1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ጎንደር ታጋቾችን የማስፈታት ጥረት

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2011

ከጎንደር ወደ ገንደውሐ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ የታገቱት ሰዎች አሁንም እንዳልተለቀቁ ተነገረ። እገታዉ የተፈፀመዉ ከቅማንት ማኅበረሰብ ጥያቄ እና ከተገኘ መልስ እንዲሁም መልሱ ባልጠዋጠላቸዉ ሰዎች ምክንያት በተከሰተ የብቀላ መሰል ርምጃ ጋር ነዉም ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/3Dnzz
Äthiopien - Gonder
ምስል DW/A. Mekonnen

ከጎንደር ወደ ገንደውሐ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ የታገቱት ሰዎች አሁንም እንዳልተለቀቁ ተነገረ። አካባቢዉ ላይ የሚገኙ የፀጥታ ኃይላት ከእገታዉ ጋር ተያያዥነት አላቸዉ የተባሉ ሰዎችን ከረቡዕ ጀምሮ በቁጥጥር ስር እያዋለ ነውም ተብሏል። እንዲያም ሆኖ በአነስተኛ ጫካ ዉስጥ ተሸሽገዉ በነበሩ እና ጥቂት የጦር መሣሪያ በያዙ ሰዎች የታገቱት ሰዎች ቁጥር ግን ከስምንት እንደማይበልጥ እና ታጋቾቹ ነፃ እንደሚሆኑ የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደሕንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰዉ ዛሬ ለ«DW» ተናግረዋል። 

በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ በምዕራብ ጎንደር ዞን መቃ በተባለች አነስተኛ ከተማ በተሽከርካሪ ጉዞ ላይ ሳሉ የታገቱት  ነዋሪዎችን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  ተጠርጣሪዎችም እየተያዙ መሆኑ ተነግሯል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደሕንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰዉ ለ «DW» እንደገለፁት ይህ እገታ የተፈፀመዉ ከቅማንት ማኅበረሰብ ጥያቄ እና ከተገኘ መልስ እንዲሁም መልሱ ባልጠዋጠላቸዉ ሰዎች ምክንያት በተከሰተ የብቀላ መሰል ርምጃ ጋር ነዉ።

ይህ ብቀላ በሚመስለው ርምጃ ሰበብ በታገቱትም ሆነ አገቱ ከሚባሉት ቤተሰቦች ዘንድ አስከፊ ነገር እንደማይደርስ ሰምተናል፤ የተያዙትን ለማስፈታት ጥረት ላይ ነን ሲሉም አቶ ደስአለኝ ጣሰዉ አክለው ተናግረዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የሕዝብ ደሕንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አጋቾቹ « ከ17 ያላነሰ ሰው ጉባይ ጀጀቢት ወደሚባል ቦታ ይዘው ሄደዋል፤ ከታጋቾቹ መካከል ሁለት ልጆች የያዙ አንዲት እናት አሉበት» የተባለዉ ትክክል እንዳልሆነ እና የታገቱት ከስምንት እንደማይበልጡ ነው ለDW የገለፁት። ባለፉት ቀናት አካባቢዉ ተረጋግቶአል ያሉት  አቶ ደስ አለኝ የተከሰተዉ የእገታ ወንጀል ማኅበረሰቡ በማያዉቀዉ ሁኔታ አራት አምስት ሰዎች መሣርያ ይዘዉ የሚፈፅሙት ሕገወጥ ድርጊት ነዉ ፤ ነገር ግን ከመንግሥት ቁጥጥር ዉጭ እንደማይወጣ እምኔቴ ነዉ ሲሉም ተናግረዋል።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ