ዓርብ፣ ሐምሌ 20 2010

ሒፕ ሆፕ እና ራፕ የሙዚቃ ሥልቶች በሴኔጋል ለሰብዓዊ መብት መከበር እና በኢ-ፍትሐዊነት በሚደረገው ትግል እንደ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ። በ1980ዎቹ በሴኔጋል የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የተቀሰቀሱ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እና የተማሪዎች ተቃውሞዎች ይኸው የሙዚቃ ሥልት በአገሪቱ እንዲያብብ እና እንዲያድግ አስተዋፅዖ አድርገዋል። #77% #77ከመቶው

https://p.dw.com/p/32DQH
Symbolbild Mikrophon Rap Musik
ምስል Ignatius Wooster/Fotolia

ራፕ እና ሒፕ ሆፕ ለሴኔጋል ወጣቶች የመታገያ መሳሪያ ሆነዋል

የሒፕ ሆፕ የሙዚቃ ሥልት ከምዕራቡ ዓለም ተሻግሮ ሴኔጋል ሲደርስ በሒደት የሚጠፋ የአንድ ሰሞን ዝንባሌ ተደርጎ ይታይ ነበር። የተገመተው ሳይሆን ቀርቶ የሙዚቃ ሥልቱ ወደ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሐሳብን የመግለጫ እንቅስቃሴ ቀይሮ ከ30 አመታት በኋላም አሁን ሊከበር በቃ። በሥርዓቱ የተገፉ ወጣቶች በፍጥነት ለመዱት፣ ለራሳቸው እንዲስማማ አድርገው ለወጡት፣ ግጥሞቹን በአገሪቱ በሚነገረው የዎሎፍ ቋንቋ ጻፉ ከዚያም የራሳቸው ድምፅ አደረጉት። 
ለመሆኑ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1988 አዲስ የዜማ እና የግጥም ትውልድ እንዲፈጠር ያደረገው ብልጭታ ምን ነበር? በደካማ የትምህርት ሥርዓት፣ የመምህራን ሥራ ማቆም አድማ እና የተማሪዎች ተቃውሞ ምክንያት የአመቱ ትምህርት ጊዜ ተሰረዘ፤ ተማሪዎችም አንድ አመት ወደ ኋላ ለመጎተት ተገደዱ። የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ማታዶር በዚህ ዓመት የተዘጋጀውን የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጀው የአፍሪካልቸርአርባን ማኅበር መስራች ነው። 

“በ1998 ባዶ ብለን የጠራነው አመት ነበር። አብዛኞቹ የእኔ ትውልድ አባላት ከትምህርት ጊዜያቸው አንድ አመት ተቃጥሎባቸዋል። በዚያ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት አንሔድም። ለትግሉ ቁርጠኛ ሆነን ጊዜያችንን የራፕ ግጥሞች ስንፅፍ እና የትምህርት ሥርዓቱን እጅግ መጥፎ ያደረገውን መንግሥት በመታገል እናሳልፍ ነበር። አንድ አመት እንደዚያ መቃጠሉን ለማመን ይቸግራል”                                                                                                                                                                                                
ከ30 አመታትም በኋላ ራፕ ተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳዮችን ያነሳል። የፍትኅ እጦት የተጫነው፣ የመደብ ልዩነት የከፋበት ማኅበረሰብ። ማታዶር "30 አመታት ነጎዱ፣ ያኔ ሥልጣን ላይ የነበረው እና ዜጎቹን ማርካት የተሳነው ሥርዓት አሁንም አለ። በተለይ ከከተሞች ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች እና ችላ በተባሉ የመኖሪያ መንደሮች ምንም የለም። ከ30 አመታት በኋላም በዚች አገር ምላሽ የሚፈልጉ ችግሮች በመኖራቸው እኛ አሁንም አለን። መፍትሔ ለማግኘት ስለ ችግሮቹ መነጋገር አለብን። ያን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኞች ናቸው" ሲል ይናገራል።
የራፕ እና የሒፕ ሆፕ የሙዚቃ ሥልቶች በአሜሪካ ብቅ ያሉት በጎርጎሮሳዊው 1970ዎቹ አመታት ነበር።  ሴኔጋል ከአትላንቲክ ባሻገር በሚነፍሰው የሁለቱ የሙዚቃ ሥልቶች ተፅዕኖ አድሮባት የራሷን ድምፅ ለማበጀት አልዘገየችም። ኒክስ በሚል የመድረክ ስሙ የሚታወቀው የሴኔጋል የሒፕ ሆፕ የሙዚቃ አቀንቃኝ ኒኮላስ ኦማር ዲዮፕ እንደሚለው ሁለቱን የሙዚቃ ሥልቶች ቀድማ በመቀበል ሴኔጋል ከአፍሪቃ ቀዳሚ አገሮች አንዷ ነች። 
ኒክስ “ለዩናይትድ ስቴትስ ያላት ቅርበት ትልቅ ሚና ነበረው። ምክንያቱም ብዙ ሴኔጋላውያን ኒው ዮርክን በመሳሰሉ ከተሞች ይሰራሉ፤ ይኖራሉም። በሐርለም 116ኛው ጎዳና ትንሿ ሴኔጋል የተባለ መንደር ይገኛል። ብዙ ሴኔጋላውያን ወደ አሜሪካ ስለሚመላለሱ በዚያ ስለሚሆነው ነገር ብዙ መረጃ ነበረን። ልጅ እያለሁ በአሜሪካ የሙዚቃ ገበያ የሚወጡ አዳዲስ የሙዚቃ ቪዲዮዎች አግኝተን እንለዋወጥ ነበር። ለሒፕ ሆፕ በጣም ቅርበት ነበረን" ሲል የልጅነት ዘመኑን ያስታውሳል።
ኒኮላስ ኦማር ዲዮፕ እንደሚለው የአዲሱ ትውልድ የራፕ አቀንቃኞች ሥልቱን ከማኅበረሰባዊው ሙዚቃ ጋር በመቀላቀል የራሱ የሆነ ድምፅ ሰጥተውታል። “ዛሬ አዲሱ ትውልድ አዲስ ነገር አቅርቧል። ትራፕ፣ አፍሮ-ትራፕ የመሳሰሉት የአሁኖቹ የራፕ ሥልቶች ከአፍሪካ እና የሴኔጋል ዜማዎች ጋር የተቀላቀሉ ናቸው። ይኸ መጥፎ አይደለም። እንዲያውም አስደናቂ ነው"

የቀደሙትን ከአዲሶቹ ከመቀላቀል ባሻገር አቀንቃኞች ሙዚቃቸውን ለማውገዝ እና ለመተቸት ጭምር ይጠቀሙበታል። መቀመጫውን በደቡባዊ ሴኔጋል ላደረገው ሐርድኮር ሳይድ የተባለ የሙዚቃ ቡድን በነፃ አውጪ አማፅያን እና በመንግሥት መካከል ያለው ትንቅንቅ በሥራቸው ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ አለው። ፓፓ ንዲያዬ ቲዮ ከሶስቱ የሙዚቃ ቡድኑ አባላት መካከል አንዱ ነው። 
“በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሐሳቦች ለሥራችን መነሳሳት ይፈጥሩልናል። በአገራችን በነፃ አውጪዎች እና በሴኔጋል መንግሥት መካከል ግጭት አለ። ሰላም ተመልሶ እስኪሰፍን የመታገል ግዴታ አለብን። 

የመምህራን የሥራ ማቆም አድማዎች፣ ጦርነቶች፣ ፖለቲካዊ ኹከት.....የራፕ አቀንቃኞች እና ገጣምያን ሥራዎቻቸው ሁሉ በዙሪያቸው እየሆነ ባለው የተቃኘ ነው። የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኞቹ ዜናን እንዳዩት ያለ ወገንተኝነት እንደ ወረደ እነሱ ጠቃሚ ነው ብለው ባመኑት መንገድ የሚያቀርቡበት የዜና መጽሔት  ለእነሱ ተስማሚ ነው። እንዲህ አይነቱን አቀራረብ የፈጠሩት በጣምራ የሒፕ ሆፕ ሙዚቃን የሚያቀነቅኑት ኹመን እና ኬይቲ ናቸው። ለዦርናል ራፔ ወይም ዜና በራፕ የተሰኘው መሰናዶ ፖለቲከኞችን ይገዳደራል፤ ብዙውን ጊዜ የከፋውንም አጥብቆ ይተቻል። መሰናዶውን ኹመን በፈረንሳይኛ ጄይቲ ደግሞ በዎሎፍ ያቀርባሉ። 
ሁለቱ አቀንቃኞች ጠንካራ ተከታታይ አላቸው። በዩቲዩብ እንኳ እያንዳንዱ ሥራቸው ከ40,000 ጊዜ በላይ ታይቷል። ኹመን   "መንግሥትን በሚያገለግሉ መገናኛ ብዙኃን የሚቀርብ መረጃ ወገንተኛ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚደርሰን መረጃ በማጣሪያ ውስጥ የሚያልፍ ነው። ምን አልባት በጥንቃቄ ማጣሪያውን መመልከት ከቻልን ነገሮችን በተለየ መንገድ ልንገነዘብ እንችላለን። በመካከል ያለውን እንቅፋት በማስወገድ ሰዎች ያለ ማጣሪያ ነገሮችን ጥርት አድርገው መመልከት እንዲችሉ መረጃ በቀላሉ የሚገኝ እንዲሁን ማድረግ እፈልጋለሁ" ይላል።  

የ47 አመቷ አርቲስት እና ፊልም አዘጋጅ ፋቱ ካንዴ ሴንጎር በተደጋጋሚ ከሒፕ ሆፕ ጋር የዕድሜ እኩዮች ነን ሲሉ ይደመጣል። በአሁኑ ወቅት በሚያዘጋጁት ፊልም የሙዚቃ ሥልቱን ታሪክ እየሰሩ ነው። 
 
“ቋንቋችን ፍሰት ስላለው ለሙዚቃ ሥልቱ የተመቸ ነው። ሴኔጋላውያን ሳልሳ፣ አር ኤንድ ቢ እና ሬጌ የመሳሰሉ ሙዚቃዎችን ያደምጣሉ፣ ይደንሳሉም። የሬጌ ሙዚቃ ለእያንዳንዱ ዜጋ እጅግ ቅርብ ነው።  ሁሉም የሙዚቃ ሥልቶች ይስማሙናል። 

ፋቱ ከሶስት አመታት በፊት በሴኔጋል የራፕ የሙዚቃ ሥልት ላይ ያተኮረ መፅሀፋቸው ለንባብ በቅቷል። ባለሙያዋ የመፅሀፍ ሥራቸው ዛሬ ላሉበት ደረጃ ላደረሳቸው የሙዚቃ ሥልት እንደ እጅ መንሻ ያቀረቡት ነው። 
“በሙዚቃ ስልቱ ላይ የተዘጋጀ የመጀመሪያው መፅሀፍ ነው። ምግብ የማብሰል ስራዋ...  ስብሰባዎቿ ሲጠናቀቁ ልጇን በጀርባዋ አዝላ ወደ ሙዚቃ ድግሶች ትሔድ በነበረች ሴት የተዘጋጀ የመጀመሪያው መፅሀፍ ነው። ከዚያ ሁሉ ባሻገር  ሙዚቃውን አዳምጣለሁ፣ ኮንሰርቶቹን እመለከታለሁ...ያለ ምንም ማወሳሰብ ሙዚ ቃውን አጣጥማለሁ
ፋቱ የራፕ የሙዚቃ ሥልት የባህል እና የዕድሜ ልዩነቶች የሚሻገር ለመሆኑ ምስክር ናቸው። ከ30 አመታት በኋም ራፕ በሴኔጋል እያደገ ነው። ከፊቱ ግን መልካም ዕድል እና በርካታ ሥራ ይጠብቀዋል።  
ኢማኑዌል ላንዳይስ /እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ