1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2011

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዘ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተከሰተ ግጭት፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ እና የአንድነት ሀገር አቀፍ ስብሰባ አስመልክቶ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተጻፉ አስተያየቶች አሰባስበናል። 

https://p.dw.com/p/3HtI1
Instagram-Icon
ምስል picture-alliance/xim

«..ትልቅ ሰው አጣን» የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ኅልፈት

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በ76 ዓመታቸው ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።  የ76 ዓመቱ ዶ/ር ነጋሶ ላለፉት 30 ዓመታት በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ አድርገዋል። ለሰባት ዓመታትም አገራቸውን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል፡፡ 
መዘሚር ማሞ «የእውነት ኖሮ የእውነት መሞት ምንኛ መታደል ነው? ትልቅ ሰው አጣን» ብለዋል በፌስቡክ የዶ/ር ነጋሶን ሞት አስመልክቶ በጻፉት አስተያየት። ለሁሉም ሰላም የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው «ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በ1986 ዓ.ም የካድሬ ስልጠና ከሰጡኝ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ናቸው። የሳቸው ርዕስ የኦሮሞ የገዳ ሲስተም የኦሮሞ መስፋፋት ሁኔታን በሚገባን ቋንቋ ከዘረኝነት በጸዳ እውነተኛ የኦሮሞ አቃፊ እንጅ ጠባብ ብሄርተኝነት ያልነበረውና ለወደፊትም የማይኖረው ህዝብ መሆኑን በወጣትነት ዘመኔ አስገንዝበውኛል። ብቻዬንም አልነበርኩም ከሀምሳ በላይ የአገራችን ብሄር ብሄረሰብ ተወላጅ ካድሬዎችን ያሰለጠኑ በአቋማቸው የጸኑ ለሆድ ያላደሩ የተመቸን ቦታ በመልቀቅ በእግራቸው በህዝብ ታክሲ እስከ መጓዝ የደረሱ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ነበሩ። እግዚአብሄር ነብሳቸውን ይማርልን።» ብለዋል። 
ዘሪሁን ሆላንሶ አሼ «እሳቸውን የበደለው የኢህአዴግ መንግስት ነው። የሀገሪቱ መሪ የነበሩ ሰው ታክሲ ጠብቀው እስከመሳፈር ድረስ ዝም መባላቸው ሳያንስ በተገቢው እንኳን እንዳይታከሙ ደመወዝና ሌላ ጥቅማ ጥቅም ተከልክለው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ከአንደበታቸው ሰምተናል። በእሳቸው ላይ የዚህን ዓይነት ግፍ የሰሩ ሰዎች የእጃቸውን ዋጋ ማግኘታቸው የማይቀር ቢሆንም እሳቸው ግን ለትውልዱ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው ያለፉ አባት ስለመሆናቸው ሁሉም ሲዘክር ይኖራል» ብለዋል። 
ርዕዮት አለሙ በትዊተር «ዶ/ር ነጋሶ እየሄዱበት ያለው መንገድ ልክ እንዳልሆነ ሲረዱ በጥፋት ያለመቀጠልን እንዲሁም ላመኑበት ጉዳይ ሲሉ ትልቅ የመሰለውን ምድራዊ ነገር ሁሉ ለማጣት መፍቀድን በተግባር ያሳዩ ፖለቲከኛ ነበሩ» ስትል ጽፋለች።
"ታሪክ ሰሪ" ይሏቸዋል ብርሀኑ ሻሎሞ ብሬክስ «ዶ/ር ነጋሶ በእርግጥ ታሪክ ሰሪ ለእውነት የሚታገሉ ባለስልጣን ውስጥ አንዱ ናቸው። ፈጣሪ ነብስዎን ይማር ... ስለዚህ ለሀገር ብሎ ለኢትዮጵያ የሚታገል መሪ በእውነት እርሱ ነው ምርጥ ኢትዮጵያዊ።» ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ሌላዉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተቀሰቀሰ ግጭት ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች የሚያሳዩ እና በማህበራዊ ድረ- ገጽ የተለቀቁ ዘግናኝ ፎቶዎች በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ባለፈው ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዘ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በሁለት ዕቃ ጫኝ እና  አውራጅ ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ የጉልበት ስራ ዋጋ አለመግባባት ተከሰተ በተባለው ግጭት፤ የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፤ በማህበራዊ ድረ ገጾችም ይሄው ተስተጋብቷል።
ጊዜ የሚስጥር በሚል የፌስ ቡክ ስም በሰጡት አስተያየት «በሰው ነፍስ ዕቃቃ ነው የተያዘው፤ መንግስት ምን እስኪፈጠር እንደሚጠብቅ አልገባኝም። ያውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባት ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ፤ ይህ ሁሉ ግድያ ሲፈጸም ዝምታ» ብለዋል። 
በትዊተር ገጻቸው ዘመኑ የተባሉት አስተያየት ሰጪም «በቀስት የተወጋው ህጻን ልጅ ምስል አዕምሮዬ ውስጥ ተሰንቅሮ እንዴት እንደምተኛ እንኳን አላውቅም»
ሲሉ በሌላም ጽሁፍ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ «በየቦታው የሚታየውን እልቂት መንግስት መቆጣጠር አይችልም? ለአይን የሚከብዱ አሰቃቂ ብሔር-ተኮር ግድያዎች ሲፈጸሙ ምንም ማድረግ የማይችል መንግስት መኖሩ ጥቅሙ ምንድን ነው።» ሲሉም ጽፈዋል።
«እኛ እርስ በርስ ካልተከባበርን መንግስት የመቶ ሚሊዮን ህዝብ ጒዋሮ ሊጠብቅ እንዴት ይችላል?» ይላሉ በጥያቄ ኤልያስ በትዊተር አስተያየታቸው ሰተዋል።
ናትናኤል መኮንን እብደት ነው ይላሉ በቲዊተር ገጽ ጽሁፋቸው «ዘረኝነት ማለት ከግጭቱ መነሻ ጋር ቀጥታ ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች ላይ ጥቃት እንድታደርስ የሚገፋፋ እብደት ነው። በመተከል የሆነውም ይሄው ነው! ዘረኝነት ይውደም::» ሲቀጥሉም «በየክልሎቹ የክልል ልዩ ሀይል ፖሊስን ፍርድ ቤትን በክልል እና በዘር በተደራጀበት ሀገር ላይ ፍትህ ተቆፍሮ ተቀብሯል። እመነኝ ፍታዊ የሆነ ፍትህ ከሌለ መቼም ቢሆን ሰላም የሚባል ነገር አይኖርም። ሞት ይቀጥላል!!!» ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።   
ከተነሳው ግጭት ጋር በተገናኘ ለመፍታት ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ታውቋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ምርመራው ኅብረተሰቡን ባሳተፈ እየተከናዎነ እንደሆነ፤ ከጉዳዩ ጋር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ታውቆ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ማረጋጋት ስራ ላይ እንዳሉ የክልሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።  
እየተወሰደ ነው የሚባለው እርምጃ ውብሸት በላቸው እንዲህ በሰጡት አስተያየት ይቃወሙታል። «የህግ ማስከበር ጉዳይን በተመለከተ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱ አቋም ግልጽነት አጥቷል። እርምጃም እየተወሰደ አይደለም። ይህ ሁኔታ በህዝብ ልቦና ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ በመንግስት አለመተማመን እንዲሁም ስጋት ከፈጠረ ውሎ አድሯል። በመከላከያና በክልል የጸጥታ ሀይሎች መናበብ የለም። የተምታታ መግለጫ በአንድ ጉዳይ ላይ ይሰጣል። አሁን አገሩን እያሸበሩ ያሉት ህገ ወጥ የወጣት ስብስቦችና ለውጡን የሚገዳደሩ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሀይሎች ናቸው። መንግስት ይህንን ጉዳይ በግልጽ ለህዝብ ይፋ በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ህዝብ እንዲያውቅና በዚህ መስመር ውስጥ ያሉትም እንዲማሩበት ያስፈልጋል። እሽሩሩ ማለት በቃ።» ብለዋል። ቃሌ ክፍሌ በሚል የፌስ ቡክ አስተያየትም «በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት አለ ለማለት እኔ ይከብደኛል ብቻ እግዚአብሄር እጆቹን ወደ ኢትዮጵያ ይዘርጋ» ሲሉ ልመናቸውን ወደ ፈጣይ ያቀርባሉ። ሃዋ ሁሴንም እንደ ቃሌ ክፍሌ ሁሉ «ኢትዮጵያ አሁን መንግስት አለ ለማለት ይከብዳል። የተከበረው የሰው ልጅ ህይወት በቀስት እየታደነ ሲጨፈጨፍ በጣም ያሳዝናል። አላህ በእዝነት አይንህ አገራችንን እያት ከአንተ የሆነን ሰላም አውርድልን አገራችን ላይ» ብለዋል በጽሁፋቸው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ እና አንድነት የምክክር መድረክ ትናንት ተካሄዷል። የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት መሰረታዊ እርምጃ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት፤ ይሄው የምክክል መድረክ የተቋማዊ ለውጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማስማማት ጥረት እንደተደረገ ታውቋል።
«የዛሬው ውሎ በራሱ ትልቅ ክስተት ነው» ይላሉ ሞባሸር ሀበሻ በመንደርደሪያ ጽሁፋቸው  «የመንግስት ጣልቃ ገብነት በሌለበት (እንዲያውም መንግስት ለመፍትሄው የአንበሳውን ድርሻ በወሰደበት ሁኔታ) ሙስሊሙ እርስ በርሱ በነጻነት ተፋጭቶ መጻኢ እድሉን በእጁ የጨበጠበት ዕለት ነው። ልዩነቶቻችን ጠፍተዋል ማለት ግን አይደለም። በዛሬው ቀን የተማርነው ትልቁ ነገር ጥሩ መሪ ሲያገኝ አብዛኛው ሙስሊም ለትልልቆጡ ግቦቹ ሲል ጊዜያዊ ስሜቶቹን ለመግራት እንደማይቸገር ነው። ይህ ያማረ ጅማሮ ከዳር የሚዘልቀው ብዙሃኑ በዛሬው መንፈስ ሲሰለፍና ሃላፊነት የተጣለባቸው አባቶች በዘጠኙ ኮሚቴ ልክ በዕልክና በወኔ ሲሰሩ ነው። ሂደቱን ሲሞግቱ የነበሩ ወንድሞች ከፕሮግራሙ መጠናቀቅ በሃላ እየሰጡት ያለው አስተያየትም ለብዙሀኑ ሃሳብ የመገዛትና ቀጣዩን ሂደት የመደገፍ አዝማሚያ መሆኑ የበለጠ ልብን ያሞቃል። ስንተባበር ሁላችንም እናሸንፋለን። እርቅና አውፉታችን የምር ለአላህ እናድርግ።» ሲሉ በጽሁፋቸው ጠቅሰዋል።

Äthiopien  Institutioneller Reformausschuss der Muslime
ምስል DW/Y. Gebrezihaber
Negasso Gidada ehemaliger Präsident von Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebregziabher

«ለህዝበ ሙስሊም ወንድሞቻችን እህቶቻችን በግልም ጓደኞቼ እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች በሙሉ ዛሬ መልካም ዜና የምትሰሙበት ዕለት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ምን ያህል አባቶቻችን ለሁለት ሲኖዶስ ተከፍለው ውስጣችን እንዳዘነ እና ወደ አንድነት ሲመጡ ምን ያህል ደስታ እንደተሰማን ስለማውቅ ለእናንተም መልካሙን ሁሉ ትሰሙ ዘንድ መልካም ምኞቼ ነው። ፈጣሪ ከእናንተ ጋር ይሁን።» ፈቃዱ ፈለቀ በፌስ ቡክ ያሰፈሩት ጽሁፍ ነበር።

አናን አሞሃቢብ የተባሉ እንዲህ ብለዋል «ውስጤ ደንዳና እንባ አወጣለው ብዬ አላስብም ነበር። የሙፈሪያት እንባ ከውስጤ ፈንቅሎ ወጣ መንገድ ላይ ነበርኩ ሰው እንዳያየኝ ዝቅ ብዬ ከአንዴም ሁለቴ አልቻልኩም በቃ» ሲሉ በወቅቱ የተሰማቸው በፌስ ቡክ ጽፈዋል።
«ምን ብዬ እንደምገልጸው ባላውቅም ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበት ብዙዎች የታሰሩበት፣ የተደበደቡበት፣ ከሀገር የተሰደዱበት፣ ብዙዎች የሞቱበትም ነው። ብቻ ለብዙ ዓመታት ሙስሊሙ ህብረተሰብ የታገለለት መብቱ ሚያዝያ 23 ለድል የበቃበት ቀን ነው።» የአማን ማምዬ የፌስ ቡክ ጽሁፍ ነው።
ይሳኮር ዘጦቢያ ወቅኔ «ውድ ሙስሊም ወገኖቼ መሰባሰባችሁ በጎ ነገርን ይዞ እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም» ሲሉ እምነታቸውን ያስረግጣሉ። መልዕክታቸውንም ሲቀጥሉ «ያለ እናንተ እኛ ባዶ ነን ወንድም ከወንድሙ ሲተባበር ሲደጋገፍ ሀገር በጽኑ መሰረት ላይ ትገነባለች። እናንተ የፍቅር ተምሳሌቶች ስለ እናንተ ቸር ቸሩን ያሰማን ወንድሞቼ።» ሲሉ መልዕክታቸውን ይደመድማሉ። ሰምሃር ተክሌ በቲዊተር ገጽ እንዲህ ብሏል «እስቲ ይህን ቀን በታሪካችን ውስጥ እንፃፈው!» 

ነጃት ኢብራሒም

እሸቴ በቀለ