1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል መሣሪያ የማውደም ተግባር

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2016

በትግራይ ክልል ትልቁ የሕክምና ተቋም ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ሆን ተብሎ የሕክምና መሣርያዎችን የማውደም ተግባር መፈፀሙ ተገለፀ። ይህ የማውደም ድርጊት ሲፈፀም የሚያሳይ በድህንነት ካሜራ የተቀረፀ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታር በኩል የተሰራጨ ሲሆን፥ ፖሊስ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎችን መያዙ ዐስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/4ehvZ
Äthiopien Tigray-Region Mekelle 2024 | Ayder Krankenhaus
ምስል Million H. Silase/DW

የሕክምና መሣሪያዎቹ ሆነ ተብሎ ሲወድሙ ታይቷል

በትግራይ ክልል ትልቁ የሕክምና ተቋም ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ሆን ተብሎ የሕክምና መሣርያዎችን የማውደም ተግባር መፈፀሙ ተገለፀ። ይህ የማውደም ድርጊት ሲፈፀም የሚያሳይ በድህንነት ካሜራ የተቀረፀ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታር በኩል የተሰራጨ ሲሆን፥ ፖሊስ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎችን መያዙ ዐስታውቋል ። 

በትግራይ ክልል ትልቁ በሆነው እና መቐለ በሚገኙ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በሕክምና መሳርያዎች የሚፈፀም ውድመት እንዲሁም የመድኃኒቶች እና ሌሎች ቁሶች ዝርፍያ አሳሳቢ ሆኖ እንዳለ በተቋሙ ሠራተኞች እንዲሁም ተገልጋዮች ይገለፃል። በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የትግራይ የጤና ዘርፍ መልሶ ለመገንባት ጥረት በሚደረግበት ወቅት በቅርቡ  በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል  ትላልቅ የሕክምና መገልገያ ማሽኖች ሆን ተብሎ የተፈፀመው የማውደም ድርጊት አነጋጋሪ ሆኗል።

በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ገጾች የተሰራጨ እና ሆስፒታሉ ትክክለኛ መሆኑ ያረጋገጠልን በደህንነት ካሜራ የተቀረፀ ምስል ማንነት እንዳይለይ እራሱን የሸፈነ ግለሰብ በሆስፒታሉ ትልቅ ማሽን ላይ ጉዳት ሲያደርስ ያሳያል። እንደ የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃ ገብረእግዚአብሔር ገለፃ በዚህ ሆን ተብሎ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 21 ለሊት የተፈፀመ ድርጊት የሆስፒታሉ ንብረት የሆነ እና ከአንድ መቶ በላይ ምርመራዎች ማድረግ የሚችል ኮባስ ስድስት ሺህ የተባለ ማሽን ላይ ጉዳት መድረሱ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራርያ አንስተዋል።

ይህ ሆን ተብሎ የተፈፀመ የሕክምና መሣርያ የማውደም ተግባር ፖሊስ እየተከታተለው መሆኑ እንዲሁም አራት የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሆኑ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ደግሞ የዓይደረ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ገብረክርስቶስ ፋሲል ተናግረዋል።

በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ጨምሮ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት  የምርመራ ማሽን ተበላሽቷል፣ ግብአት የለም በሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ተገልጋዮች የተለያዩ ምርመራዎች ውጭ ባሉ የግል ተቋማት እንዲያደርጉ እንደሚደረግበት፥ በዚህም ላልተፈለገ ከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩ በማንሳት ቅሬታ የሚያቀርቡት በርካታ ናቸው። በሆስፒታሉ አገልግሎት ሲያገኝ ያገኘነው አስተያየት የሰጠን አቶ ያሬድ ፀጋብርሃን ድርጊቱ በአጠቃላይ የጤና ስርዓቱ ያለ መጥፎ ሁኔታ ያጋለጠ አሳፋሪ ተግባር ይለዋል።

በመቐለ፤ ትግራይ ክልል የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ። ፎቶ ከማኅደር
በመቐለ፤ ትግራይ ክልል የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Million Hailesilassie/DW

አስተያየት ሰጪው በተለያየ ግዜያት ማሽን ተበላሽቷል፣ ግብአቶች የሉም፣ መድሃኒት የለም በሚሉ ምክንያቶች ከሆስፒታሉ ውጭ ሄዶ ምርመራዎች እንዲያሰራ መደረጉ የሚገልፅ ሲሆን ይህ የሚሆነው ውስጥና ውጭ ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች ተመሳጥረው በሚፈፅሙት ሴራ ሳይሆን እንደማይቀር ለነበረው ጥርጣሬ የሰሞኑ ክስተት ትልቅ ተጨማሪ ማሳያ እንደሆነው ይናገራል።

በትግራይ በጦርነቱ ወቅት 80 በመቶ በሚሆኑ  የጤና ተቋማት  ላይ በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት የደረሰ ሲሆን፥ እነዚህ መልሶ ለመጠገን እንዲሁም ከሥራ ውጭ የሆኑ ወደ ስራ ለመመለስ ጥረቶች እያደረጉ መሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ ይገልፃል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ