1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻ መሸጥ ያዋጣ ይሆን?

ረቡዕ፣ ግንቦት 29 2010

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መንግሥት በብቸኝነት የተቆጣጠራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻ "ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል" ለመሸጥ አቅዷል። ውሳኔው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ከሚከተለው አቋም የተለየ ነው። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ግን ውሳኔው ውድድር የሌላቸው ጥቂት ሐብታሞችን የሚፈጥር እርምጃ ሲሉ ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/2z3FU
Boeing 787 Ethiopian Airlines
ምስል Reuters

ድርሻዎቻቸው ለገበያ ከቀረቡ መካከል አየር መንገድ እና ቴሌኮም ይገኛሉ

በኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ትውልድ እየተቀባበለ ያቆማቸው ቀደምት ተቋማት እና ኢትዮጵያ የምትገነባቸውን አዳዲስ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድርሻ ለገበያ ለማቅረብ ታስቧል። በውሳኔው መሰረት የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ተቋማት ድርሻዎች ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች በሽያጭ ለማስተላለፍ ታቅዷል። በተቋማቱ ውስጥ "ትልቁ" ድርሻ ግን በመንግሥት እጅ ይቆያል።

ከዚህ በተጨማሪ "በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ" ለማስተላለፍ ታቅዷል።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን ውሳኔ "ተራማጅ" ብለውታል። ጠቅላይ ምኒስትሩ እንደሚሉት ይኸ ውሳኔ የስራ አጥነትን፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የገበያ ትስስር ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል።

የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የተቆጣጠራቸው የሥራ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ እና ለውጭ ባለወረቶች ይከፈቱ ዘንድ ይወተውቱ ነበር። እስካለፈው ሚያዝያ ድረስ እንዲህ አይነት ጥቆማዎችን ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ አልነበረችም። ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ያሉት እንዲያ ነበር።

Äthiopien Addis Ababa - Neuer Zug verbindet Hafen und Stadtzentrum
ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

ኢትዮ-ቴሌኮምን ከምትታለብ ጥገት ላም ያነፃፅር የነበረው ኢሕአዴግ ከዚህ ውሳኔ ምን አደረሰው? የመዋዕለ-ንዋይ እና ፖሊሲ አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም የኢሕአዴግ ልሒቃን የሚያቀነቅኑት መንግሥት መር የዕድገት ሞዴል ገደብ እንዳለበት መገንዘባቸው ቀዳሚው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ያምናሉ።

"ምንም እንኳን ለመቀበል ባይፈልጉም እስከ ዛሬ ሲከተሉት የነበረው በመንግሥት መዋዕለ-ንዋይ የሚመራ የዕድገት ስልት ገደብ እንዳለው ገብቷቸዋል፤አውቀዋል። የመጀመሪያው እና ትልቁ ምክንያት እሱ ነው። መንግሥት መር የሆነው የእድገት ስልት ከዚህ በላይ ሊገፋ አይችልም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እነ ዓለም ባንክ ይሉት እንደነበረው ኤኮኖሚውን የግል ዘርፉ የሚበረታታበት፤ ዋና ወደ ሆነ የኤኮኖሚ ተዋናይነት ሊቀየር የሚችልበትን ዕድል በጊዜ ሒደት መፍጠር እንዳለበት ገብቷቸዋል"

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያን "የከፋ የዕዳ ጫና ሥጋት" ካለባቸው አገራት ጎራ ቀላቅሏታል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የወጪ እና ገቢ ንግድ ሚዛኑ መጓደል አሁንም መፍትሔ አልተበጀለትም። አቶ ጌታቸው እነዚህ ተያያዥ ጉዳዮች ለኢሕአዴግ ውሳኔ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ውስጥ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የመረጠው መንገድ ግን "ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ተብሎ የረዥም ጊዜ መከራ እና ችግርን ማምጣት ማለት ነው" የሚሉት በኩዌት የሳይንሳዊ ጥናት ማዕከል የኤኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር አየለ ገላን ናቸው። የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው "እነዚህን ኩባንያዎች ለመግዛት በአንድ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ የካፒታል ፍሰት ሊመጣ ይችላል። እነዚህ ኩባንያዎች እስካሉ እና የእነሱ ባለቤትነት እስከቀጠለ ድረስ ካፒታል ወደ ውጪ ይፈሳል። ምክንያቱም የተገኘው ገቢ በትርፍ ክፍፍል መልክ ወደ ዶላር ተቀይሮ ወደ ውጪ ይሔዳል" ሲሉ ያስረዳሉ።

Bauboom in Addis Ababa, Äthiopien
ምስል picture alliance/dpa/D. Kurokawa

የኢትዮጵያ በሮች ለውጭ ባለወረቶች እስኪከፈቱ ይጠብቁ ለነበሩ ኩባንያዎች የትናንትናው የኢሕአዴግ ውሳኔ የምሥራች ይመስላል። የደቡብ አፍሪቃዎቹ የቴሌኮም ኩባንያዎች ኤምቲ ኤን እና ቮዳኮም የኢትዮጵያን ውሳኔ በማወደስ ቀዳሚ ሆነዋል።

ኢሕአዴግ በብቸኝነት የወሰነው እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳ ውይይት ያልተደረገበው ውሳኔ ለበርካቶች አስደንጋጭ ነው። ዶክተር አየለ ገላን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አሁን ኢሕአዴግ በወሰነው መንገድ ለሽያጭ ለማቅረብ የሚያስገድድ አጣዳፊ ምክንያት የለም ሲሉ ይተቻሉ። የአገሪቱ ነባራዊ ፖለቲካል ኤኮኖሚ አይፈቅድም የሚሉት የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው ጉዳዩ በጥልቀት ሊጠና ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ተቋማት እንዲሸጡ የወሰነው ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን አካታች (inclusive growth) እንዲሆን ለማድረግ ነው የሚል ምክንያት አስቀምጧል። አቶ ጌታቸው በዚህ ውሳኔ እንዴት የታቀደው እንደሚሳካ እርግጠኛ አይደሉም። አቶ ጌታቸው "ይህ እርምጃ በምን አይነት ኤኮኖሚያዊ አመክንዮ ዕድገቱን አካታች እንደሚያደርግ አላውቅም። በምን አይነት መንገድ ዕድገቱን ቀጣይነቱን እንደሚያረጋግጥ አላውቅም። የውድድር ሕጎቹ ሳይቀየሩ የመንግሥት ድርጅቶችን ድርሻ ብቻ ከመንግሥት ወደ ግል ባለሐብቶች በማዘዋወር የሚገኝ አካታችነት ወይም ቀጣይነት የለም "  ሲሉ ይተቻሉ። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ