1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ ዓመት እና የወጣቶች ግብታዊ እርምጃዎች

ዓርብ፣ መስከረም 4 2011

የ2011 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ DW ለወጣት አድማጮቹ የተለያዩ ጥያቄዎች አቅርቦ ነበር። ባለፈው ዓመት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ ወጣቶች ዘንድ የተስተዋለው የስርዓት አልበኝነት እና የመንጋ ፍርድን አስመልክቶ የቀረበው ጥያቄ አንዱ ሲሆን “በአሁኑ ወቅት የወጣቶች ዋነኛ ጥያቄዎች ምንድናቸው?”  የሚለው ደግሞ ሌላኛው ነው።

https://p.dw.com/p/34tEy
Äthiopien Demonstration Untersützung für Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

አዲሱ ዓመት እና የወጣቶች ግብታዊ እርምጃዎች

በኢትዮጵያ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ለውጥ ዋናውን ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ወጣቶች ከቀናት በፊት የተሰናበትነውን 2010 ዓ. ም. ያሳለፉት በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ነበር። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ በርካታ ወጣቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ጉዳት የደረሰባቸውም ብዙዎች ናቸው። በሺህዎች የሚቆጠሩቱ ደግሞ በጊዜውታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በሀገሪቱ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ መሪነት መንበር ከመጡ በኋላ የታዩ ለውጦች ግን ብዙ ወጣቶችን ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረጋቸው ይመስላል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም በየቦታው ተቃውሞዎች አልቆሙም። ወጣቶች በየቦታው እየወሰዷቸው ባሉ እርምጃዎች ስርዓት አልበኝነት እና የመንጋ ፍርድ እየተስፋፋ ነው የሚል ስጋት ይደመጣል። የወጣቶች ግብታዊ እርምጃዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ትልቅ ፈተና እንደሆነ የሚናገሩም አሉ።በአማራ ክልል የሀብሩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ኑርዬ ይማም የተባሉ የDW ተከታታይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እየወሰዷቸው ላሏቸው ለውጦች በጎ አመላካከት አላቸው። ሆኖም በአካባቢያቸው የሚያስተውሏቸው የወጣቶች እርምጃዎች የመንግስትን መኖር እስከመጠራጠር እንዳደረሳቸው ይናገራሉ። 

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

“በጣም የሚገርማችሁ አሁን ባለንበት ጊዜ በየአስፋልቱ፣ በየከተማው፣ በየገጠሩ ባሉት አስፋልቶች አካባቢ ሁሉም ሌባ ሆኖ እየተዘራረፈ ይገኛል። አብይ እየገዛው ነው ለማለት ደፍረን ለመናገር አንችልም፤ አልቻልንም። በቃ! አንዱ አንዱን እየተዘራረፈ፣ ታሳቢ መኪኖች በድንጋይ ድርድር፣ በመሳሪያ እየታገዱ [ነው]። ሁሉም መሳሪያ ገዝቷል። ማንኛው ህጋዊ ነው፣ ማንኛው ህገ ወጥ ነው ሊታወቅ አልቻለም። ያው አብይ አህመድ እንደ ንግግሩ፣ እንደ አፉ ጥሩ ነው። ያው ግን ስራውን አልጀመረም። ምንም የሰራው ነገር የለም። እልቂት፣ መፈናቀል፣ መጋደል፣ አንዱ አንዱን መበደል እንጂ ምንም የታየ ነገር የለም” ብለዋል። 

ከዚያው ከአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ አስተያየታቸውን የላኩልን ይትባረክ የተባሉ ወጣትም “የለውጡ ደጋፊ ነን” በሚሉ ወጣቶች አማካኝነት በአካባቢያቸው ችግር መከሰቱን ይገልጻሉ። ወጣቶቹ “ከዚህ ቀደም በስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን በጅምላ ወንጀለኛ በማድረግ፣ ሌቦች ናቸው ቤታቸው ይፈተሽ በማለት ህብረተሰቡን ግጭት ውስጥ እየከተቱት ነው” ይላሉ። ለዚህም ሰሞኑን በሚኖሩበት አካባቢ የተከሰተውን በምሳሌነት ያነሳሉ። 

“ሰሞኑን የወረዳ አመራሮች ወደዚህ ወደ እኛ ሰፈር ቀበሌ ነችና የቀበሌ አመራር ለመገምገም ይመጣሉ። ሲገመግሙ 15 ወጣቶች የለውጥ ደጋፊ ነን ብለው ተደራጅተዋል።  ዘጠና ዘጠን በመቶ የሚሆነው ህብረተሰብ ድሮ የነበረው ሊቀመንበር ደጋፊ ነው። ወይም ያ እንዲቀየር አይፈልግም።  የወረዳዎቹ አመራሮች መጥተው ከመረጡ በኋላ እነርሱን አላስኬድም ብለው መንገድ ዘጉ፣ በጣም ብዙ መኪና [ቆመ]።  አስራ አምስቱ ወጣቶች ወደ ስድስት ሰዓት አካባቢ መንገድ ዘግተው፣ የተወሰነ ግርግር ተፈጥሮ ነበር። አሁንም ራሱ የተለያዩ አድማዎች አሉ። ብቻ ትንሽ ነጻነቱን ያለመሸከም ነገር አለ። ያ ትንሽ ስጋት ላይ ጥሎናል። እኛ ወጣቶች ላይ በጣም ትልቅ ችግር አለ” ይላሉ የለጋምቦው ወጣት። 

Äthiopische Volksgruppe der Oromos Protest
ምስል Getty Images/AFP

ከመንገድ መዝጋት እስከ ዘረፋ፣ ከድብደባ እስከ የሰው ህይወት ማጥፋት ድረስ ወጣቶች በየአካባቢው እየወሰዷቸው ያሏቸው እርምጃዎች መንግስትንም ያሳሰበው ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ነሐሴ ወር በሰጡት መግለጫ “ለሕግ ተገዥነትን ወደ ጎን የማድረግ ትልቅ ዝንባሌ በኢትዮጵያ እየታየ ነው” ብለው ነበር። “በስሜትና በጥላቻ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ሕግን ወደ ራስ ፍላጎት እና ስሜት በመውሰድ በመንጋ የሚሰጡ ስርአት አልባ ፍርዶች፣ ለሕግ የበላይነት ትልቅ ፈተና ” መሆኑን ገልጸው ነበር። 

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ “አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎችን” መንግስታቸው እንደማይታገስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስጠነቀቁ በኋላ አጥፊዎች ናቸው የተባሉ መታሰራቸው ቢነገርም ድርጊቶቹ ግን ጭርሱኑ  አልቆሙም። አደረጃጀታቸው በግልጽ በማይታወቀው እንደ ቄሮ እና ፋኖ ባሉ የወጣት ስብስቦች ስም በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች መከሰታቸውን ቀጥለዋል።

ራሳቸውን የፋኖ አርበኛ ብለው የሚጠሩ አንድ የDW አድማጭ “የወጣቱም ሆነ የህዝቡ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ተቃውሞው በየትኛውም ቦታ ሊቆም አይችልም” ብለዋል። ምክንያቱም ይላሉ እኚህ አድማጭ ፦ 

“ምክንያቱም ህዝቡ የጠየቀው ሌላ ነው፤ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሌላ ነው። ስለዚህ ከቃላት የዘለለ ነገር አልታየም። ሰዎች፣ ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ። ዛሬም በራያ፣ በወልቃየት እና በጸለምት አካባቢ ብዙዎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ። ስለዚህ የለውጡ ኃይል ይህን ነገር ማስተካከል እስካልቻለ ድረስ፣ ስርዓቱን መቀየር፣ ህገ መንግስቱን ማሻሻል፣ በህወሓት ላይ እርምጃ መውሰድ እና የህግ አስፈጻሚው አካል ጉልበት አግኝቶ የህግ ተጠያቂነት እስካላሰፈነ ድረስ ተቃውሞውም እንደሚቀጥል ነው የምናውቀው” ይላሉ የፋኖ አርበኛ ነኝ የሚሉት አድማጭ። 

“የወጣቶች አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምንድናቸው?” ስንል ለአድማጮች ላቀረብነው ጥያቄ ከተሰጡ ምላሾች በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ የተነሳው የስራ አጥነት ችግር ነው። በአዲሱ ዓመት ወጣቶች ለእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ማግኘት ይጀምራሉ የሚል እምነት ያላቸው አድማጮቻችን በርከት ብለው ታይተዋል። በወጣቶች በኩል የሚታየው የደቦ ፍርድ እና ግብታዊ እርምጃዎችም እየተቀየሩ ይመጣሉ የሚል ተስፋ አላቸው።   

(ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ) 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ