1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜቴክ ሙስና፤ ዘግናኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት

ዓርብ፣ ኅዳር 7 2011

የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ በተለያዩ እስር ቤቶች የተፈፀሙ ስቅይት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና የብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ የሙስናና ብልሹ አሰራርን በሚመለከት የተሰጠዉ መግለጫ እና የተጠርጣሪዎች መያዝ፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ።

https://p.dw.com/p/38Pp3
Police have detained Major General Kinfe Dagnew, former Director General of the state-owned Metals and Engineering Corporation
ምስል Ethiopian government communication

«ለሕዝብም ለብሔርም ብሎ የሚዘርፍ የለም»

የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቬ ህግ በሜቴክ ተፈፅሟል ያለዉን ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም በተለያዩ ዕስር ቤቶች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ባለፈዉ ሰኞ ያወጣዉ መግለጫ እና በርካታ ሹማምንት በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረዉ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ የዛሬዉ የማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሚያተኩርባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ያለዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ባለፉት ጥቂት ቀናት አስደንጋጭ ፣ አስገራሚና አነጋጋሪ  የሚባሉ ክስተቶችን አስተናግዷል። የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ባለፈዉ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ኃላፊዎች ፈፅመዉታል ያሉትን ሙስና  ይፋ አድርገዋል። ይህ ግዙፍ ድርጅት ላለፉት ስድስት ዓመታት የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ግዥ ሲፈፅም ያለ ምንም ጨረታ መሆኑንም ተናግረዋል።በመግለጫዉ የሙስና ወንጀል ምርመራ ግኝቶች ከተባሉት ዉስጥም የመርከብና አዉሮፕላን ግዢና ሽያጭ ይገኝበታል።በዚህም የ37 ብሊዮን ብር  ግዥ ያለ ምንም ጨረታ መፈፀሙ ተመልክቷል።ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ በማህበራዊ በመገናኛ ዘዴዎች ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ።

ጋዜጠኛ ሀይሉ ስጤ በፌስ ቡክ ገፁ ባሰፈረዉ ፅሁፍ ከድሃዉ ህዝብ በግፍ የተዘረፈዉ ገንዘብ  «በራስ ሀገር ዜጋ ሳይሆን በቀኝ ገዢም ይደረጋል ለማለት ይከብዳል ፡፡ » በማለት ፅፏል።

ሌላዉ «ሀሁ» የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ።«ወገን ሜቴክ ባለፉት ዓመታት አባከነ የተባለዉ ቢሊዮን የሚቆጠር ብር እኮ የሀገሪቱን የ10 ዓመት በጀት ማለት ነዉ።ስንት ሆስፒታል ስንት ትምህርት ቤት ወዘተ ልንሰራ እንችል እንደነበር ማስላት ነዉ »  ሲሉ አማሬሳ ነኝ ያሉ ሰዉ ደግሞ« እኔ በበኩሌ ገንዘብ ሳይሆን ሀገር እንደጠፋ ነዉ የምቆጥረዉ።ብለዋል።

በሌላ በኩልም የጠቅላይ አቃቤ ህግ በቁጥጥር ስር በዋሉ ተጠርጣሪ ዜጎች ላይ ተፈፅሟል ያለዉን ለጀሮ የሚከብድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይፋ አድርጓል።ይህ መግለጫ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት የተቀባበሉትና አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ኤዶም ካሳዬ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ በታሰረችበት ወቅት ያጋጠማትን በቲዉተር ገጿ እንዲህ ፅፋዋለች።

Schild Äthiopisches Bundesgericht
ምስል DW/G.Egziabher

 «እኔና ጓደኞቼ የታስርን ቀን አርብ ሚያዚያ 17,2006ዓ.ም ማዕከላዊ እያደናበሩ እና እየገፈታተሩ ርቃኔን ቁጭ ብድግ እያልኩ የተፈተሽኩት፣(በዱብ እዳ ወስደው ምን ትይዛለች ብለው እንዳሰቡና እንዳዋከቡኝ እስከዛሬ ሊገባኝ አልቻለም)፣እናቴ እኔን ለማየት እግሯ እስኪቀጥን ማዕከላዊ ስትመላለስ አናስገባም ብለዋት የለበሰችውን ነጠላ መሬት አንጥፋ የልጄን ሬሳ ስጡኝ ብላ ስታለቅስ (ጠንካራዋን፣ብርቱዋን እናቴን) ምን ያስጮሆታል ያላት መርማሪ ፖሊስ ዛሬ መታሰሩን ሰማሁ።ለአስራ አምስት ቀናት ቤተሰብና ጠበቃ ማንም ሳያየን ለመጀመሪያ ጊዜ አባቴን ሳገኛው በህይወቴ ሙሉ አይቼው የማላውቀው ፊቱ ላይ የሚነበበው የአቅም ማጣት ስሜት እና እምባው፣የማዕከላዊ በደል ዛሬ አዲስ ይመስላል እንጅ፤የህይወቱ አካል ለሆንነዉ አዲስም  አይደል።ምኞቴ ማንም እኛ ባለፍንበት የግፍ መንገድ እንዳያልፍ ፤ አሁን ያለዉ የፍትህ ተቋም ከፖለቲካ ጥቅም ባሻገር አዙሪቱን በመስበር ለፍትህ ዘብ እንዲቆም ነዉ።» ሞቱማ አሰፋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ«አብዛኛዉ ሰዉ በአዉሮፕላንና በመርከብ መጥፋት ላይ  ትኩረት አድርጎ ነዉ  አስተያየት የሚሰጠዉ ።ይህ ጉዳይ የሚያረጋግጥልኝ ከምንም በላይ ቁሳቁስ ስሜታችንን መግዛቱ ነዉ ። ከበደልም በደል የሚባለዉ ግን በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈፀመዉ በደል ነዉ።» ብለዋል

አበበች በቀለ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ« የተፈፀመዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እኛ ስንሰማዉ ዉስጣችን እንዲህ የቆሰለ፤ጉዳቱ የደረሰባቸዉ ወገኖች እንዴት ተወጡት?  ሲሉ ይጠይቃሉ።ቀጥለዉም «ክብር በስቃያችሁ ይችን ቀን ላመጣችሁ የግፍ ሰለባዎች»በማለት ፅፈዋል።

የጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሀላፊ አቶ ብርሐኑ መግለጫዉን ከሰጡ ከአንድ ቀን በኋላም የሜቴክ ዋና ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን እንዲሁም የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሀላፊ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በርካታ በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ የመንግስት ባለስልጣናት ተይዘዉ በቁጥጥር ስር ዉለዋል። እየዋሉም ይገኛሉ።የባለስልጣናቱን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችን በሁለት ጎራ ከፍሎ ሲያከራክር ተስተዉሏል።በአንድ በኩል ጉዳዩ ለፖለቲካ ጫወታና ለመጠቃቂያ እየዋለ ነዉ በሚል አስተያየት የሚፅፉ ሲኖሩ በሌላ በኩል ግን »መንግስት ከአሁን ቀደም ወደ እርምጃ አልገባም» እየተባለ ሲታማበት የነበረዉን ጉዳይ ፉርሽ አድርጎ ወደ ተጨባጭ እርምጃ እየገባ መሆኑን  የሚያሳይ ነዉ በማለት አስተያየት የሰጡ አሉ።

አባተ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ «እንግዲህ በቁጥጥር ስር ስታዉሉ ቀጣዩ ትዉልድ በቁጥጥር ስር ያዉለናል ብላችሁ እያሰባችሁ መሆን አለበት ።ትዉልዱ ኢትዮጵያያ ዉስጥ ያለዉን ድራማና ሴራ እየተመለከተ ነዉና።»ብለዋል

ጋዜጠኛ ኤልያስ አማን በፌስ ቡክ ገፁ የሚከተለዉን ፅፏል «እኔን እያስፈሩኝ ያሉት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥተው ይህንን ሀገራዊ ግፍና ሌብነት ከማውገዝ ይልቅ፣ ዳር ዳሩን የሚዞሩና ከሌላ አጀንዳ ጋር ለማላጠፍ የሚሞክሩ ዜጎቻችን ናቸው!! ወደፊት ዕድሉን ካገኙ ይህንን ክፋት ከመድገም ወድሁዋላ የማይል የከሰረ ሞራል ይታይባቸዋልና!! ለኔ የየትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሆነ ህዝብ የመጀመሪያው የሞራል ልዕልና መገለጫ እንዲህ ዓይነቱ ኢሰብዓዊ ድርጊት በራሱ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌላ በማንኛውም የዓለም ህዝብ ላይ ሲደርሥ ከማውገዝ ይጀምራል!!»

ክብሮም አድሃኖም ገ/የሱስ የተባሉ ሰዉ በፌስቡክ ያሰፈሩት ደግሞ እንዲህ ይላል።«ጉዳዩ የፖለቲካ ነዉ። በቀል ነዉ ።ለሚሉት መልሳችን የቤተክርስቲያን አባቶቻችን እንደሚሉት »ከሰዉ ከሆነ ይጠፋል ከእግዚዓብሄር ከሆነ ግን ይገፋል»ነዉ።

«የማይነኩ የሚመስሉ ግን ደግሞ እየተነኩ ብሎም እየተገረሰሱ ያሉ የስልጣን ቋጥኞች አሁን ቦታቸዉን እያገኙ ነዉ።እስከ ክልልና ዞን መዉረድ ግን አለበት።»ሲሉ አስናቀ የተባሉ ሰዉ በቲዉተር ገፃቸዉ ጽፈዋል።

የሜጄር ጀነራል ክንፈ ዳኜዉ የፍርድ ቤት ዉሎም ሌላዉ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር። በተለይም ጡረተኛና የ4 ሽህ ብር ደሞዝተኛ በመሆኔ የገንዘብ ዓቅም የለኝም መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ ማለታቸዉን  ።በርካቶችን ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።

መሰረት ገዳሙ የተባሉ «ይህቺ ሀገር ወዴት እየሄደች ነው ? 27 ዓመት ሀገራቸውን በቅንነት የመሩና ኢኮኖሚውን በሁለት ዲጅት ያሳደጉ ባለውለታዎቿን እንዴት በስማቸው ቤት ሳይኖራቸውና በ4 ሺህ ብር ጡረታ ታሰናብታለች።በማለት ፅሁፋቸዉን በትዕምርተ ስላቅ ቋጭተዋል።

ሀገሬ ኢትዮጵያ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ «ግለሰቡ እኮ ተጠርጣሪ እንጅ ወንጀላቸዉ አልተረጋገጠም። ስለዚህ እንደማንኛዉም ተጠርጣሪ መጠየቅ መብታቸዉ ነዉ»ሲሉ ፅፈዋል ።

Äthiopien verhaftet 63 wegen Verdachts auf Menschenrechtsverletzungen, Korruption. Der Generalstaatsanwalt Berhanu Tsegaye sagte heute (03.11.2018) lokalen Journalisten, dass die Inhaftierung nach fünf Monaten Ermittlungen erfolgt.
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

መግለጫዉን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን «ምናባዊዉ» በሚል ርዕስ የተላለፈዉና በሜቴክ ያልተገባ አሰራርን ላይ ያተኮረዉ የዶክመንተሪ ፕሮግራምም በሳምንቱ ብዙ አነጋግሯል።በተለይ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ «ለህዝብም ለብሄርም ብሎ የሚዘርፍ የለም።የሚዘርፈዉ ለራሱ ነዉ።ዘራፊ ሀገርም ሞራልም የለዉም» የሚለዉ የአምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ንግግር በርካታ የፌስቡክ ተከታታዩች የተቀባበሉት ነበር።አምባሳደሩ ከዚህ በፊት ለሜቴክ ፅፈዉት ነበር የተባለ የአቤቱታ ደብዳቤም እንዲሁ። በአንፃሩም የሜቴክ ጉዳዩ በፍርድ ቤትና በምርመራ ላይ ባለበት ወቅት  ኢቲቪ ዘጋቢ ፊልሙን ማቅረቡ ተገቢ አይደለም በሚል  ዘጋቢ ፊልሙን የተቹም አሉ። አለማየሁ ገብሬ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ « ፕሮግራሙ በሀገር ላይ የደረሰዉን ጥፋት በስፋትና በጥልቀት የሚያሳይ ቢሆንም፤ኢቲቪ አሁንም «ጅሃዳዊ ሀረካትን»ና «አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ» በሰራበት ስታይሉ እየቀጠለ ያለ ነዉ የሚመስለዉ።ይህንን ሁሉ ጉድ እስካሁን ለምን አላሳየንም።ከዕስራት በፊት ዶክመንተሪ ይሉሃል ይሄ ነዉ።» ሲሉ ፅፈዋል።

በመንግስት እየተወሰደ ያለዉን የሰሞኑን ርምጃ  በመደገፍም የአማራ ፣የትግራይ እንዲሁም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና  ህዝቦች ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ድጋፋቸዉን የሚያሳይ መግለጫ  ያወጡ ሲሆን፤  በትናንትናዉ ዕለትም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ «ካንሰርን እንዋጋ »በሚል ርዕስ በፅሁፍ በሰጡት መግለጫ «ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረቡ  ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል » ማለታቸዉና «ድሮ ወንጀለኛ የሚደበቀው ጫካ ውስጥ ነበር አሁን ደገሞ ወንጀለኞች የሚደበቁት ብሔር እና ጎሳቸው ውስጥ ሆኗል» ማለታቸዉ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተከታታዮች ትኩረት ሆኖ ታይቷል።ብዙወችም ተቀባብለዉታል።

አሻግሬ ተረፈ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ «ለጠቅላይ ሚንስትሩ ነገሩን ከባድ ያደረገባቸው ይኸው ጉዳይ ነው።ማንም ደካማ ዘርፎ ዘሩ ላይ ሄዶ ከተወሽቀ አስቸጋሪ ነዉ»ሲሉ ፅፈዋል። የክልሎቹን መግለጫ በተመለከተ«ሲበላ ሳቀ» በሚል ርዕስ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በፌስቡክ ገፁ እንዲህ አስፍሯል።
«በሀገራችን ሲፈጠር የነበረው ችግር ሁሉ በአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ ነው ወይ የተፈጠረው? በየአካባቢው ዛፉን ሲያስቆርጡ የነበሩ ጠማማ የመጥረቢያ እጀታዎች አልነበሩም ወይ?  በማለት ይጠይቅና፤ክልሎቹ የፌዴራሉ መንግሥት ለወሰደው ርምጃ ድጋፋቸውን በመግለጫ እየገለጡ ነው፡፡ ከመግለጫው ይልቅ ግን የራስን ጠማማ ነቅሶ በማወጣት ቢገልጡ ይሻል ነበር፡፡ በማለት አስተያየቱን አስፍሯል።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሐመድ