1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመካነ-ቅርፅ ተማራማሪዉ ተገኑ ጎሳ አሬዶ

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ነሐሴ 10 2010

አቶ ተገኑ ጎሳ አሬዶ እስራኤል በሚገኘዉ የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዲግሪያቸዉን በመካነ-ቅርፅ ትምህርት እየተከታተሉ ይገኛሉ። በዚሁ የትምህርት መስክ ኢትዮጵያ ባጠቃላይ ለአፍሪቃ የማዕዘን ድንጋይ ሆና እንደምታገለግል አቶ ተገኑ ይናገራሉ። በመስኩ ተግዳሮቶች እንዳሉም ግን ተመራማሪው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

https://p.dw.com/p/33EMX
Äthopien, Melka Wakena: Spurensuche nach afrikanischen Wurzeln
ምስል DW/T. Gossa Aredo

በሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዲግሪያቸዉን በመካነ-ቅርፅ ትምህርት ተከታትለዋል

አቶ ተገኑ ጎሳ አሬዶ በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸዉን በዋናነት የሰሩት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደ ሆነ ይናገራሉ። የሁለተኛ ዲግር ትምህርታቸዉን በመካነ-ቅርፅ ወይም በArcheology በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። አሁን በኢየሩሳሌም  የሂብርዉ ዩኒቨርሲቲ በሚከታተሉት የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት የጀመሩት ጥናታቸው በመካነ-ቅርፅ ትምህርት መስክ በቅድመ-ታሪክ በነበረው የሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ ወይም Evolution ላይ  እንደሚያተኩር ይናገራሉ።

አቶ ተገኑ ጎሳ አሬዶ ከታሪክ ትምህርት ወደ መካነ-ቅርፅ ወይም Archeology ትምህርት የተዛወሩት የታሪክ ተማሪ እያሉ መካነ-ቅርፅን የሚመለከቱ ሁለት ኮርሶችን በመዉሰዳቸዉ እንደሆነ ይናገራሉ። «በቅኝ-ግዛት ጊዜም ሆነ በፊት አፍሪቃ የምትታወቀዉ እንደ ጨለማ አህጉር ነው፤ ስልጣኔ የለለበት አህጉር ሆና ስትታይ ቆይታለች። የአፍሪቃ ታሪክ በነጮች ሲጻፍም እንድህ ተደርጎ ነዉ የተፀፈዉ። ግን የArcheology ሳይንስ እየሰፋ ሲመጣ አፍሪቃ የጨለማ አህጉር ሳይሆን በተቃራኒዉ አፍርቃ ለሰዉ ልጅ አመጣጥና እድገት ቁልፍ ሚና እንዳላት ነዉ። ታሪኩም ተገልብጦ አፍርቃ የስልጣኔዎች ሁሉ ምንጭ እንደሆነች ተደርሶበታል። እየቀጠለ ያለዉ ሳይንስ ይህንኑ የምያረጋግጥ ነዉ። እነዚህን ፍንጮች ያገኘሁት ከነዛ ከመካነ-ቅርፅ ሁለት ኮርሶች ስለሆነ በጊዜ ሂደት ወደዚህ ተስቤያለሁ። በመካነ-ቅርፅ እምቅ ሀበት ካላት ከኢትዮጵያ መምጣቴም አንዱ ምክንያት ነዉ።»

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በረሃ በስተ-ደቡብ ከምገኙት አገራት በበለጠ በመካነ-ቅርፅ ወይም በአርኪዮሎጂካል ግኝቶችና ታሪካዊ ሕንፃዎች እጅግ በጣም የላቀ እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ። በምሳሌነት የሚጠቀሱም ከ3,2 ሚሊዮን አመት በፍት እንደኖረች የምነገርላት ሉሲ ወይም ድንቅነሽ፤ የመካከለኛ ዘመን የድንጋይ መሣሪያዎች የተገኙበት የጥንት  አርኪኦሎጂካል ቦታ እንድሁም ሌሎች ይገኙበታል። በምስራቅ አፍሪቃ የስምጥ-ሸለቆ ውስጥ የነበሩ እንስሳትና ተክሎች ዘር በሙሉ  ወደ ላይ ወጥቶ መታየታቸዉ ለጥናታቸዉ መሰረት እንደሆኗቸው ነው አቶ ተገኑ የገለጹት።

Äthopien, Melka Wakena: Spurensuche nach afrikanischen Wurzeln
ምስል DW/T. Gossa Aredo

አቶ ተገኑ፣ «ጥናቴን የምሠራዉ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የመልካ ዋካና ግድብ አከባቢ አዲስ የተገኘ የመካነ-ቅርፅ ቦታ አለ። ከዛ በፊትም «ጋዳብ» በመባል የምታወቀዉ ቦታ ላይ ሰርቻለሁ። ከነዚህ ዉጭ በስፋት የመካነ-ቅርፅ ቦታዎች ያሉት በአፋር፤ በኦሞ ሸለቆና አጠቃላይ ስምጥ ሸለቆዉ አቋርጦ በሚያልፍባቸዉ ቦታዎች ነዉ።»

የመካነ-ቅርፅ ወይም የአርኪዮሎጂካል ግኝቶች የሚያጠቃልሉት የእንስሳትና የሰዉ ልጆች ቅሬተ-አካሎች ይገኛሉ፤ በተጨማሪም የሰዉ ልጅ የተጠቀባቸው መሣሪያዎች እንደሚገኙም አቶ ተገኑ ይናገራሉ። እነዚህ ምልክቶች መሬት ላይ ከታዩና ሰፊ የጥናት እድል የሚሰጡ ከሆነ ቦታ በጥንቃቄ ይቆፈርና መካነ-ቅርፆቹ እንደሚሰበሰቡ ተናግረዋል። «ተቆፍሮ ከወጡ በኋላ ወደ ላብራቶሪ ይወሰድና እድሜያቸዉ ምን ያህል እንደሆነ ይመረመራል። የመስክም ሆነ የላብሮቶሪው ስራ ብዙ ግዜ ይወስዳል፤» ይላሉ አቶ ተገኑ።

የነፃ የትምህርት እድል አግኝተው በእስራኤል የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በማጥናት ላይ ያሉት አቶ ተገኑ አሁን በሚማሩበት አገር ብዙም ተግዳሮት እንዳላጋጠማቸዉ ይናገራሉ። ምክንያቱም «ብዙ ቤቴ-እሥራኤላውያን በስፋት ስለሚገኙ» ይላሉ። ግን በጥናት ሂደቱ የመስክ ስራዉ እትዮጵያ ስለሆነ «ብዙ ምልልስ» ስላለዉ የትምህርት ጊዜዉ እንዲራዘም እንደሚያደርግባቸዉ አቶ ተገኑ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ባጠቃላይ አህጉሩ ወደ ኋላ ለመቅረቷ የባህል ሃብት እጦት አንዱ አስተዋህፆ  መሆኑን አቶ ተገኑ አክለው ገልጸዋል። አንዱ የባህል ሃብት አካል የሆነዉ የመካነ-ቅርፅ መስክ «ማንነትን አጉልቶ ስለሚያሳይ» ጠለቅ ያለ ምርምር መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ