1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰው የመኪና አደጋ፤ የፈረንሳዊው ጋዜጠኛ እስርና የሶማሊላንድ የሀገርነት ጥረት

ዓርብ፣ የካቲት 22 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተው የመኪና አደጋ መባባስ፤ የፈረንሳዊው ጋዜጠኛ እስር እንዲሁም የሶማሊላንድን የሀገርነት ጥረት በሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ መገናኛው ከተሰጡ አስተያየቶች ሚዛናዊ ያልናቸውን መራርጠናል።

https://p.dw.com/p/4d2pp
ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ ላይ የአውቶቡስ አደጋ
የመኪና አደጋ ለብዙዎች ሕይወት መቀጠፍ፤ አካል መጉደል እና ንብረት ውድመት መንስኤ እየሆነ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ ላይ የአውቶቡስ አደጋ ምስል DW/S. Muchie

የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የመኪና አደጋ እንዴት ይቀንስ?

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በየጊዜው መድረሱ የሚሰማው የመኪና አደጋ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ፤ አካል እያጎደለ፤ ንብረትም እያወደመ መቀጠሉ እየተሰማ ነው። ባሳለፍናቸው ቀናት በተከታታይ የተሰሙ የመኪና አደጋ ዜናዎች ጉዳዩን ዳግም የብዙዎች መነጋሪያ አድርጎታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ቢደረግ ይበጃል ያሉትን ሃሳብም የሰነዘሩ ጥቂት አይደሉም። በፌስቡክ ሃሳባቸውን የሰጡት መካከል «ከጦርነት በላይ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የመኪና አደጋ እጅግ አሳሳብ ደረጃ ላይ ደርሷል።» ያሉት መስፍን ሉቃስ፤ መፍትሔዎች ያሏቸውን ሲዘረዝሩ፤ «ጠጥቶ አለማሽከርከር፣ ጫት ሳይቅሙ ማሽከርከር፤ ፍጥነት መቀነስ እና ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት፤ የመኪናው የእጅና የእግር ፍሬን ያለበትን ደረጃ ማወቅና መፈተሽ አማራጭ የሌለዉ መፍትሔ ነው። ፈጣሪ ከድንገተኛ አደጋ ይጠብቀን ወገን!» ብለዋል። ሀድራ አሊ በበኩላቸው አደጋው የሚቀንሰው« ችሎታ እና ልምምድ ሳይኖር ብር ከፍለህ ቤትህ ድረስ መንጃ ፍቃድ መሰጠት ሲቆም፤ ሕግ አስከባሪውም ለሆዱ ሳይሆን ለሕሊናው መሥራት ሲጀምር፤ እንደ መታወቂያ መንጃ ፍቃድ በየክልሉ መስጠት ሲቀር» ነው ይላሉ። ተካልኝ በለጠ በአጭሩ፤ «የመንጃ ፍቃድ አሱጣጡን ስርዓት በደንብ መፈተሽና ማዘመን ሲቻል ብቻ ነው» የመኪና አደናኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀንሰው ብለዋል።

በዋና ከተማ አዲስ አበባ የመኪና አደጋ ፎቶ ከማኅደር
በዋና ከተማ አዲስ አበባ የመኪና አደጋ ፎቶ ከማኅደር ምስል DW/S. Muchie

ማሬው ቦረና ለአደጋ መንስኤ ያሏቸውን ሲዘረዝሩ፤ «የመንገድ ጥራት ችግር፣ የአሽከርካሪ ብቃት ችግርና የትኩርት ማነስ እንዲሁም የመኪኖች ጥራት ችግር ናቸው።» ይላሉ። መሀመድ አብደራህማን አቡ አፍናንም ተቀራራቢ አስተያየት ነው ያላቸው፤ «የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ አቋም ፍተሻ ካልዘመነ በስተቀር ፣ የመለዋወጫ ዕቃ አጥተው፤  «በአላህ ወኪል» ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖች መብዛት እና የቴክኑክ ፍተሻ ላይ አገር ወዳድ ስዎች እስካልተመደቡ ድረስ አደጋን መቀነስ ከባድ ነው።» ነው የሚሉት። ተስፍሽ ማጎና ያተኮሩት የአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ይመስላል፤ «በሀገሪቱ ውስጥ እንደ አሸን የፈሉትን የውሸት የሾፌር ማሰልጠኛ ተቋማት እንዳለ መዝጋትና እንደ አዲስ በመስኩ የጠለቀ ዕውቀት ኖሯቸው በዲግሪ ደረጃ ለተመረቁት ብቻ ማሰልጠኛውን እንዲከፍቱና በሀላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል።» በማለትም ይመክራሉ። እንደገና ጋሻውም፤ «በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዘመዳቸውን እየመርጡ መቅጠርና መንጃ ፈቃድ መስጠት ሳይሆን አወዳድሮ መቅጠር ሲቻል ብቻ ነው። በዋነኝነት ግን መንግሥት ሰው እንዲያልቅ ያመቻቸዉ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ነው። ወደኋላና ወደፊት ሜዳ ላይ ፈትኖ የመጨርሻ እርከኑን መንጃ ፈቃድ ይሰጣል። እና ሰው ሞተ ይባላል? ተቀነሰ እንጅ» የሚል ተቀራራቢ አስተያየት ነው ያጋሩት። ሳድማ ሱለይማንም፤ «የወንጀሎች ቁንጮ የሆነዉን መጠጥን እንዲሁም ድምፅ አልባዉ አሲድ ጫትን በሚጠቀሙ ሹፌሮች ላይ ከበድ ያለ እርምጃ መዉሰድ።» ይላሉ።

የታሰረው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ  

37ተኛውን የአፍሪቃ ሕብረት ስብሰባ ለመዘገብ ፈቃድ አንግኝቶ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው አፍሪካን ኢንቴሌጀንስ የተሰኘው ድረገጽ ዘጋቢ ፈረንሳዊውአንቶኒ ጋሊንዶ ባለፈው ሳምንት በጸጥታ ኃይሎች መያዙ ተነግሯል። የዜና አውታሩ እና ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱ ተቋማት ጋሊንዶ ባስቸኳይ እንዲለቀቅ ሲጠይቁ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኛው ከተሰጠው የዘገባ ፈቃድ ውጪ መረጃዎችን ለመሰብሰብ መንቀሳቀሱ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው ብሏል።

CPJ አርማ
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው CPJ አርማ

ኢስሚ ኡመር ካስትሮ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ለማንም የማትበገር አገር ስላለችኝ ደስተኛ ነኝ» ሲሉ፤ ዳኒ ክፍሌ፤ «በቀጭን ትዕዛዝ ይፈታል፤ የሚያሳዝኑት የእኛዎቹ ናቸው» ብለዋል። መብረቁ ሚዲያ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኛ እስር ብርቅ ነዉ እንዴ?» በማለት ነው የጠየቁት። ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ የተያዘበትን ምክንያት «ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የሚድያ አንቂዎችና ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ ከሚያስባቸው ሰዎች መረጃዎችን ሲያሰባባስ ቆይቷል» በማለት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል። ቸኮል ሞገስ ታዲያ፤ «የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር መገናኘት እንዴት ወንጀል ሊሆን ይችላል? ባይሆን እንደ ድሮው- ከሽብርተኞች ጋር በመገናኘት ብትሉት ያምር ነበር።» ሲሉ፤ ተመስገን መላኩም፤ «ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ሲገናኝ ነበር» የሚለው ደግመው የሳቅ ምልክቶችን አክለዋል። ተፈሪ ፋንታሁን፤ «መረጃ ሰብስቦ ለህዝብ ማድረስ የጋዜጠኛ ወናው ስራ መሆኑ አይታወቅም ማለት ነው?» በማለት ሲጠይቁ ።፤ ሁሴን ሳልህ ደግሞ፤ «ጋዜጠኛው የታሰረው ኢትዮጵያ ራሀብ የለም ግጭት የለም ስትል ነበር ለዓለም፤ ጋዜጠኛው ግን ጅግና ነው ሀቁን በደንብ አግኝቶታል።»

ብርሃኑ ደበሌ ግን፤ «ሕግና በሕግ ብቻ ፤ ከሙያ ስነምግባር ውጭ የሚንቀሰቃስ ማንኛውም ሰው በሕግ ይጠያቀል።» ነው ያሉት። ጤና ደስታ በበኩላቸው፤ «የእስር ቤቱንም የእስረኞች አያያዝ በደንብ ዘግቦ ይወጣል:: ጥሩ አጋጣሚ ነው::» ይላሉ፤ ሰይድ መሀመድ ግን ፤ «አይ እውነት ከሕሊና ታሣሪዎች ጋ በአንድ ያሥሩታል ብላችሁ ትገምታላችሁ? የእኛ ፖለቲካ ብልጣብልጥ መሆኑን አንርሣ» ብለዋል።

የሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ስምምነትና ሶማሊያ

ለሉአላዊ መንግሥትነት እውቅና የምትሻው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የባሕር ወደብ ግዛቷ ጋር በተገናኘ የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ መነጋገሪያነቱ አልበረደም። ስምምነቱን የተቃወመችው ሶማሊያ ያለእኔ እውቅና እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ አልነበረባትም በሚል በዙሪያዋ አጋሮች ማሰባሰቧን ቀጥላለች። ከሰሞኑንም ከቱርክ ጋር የባሕር ግዛቷን ለማስከበር በሚል ስምምነት መፈራረሟን አስታውቃለች። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ አስመልክተው ከተሰጡ አስተያየቶች፤ መስፍን ገዛኸኝ፤ «ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚደገፍ ሲሆን የበሰለ የዲፕሎማስ አካሔድ በአግባቡ የተጠቀመች ነው። ሃገራትም ከኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት እና ቀጣይ እጣ ፋንታ አኳያ በማዬት ሐሳባቸውን መስጠት ይገባቸዋል እንጂ ከጭፍን እይታ አንጻር መሆን የለበትም።» ይላሉ።

የሶማሊላንድ የባሕር ወደብ በርበራ
የሶማሊላንድ የባሕር ወደብ በርበራ ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Brian Inganga/AP/picture alliance

ጸለምቲ ዴይሊ ፖስት ደግሞ፤ «የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ደረጃ የነበረው በንጉሡ ኃ/ሥላሴ እና በመለስ ዜናዊ ዘመን ነበር።» ነው የሚሉት። አሊ ኤች ዋቅጅራ፤ «ስምምነቱ ጠቃሚ ነው።» ይላሉ፤ «ግን ይህንን ማሳካት የሚችል ዲፕሎማት አለ ብዬ አላምንም። አብዛኞቹ ዲፕሎማቶቻችን የኢህአደግ በለሥልጣናት ሲሆኑ ወደ ሥልጠን የመጡት በብሔር ሽፋን እንጂ አቅም ኖሯቸው አልነበረምና። ጠቅላይ ሚንስትራችንም ቢሆኑ ችኩል እንጂ ብስለት ያላቸው አይመሰለኝም። በበኩሌ ብዙም ተስፋ አላደርግም።» በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ዘማች አምቦ በበኩላቸው፤ «ብሔራዊ ጥቅም በዲኘሎማሲ መንገድ ማሰጠበቅ ነው። አልፎ ከመጣ መስዋዕትነት እንከፈላለን። እኛ ኢትዮጵያዊያን ተነጥቀን እንጅ ነጥቀን አይደለም።» ነው የሚሉት። ውልጫፎ ገብሬ ግን፤ «ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ሳትሰጥ የኢኮኖሚ ግንኙነት ማድረግ ትችል ነበረ። ከሁለቱም ሶማሊዎች እና ከሌላ ሃገራትም ጋር የዲፕሎማሲ ችግር አያመጣም ነበር።» ይላሉ።

ጥላሁን ጌታቸው ጌታቸው ደግሞ፤ «ሱማሊያ ትልቅ የባሕር በር ያላት ሀገር ናት። ሱማሊያ እራሷ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ብትሰጠን እኮ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይደለችም። ሶማሊላንድ የራሷ መንግሥት ያላት በራሷ ፓስፖርት ሀገር ነች። ስለዚህ ሶማሊያ እራሷ ለሶማሊላንድ እውቅና ሰጥታ በጋራ ቢናለማ ምን ችግር አለው?» በማለት ይጠይቃሉ። በረከት ጌታቸውም ሊያግባባ ይችላል ያሉትን ሃሳብ ሲገልጹ፤ «ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ተገናኝቶ መወያየት ወሳኝ ነው፤ ምናልባት መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። የሶማሊያ አቋም ከእራስ ጥቅም አንጻር ይመስላል፤ አንድ ሦስተኛውን የሀገራቸውን ግዛት ሊያሳጣቸው ስለሚችል ሊኮነኑ አይገባም። ምናልባት ኢትዮጵያ ተሳስታ ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ በኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ስለምንገኝ መፍትሄ እየፈለግን ነው።» ነው ያሉት። ብሮከር ያሲኖ ደግሞ፤ «የመቋዲሾ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደር የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ቀደሞም የአሜሪካ መንግሥት የጦር ካምፕ ግንባታ ስምምነትን ሰምተናል!! የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት እንደዚህ ያሉ በርካታ ወላ ከዚህም ከረር ጠበቅ ያሉ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙና እንደምን እንደሚመከቱ ሳያሰላ በጎረምሳ ስሜት የወሰነው ተራ ነገር አይደለምና እዳው ገብስ...... ደግሞ ፈፅሞ መዘንጋት የማይገባው ነጥብ የመቋዲሾ መንግሥትን በአንቀልባ አዝሎ ሰባራ ወንበሩ ላይ ያስቀመጠው ክንደ ብርቱው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የመሆኑ ነገር ነው።» ብለዋል። አብርሃም ደፍቴ ግን፤ «መጀመርያ መቀመጫየን አለች ይባላል ዝንጀሮ። ስለ ባሕር በር ከመጠየቄ ቅድሚያ ሰላምና መረጋጋትን እሻለሁ እኔ።» ነው ያሉት።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ