1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሪፐብሊኩ ጥበቃዎችና የሻሸመኔው ተንቀሳቃሽ ምስል

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 19 2011

በ​​​​​​ሻሸመኔ ከተማ ወጣቶች አዛውንቶችን መሬት ለመሬት እያንከባለሉ ሲረግጡ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል ሰፊ መነጋገሪያ ኾኗል። ከደብዳቢዎቹ መካከል በቅጡ ሱሪውን መታጠቅ ተስኖት የመቀመጫውን መለመላ እያሳየ ለድብደባ የሚቅበዘበዝ የመኖሩን ያኽል፤ ሌላ ወጣት በአጣና ሽምግሌዎቹን ለመምታት ሲቃጣ ስንዘራውን ተከላክሎ የሚያስጥል ወጣትም ነበረበት።

https://p.dw.com/p/3AhG1
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

«የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል» ጀበናዎችን መሰባበራቸው ለበርካታ ትችትና ስላቅ ሰበብ ኾኗል

ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ሰፊ መነጋገሪያ ኾነው የቆዩ ኹለት ርእሰ ጉዳዮችን እንመለከታለን። ጠቅላይ ሚንሥትሩን ጨምሮ የከፍተኛ አስፈጻሚ አካላት ደኅንነትን «በአስተማማኝ መልኩ» ይጠብቃሉ የተባለላቸው ልዩ ኃይላት ወታደራዊ ትርኢት ማሳየታቸው የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። «የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል» የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ወታደሮች ጠቅላይ ሚንሥትሩ ባሉበት አየር ላይ ጀበናዎችን መስበርን ጨምሮ ያሳዩት ትርኢት እንዲሁም ስያሜያቸው አንስቶ በስፋት አነጋጋሪ ኾኗል። በእድሜ የገፉ ሙስሊም አዛውንቶች በወጣቶች ሲደበደቡ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ላይ እጅግ አነጋግሯል። አስተያየቶችን አሰባስበናል።

​​​​​​የሻሸመኔው ተንቀሳቃሽ ምስል

ሰሞኑን ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ወጣቶች ተሰብስበው አዛውንቶች እና በእድሜ የገፉ ሰዎችን ሲደበድቡ የሚታይበት አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙዎችን አስቆጥቷል። በተንቀሳቃሽ ምስሉ የሙስሊም ቆብ ያጠለቁ የእድሜ ባለጸጎች በአፍላ ወጣቶች በቡጢ ሲነጠረቁ፣ መሬት ላይ ሲወረወሩ፣ ከሚወርድባቸው እርግጫ እና ጡጫ ለመከላከል ራሳቸውን በሁለት እጆቻቸው ይዘው ለመከላከል ሲሞክሩ፤ ምስቅልቅል ያለ ድርጊት ይታይበታል።

ኢ ቲ በሚል የእንግሊዝኛ ምኅጻር የተጻፈ የትዊተር መልእክት እንዲህ ይነበባል፦ «ሳር ላይ እራሳቸውን ለማዳን ሲንከባለሉ ጭንቅላታቸውን በእርግጫ ሲመቱ የነበሩት አባት ምስል ህሊና ላለው ሰው መቼም ከአይምሮ አይጠፋም መንግስት እነዚህን አውሬዎች ለፍት እንደሚያቀርብ ተስፋ አደርጋለው።»

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ከሚታዩት ደብዳቢ ወጣቶቹ መካከል በቅጡ ሱሪውን መታጠቅ ተስኖት የመቀመጫውን መለመላ እያሳየ ለድብደባ የሚቅበዘበዝ የመኖሩን ያኽል፤ ሌላ ወጣት በአጣና ሽምግሌዎቹን ለመምታት ሲቃጣ ስንዘራውን ተከላክሎ የሚያስጥል ወጣትም ነበረበት። ይኽ አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል በይነ-መረብ አውዶች ላይ በተለቀቀበት ቅጽበት በርካቶች ጋር ለመድረስ አፍታም አልቆየበትም።

የተንቀሳቃሽ ምስሉ በፍጥነት ብዙ ሰዎች ጋር መድረሱን ተከትሎ የከተማው ከንቲባ አቶ አደም ከማል፦«ጉዳዩ የተፈጠረው የዛሬ ሁለት ወር አካባቢ» መኾኑን ለመገናኛ አውታሮች ገልጠዋል። «ዋናው ምክንያት የነበረው በወቅቱ የተወሰኑ የመጅሊስ ተወካይ ነን የሚሉ እና አይ አትወክሉንም የሚሉ ሰዎች ስብሰባ» መጥራታቸው መኾኑን አያይዘው ለDW ተናግረዋል።

Symbolbild Twitter
ምስል Imago/imagebroker/M. Wolf

አቤል አሥራት በትዊተር ገጹ፦ «ሽማግሌ መደብደብ እንደ ወይን መጥመቅ በጊዜ የሚሻሻል አይደለም እኮ። አይ ከሁለት ወር በፊት ነው ምናምን ይላሉ» ሲል ጽፏል።  ማዳም ደመቂያ በበኩሏ፦ «ምን ይፈይድልኛል ፀቡ በምን እንደተነሳ ወይም መቼ እንደተከሰተ ማወቅ? አዛውንቶችን ጧሪ ሳይሆን ደብዳቢ ወጣቶችን ኢትዮጵያ ማፍራቷ ነው ልብ የሚሰብረው» የሚል መልእክት ትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች።

እዮብ ዘውዴ፦«ድብደባው ዛሬም፣ የዛሬ አመትም፣ የዛሬ ሁለት ወርም ይፈጸም ኢ-ሰብአዊ እና አሳፋሪ ነው። ሊወገዝ ይገባል፣ ድርጊቱን የፈጸሙትም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል» ብሏል። ዳናይት በበኩሏ ትዊተር ገጿ ላይ፦ «በጣም የሚገርመው ደግሞ ተመልከቱ ቆይቷል ብሎ ያስተባባዩ ብዛት» ስትል ጽፋለች። 

አባ ቦራ በትዊተር ጽሑፉ፦ «ሽማግሌዎችን የማያከብር ትውልድ ለሀገር እዳ ነው። የሻሸመኔ ጥቃት አድራሾች በሙሉ ዛሬውኑ ተሰብስበው ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል! ይህንን ጥቃት ተገን አድርጎ በጅምላ መፈረጅና ጥላቻን መስበክም ትክክል አይደለም» ብሏል።  

እሙዬ ፎኒክስ በሚል የትዊተር ገጽ የቀረበ ጽሑፍ ደግሞ እንዲህ ይነበባል። «ሽማግሌ አባትን መገንድ ላይ ቆርጠን እንዳናልፍ ያስተማረችን አገር፤ ሽምግሌ አባትን ተነስትን እንድናስቀምጥ ያስለመደችን አገር፤ ዛሬ ሽማግሌ አባቶች በጠራራ ፀሓይ ተጥለው የአባትነት ክብራቸውን ተነጥቀው በወጣቶች በጭካኔ ተደብድበዋል!!!»

ይኽንኑ የሻሸመኔው አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል በተመለከተ አሌክስ አብርሃም፦ «ክፉዎች ስለሆንን ከፉ ነገር ቶሎ ይስበናል!»  በሚል ርእስ ፌስቡክ ላይ ጽፏል። «ሻሸመኔ ወጣቶች አዛውንቶችን ሲደበደቡና ሲገፈታተሩ የሚያሳይ ቪዲዮ እዚህ ፌስቡክ ላይ ተለቆ ነበር ነገሩ አሳዛኝ ነው! ጥያቄ የለውም! አንድ ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ሸር ያደረገው ህዝብ ብዛት» ሲል መደነቁን ገልጧል። በዛው መጠን ግን ሰዉ ለበጎ ነገር እምብዛም ቁብ አለመስጠቱትን በመግለጥ አዛውንቶችን ለመርዳት ሜቄዶንያ ከዚህ ቀደም ለቆት የነበረውን ቪዲዮ ያጣቅሳል። «ይህንን ቪዲዮ ከብዙ ዓመታት በኋላ ያጋራውን ሰው ቁጥር ብትመለከቱ የሻሸመኔው ብልግና በአንድ ሰዓት ሸር የተደረገውን ግማሽ ያህል እንኳን ሰው እንዳልተቀባበለው ትረዳላችሁ» ብሏል።

«እግዚኦ ማኅረነ ክርስቶስ! ሞት ይሻላል በዘመኔ ይሄን ዝቅጠት ከማይ»  የኤሊያስ ከበደ ጣፋ የፌስቡክ መልእክት ነው።

በDW የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። ላቭድ ሙን በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበው ጽሑፍ ቀጣዩን መልእክት ይዟል። «የከተማይቱ ካንቲባ ጋጠ ወጥ ወጣቶችን ድርጊት ከማውዝ ይልቅ የዛሬ 2 ወር የተከሰተ ነው ምናምን ብለው ለመሸፋፈን መሞከራቸውና ይባስ ብለውም ተደብዳቢ አዛውንቶችን ገ ወጥ ተሰብሳቢ አስመስለው መልስ መስጠታቸው በራሱ አሳፋሪ ነው» ብሏል።

ደርበው ታደሰ፦ «ድርጊቱ የተፈመበት ጊዜ መርዘም ድርጊቱ እንዳልተፈመ አያስቆጥርም። ነገሩ ከባድ ሆኖ እያለ አጥፊዎችን ለህግ ከማቅረብ ይልቅ በእርቅ ሰበብ ወንጀሉ ተቋረጠ መባሉ መንግስት ህግ የማስከበር አቅም የለውም ማለት ነው እንዴት አሳፋሪ በሆነ መንገድ አባቶችን የቀጠቀጡ ወጣቶች አይቀጡሞ?» ሲል ጠይቋል። 

Facebook-App auf Smartphone
ምስል Imago/Zumapress/J. Arriens

«ድርጊቱ ከተፈጸመ ሲፈልግ ለምን 20 አመት አይሆንም ። መቼም ይፈጸም መቼ ድርጊቱን የፈጸሙ ለህግ መቅረብ አለባቸው። ቅጣቱም ከፍተኛ ቅጣት መሆን አለበት። አይደለም አባትን ያክል ይቅርና ታላቅ ወንድም በሚከበርበት ሀገር ይሄ አስነዋሪ ተግባር ነው። የምን ማስተባበል» የኄኖክ ሥዩም መልእክት ነው። «የዛሬ ሁለት ወርም ሆነ የዛሬ ሺ አመት ልዩነት የለውም ነውር ሁሌም ነውር ነው» በዳልቄሮ ዳልቄሮ የተሰጠ አስተያየት። ወንዴ ላቀው ገብሬ፦ «የትም ሀገር አዛውንቶች በጎረምሶች ተደበደቡ ሲባል ያሳዝናል፣ያስከፋል» ሲል፤ አብዱ ሸ ደግሞ፦ «ለአባቶቻችን ክብር መሰጠት ሲገባን አባቶቻችን ላይ እጅ ማንሳት አለመማራችንን ያሳያል» የሚል አስተያየት አስፍሯል።

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል

ሌላው በሳምንቱ የብዙዎችን ቀልብ ገዝቶ ያነጋገረው ጉዳይ «የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል» የተባሉ ልዩ ሥልጠና የወሰዱ ወታደሮች ለጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ያሳዩት ትርዒት ነበር። 

ይኽንኑ  ጉዳይ  በተመለከተ ተስፋይ ኃይለማርያም ፌስቡክ ላይ በሰጠው አስተያየት፦« የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል የሚባል ነገር ተቋቁሟል። ይህ ኃይል ዓላማው የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ቤተሰቦቻቸውን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመ የደህንነት ኃይል ነው። ዓላማው ጥሩ ነው። ነገር ግን እስከዛሬ ይሠራበት የነበረው የልዩ ኃይል ችግር ምን ሆነና ነው ይህ የተቋቋመው። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ቁጥር 10 ሺህ ደረሰ እንዴ?» ሲል ጠይቋል።

«የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል» ትርኢት ባቀረቡበት ወቅት ጀበናዎችን መሰባበራቸው ለበርካታ ትችት እና ስላቅ ሰበብ ኾኗል። በዛ ያለው የማኅበራዊ መገናኛ አስተያየት ሰጪ ጀበና የኢትዮጵያ የምጣኔ ሐብት የኾነው ቡና ማፍያ ኾኖ ሳለ በርካታ ድሃ እናቶች የእለት ጉርሳቸውን የሚደጉሙበትን ቁስ መስበር ተገቢ አይደለም የሚል ነው።

ኤሊያስ ትዊተር ላይ፦«የአገሬን ቡና ከሽና የምትጠምቅልኝን ጀበናን እንዲህ ማሰቃየት ለእኔ ምቾት አልሰጠኝም። ሌላ ነገር ቢጠቀሙ መልካም ነበር። የሪፐብሊኩ ጠባቂዎች ከጀበና ላይ እጃችሁን አንሱ ብያለሁ!» ሲል ጽፏል። «የጀበናዉን ጥንካሬ ያዩ ደንበኞች ከሀገርም ከዉጭም ብዛት ያለቸዉ ትዕዛዞች እየሰጡ ነዉ።» ይኼ ደግሞ የአቤሴሎም ሳምሶን ዮሴፍ አስተያየት ነው።

ጸጉሯን በጀበና ቅርጽ የተቆነደለች ወጣት ፎቶግራፍን ያያዘው ጆማኔክስ፦ «ይህቺ ወ/ሮ/ወሪት/ጉብል/ሴት የሪፐብሊኩ ጋርድ በማይደርስበት ትቀመጥ» ሲል ጽፏል። ትርዒቱ ለጠቅላይ ሚንሥትሩ በቀረበበት ወቅት አንዲት «የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል» ባልደረባ አጎንብሳ በእግሮቿ መሀል ወደ ኋላ በማነጣጠር የተንጠለጠለ ጀበና በጥይት ስትበረቅስ ይታያል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ