1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሎኔል መንግስቱ በዚምባቡዌ መቆየት አጠያይቋል

ዓርብ፣ ኅዳር 8 2010

የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ስልጣን መነጠቅና የፕሬዝዳንት መንግስቱ ዕጣ ፈንታ፣ በእስር ላይ የሚገኘው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል ኡስታዝ አህመዲን ጀበል “ህክምና ተከልክሏል” መባሉ እንደዚሁም ኤርትራውያን በአዲስ አበባ ያደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ በሳምንቱ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከነበሩ አርዕስተ ጉዳዮች ውስጥ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2npn1
Simbabwe Constantine Chiwenga und Robert Mugabe
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

የኮሎኔል መንግስቱ በዚምባቡዌ መቆየት አጠያይቋል

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ሰቅዞ ይዟቸው የነበረው ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ካለፈው ሁለት ሳምንት ወዲህ ዓለም አቀፍ ትኩረት በሳቡ ክስተቶች ሲጠመዱ ተስተውለዋል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ የፖለቲካ ሽኩቻ ለኢትዮጵያ ስላለው አንድምታ ተነጋግረው ሳይጨርሱ የዚምባቡዌው ደም ያላፋሰሰ መፈንቅለ ስልጣን ተደርቦላቸዋል፡፡ በሁለቱም ሀገራት ባለው የስልጣን ትንቅንቅ ስማቸው የገዘፈ ኢትዮጵያውያን ስም ተያይዞ መነሳቱ ነው ነገሩን ለኢትዮጵያውያኑ ልብ ቅርብ እንዲሆን ያደረገው፡፡

በሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን በታወጀው የሙስና መዋጋት ዘመቻ በቁጥጥር ስር የዋሉት የትውልደ ኢትዮጵያዊው ቱጃር የሼህ መሐመድ አላሙዲ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብዙዎች የተቀባበሉት መረጃ አላሙዲ ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ቢጠቁምም በስተኋላ የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ 

Zimbabwe Robert Mugabe
ምስል picture alliance/AP Photo/T.Mukwazhi

የአላሙዲ ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ነበር ከወደዚምባቡዌ ያልተጠበቀ ዜና የተሰማው፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ምክትላቸውን ኤመርሰን ማናጋግዋን ባለፈው ሳምንት ከስልጣናቸው ማሰናበታቸውን ተከትሎ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የከረመው የፖለቲካ ሽኩቻ የፈነዳው ባለፈው ረቡዕ ጠዋት ነበር፡፡ ለሊቱን መንግስታዊውን ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ የተቆጣጠረው የሀገሪቱ ጦር ረቡዕ ንጋት ላይ በቃል አቃባዩ በኩል በሙጋቤ ዙሪያ ያሉ ወንጀለኞችን እያጸዳ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጦሩ የወሰደው እርምጃ “መፈንቅለ መንግስት አይደለም” ሲሉ ያስተባበሉት ቃል አቃባዩ “ሙጋቤ ከባለቤታቸው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው በደህና ሁኔታ ላይ” እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ 

የሙጋቤ ከስልጣን ገለል መደረግ “ለዚምባቡዌ ምን ይዞ ይመጣል?” በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያነቱ ባይበርድም ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ግን ጉዳዩን ከቀድሞ የሀገራቸው ፕሬዝዳንት ዕጣ ፈንታን ጋር አሰናስለው መመልከትን መርጠዋል፡፡ ግንቦት 1983 ዓ.ም የኢህአዴግ ጦር ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ ነበር የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሀገር ጥለው የተሰደዱት፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ በብላቴ ጦር ሰፈር ያሉ ተማሪዎችን ለመጎብኘት በሚል በአውሮፕላን መጀመሪያ ወደ ኬንያ የገቡ ሲሆን ከዚያም ላለፉት 26 ዓመታት መኖሪያቸው ወደሆነችው የዚምባቡዌ መዲና ሀራሬ አቅንተዋል፡፡ 

ኮሎኔሉን አስመልክቶ አስተያየታቸውን በማህበራዊ መገናኛዎች ካሰፈሩት ውስጥ የተወሰኑት መንግስቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው “ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ መደረግ አለባቸው” ብለዋል፡፡ ከእዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ሲራክ ተመስገን በፌስ ቡክ ገጹ “የዚምባቡዌ ወታደር በሙጋቤ ላይ መፈንቀለ መንግስት አካሂዷል። (ወታደሩ መፈንቅለ መንግስት አይደለም ቢልም ቅሉ) አሁን ያን ሰው በላ መንግስቱ ኃይለማርያምን ለፍርድ የምናቀርብበት ጊዜ ነው” ሲል ጽፏል፡፡ 

መንሱር ቃሲም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ “በዚምባቡዌ ያለው መፈንቅለ መንግስት ከተረጋገጠ ኢትዮጵያ በስተመጨረሻ መንግስቱን በችሎት ለማቆም ሰነዶችን ታዘጋጃለች” ብለዋል፡፡ በዘሄግ የሚገኙት ሲራክ አስፋው በዚያው በትዊተር በዚምባቡዌ መጣ ላሉት “አዲስ ዘመን መልካም ዕድል” ተመኝተው ሀገሪቱ ማድረግ ያለባትን ጠቁመዋል፡፡ “አሁን መደረግ ያለበት መልካሙ እና የተከበረ ነገር መንግስቱ ኃይለማርያም በህዝባቸው እና በሀገራቸው ላይ ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ማባረር ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡ ያሃኮል በሚል የትዊተር ስም ያላቸው ተጠቃሚ ደግሞ “በቅርቡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ተቀበሉ የሚል ዜና እንሰማ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 

Äthiopien Mengistu Haile Marian
ምስል AP

ከመንግስቱ እና ዚምባቡዌ ጋር በተያያዘ የፌስቡክ እና የትዊተር ተጠቃሚዎችን ያስገረመው ከጦር ኃይሉ ስልጣን መንጠቅ ጀርባ የኮሎኔል መንግስቱ እጅ አለበት የሚል ዘገባ ነው፡፡ ሊያና ተፈሪ በትዊተር “ጉድ በል አዲሳባ! የእኛው ጉድ ለካ እስካሁን ባለስልጣን ኖሯል፡፡ የራሱን ሀገር አተራምሶ ሄዶ የሌላ ሀገር ጦር አማካሪ ነው ለካ? ጉድ ጉድ” ስትል ጽፋለች፡፡ አቤል አባተ ደምሴ ደግሞ “የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎቹ እስረኞቹን ምን ማድረግ ማድረግ እንደለባቸው ምክር ከመንግስቱ ኃይለማርያም ሲጠይቁ አስቡ፡፡ አያድርገው!” ብሏል በትዊተር ገጹ፡፡ “በዚምባብዌ ያለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ የ1966 አብዮት ጋር ትንሽ ተመሳሳይ ይመስላል” ሲል የተንደረደረው ኤርሚያስ ደጀኔ ምስስሎሹን በፌስ ቡክ እንደሚከተለው ዘርዝሯቸዋል፡፡ 

“1- ልክ እንደ ንጉሱ ሁሉ ፕሬዝዳንት ሙጋቤም በንግስናው ዙፋን እስኪጃጁ ለመቆየት መውደዳቸው:
2- ፕሬዝዳንቱን በእስር ያኖሯቸው ወታደሮች " ሙጋቤና ቤተሰባቸው በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው የሚለው" ማስተባበያ:›
3- እኛ ንጉሱን አንነካም በዙሪያቸው ያሉትን ሙሰኞችና "የህዝብ ደም መጣጮችን ነው" እንዳሉት የያኔዎቹ የእኛ ጦረኞች ዛሬም በዚምባብዌ ይሄው ትርክት መደገሙ
4- የንጉሳዊውን ዙፋን ማክተም ሊነግሩ አደባባይ ከወጡትና ከዚያም ዋና ተዋናይ መስለው ይታዩ ከነበሩት ይልቅ ዋናዎቹ ከመጋረጃ ጀርባ አድፍጠው የነበሩቱ መሆናቸው 
ይህን ሁሉ ተመሳስሎ ስናይ ይሄ ነገር እንዴት ነው? የእኛ ሰውዬ ልምድ እያካፈሉ ይሆን እንዴ ብለን ጠይቀናል” ሲል ጽፏል ፡፡

ኤርሚያስ በዚምባቡዌ እየሆነ ያለው በመንግስቱ እጣፈንታ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለማወቅ “ጊዜው ገና ይመስላል” ብሎ ያምናል፡፡ ባዩሽ አበበ መንግስቱ ላይ ክፉ አይደርስም ብለው ከሚያምኑት ውስጥ ናቸው፡፡ “መንግስቱ ኃይለማርያም ደሀ እንደሚወድ የዚምባቡዌ ምሁር ያውቃል፡፡ ምንም አያደርጉት፡፡ የዚምባቡዌ ምሁሮች እንደሌላው ሀገር ባለማስተዋል አይጓዙም፡፡ የመንግስቱን ውለታ አይረሱም” ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ለመንግስቱ በጎ አስተያየት ያለው ሶሊ ታድ ተከታዩን በፌስ ቡክ አካፍሏል፡፡ “ጀግናው እና ቆፍጣናው መሪ እንወድሀለን።አንተ ወደዚች ሀገር መጥተህ፣ እንደገና መንግስት መስርተህ፣ ህዝብ ይቅርታ  እንዲያደርግልህ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም አንተ ሀገራችንን አንድ ለማድረግ እንጂ ለመከፋፈል አይደለም ስትሰራ የነበረው። ከሁሉ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለማስቀጠል የከፈልክውን መስዋዕትነት እስከመቼም አልረሳውም፡፡”

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ስንሸጋገር የኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ጉዳይ እንናኛለን፡፡ ከህዝበ ሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆነው እና አሁን በእስር ላይ የሚገኘው አህመዲን ህክምና እንዳያገኝ መከልከሉን ቤተሰቦቹ ካሳወቁ በኋላ እርምጃው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ውግዘት አስከትሏል፡፡ አህመዲን ህክምና እንዲያገኝ ይፈቀድለት ዘንድም ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ ዘመቻውን ከተቀላቀሉት መካከል ከዓመታት በፊት “የሙስሊሞች ጉዳይ” በተሰኘው መጽሔት የአህመዲን ባልደረባ የነበረው ይስሐቅ እሸቱ ይገኝበታል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ንቁ ተሳታፊ የሆነውን ይስሐቅን የመገናኛ ዘዴዎቹ ተጠቃሚዎች ስለጋሯቸው አስተያየቶች እና መልዕክቶች ትላንት ማምሻውን ጠይቄው ነበር፡፡ 

Äthiopischer "Muslim Arbitration" Komitee Mitglied
ምስል A. Ahmed

“አህመዲን ጀበልን አስመልከቶ ከትላንት ወዲያ ጀምሮ ነው ከቃሊቲ የመጣ መረጃ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ባሉ የመገናኛ ብዙሃን ገጾች ላይ ወጥቶ ነበር፡፡ ያው አህመዲን ጀበል ከኩላሊት በሽታ ጋር በተያያዘ ህክምና እያደረገ ነበር፡፡ በዚያ ህክምና የተተከሉለት ቱቦዎች ነበሩ እና ለዚያ ደግሞ የሁለት ወር ቀጠሮ ነው የተሰጠው፡፡ ቢሆንም ‘ድንገት ህመም ካመመህ ና’ የሚል ነገር ነበር እና ያው እንደተለመደው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ እስረኞች በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በጣም ይበደላሉ እና አህመዲንም ወደ [ህክምና] እንዳይሄድ መከልከሉን የሚገልጹ መረጃዎች ወጡ፡፡ 

ጉዳዩ ደግሞ አህመዲን ጀበል ታዋቂ የታሪክ ጸሀፊ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ ከምንም በላይ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የሚታወቅለት የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሆኖ የህዝበ ሙስሊሙን ድምጽ በማሰማት እና የህዝብ ግንኙነቱን ስራ በመስራት የቆየ ወንድም ነው፡፡ የታሪክ ምሁር ነው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ የታወቁ ብዙ ስራዎች አሉት፡፡ እንዲሁም በሙስሊሞች ጉዳይ መፅሄት አምደኛ የነበረ እና ከመስራቾቹ አንዱ የነበረ መሆኑ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደመሆኑ ያው በብዙ ሰሰው ዘንድ ይታወቃል፡፡ እና አህመዲን እንዲህ አይነት ህመም እንደገጠመው እና በዚያ ህመሙን ለመታከም በቂ አገልግሎት እየተሰጠው እንዳልሆነ፣ ማረሚያ ቤቱ ይህንን መብቱን እየከለከለው እንደሆነ መረጃ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ሰዎች ተረበሹ፡፡ 

መንግስት ከማሰሩ አልፎ ደግሞ ፍርደኛ ሆኖ ጊዜውን እያገለገለ የሚገኘን እስረኛ እንዴት እንደዚህ ይበደላል፣ ለምንስ ህገ-መንግስታዊ መብቱ ይጣሳል በሚል ያው ሰዎች ድምጻቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጎላ ባለ መልኩ ደግሞ በፌስ ቡክ ሁሉም ሰው ግድግዳው ላይ እየገባ መጻፍ ጀመረ፡፡ የተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን አካባቢ ያሉ ሰዎች ደግሞ በ‘ሃሽታግ’ እናድርገው በሚል በ‘ሃሽታግ’ ይህን ነገር ማስፋፋት ቀጠሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ጉዳዩ አሳስቧቸዋል፡፡ የመለያ ፎቷቸውን (profile pictures) ቀይረዋል፡፡ በተለይ የወጡት ፎቶዎች ላይ በፊት አህመዲን ፈቱ ወፈር ያለ ነበር እና የአሁኖቹ ላይ ፊቱ ከሳ ብሎ መታየቱ በብዙዎች ዘንድ ይህ ነገር ቅሬታ እንዲሰማቸውና በጣም አንዲደነግጡ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ መነሳት፣ መንቀሳቀስ አይችልም የሚሉ መረጃዎች እየወጡ እንደመሆናቸው፤ አስቸኳይ ህክምና ስለሚያስፈልገውም፤ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ይህን መብቱን እንዲያከብሩለት ነው ሰው እየጮኸ ያለው” ብሏል ይስሐቅ ሰፋ ባለ ማብራሪያው፡፡ 

ከአህመዲን ጀበል ሁኔታ ጋር በተያያዘ በትዊትር ሀሳባቸውን ካሰፈሩት መካከል ሲያኔ አንለይ “በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት በለሌበት እስር፤ ከሞት ፍርድ ተመጣጣኝ ነው” ብላለች፡፡ አህመድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ “የአህመዲን የአካል ጉስቁልና የስርዓቱን ኢ-ሰብዓዊ የእስረኞች አያያዝ ገላጭ ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ “ለአህመዲን ህክምና” የሚለውን ሃሽታግ ተጠቅመው መልዕክታቸውን በትዊተር ያስተላለፉት ሃይልዬ “የእኩልነት ተሟጋች፣ የሃይማኖት ሰባኪ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ የትውልድ ተምሳሌት፣የዘመኑ ጀግና የጤና ሁኔታ ያሳስበኛል” ብለዋል፡፡ 

Karte Ethiopia und Eritrea ENG

አጠር አድርገን ወደምንመለከተው የመጨረሻው ርዕሰ ጉዳይ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ ሰልፈኞቹ ከአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ባደረጉት ሰልፍ ኤርትራ ታደርሳዋለች ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቃውመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን ያነጋገረው ግን ለኢትዮጵያውያን ያዳገተው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ለኤርትራውያን ቀልሎ መገኘቱ ነው፡፡ 

ኬኛ ኤጌሬን ጉተማ የተባሉ ግለሰብ በፌስ ቡክ ተከታዩን አጋርተዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የራሷ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ሰልፈኞችን በጭካኔ ትገላላች፤ ታስራለች። ነገር ግን ኤርትራውያን ሲሰለፉ ዝም ብላ እንዲውም የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ትሰጣለች። የራሷ ዜጎች በሀይማኖት ስም ያለምንም ጥፋት በገፍ በእስር ቤት እየማቀቁ ስለ ኤርትራ ሃይማኖት ጭቆና ስታወራ ድክም ነው ያልኩት። ቅድሚያ ለዜጋ ፣ ለያዙት፣ ላቀዱት አላማ ይልሃል ይሄ ነው” ብለዋል፡፡ ፌቬን ሙላት “ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን በለጡና ለእነሱ ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ ተፈቀደላቸው፡፡ በእውነት ይህቺ ናት ብቸኛዋ፣ የራሷን ዜጋ የቀበረች ሃገር- ኢትዮጵያ” ሲሉ አስተያየታቸውን በፌስ ቡክ አስፍረዋል፡፡ “ወይ ሀገሬ ለዜጎችሽ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ የተለያዩ ህጎችና ወጥመዶች እየተረቀቁ ኤርትራውያን አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ይወጣሉ” ሲል ግርምቱን በፌስ ቡክ ያካፈለው ደግሞ ሄኖክ የአዳም ዘር ነው፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ