1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይማኖት አባቶች የመስጊዶቹ መቃጠልን አወገዙ

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2011

ሰሞኑን በጎንደር እስቴ እና አንዳቤት አካባቢ በመስጊዶች ላይ የደረሰዉን ቃጠሎ የሃይማኖት መሪዎች «እኩይ ተግባር» በማለት ተቃወሙት። የባሕር ዳርና የአማራ ክልል የክርስትና እና የሙስሊም የሃይማኖት አባቶች እንደሚሉት ቃጠሎዎቹ ኅብረተሰቡን ወደ አልተገባ ርምጃ ለማስገባት የሚደረጉ ጥረቶች በመሆናቸው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/3DE0W
Symbolbild Religion Islam Christentum
ምስል AP Graphic / DW-Fotomontage

«ለትርምስ ኃይሎች ክፍተት መፈጠር የለበትም»

ምዕራባዊና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በተለያዩ ግጭቶች ሲታመሱ፣ ቤቶች ሲቃጠሉ ህይዎት ሲጠፋና መንገዶች ሲዘጉ ሰንብተዋል፣ አሁንም ቢሆን በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም አለ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ያለ አይመስልም፡፡

በነዚህ ዞኖች ያለው ችግር መቋጫ ሳያገኝ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከደብረ ታቦር ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የዓለም ሳጋ ጥብቅ ደን ላይ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ በህበረተሰቡ ርብርብ እሳቱ ሳይዛመት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ጎንደር አዘዞ በማደሪያ ቤት ያሉ 51 የቀንድ ከብቶች በእሳት ተቃትለው ሞተዋል፡፡

በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ጎንደር አስቴ ወረዳ መካነ እየሱስ በአንድ የሙስሊም ሰርግ ላይ ክርስትናን የሚነቅፍ ሁኔታ ታይቷል በሚል ሁለት መስጊዶች ተቃትለዋል፣ ሱቆችም ተዘርፈዋል፡፡ ጥቂት ሳይቆይ በዚሁ ዞን አንዳቤት ወረዳ ጃራ ገዶ በተባለ አካባቢ አሁንም ሌላ መስጊድ በእሳት ነዷል፣ ቅዱሳት መጽሐፍትም ተቃጥለዋል፡፡

ሼህ ሰኢድ ሙሀመድ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕረዚደንትና የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ምክትል ሰብሳቢ እንደሚሉት አስልምናና ክርስትና እየተደጋገፉ የኖሩ፣ ቤተ እምነታቸውን በጋራ ሲሰሩ የኖሩ ናቸው እናም እውነተኛ አማኞች ቤተ እምነትን አያቃጥሉም፡፡

የህግ አካላት አጥፊዎችን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚናገሩት ሼህ ሰኢድ ህብረተሰቡ በመደራጀትና አንድነትን በመፍጠር ለትርምስ ኃይሎች ክፍተት መፍጠር የለበትም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህር ዳር አገረ ስብከት ስራ አስኪያጅና የአማራ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ መለአከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለምም ቢሆን ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግስት ቀድሞ መድረስ አለበት፣ ህብረተሰቡም በመራጀት አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ እንደ መለአከ ሰላም ኤፍሬም “ሀይማኖት የሚሞቱለት እንጂ የሚገሉለት አይደለም።” ፖሊስ እስካሁን እያደረገ ያለው ምርመራ  አጥጋቢ አይደለም ያሉት ሼህ ሰኢድ በዚህ ረገድ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አጠቃላይ ስላለው ሁኔታ እንዲያስረዳኝ የኮሚሽኑን ምክትል ኮሚሽነር ብጠይቅም ጉዳዩ በምርመራ ላይ ስለሆነ ዝርዝር መረጃ አልሰጥም ብሏል፡፡ ምርመራ ሲጠናቀቅ ለህዝብይፋ እንደሚያደርግ በመጥቀስ፡፡

ዓለምነው መኮንን 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ