1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጤ እና ተዛማች አረሞች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2011

አንዳንድ እፅዋት በተፈጥሮ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ወደ ስፍራ በየትኛውም አጋጣሚ ተዛውረው ሲስፋፉ በመጤነት እንደሚፈረጁ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የምርምር ጽሑፎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆን ተብለውም ሆነ በአጋጣሚ ወደ ሀገር የገቡ መጤ ተክሎች ወይም አረሞች ውለው አድረው ለመሬቱም ሆነ ለውኃ አካላት ስጋት መሆን መጀመራቸው እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/3IUdL
Invasive Species, Everyday Africa
ምስል Maheder Haileselassie

የመጤና ተዛማች አረሞች ስጋት

 

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ሆን ተብለውም ሆነ ሳይታወቅ ከገቡ ከ30 በላይ ከሚሆኑ መጤ እና ተዛማች አረሞች፤ አንዳንዶቹ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊየን ሄክታር የግጦሽ እና የእርሻ መሬት መውረራቸውን አንድ ተመራማሪ የዶይቼ ቬለ DW ገለፁ።  የደን እና የሥነምሕዳር ተመራማሪዎች በሳይንሳዊ ስማቸው ቢጠሯቸውም በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በተለያየ አጋጣሚ የገቡ መጤ ተክሎች ወይም አረሞች ሀገሬው እንደየአካባቢውና ወቅቱ ስም ይሰጣቸዋል ይላሉ የደን ዘርፍ ተመራማሪው ዶክተር አደፍርስ ወርቁ። የተለያዩ ጥናቶች በጉዳዩ ለመደረጉን የሚናገሩት ለዓመታት በምርምር ሥራ የቆዩት የደን ባለሙያ መጤ አረሞቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ውለው አድረው በሚገኙበት አካባቢ ሥነምህዳር ላይ ተፅዕኖ ማስከተላቸውን ያስረዳሉ።

«በርካታ ጥናቶች ለማድረግ ተሞክሯል እዚህ ሀገር ውስጥ፤ ብዙ ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ በውኃ አካላት ላይም ያሉ ወራሪዎች ለምሳሌ እንደ እንቦጭ ይሔ ፔሪፌሪያል ኤኮሲስተም ላይ ያሉት ደግሞ እንደፓርቲኒየም የሚባለው፤ እንደፕሮሶፖስ ወይም በአካባቢው አጠራር ወያኔ ይሉታል፤ ላንታና ካማራ ይሔ የወፍ ቆሎ የምንለው፤ በተለያየ ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ዝርያዎች አሉ።»

Äthiopien - Tana See - Kleine Maschine
ምስል Aragaw Desta

ፕሮሶፖስ ወይም ሀገሬው ወያኔ ሲል የሚጠራው ተክል በአፋር እና በሶማሌ በረሃማነትን ለመከላከል የአሸዋውን እንቅስቃሴም ለመቆጣጠር ታልሞ ወደ ሀገር መግባቱን ነው ዶክተር አደፍርስ የሚናገሩት። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአካባቢው ጥናት ሲያካሂዱ 400 ሄክታር በማይሞላ መሬት ላይ ተወስኖ የነበረው ይህ መጤ አረም ከዓመታት በኋላ እጅግ ተስፋፍቶ አርብቶ አደሮቹ ለከብቶቻቸው የሚፈልጉትን የግጦሽ እጅግ ሰፊ መሬት ቆጣጠሩን በምሳሌነት ዘርዝረዋል።

«ዝርያው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ወረራ አድርጓል፤ አፋር ክልል ላይ ብቻ የቅርብ ጥናቶች የሚያሳዩት ወደ 1,8 ሚሊየን ሄክታር መሬት እጅግ ለአፋር ማኅበረሰብ፤ ለአፋር ብቻም አይደለም ከሌላ አካባቢም ለሚመጡ አርብቶ አድር እና ከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ሁሉ በተለይ በዚህ በበጋ ጊዜ ከብቶቻቸውን አቆይተው የሚመለሱባቸው፤ የቦና ወይ ደግሞ የደረቅ ጊዜያት ግጦሽ መሬታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አጥፍቶባቸዋል። በተለይ ለመድኃኒትነት ለእንስሳት መኖነት ለምግብነት የሚያገለግሉ የአካባቢውን ዝርያዎች አጥፍቶ ነው ቦታውን የወሰደው።»

ይህ መጤ ተክል ጥፋቱ በግጦሽ መሬት ወረራ ብቻ አልተገታም፤ የእርሻ መሬትን እንዲሁም የመኖሪያ አካባቢዎችንም ሁሉ በማዳረሱ፤ ዝርያው በጣም እሾሃማ በመሆኑ መንጥሮ ለመግባት ሁሉ ማዳገቱን  ነው ባለሙያው ያስረዱት።  በዚህም አላበቃ በአዋሽ ወንዝ ዳርቻ ይገኙ የነበሩ ለየት ያሉ የወንዝ ዳር ተክሎችን አጥፍቷል።

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana
ምስል Kalkidan Tsena

እንዲህ ያሉት ወራሪ መጤ እና ተዛማች አረሞች ሆነ ተብሎም፤ ሳይታወቅም ወደ ሀገር ሊገቡ እንደሚችሉ ነው የደን ባለሙያው የሚናገሩት። እምቦጭ ይላሉ ዶክተር አደፍርስ የዛሬ 10 ዓመት እሳቸው እና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት ሲያካሂዱ ጣና ሐይቅ ላይ አልተከሰተም ነበር። እሳቸው እንደሚሉት ያኔ ለውበት ተብሎ የመጣው እምቦጭ የወረረው እነ ቆቃ፤ አባ ሳሙኤል እና ባቅራቢያቸው የሚገኙ የውኃ አካላትን ነበር። አሁን ደግሞ የሀገር አድባር የሆነው ባለብዙ ምሥጢሩ የጣና ሐይቅን ባቻ ሳይሆን ሌሎችን የውኃ አካላትንም አጥለቅልቆ ከባድ ስጋት ሆኗል። እንደእምቦጭ ሁሉ የትኞቹም መጤና ተዛማች አረሞች የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ዶክተር አደፍርስ፤

«እንደእፅዋት ስታያቸው እንደማንኛውም እፅዋት ናቸው፤ እንደባሕር ዛፉ፣ እንደ ጽዱ፣ እንደ ዝግባው ናቸው። ነገር ግን ከእነዚህ እፅዋት እነሱን የሚለያቸው ምንድነው? የመስፋፋት ባህሪያቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመዛመት ባሕሪያቸው በጣም ከፍተኛ ነው።»

ባለሙያው አክለው ኢትዮጵያ ውስጥ መጤ አረሞች እንዲስፋፉ መንገድ የጠረገላቸው የተጎዳው የተፈጥሮ አካባቢ መሆኑን ነው አብክረው የሚያስረዱት።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ልዩ ልዩ ዝርያዎች በተለያዩ ምክንያቶች እና መንገዶች መግባታቸውን ነው ዶክተር አደርፍር የሚናገሩት። ነገር ግን የገቡት መጤ ዘሮች ሁሉ በምን አይነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚለውን የሚያጣራ ጥናት አልተደረገም። ዘሮቹም ምናልባት ባሕርያቸውን ለውጠው ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዱት ተመራማሪው ባካሄዱት ጥናት ግን 37 መጤ ተዛማች አረሞች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ገልጸውልናል። ሆኖም ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊጨምር እንደሚችልም እንዲሁ። ችግር መኖሩ መታወቁ መፍትሄ ለመሻት መንገድ ነው እና፤ ለመሆኑ ሊያጠፋቸው የሚችል አንድ ወጥ መንገድ ይኖር ይሆን? አልናቸው፤ ዋናው ነገር ወደ ሀገር እንዳይገቡ ማድረግ ከገቡም ደግሞ ከአንዱ ቀበሌ ወደሌላው እንዳይዛመቱ መከላከሉ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት፤ አራት አይነት መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እሳቸው ግን ሁሉንም ያደባለቀ ስልት መጠቀም ውጤታማ ሊያደርግ ይችላል ብለው አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ይናገራሉ።

Äthiopien Dürre Wassertransport
ምስል picture-alliance-akg-images/Y. Travert

ዋናው ነገር ይላሉ ተመራማሪው ይህን ጉዳይ የሚመለከት ራሱን የቻለ አካል ማዋቀር ያስፈልጋል። ጥናቶች በተለያዩ አካላት በተናጠል ቢጠኑም አልተቀናጁም፤ የምርምር ጥረቱም እንዲሁ ማዕከል ያስፈልገዋል። ዛሬ ከትናንሽ አካባቢዎች ተነስቶ ሰፋፊ የእርሻ የግጦሽ እና የውኃ አካላትን ያዳረሱት መጤ አረሞች ነገ ነባሩን ብዝሃ ሕይወት አጥፍተው ሊታረም የማይችል የከፋ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊትም ይህ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑንም አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ