1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ተፋላሚ ኃይላት ስምምነትና ዉጊያ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2011

የጦርነቱ መራዘም፤ በሰላማዊዉ ሕዝብ ላይ የደረሰዉ እልቂት፤ ረሐብ እና በሽታ፣ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂ ግድያ ጋር ተዳምሮ በየአካባቢዉ የጫረዉ ተቃዉሞ የጦርነቱ አቀጣጣዮች መስማት ያልፈለጉትን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

https://p.dw.com/p/3AH70
Schweden | Friedensgespräche Jemen-Konflikt in Rimbo
ምስል picture-alliance/dpa/TT NYHETSBYRÅN/P. Lunahl

የመን፤ ሠላም እና ጦርነት

የየመን ተፋላሚ ኃይላት ሰላም ለማዉረድ «የመጀመሪያ» የተባለዉን ዉል ተፈራረሙ።የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተሮች የፕሬዝደንታቸዉን አቋም ተቃርነዉ ወሰኑ።የቴሕራን-ሪያድ ባላንጣ መንግሥታት፣የዋሽግተን-ኒዮርክ ዲፕሎማቶች ስምምነቱን ደገፉ።የሠላም ተስፋ ያጣዉ የየመን ሕዝብ እንደገና ተስፋ አደረገ።የተፋላሚ ኃይላት የቃላት እንኪያ ሠላንታ፤ የሥልታዊቱ የወደብ ከተማ ዉጊያ ጥፋት ግን በስምነት ተስፋዉ ብልጭታ ማግሥትም እንደቀጠለ ነዉ።ተስፋ እና ቀቢፀ ተስፋ።የስምምነቱ ይዘት፤ የድጋፍ-ግፊቱ ብርታት፤ ተስፋ ቀቢፀ ተስፋዉ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሪምቦ።የመኖር እስትፋንሷ በትልቅ፣ደማቂቱ ስቶክሆልም ላይ የተመሠረተ ትንሽ ከተማ ናት።እንቅልፍ የሚያጎላጃት ይመስል ዝም ያለች ናት።ፀጥ።በዚያ ላይ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ክረምት ከሰሜንም-የሰሜን አዉሮፓዊቱን ከተማ አየር ክፉኛ ተጫችኖታል።ይበርዳል።ጨለማ ነዉ።ለእንግዳ ቀኑን ከሌቱ መለየት ይከብዳ።

የሰነዓን ግርግር፣ ትርምስ፤ የሪያድን ሙቀት-ድምቀት ለለመደ ሰዉማ የቀዝቃዛ-ጨለማ፣ አንቃላፊዋን ከተማ አየር መላመድ አዳጋች ነዉ።የመናዊ ስዊድንቷ ጋዜጠኛ አፍራሕ ናስር እንደምትለዉ ደግሞ ከባዱ አየር፤ ጭለማ እና ዝምታዉ ለእንግዶቹ አይደለም ለሷ እና ለብዙ ብጤዎችዋ ጋዜጠኞችም ከባድ ነበር።መረጃ ለማግኘት እንደልብ መሯሯጥ አይቻልም።በዚያ ላይ ድርድሩ የሚደረገዉ በዝግ ነዉ።የጋዜጣዊ መግለጫዉ ጊዜ ይቀያየራል።

ተደራዳሪዎች በየነጥቦቹ ላይ ለመወሰን ሰነዓ እና ሪያድ ከሚገኙ አለቆቻቸዉ ፈቃድ እስኪያገኙ ድረስ መጠበቅ ግድ ነዉ።«አብዱልመልክ አል ሁቲ (የአማፂያኑ ቡድን መሪ) ከሰነዓ እና አብድረቦ መንሱር ሐዲ (የስደተኛዉ የየመን መንግስት ፕሬዝደንት) ከሪያድ መጥተዉ ቀጥታ ቢደራደሩ ሳይሻል አይቀርም ነበር የሚሉም ነበሩ» ትላለች ጋዜጠኛዋ።ግን የጦርነቱ መራዘም፤ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ጥፋት፤የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂ ግድያ የቀሰቀዉ አዋራ የዋሽግተን-ለንደን ወዳጆችን፤ የሪያድ-አቡዳቢ ተከታዮቻቸዉንም በጥፍራቸዉ ስላቆመ-የሪምቦ ተሰብሳቢ-ሰብሳቢዎች ቅዝቃዜ፣ጭለማ ዝምታዉን ሰብረዉ ማድረግ ያለባቸዉን ማድረግ ነበረባቸዉ።አደረጉ።ባለፈዉ ሰወስት ዓመት ከመንፈቅ የመን ላይ ይሆናል ተብሎ የማይታሰበዉ ሆነ።አርብ።የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ተጨባበጡ።

Schweden | Friedensgespräche Jemen-Konflikt in Rimbo
ምስል picture-alliance/dpa/TT NYHETSBYRÅN/P. Lunahl

ሁለቱን ለማጨባበጥ ከኒዮርክ ሪምቦ የበረሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንዳሉት ስምነቱ የሚሊዮን የመናዉያንን ችግር ለማቃለል ጠቃሚ ነዉ።

 «ስለሁዴይዳ ወደብ እና ከተማ ተስማምተናል።በስምነቱ መሠረት የሁለቱም ወገኖች ተፋላሚዎች ከወደቡ እና ከከተማዋ ይወጣሉ።በመላዉ አስተዳደር ተኩስ ይቆማል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወደቡ አጠቃቀም ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታል።ይሕ ለሰላማዊዉ ሕዝብ የሰብአዊ ርዳታ ቁሳቁስ ማድረስን ያጠቃልላል።የብዙ ሚሊዮን የመናዉያንን ኑሮ ለማሻሻል ይጠቅማል።»

ተፋላሚዎች ስለ ወደብ ከተማይቱ ከመስማማታቸዉ በፊት የምርኮኛ ልዉዉጥ ለማድረግ ተስማምተዋል።በስምነቱ መሠረት የሁቲ አማፂያን የቀድሞዉን የየመን መከላከያ ሚንስትር እና  የሳዑዲ አረቢያ ወታደሮችን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ምርከኞችን ይለቃሉ።የፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ስደተኛ መንግሥት ደጋፊዎች እና ሳዑዲ አረቢያ የምትመራዉ የተባባሪ ሐገራት ጦርም የማረካቸዉን የሁቲ አማፂያንን ይለቃሉ።

ስምምነቱ የቦምብ-ሚሳየል፤ የጥይት-አዳፍኔ አረር ያጋጋለዉን ስሜት የሪምቦ ከባድ ቅዝቃዜ-ጥልቅ ዝምታ እና ድቅድቁ  ጨለማ ቀዝቀዝ፣ሰከን፤ ዋጥ ያደረገዉ አስመስሎታል።ከመሰለዉ ይልቅ ግን ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ሳዑዲ አረቢያ የምትመራዉን ጦር በገፍ የምታስታጥቀዉ የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ሪምቦ ላይ የሆነዉ እንዲሆን ትልቅ ጫና አሳድሯል።

ሐሙስ ቀን የተሰየመዉ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔት በአብላጫ ድምፅ ባሳለፈዉ ዉሳኔ ኢስታንቡል-ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ ቆስላ ዉስጥ ለተገደለዉ ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂ ግድያ የሳዑዲ አረቢያዉን አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን (MBS ይሏቸዋል) ተጠያቂ አድርጓል።

በጋዜጠኛዉ መገደል እና የመን ዉስጥ በደረሰዉ ጥፋት ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ፣ የሳዑዲ አረቢያን ጦር ማስታጠቅ እና መርዳታዋን እንድታቆምም ወስኗል።ዉሳኔዉ በርግጥ ምልክታዊ ከመሆን ባለፍ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለሪያድ ነገስታት የሚሰጠዉን ድጋፍ እንዲያቆም አያስገድድም። ይሁና ለፓርቲ ያልወገኑት ሴናተር ቤርኒ ሳንደርስ እንዳሉት መልዕክቱ ጠንካራ ነዉ።

Schweden Friedensgespräche für Jemen starten vor Drohkulisse
ምስል Reuters/TT News Agency/S. Stjernkvist

                             

«የሕግ መወሳኛዉ ምክር ቤት ዛሬ በግልፅ ያለዉ፣ ጦራችን የአምባገነኑ እና የገዳዩ የሳዑዲ አረቢያ ሥርዓትን ተባባሪ እና ትዕዛዝ ፈፃሚ አይሆንም ነዉ።ዴሞክራሲን የማያከብር፤ሰብአዊ መብትን የማያከብር ሥርዓት ነዉ።የሥርዓቱ መሪ ፣ኢስታንቡል ቱርክ  በሚገኘዉ የሳዑዲ ቆስላ ዉስጥ ስደተኛዉን ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂን ለማስገደል እጃቸዉ እንዳለበት ማንም አይጠራጥርም።»

የየመንን ጦርነት ለማስቆም መፍትሔዉ ከሁቲ እና ከስደተኛዉ የየመን መንግስት ይልቅ በሪያድ፤በአብዳቢ፣ በቴሕራን፤ በዋሽግተን እና በለንደን መንግሥታት እጅ እንደሆነ የፖለቲካ ታዛቢዎች በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ነበር።የሰማቸዉ አልነበረም።

የጦርነቱ መራዘም፤ በሰላማዊዉ ሕዝብ ላይ የደረሰዉ እልቂት፤ ረሐብ እና በሽታ፣ ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂ ግድያ ጋር ተዳምሮ በየአካባቢዉ የጫረዉ ተቃዉሞ የጦርነቱ አቀጣጣዮች መስማት ያልፈለጉትን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

ለሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከራሳቸዉ ፓርቲ እንደራሴዎች ሳይቀር ግፊቱ ሲያይልባቸዉ፣ እሳቸዉ በተራቸዉ የሪያድ እና የአቡዳቢ ነገስታት ለድርድር እንዲገዙ ጫና ማሳደራቸዉ ሐቅ ነዉ።

ስምነቱ መፈረሙ ከስዊድን እንደተሰማ ለተስማሚዎች የምስራች ለመላክም የትራምፕን አስተዳደር የቀደም የለም።ለወትሮዉ በኢራን ይደገፋሉ የሚሏቸዉን ሁቲዎችን እናጠፋለን እያሉ ሲፎክሩ የነበሩት የሪያድ ገዢዎችም የዋሽግተን ደጋፊዎቻቸዉን ተከትለዉ ስምምነቱን አወድሰዋል።የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ እንዳለዉ በንጉስ ሠልማን እና በልጃቸዉ በአልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሠልማን ስም የወጣዉ መግለጫ «የመጀመሪያ» ከተባለዉ ስምምነትም በላይ ለዘላቂ ስምምነት ተጨማሪ ድርድር እንዲደረግ የሚጠይቅ ነዉ።

ሁቲዎችን ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ይረዳሉ የሚባሉት የቴሕራን ገዢዎችም ሥምምነቱን ደግፈዋል።ተፋላሚ ኃይላት ዘላቂ ሠላም ለማዉረድ የጀመሩትን ድርድር እንዲቀጥሉ አሳስበዋልም።ለወትሮዉ የየመን ጦርነት ሲነሳ ፣ ሪያዶች-ቴሕራኖችን፣ ቴሕራኖች በተቃራኒዉ ሪያዶችን ሳያወግዙ አያልፉም።

የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለፈዉ አርብ ባወጣዉ መግለጫ ስምምነቱን ከማድነቅ ባለፍ ሳዑዲ አረቢያን በስም አልጠቀሰም።የሳዑዲ አረቢያ መግለጫም ነቢዩ ሲራክ እንዳለዉ ኢራንን የጠቀሰዉ ባንድ ምክንያት አንዴ ብቻ ነዉ።

አሁን የተደረገዉ ስምምነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነዉ።የምርኮኛ ልዉዉጥ እና የወደብ ከተማይቱ የሁዴይዳ አስተዳደር ጉዳይ ።በየመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ግሪፊቲስ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገሩት ግን ያሁኑ ስምምነት በቀጥታ ከሚሰጠዉ ጥቅም ይልቅ ለወደፊት ለሚደረገዉ ድርድር ፈርቀዳጅ መሆኑ ነዉ-ትልቁ ተስፋ።

«ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ የባከነ ጊዜ በኋላ-አሁን፣የየመኑን ጦርነት ለማስቆም፣ አጠቃላይ መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገዉ ጥረት ተጀምሯል ማለት ተገቢ ነዉ።በዚሕ ሳምንት ስዊድን ዉስጥ ባደረግነዉ ስምምነት ተፋላሚ ኃይላት በብዙ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።»

የእርዳታ ድርጅቶች እንደዘገቡት ሰወስተኛ ዓመቱን ያገባደደዉ ጦርነት እና ጦርነቱ ያስከተለዉ በሽታ እና ረሐብ ከ57 ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅሏል።ከአስራ አራት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሐብ አጋልጧል።ጦርነቱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለዉ 15 ሚሊዮን ለሚገመቱ ሕፃናት ደግሞ የመንን «የምድር ላይ ሲዖል» አድርጎባቸዋል።

ዘመድ፣ወዳጅ፣ ወላጅ ዉላጁን ቀብሮ በመኖር-አለመኖር መሐል ለተቃረጠዉ የመናዊ ያሁኑ ስምምነት በርግጥ ትልቅ ተስፋ ነዉ።ይሁን የስምምነቱ መፈረም ከስዊድን እንደተሰማ ስልታዊቱ የወደብ ከተማ ሁዴይዳ በሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ቦምብ ሚሳዬል መንፈር ጀምራለች።ባለፈዉ ቅዳሜ በተጣለዉ ቦምብ እና ሚሳዬል ብቻ 21 ሰዉ መገደሉ ተዘግቧል።በስምምነቱ መሰረት በወደብ ከተማይቱ ላይ የታወጀዉ ተኩስ አቁም የሚፀናዉ ከነገ ጀምሮ ነዉ።

Jemen Sanaa Zerstörung
ምስል picture-alliance/Photoshot/Hani Ali

አንድ የሁቲ አማፂ ጦር አዛዥ ትናንት እንዳስጠነቀቁት በሳዑዲ አረቢያ የሚመራዉ ጦር በስምምነቱ መሠረት ነገ ማክሰኞ  ተኩስ ካላቆመ ጦራቸዉ አፀፋ ተኩስ ይከፍታል።«እነሱ ባሉት መሠረት ተኩስ አቁሙ የሚጀመረዉ ታሕሳስ 18 ነዉ።ከነገወዲያ ማለት ነዉ።ቃላቸዉን ያከብራሉ የሚል ተስፋ አለን።አለበለዚያ አፀፋ እርምጃ ለመዉሰድ ዝግጁ ነዉ።»

ድርድር እየተቀጠረ ሲቋረጥባት፤ ሰላም እየተወራ ጦርነት ሲያወድማት ሰወስት ዓመት ከመንፈቅ ላሳለፈችዉ የመን ፣ ቃል ገብቶ ቃል ማጠፍ በርግጥ አዲሷ አይደለም።ተኩስ አቁም አዉጆ ተኩስ እየተከፈተ ሥለዘላቂ ሰላም ተስፋ ማድረጉም ያሳስት ይሆናል።ይሁንና የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት የዉጪዉ ግፊት፤ መሰላቸቱ፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ አለመለየቱም ተፋላሚዎች ዉጊያዉን እንዲያቆሙ ያስገድዳቸዋል።የሁዴይዳ ድብደባ፤ ግጭት ወይም ያፀፋ ዉጊያ ዛቻዉም «ሒሳብን ከማወራረድ» ብቀላ ባለፍ ስምምነቱን የመጣስ ዓላማ የለዉም ባዮች ያይላሉ።ብቻ  እዉነቱን ያዉ ጊዜ ነዉ በያኙ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ