1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህፀን ጫፍ ካንሰርና ክትባቱ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29 2010

በአለም ላይ በገዳይነታቸዉ ከሚታወቁት የካንሰር አይነቶች የሴቶችን የመራቢያ ክፍል የሚያጠቃዉ የማህፀን ጫፍ ካንሰር አንዱ ነዉ። በሽታዉ በኢትዮጵያም በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነዉ።

https://p.dw.com/p/34Iji
Symbolbild Pilzinfektion im Genitalbereich
ምስል Colourbox

የማሕጸን ጫፍ ካንሰር

 ይህ የካንሰር በሽታ  የገዳይነቱን ያህልም  ቀድሞ መከላለክልና ማዳን  የሚቻል በመሆኑ፤ በሽታዉን ለመላከል ከሚደረግ ጥንቃቄ ጎንለጎን  የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመረች ሴት በአመት አንድ ጊዜ ቅድመ ምርመራ እንድታደርግ  ባለሙያወች ይመከራሉ። በሽታዉን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት መዉሰድም በባለሙያወች የሚመከር ሌላዉ መንገድ ነዉ።
የማህፀን ጫፍ ካንሰር ወይም በኢንግሊዝኛዉ አጠራር «ሰርቪካል ካንሰር» በአለም ላይ በየ አመቱ 528 ሺህ ሴቶችን የሚያጠቃ ሲሆን 270 ሺህ ያህሉን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ይዳርጋል። ከዚህም ዉስጥ 85 በመቶ የሚሆነዉ የሞት መጠን በአዳጊ ሀገራት የሚመዘገብ ነዉ።ለዚህ ደግሞ የቅድመ ምርመራ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን፤በሽታዉን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤና መረጃ እጦት እንዲሁም የመከላከያ ክትባት አለማግኔት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመለስም በየ አመቱ 4,600 ሴቶች በየአመቱ በማህፀን ጫፍ ካንሰር ይያዛሉ።ከዚህም ዉስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ማለትም በቁጥር ወደ 3,200 የሚሆኑ ሴቶች የመዳን ዕድል ሳያገኙ ይሞታሉ። 
ለማህፀን ጫፍ ካንሰር  ዋነኛ መነሻዉ ሂዉማን ፓፒሎማ ቫይረስ ሲሆን በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሴቶች 70 በመቶ በማህጸን ጫፍ ካንሰር የመጠቃት ዕድል አንዳላቸዉ የጤና ባለሙያወች ይናገራሉ።ይህ ሻይረስ በንክኪና  በግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በመሆኑም በአብዛኛዉ በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች በበሽታዉ ይጠቃሉ።የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ይርጉ ገብረ ህይወት እንደሚሉት የማህፀን ጫፍ ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሀገራችን በብዛት የሚታይ ነዉ። ከስሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት በተለይም በምስራቅና መካከለኛዉ እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ ያሉ ሴቶች በሽታዉ በብዛት ያጠቃቸዋል ብለዋል።
በመሆኑም ክትባቱ የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመሩና ለመጀመር በሚያስችል የዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ሴቶች እንዲሰጥ ቢደረግ የማህፀን ጫፍ  ካንሰርን ከመሰረቱ መከላከል እንደሚቻል ነዉ ጥናቶች የሚያሳዩት።
በሽታዉ በተነፃጻሪ ከ15 እስከ 25 እድሜ ክልል ያሉ ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃ ቢሆንም የሞት መጠን የሚጨምረዉ ግን በ40 ዎቹ እድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ነዉ። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰዉ የበሽታዉ ምልክትና ጉዳት ዘግይቶ የሚታይ በመሆኑ ነዉ።በሽታዉ ግን በሁሉም የእድሜ ክልል  ሊከሰት ይችላል ነዉ ያሉት የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት።
ይህ በሽታ  የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስም የተለያዩ ሀገሮች በዘመቻ መልክ 14 አመትና ከዚያ  በላይ ለሆኑ  ሴቶች ክትባት ይሰጣሉ።በኢትዮጵያም በመጭዉ ጥቅምት 2011 አ/ም   14 አመት ለሆናቸዉ ልጃገረዶች ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን ከጤና ጥበቃ ሚንስትር የወጣዉ መረጃ ያሳያል። ከዚህ ቀደምም በኦሮሚያና በትግራይ ሁለት ወረዳወች ክትባቱ በሙከራ መልክ ተሰጥቶ  ዉጤታማ መሆኑ ታዉቋል።
የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከተገኜላቸዉ እንደ ሳንባ ነቀርሳና የወንድ የዘር ፍሬ ካንሰርን ከመሳሰሉ ጥቂት የካንሰር በሽታወች ዉስጥ አንዱ ሲሆን የክትባቱ ስራም የካንሰር በሽታ ሊያስከትል የሚችለዉን የቫይረስ ኢንፌክሽን መከላከል ነዉ። 
በጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2007 በአዉስትራሊያ የተጀመረዉ የልጃገረዶች የክትባት ዘመቻ በበሽታዉ ከመያዝ  በፊት ክትባቱ ከተሰጠ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ አስተማማኝ ዉጤት ያለዉ መሆኑን መረጃወች ያሳያሉ። ክትባቱ 15 እና ከዚያ በታች ላሉ ልጃገረዶች ይሰጣል።በሽታን የመከላከል  አቅማቸዉ ከፍተኛ በመሆኑ፤በስድስት ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ፤ከ15 አመት በላይ ለሆኑት ደግሞ በስድስት ወር ልዩነት ሶስት ጊዜ ይሰጣል። ነገር ግን የክትባቱ ዋጋ በወጭ ደረጃ ዉድ በመሆኑ በርካታ ሀገራት ሁለት ጊዜ ብቻ ክትባቱ እንደሚካሄድ ባለሙያዉ ገልፀዋል።
የማህጸን ጫፍ ካንሰር ክትባት ለእርጉዝ ሴቶች፤የፈንገስ አለርጅ ላለባቸዉና የደም መፍሰስ ችግር ላለባቸዉ ሴቶች የማይሰጥ መሆኑንም ባለሙያወቹ ያስጠነቅቃሉ።

Krebs Krebszelle Illustration Gebärmutterhalskrebs
ምስል picture-alliance/picture-alliance/OKAPIA KG
Papillomavirus in Zellen von Gebärmutter
ምስል picture-alliance/OKAPIA

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።


ፀሐይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ