1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 14 2011

በሰበአዊ መብት ጥሰትም ሆነ በሙስና የሚጠረጠሩት እስካሁን የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱት ብቻ አይደሉም የሚል አስተያየት የሰጡ ብዙ ናቸዉ።ሱቱማ ጌይታ «ኦሮሚያን የሸጡ» ያሏቸዉን፣ «ሙክታር፤ አባዱላ፤ አስቴር፣ ኩማ» ይሉና ዋናዋናዎቹ እንዳይቀሩ።» ብለዉ ያሳርጋሉ

https://p.dw.com/p/38oI6
Myanmar Facebook
ምስል Getty Images/AFP/Y. A. Thu

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የቀድሞዋ ዳኛ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እና እስረኛ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሊቀመንበርነት መሾማቸዉ፤ የትግራይ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሥለ እስረኞች እና ድብቅ እስር ቤት የሰጡት አስተያየት፤ እና የፍርድ ቤት ሙግት የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን እንዳራኮተ-ሳምንቱ በሳምት ሊተካ ዛሬ ላይ ደረስን።አርብ።የዛሬ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።                                       

ከመጨረሻዉ እንጀምር።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ በሰብአዊ መብት ረገጣ እና በሙስና የሚጠረጠሩ ሰዎችን ከእያካባቢዉ እያሳደነ ማሰር-መክሰሱን ባለፈዉ ሕዳር 3 ይፋ ካደረገ ወዲሕ ላለፉት ሰባት ወራት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረዉ የፍርድ ቤት እሰጥ-አገባ ከቅድመ-ሰባት ወሩ በተቃራኒ ግን እንደ ቅድመ ሰባት ወሩ እንደገና ተጋጋግሟል።

በትንሹ 63 የቀድሞ የመረጃ እና ደሕንነት፤ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና የፖሊስ አዛዦች ተጠርጥረዉ የታሰሩበት የሰብአዊ መብት ጥሰት፤እና የሐብት ዘረፋ ከፍርድ ቤት ዉጪ፣ ከቤት-ለቤት ወሬ እስከ ምክር ቤት አዳራሽ መነጋገሪያ ሆነ ነዉ-የሰነበተዉ።«የዘንድሮዉ ግንቦት ሃያ ቂሊጦ ይከበራል» ይላል አንዱ የፌስ ቡክ ፌዘኛ።ስሙን ያልጠቀስነዉ አዉቀን ነዉ።አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ሥልጣን የያዙበትን የ1983ቱን ግንቦት ሃያን ለመጥቀስ።

የዚያን ቀን ኢሕአዲጎች የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያን ሲይዙ «ለሰፊዉ ሕዝብ ጥቅም--ተቆጣጠረ»ን ነበር የሰማነዉ?።ሰዒድ መሐመድ ትናንት በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አጭር አስተያየት እንዳሉት ግን ያኔ «ለሰፊዉ ሕዝብ ጥቅም» ያሉን ሹማምንት ያደረጉት ተቃራኒዉን ነዉ። «መዝረፍ ሙያ መሆኑን የተማሩት አይነ ደረቆች» ይላሉ አስተያየት ሰጪዉ  «ሀገር ሽጠው ቤት የገነቡ» እያሉ ቀጠሉም።

በሰበአዊ መብት ጥሰትም ሆነ በሙስና የሚጠረጠሩት እስካሁን የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱት ብቻ አይደሉም የሚል አስተያየት የሰጡ ብዙ ናቸዉ።ሱቱማ ጌይታ «ኦሮሚያን የሸጡ» ያሏቸዉን፣ «ሙክታር፤ አባዱላ፤ አስቴር፣ ኩማ» ይሉና ዋናዋናዎቹ እንዳይቀሩ።» ብለዉ ያሳርጋሉ።ገብረጊየርጊስ ገብረዮሐንስ፤-«ጄኔራል አበበ (የቀድሞዉ የአየር ኃይል አዛዥ) ለኢትዮጲስ ጋዜጣ የሰጡት አስተያየት» ያሉትን ፅሑፍ በቴሌግራም ገፃችን ላይ ለጥፈዉታል።

ጀሚላ ሐቢብ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት አስተያየት ተጠርጣሪዎችን መዘርዘሩን ወይም ተጠርጥረዉ የተከሰሱ እና የታሰሩትን እንደወንጀለኛ መቁጠሩን የሕገ-መንግሥቱን አንቀፅ 25 ድንጋጌን የሚቃረን መሆኑን ይጠቅሳሉ።«ማንኛዉ ተጠርጣሪ ጥፈተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት እስኪረጋገጥ ድረስ እንደ ነፃ ሰዉ የመታየት መብቱ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፣ ይሕ መከበር አለበት» ይላሉ ጀሚላ።

Äthiopien Debretsion Gebremichael
ምስል DW/M. Haileselassie

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግርም በሰብአዊ መብትም ሆነ በሙስና የሚጠረጠሩ ሰዎችን መንግስታቸዉ ለማሰር ቢፈልግ «አንድ አዲስ ከተማም ቢያዘጋጅ ለእስር ቤት አይበቃዉም ዓይነት ብለዋል።ጠቅላይ ሚንስሩ ከዋና ዋናዎቹ በስተቀር የሌሎቹን ጉዳይ የእርቅ ኮሚሽን መፍትሔ እንዲፈልግለት ማቀዱን ነዉ ያስታወቁት።

የጠቅላይ ሚንስትሩን አስተያየት እንደ መፍትሔ መቀበሉን ያልፈለጉ አስተያየቶች በተለይ በፌስ ቡክ ተነበዋል።

ገብረፃዲቅ ገብረ መድሕን፤«ዋና ዋና ማለት፤ ብሔር ተኮር ማለት፤ የትግራይ ተወላጆች ማለታቸዉ ይሆን የተከበሩ ዶክተር ዓብይ?» በማለት ይጠይቃሉ።«የቦርድ አለቃ (ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር) ደመቀ ሳይጠየቅ፣ የበታቹ የሆነዉ ክንፈ በምን ምክንያት ነዉ ዋናዋናዎቹ የሚባለዉ? በደሕንነት ከሆነ አለቃዉ (ጠቅላይ ሚንስትር) ሐይለ ማርያም መሆናቸዉን  ሕጉ ይደነግጋል።የደሕንነት ኃላፊዎች ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት እያለባቸዉ፤ (ኃይለ ማርያም) የፖሊስ ኮሚሽነርን የማዘዝ ሥልጣን እያላቸዉ-----በየትኛዉ መመዘኛ ነዉ ደሕንነት ለብቻዉ ተጠያቂ የሚሆነዉ?» ይላሉ ቀጥለዋልም።የገብረፃዲቅን አስተያየት ማዕረግ እና የቃላት አሰካክ አስተካክለናል።

ከተጠርጣሪዎች እነማንነት እና ብዛት ይልቅ በአያያዛቸዉ ላይ የሚሰጠዉ አስተያየት ጠንከር፤ከረር፤ ዘርዘር፤ ዘር-ጎሳ ለበስም ነዉ።ዋና ማቀጣጠያዉ ግን የትግራይ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ባለፈዉ ሰኞ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነዉ።

በተጠርጣሪዎች ላይ የሚወሰደዉን የማሰር እና ፍርድ ቤት የማቅረብ ሒደትን የትግራዩ ርዕሠ-መስተዳድር፣ ከሕጋዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ነዉ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር ነዉ፤ ተጠርጣሪዎች እጃቸዉ በካቴና መታሰር አልነበረበትም፤ የዉጪ ተፅዕኖ አለበት» ማለታቸዉ የብዙዎችን ቁጣ ሳይቀሰቅስ አልቀረም።

 

ፍቱን አማራ፣- በፌስ ቡክ ካሰፈሩት አስተያየት እንዲሕ የሚል አለበት።«የትግራይ ህዝብ የቆመው በሌቦቹ አቅም ይመስል ሌቦች ሲያዙ እና ሲታደኑ እርምጃው የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ ነው ብሎ ማለት የትግራይ ህዝብን መስደብ ነው! ይመስለኛል ደብረፂዮን በክሽፍ አክቲቪስቶቻቸው ተፅዕኖ ስር ወድቀዋል! ጭራሽ ብለው ብለው የሌቦች አደናውን የውጪ ሃይሎች ፍላጎት እንደሆነ አድርገው መግለጫ ሰጥተዋል ... ያሳዝናል!»

 

አዲስ ቸኮል፤ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2013 እስከ 2017 የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ወይዘሮ ፓርክ ጌዩን ሐዬ በሙስና ተወንጅለዉ እጃቸዉ በፌሮ ታስሮ በሚያሳየዉ ፎቶ-ግራፍ በተደገፈ መጣጥፋቸዉ  «እስኪ ከብሽሽቅ መንፈስ ወጥተን እንወያይ» ይላሉ።አዲስ ቸኮል፣ ወይዘሮ ፓርክ ጌዩን ሐየ «የተከሰሱበት ወንጀል ከኛ ሐገር ጋር ሲነፃፀር ኢምንት» ይሉታል።

«ፍርድቤት ሲቀርቡ በካቴና ታስረው ነው:: እኛ ሃገር እነ አቶ መረራ ጉዲና (ዶከተር በሚለዉ ይስተካከል) በካቴና ታስረው ስናያቸው እንዳዘንን ሁሉ ሳያስቸግሩ እጅ የሰጡት አቶ ክንፈ ዳኜው በካቴና ታስረው ማየታቸው እንዳላስደሰታቸው የትግራዩ አቶ ደብረጽዮን በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል::

እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይ አዛውንትም ቢሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በካቴና መታሰራቸው ከህግ በታች መሆናቸውን ስለሚያሳይ በካቴና መታሰር አለባቸው ይላሉ ወይስ ደጋፊ ያላቸው ፖለቲከኞችም ሆኑ ታዋቂ ሰዎች እስካልተፈረደባቸው እና ያስቸግራሉ ተብሎ እስካልተገመተ ድረስ በካቴና ባይታሰሩ ምንም ችግርየለውም ብለው ያምናሉ??»

ዓረፍተ ነገራቸዉን በሁለት የጥያቄ ምልክት ደመደሙ።ጥያቄዉ ለትግራይ ርዕሠ መስተዳድር ለዶክተር ደብረፅዮን ነዉ።

ኤፍሬም አለሙ ግን ይመክራሉ፤-«እውነቱ እስኪረጋገጥ ብንጠብቅ ምን አለበት፡እስኪ እዚያ ቦታ የተገኘው የኔ አባት ቢሆንስ ብለን እናስብ እባካችሁ» እያሉ

ዘሙሌ ዘፀሐ ደግሞ  ይጠይቃሉ፣ «ሌባ እና የግግራይ ሕዝብ ምን አገናኘዉ እያሉ»

Äthiopien Birtukan Midekssa Vorstand Wahlkommission
ምስል DW/G. Giorgis

«ሕዝቡ ራሱ በስሙ እየተነገደ ስለሆነ፣ እዉነተኛ የህዝብ መሪ ብትሆን በሕግ ለመፋረድ ትወስን ነበር።አንተ ግን የሌቦቹ መሪ እንጂ ነፃነትን ፍለጋ ልጁን የገበረ ሕዝብን የሚወክል ሞራልና ተቆርቋሪነት አይታይብሕም።-----ለተራማጅ ወጣቶች ቦታሕን ልቀቅ።»

 

የትግራይ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ስለ ተጠርጣሪዎቹ አያያዝ እና የፍርድ ሒደት፤ ትግራይ ዉስጥ የድብቅ እስር ቤት አለ ሥለመባሉ የሰጡት ማስተባበያም ብዙ አስተያየት አስከትሏል።እኛ በአሌክስ ማምዝ አጭር መልዕክት እናሳርግ እስረኞቹ፣ «ሐይላድ አይንጠልጠልባቸዉ እንጂ ካቴናዉ ሽግር የለዉም» አሌክስ ማምዝ ።በፌስ ቡክ።                                    

ትናት አዲስ አበባ።ተሾሙ ቃል ቀቡ።ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ።

የቀድሞዋ ዳኛ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እና እስረኛ የሐገሪቱን የምርጫ ሒደት እና ዉጤትን የሚያዘጋጅ እና በበላይት የሚቆጣጠረዉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበላይ ሆነዉ መሾማቸዉ ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ከሳምንቱ ርዕሶች ትልቁ ነዉ።

ልዑል መኮንን በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት ፅሁፍ «ለስፍራዉ ተገቢ ሰዉ» ይላሉ።ምስጋና ለጠቅላይ ሚንትሩ እና ለለማ ቡድን» አከሉ ልዑል።

ሙሉጌታ ስለሺ የሰጡት አስተያየት አዋጅ መሠል ነዉ።« ለዘመናት የህዝቦችን ድምፅ ሲሠርቅ የነበረው የቀድሞው ምርጫ ቦርድ የህዝብን ድምፅ ለማሥጠበቅ እና የድምፅ መሥጫ ኮሮጆን ደህንነት ለማጠበቅ ሢባል በዲሞክራሲያዊ መንገድ ጀግናው የአብይ ቲም ለትክክለኛዋ የሴት ጀግና ተሠጥቷል ህዳር 2011 ዓ.ም» 

ተስፋዬ ሆንጃ ኬን፤-ሹመቱን ካደነቁ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አንዱ ናቸዉ።«ይገባሻል፤ ሲያንስሽ ነዉ» ይላሉ አዲሷን የምርጫ ቦርድ ሹም።በዚሕ አላበቁም «አገር ወዳድ እንቁ ሴት» አከሉ።

ወይዘሪት ብርቱካን በግልፅ ከሚታወቁ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለከፍተኛ ሥልጣን ሲሾሙ የመጀመሪያዋ ከፍተኛ ፖለቲከኛ ናቸዉ።አንዳድ አስተያየት ሰጪዎች በሹመቱ ላይ ቅሬታ እና ተቃዉሞ ለማንሳት ሰበብ ምክንያት የሆነዉም ይኸዉ ነዉ። የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ምክትል ሊቀመንበር፤ ኋላ ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ሊቀመንበር ሥለነበሩ ገለልተኝነትን የሚጠይቀዉን የምርጫ ቦርድን ገለልተኛ ሆነዉ እንዴት ይመራሉ ነዉ? ቅሬታ-ተቃዉሞዉ።

ዳዊት ሰላም፤-

« Birtukan ምን ያህል ነፃ ሆና ታስፈፅመዋለች ሳይሆን ዋንኛው ችግር የሚሆነው ምንያህል ታችኛውን የምርጫ አስፈፃሚ አካል ተቆጣጥራ ታስፈፅማለች ነው? ምን ያህል የክልል የህግ አስፈፃሚ ለፌዴራሉ ምርጫ ኮሚሽን ታዛዥ ይሆናሉ?»

የዳንኤል ብርሐኔ አስተያየት፣ ጠንከር፤ ፈርጠም፤ ወደ አሜሪካኖችም ሻገር ያለ ነዉ።በእንግሊዝኛ ቋንቋ በፌስ ቡክ በዝርዝር የፃፉትን በቲዊተር ቆጠር አድርገዉ አሰራጭተዉታል።ሁለተኛዉን ነዉ-የወስድነዉ።«የብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የተወሰነዉ በአሜሪካኖች።» «እነሱ (አሜሪካኖቹ ማለታቸዉ ነዉ) ለመጪዉ ምርጫ የራሳቸዉ ዕቅድ (blueprint) አላቸዉ።(ጠቅላይ ሚንስትር) ዐብይ ዕቅዱን ያስፈፅማሉ (ይከተላሉ) ተብሎ ይጠበቃል።»ኢብራሒም ሙሉሸዋ ዘለግ ባለ የፌስ ቡክ መጣጥፋቸዉ የአስታራቂ ዓይነት አስተያየት ስጥተዋል።

«ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለፍትህና ለዲሞክራሲ መርሆች መከበር የከፈሉት መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራሱ አንፀባራቂ ቦታ እንደሚይዝ ጥርጥር የለኝም።» ይላሉ ኢብራሒም።

«የተሰጣቸው ሃላፊነት እሳቸው ሲታገሉለት የነበረውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማሳካት ታላቅ ሚና የሚጫወት ነው።» አክለዉም፤  

«የወ/ሪት ብርቱካን ትግል እና የተከተሉት የፓለቲካ መስመር ግን ሁሌ እና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝላቸው አይሆንም። ሀሉም ብርቱካንን እንደ ገለልተኛ ይቆጥራል ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው።» አቋማቸዉ ያልሆነዉን አቋም እንዲሕ ይገልፁታል።

የብርቱካንን መሾም በጥርጣሬ የሚያዮ ሰዎች ስጋትን ባልጋራም አስተሳሰባቸው ግን አመክኖ የሌለው ባዶ ጭሆት አድርጎ መውሰድ በራሱ ችግር ያለበት አመለካከት ነው። ወ/ሮ ብርቱካንም ሆኑ መንግስት ይህ ስጋት ያለባቸው ሰዎችን ተቃውሞ አስመልክቶ ስጋታቸውን ለመቅረፍ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለባቸው።»

ደመረ አበበ፤ በተካረረዉ ፖለቲካዊ ክርክር የተሰላቹ ይመስላሉ።«ከእንግዲሕ ምርጫ በጣም ታማኝ ከመሆኑ የተነሳ---እንኳን ድምፃችንን ብርም የምናስቀምጠዉ እዚያ ነዉ።» ይላሉ።ገንዘብ ላለዉ መጥፎ አይደለም። ባለገንዘብ ያድርገና።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ