1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ የጋራ መከላከያ

ማክሰኞ፣ የካቲት 13 2010

በሙኒኩ ጉባኤ ላይ ብሪታንያ በፀጥታው መስክ ተባብራ እንደምትሰራ ማሰወቋን የአውሮጳ ህብረት በደስታ ነው የተቀበለው። ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከአውሮጳ በጦር ኃይል ጥንካሬ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሀገራት ሲሆኑ ሁለት የአውሮጳ ህብረት ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ይመራሉ።

https://p.dw.com/p/2t0wM
54. Münchner Sicherheitskonferenz
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gebert

የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ደቡብ ጀርመን ውስጥ ለ3 ቀናት የተካሄደው ዓመታዊው የሙኒኩ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉባኤ በዓለማችን ልዩ ልዩ የፀጥታ ስጋቶች እና መፍትሄያቸው ላይ መክሯል። በጉባኤው ላይ ጎልተው ከወጡት ሀሳቦች መካከል ሊጠናከር ይገባል የተባለው በቅርቡ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የአውሮጳ የጋራ መከላከያ  አንዱ ነው። 
ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ የፀጥታ ስጋቶች እና ችግሮች ውስጥ ነው የምትገኘው። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄዱ ግጭቶች፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የተፈጠረው የኒዩክልየር ፍጥጫ እንዲሁም በምዕራቡ ዓለም እና በሩሲያ መካከል የሚታየው ውጥረት ከዋና ዋና ማሳያዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው 54 ተኛው የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ በነዚህና በሌሎችም የፀጥታ ስጋቶች ላይ ለሦስት ቀናት መክሯል። ልዩ ልዩ የፀጥታ ችግሮች ላይ ሃሳብ በተለዋወጠው በዚህ ጉባኤ በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን አለመረጋጋት በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ከነበረው የባሰ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። የጉባኤው ሊቀመንበር ቮልፍጋንግ ኢሺንገር እንደተናገሩት የብዙዎቹ የፀጥታ ችግሮች መንስኤ ያለመተማመን እና በተለያዩ ወገኖች መካከል ውይይት መካሄድ አለመቻሉ ነው። ከአዘጋጆቹ እንደተሰማው 500 ፖለቲከኞችን ባሳተፈው ጉባኤ ላይ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል። ሆኖም በጥቅሉ ሲታይ መንግሥታት በዓለማችን ሰላም ለማስፈን ምን ዓይነት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ግን ሲናገሩ አልተሰማም እንደ አዘጋጆቹ። 
 የአውሮጳ ህብረት ከዚህ ቀደም ጀምሮ ያቆመውን የአውሮጳ የጋራ መከላከያ እውን ለማድረግ እየተጓዘ ነው። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርዶ ፊሊፕ በዚህ ረገድ የአውሮጳ ሀገራት ፍላጎት ምን እንደሆነ ለጉባኤተኞቹ አስረድተዋል።  
«የጋራ ስልት መፍጠር እንፈልጋለን። ይህ ደግሞ ለተዋሀደው የአውሮጳ መከላከያ ዋናው ቅድመ ግዴታ ነው። ይህን የአውሮጳ መከላከያ መገንባት እንፈልጋለን።ሁላችንም ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጎን ለጎን  በጋራ ይህን ለማሳካት ማለም ይገባናል። ብሬኤክዚት ቢኖርም ከብሪታንያ ጋር አንድ የሚያደርገንን ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ነው የምንገነባው ። ከነዚህ ሀገራት ጋር በሚኖረን የቅርብ ግንኙነት ደግሞ ይህ ይበልጥ ይጠናከራል።» 
የህብረቱ አባል ሀገራትም ሆነ ህብረቱ ከሚቋቋመው የጋራ መከላከያ ጋር ሌሎችም በትብብር እንዲሰሩ በጉባኤው ላይ ጥሪ አስተላልፈዋል። ጥሪው ከተላለፈላቸው መካከል አዲሱ ፕሬዝዳንቷ አውሮጳን ገለል ማድረግ የጀመሩት ዩናይትድ ስቴትስ ትገኝበታለች።  ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ካለችው ከአሜሪካን ጋር አብሮ መሥራት የጋራ ጥቅም እንደሚገኝበት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚግማር ጋብርየል በሙኒኩ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር ጠቁመዋል። እንደጋብርየል ተባብሮ መሥራት ጥቅሙ ለአውሮጳ ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካንም ጭምር ነው የሚሆነው። 
«በዓለም ላይ ተሰሚነት እንዲኖረን በአውሮጳ ያለን ጥንካሬ ብቻ በቂ እንደማይሆን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ይህ ደግሞ እኛም ሆንን ዩናይትድ ስቴትስ በተናጠል የምናሳካው አይደለም። ይህን ማድረግ የምንችለው ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ነው። ለአሜሪካን አጋሮቻችን  እና ወዳጆቻችን ከአውሮጳ ጋር የሚደረግ ጥብቅ ትብብር ለአውሮጳ ብቻ ሳይሆን ለየሀገራቱ ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ለአሜሪካ ጥቅም ጭምር ነው የሚሆነው።» 
ወደ ኋላ መለስ ብለን የአውሮጳ የጋራ ጦር ምሥረታ ሂደትን ስንቃኝ የማቋቋሙ እቅድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ነበር። ይኽው የአውሮጳ የመከላከያ ማህበረሰብ ምሥረታ እቅድ በጦርነቱ ቢሰናከልም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ውሎች ተፈርመዋል። የጋራ የመከላከያ ትብብር ሰነዶቹም ከአዲስ የጋራ የደንብ ልብስ አንስቶ እስከ ግልጽ የእዝ መዋቅር ድረስ የተተነተነባቸው ነበሩ። ያኔ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ኢጣልያ ቤልጂግ ኔዘርላንድስ እና ሉክሰምበርግ ለአውሮጳ ጦር ወታደሮችን ለማዋጣት ተስማሙ። 9 ተወካዮች የሚገኙበት የአውሮጳ ኮሚሽን ቢሮ ወታደሮችን ለውጊያ የማሰማራት ሃላፊነት ተስጥቶት ነበር። በአውሮጳ ድህረ ጦርነት ታሪክ እጅግ ያልተገደበ ፍላጎት ሳይሆን እንዳልቀረ የሚነገርለት ይህ የጋራ ወታደራዊ እቅድ ግን አልዘለቀም። በጎርጎሮሳዊው 1954 ከፈረንሳይ ፓርላማ በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት የአውሮጳ የመከላከያ ማህበረሰብ ተገታ። ከዚያም ጊዜ አንስቶ የታገደው የአውሮጳ ጦር ጉዳይ በቅርብ ዓመታት እንደገና ማንሰራራት ጀመረ። ለዚህ ምክንያት የሆኑትም አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዝዳት ለአውሮጳ ያላችው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን፣ ከሩስያ በኩል እየተጠናከረ የሄደው ዛቻ እና የብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት መልቀቅ ናቸው። እናም በነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ትልቅ የሚባለው የመጀመሪያው እርምጃ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ተግባራዊ ለመሆን በቃ። 25 የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ብሔራዊ ጦር ኃይሎችን በአንድ የአውሮጳ ህብረት ኃይል ሥር ማዋህድ በሚችለው ቋሚ የተዋቀረ ትብብር ወይም በእንግሊዘኛው ምህጻር PESCO ተስማሙ። በየሀገራቱ የጦር ኃይሎች መካከል ጥብቅ ትብብርን የመፍጠር ትልም ያለው ይህ ስምምነት የጋራ የጦር መሣሪያዎችን የተመለከቱ ፕሮጀክቶችንም ያካትታል። ትብብሩ በአውሮጳ የመከላከያ ሚኒስትሮች ፍላጎት የአውሮጳ ጦር ኃይል ምሥረታን ያመቻቻል ተብሎ ይታመናል። በአሁኑ ጊዜ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት የወሰነችው ብሪታንያ በዚህ ትብብር ውስጥ ሊኖራት የሚችለው ሚናም በሙኒኩ ጉባኤ ላይ ተነስቷል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚግማር ጋብርየል ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ ከወጣች በኋላ የፀጥታ ጉዳዮችን በሚመለከት የቀድሞውን ግንኙነት ይዞ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
«ብሪታንያ ለምዕተ ዓመታት በጣም ጠቃሚ ችሎታዎችን ልምዶችን እና ሀሳቦችን  ስታስተዋውቅ ቆይታለች። እናም ሊሆን ከሚችለው ከብሬግዚት በኋላ ይህን ከብሪታንያ ጋር ያለንን ግንኙነት በተቻለ መጠን ጥብቅ እና ፍሪያማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን። ምክንያቱም ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት  ብትወጣም አውሮጳንም ሆነ የምዕራቡን ነጻ ስርዓት አትለቅምም።»
በጉባኤው ላይ የተገኙት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይም አዎንታዊ መልስ ነው የሰጡት ሀገራቸው ለአውሮጳ ፀጥታ ያልተገደበ ድጋፍ ትሰጣለች ሲሉ። ሜይ ለጉባኤው ባሰሙት ንግግር ለንደን ከዚህ ቀደም ስትመራቸው የቆየቻቸውን ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ማዘዝዋን ትቀጥላለች፤ ህብረቱ ከተስማማም ከጎርጎሮሳዊው 2019 ዓም አንስቶ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው የስለላ መረጃ ልውውጥ ውስጥ መረጃዎችን ለማጋራት ቃል ገብታለች። የአውሮጳ ህብረትን እንጂ አውሮጳን ጥለን አንወጣም ያሉት ሜይ  የአውሮጳ አጠቃላይ የፀጥታ ውል ደጋፊ መሆናቸውን ለጉባኤው ነግረዋል።
ሜይ  ሀገራቸው የአውሮጳ ህብረትን ከለቀቀች በኋላም በአውሮጳ የፀጥታ ትብብር ውስጥ መሥራት መቀጠል እንደምትፈልግ ለጀርመን ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።  
«በንግግሬ ያልኩት ምንድነው ብሪታንያ ያለ ቅድመ ሁኔታ በአውሮጳ የፀጥታ ጉዳይ ላይ በቀድሞው አቋሟ እንደጸናች ነው።በአሁኑ ጊዜ በፀረ ሽብሩ እንቅስቃሴ ትብብር እናደርጋለን። ወደፊት በዚሁ መቀጠል የሁላችንም ፍላጎት ይመስለኛል። ለዚህም ነው እኛ ከህብረቱ ለቀን ስንወጣ በብሪታንያ እና በአውሮጳ ህብረት መካከል አንድ አዲስ የፀጥታ ውል ላይ ስንደርስ ማየት የምፈልገው።»  
በሙኒኩ ጉባኤ ላይ ብሪታንያ በፀጥታው መስክ ተባብራ እንደምትሰራ ማሰወቋን የአውሮጳ ህብረት በደስታ ነው የተቀበለው። ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከአውሮጳ በጦር ኃይል ጥንካሬ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሀገራት ሲሆኑ ሁለት የአውሮጳ ህብረት ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ይመራሉ። የአውሮጳ የጋራ መከላከያ እቅድ ገና በሁለት እግሩ ያልቆመ ነገር ግን ተስፋ የሚጣልበት ትብብር መሆኑ ይነገራል። ወደ ጋራ መከላከያው የሚያመራው ትብብር ሌሎች መሰል ድርጅቶችን ለመፎካከር የተመሰረተ አይደለም ይላሉ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ።
«አንድ ትልቅ እርምጃ ሄደናል ምክንያቱም የአውሮፓ ህብረት ከተመሰረተ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ደረጃ ህጋዊ የመከላከያ ማዕቀፍ አለን። ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃደና በሆኑ እና ወደፊት ለመራመድ አቅሙ ባላቸው ባላቸው ጥቂት ሀገራት የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች እንዳሉን ግልጽ ነው። ለኔ ዋናው ነገር ከሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ጋር የሚፎካከር አይደለም።ከጎኑ የሚቆም እንጂ ።»
የጋራ መከላከያው አካል በሆነችው በጀርመን በጦር ኃይሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተልዕኮ የሚታየው የሰው ኃይል እጥረት እና የአስፈላጊ መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች በተገቢው ጊዜ አለመቅረብ አሁንም መፍትሄ ሳያገኝ የዘለቀ ችግር መሆኑ ዛሬ ይፋ የተደረገ ዘገባ አስታውቋል። እንደ ዘገባው የጀርመን ጦር ኃይልን ይዞታ ለማሻሻል ከዚህ ቀደም የተገቡት ቃሎች ተግባራዊ አለመሆን የሀገሪቱን ወታደሮች ውጥረት እና ጭንቀት ውስጥ ከቷል። ይሁን እና የመከላከያ ሚኒስትር ፎን ዴር ላየን ለዶቼቬለ እንዳሉት የኔቶን ግቦች ለማሳካት እና ለውጭ የልማት እርዳታ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ለማውጣት ያቀደችው ሀገራቸው ለመከላከያው ዘርፍም እንዲሁ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ የመከላከያ በጀቷን ታሳድጋለች። 

MSC 2018 Ursula von der Leyen
ምስል Reuters/M. Rehle
München MSC 2018 | britische Ministerpräsidentin Theresa May
ምስል Reuters/R. Orlowski
München MSC 2018 | Außenminister Sigmar Gabriel
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe
München MSC 2018 | Wolfgang Ischinger
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ