1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ሕፃናት እልቂት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2011

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንደሚለዉ የመን ዉስጥ በቀላሉ ሊታከም በሚችል በሽታ እና በምግብ ዕጥረት ብቻ በየአስር ደቂቃዉ አንድ ሕፃን ይሞታል።1.5 ሚሊዮን ሕፃናት ተሰድዋል።ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ልጆች ይዳራሉ። ወንዶቹ ለወታደርነት ይማገዳሉ።

https://p.dw.com/p/39tws
Jemen Mann macht aus seinem Haus eine Schule für 700 Kinder
ምስል Reuters/A. Mahyoub

Jemen-Eine Hölle auf Erden - MP3-Stereo

አራተኛ ዓመቱት የያዘዉ የየመን ጦርነት ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት እና ጥፋት ማድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ አስታዉቋል። ጦርነቱ ከማንም በላይ የሚገድል እና የሚጎዳዉ፣ ለበሽታ እና ረሐብ ያጋለጠዉም ለአካለ መጠን ያልደሱ ሕፃናትን ነዉ። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እንደሚለዉ ጦርነቱ እና የጦርነቱ መዘዝ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት አልቀዋል። ሚሊዮኖች ተርበዋል፣ተሰደዋል፣ ታመዋልም።የየመን ተፋላሚ ኃይላት ሠላም እንዲያወርዱ የUNICEF ኃላፊዎች እየጠየቁ ነዉ።

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የተባባሪ ሐገራት ጦር የአንሳር አላሕ (ሁቲ) አማፂያንን በወራት ዕድሜ ለማጥፋት ፎክሮ የመንን ካየር-ከምድር ማጋየት እንደጀመረ የሙኒራ አባት ሥራ ተዘጋ።መጋቢት 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሙኒራም ከዓለም መርገምቶች አንዱን መጋፈጥ ጀመረች።ረሐብ።ያኔ 3 ዓመት ከመንፈቋ ነበር። ጠኔዉ ሲደጋገም በሽታ ሆነ።
አባት ሥራ የላቸዉም። ገንዘብ የለም። ምግብ የለም። መታከሚያምም። እንደሙኒራ ሁሉ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የመናዊ ሕፃናት ሳይፈልጉ በመጡበት ዓለም፣ በማያዉቁት ጦርነት በረሐብ አለጋ ይጠበሳሉ። በበሽታ ይቆራመዳሉ።ለየመናዊቱ እናት ለወይዘሮ ሰብሪ ዓሊ ሻዳሕ ምግብ «ትዝታ» ነዉ።«ድሮ ሥጋ፣ ምግብ፣ሠላጣ ሁሉም ነበር።ዛሬ ምንም የለም።ምንም።ያለዉ ረሐብ ብቻ ነዉ።»
ረሐብ፣ በሽታ፣ ቦምብ ጥይቱ ሕፃናቱን ተራ-በተራ ያረግፋል።የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንደሚለዉ የመን ዉስጥ በቀላሉ ሊታከም በሚችል በሽታ እና በምግብ ዕጥረት ብቻ በየአስር ደቂቃዉ አንድ ሕፃን ይሞታል።1.5 ሚሊዮን ሕፃናት ተሰድዋል።ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ልጆች ይዳራሉ። ወንዶቹ ለወታደርነት ይማገዳሉ።
በመካከለኛዉ ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪቃ  የዩኒሴፍ ተጠሪ ጌርት ካፕላሬ ባለፈዉ ሳምንት ስቶክሆልም ሲዊድን ድርድር የተቀመጡ የየመን ተፋላሚዎችን ተማፀኑ።«ለሕጻናቱ ብላችሁ» እያሉ።«በዩኒሴፍ ሥም፣ ከሁሉም በላይ በ15ት ሚሊዮኑ ሕፃናት ሥም ስዊድን ለተሰበሰቡት የማናስተላልፈዉ መልዕክት አንድ ብቻ ነዉ።እሱም የሠላም መልዕክት ነዉ።ጨካኙን ጦርነት፣ ለረጅም ጊዜ በመላዉ የመን በሕፃናት ላይ የተከፈተዉን አስከፊ ጦርነት እድታቆሙ እንጠይቃለን።»

Jemen 2016 Kind von Binnenflüchtlingen bei Sanaa
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Mohammed
Hungersnot im Jemen
ምስል Reuters/K. Abdullah

የመን እነ ወይዘሮ ሰብሪ ዓሊ «ደጉ ዘመን» በሚሉትም በቅድመ ጦርነቱ ጊዜም ቢሆን ከአረብ ሐገራት ሁሉ በጣም የደኸየች ሐገር ነበረች።ዛሬ ደግሞ ምግብ፣ መድሐኒት፤ የመጠጥ ዉኃ የላትም።ሌላ ቀርቶ ሠላማዊ እንቅልፍ እንኳ ቅንጦት ነዉ።የከፋዉ በሕፃናቱ ላይ የሚደርሰዉ ሰቆቃ ነዉ።«ዛሬ ሰባት ሚሊዮን የየመን ሕፃናት እረሐብ እየፈደፈዳቸዉ ያድራሉ።1.8 ሚሊዮኑ በከፋ ረሐብ ይሰቃያሉ።ከነዚሕ ዉስጥ 4 መቶ ሺዉ ለሕይወት የሚያሰጋ ጠኔ ያቆራምዳቸዋል።ሁለት ሚሊዮን ሕፃናት አይማሩም።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሕፃናት በጦርነቱ ተገድለዋል።ሌሎች ለእድሜ ልክ አካላቸዉን እጥተዋል።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚቀጥለዉ 2019 ዓመት የመንን ለመርዳት 540 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንዲሰጠዉ ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ እየተማፀነ።ድርጅቱ በሳዑዲ ረአቢያ መራሹ ጦር የሚረዱት እና በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን ተፋላሚ ኃይላት ለማስታረቅ እየተጣጣረም ነዉ።የዓለም ፖለቲካን ባሻዉ የሚዘዉረዉ ኃይል፣ ኃብታም ዓለም ግን እልቂት፤ጥፋት፤ሰቃይ ሰቆቃዉን ከቁብ የቆጠረዉ አይመስልም።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ