1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት እንዲከበር የባህል አብዮት?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2011

ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ኢትዮጵያ አፍሪቃ አገሮች በቀደምትነት የፈረመች ሃገር ናት። ይሁንና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ሊያጥን ይቅርና በኢትዮጵያዉያን ዘንድያለዉ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ፤ ሰዉ አክባሪነት፤ የመሳሰለዉ ባህል እየተሸረሸረ ነዉ። በርግጥ የሰዉ ልጅ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ባህሉ ማድረግ አይችል ይሆን? ካልሆነስ ለምን?

https://p.dw.com/p/3A4O3
Deutschland | Skulptur Der Rufer
ምስል picture-alliance/M. Wolff

የሰዉ ልጅ ሁሉ ክቡር ነዉ

«የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 የሰዎችን ሃሳብን ያለገደብ የመናገር ነፃነት ያጎናጽፋል። ይህ ማለት የራስን ሃሳብ በነጻነት የመናገር እና የሌሎችንም ሃሳብ የማዳመጥ ሕግን ያክትታል። ይህን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ አንቀጽ 19 የመንግሥትን ቅድመ ምርመራ ያግዳል። በያዝነዉ ወር ታህሳስ አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰዉን ልጆች መብት የሚያስከብረዉ ድንጋጌ 70 ኛ ዓመቱን ደፍኖአል።  «DW» በየእለቱ በሚያሰራጨዉ የተለያዩ 30 የዓለም ሃገራት ቋንቋዎች  እና በ«DW» አካዳሚ በኩል በዓለም ዙርያ የሚገኙ ሃገሮች ይህን ሕግ ጠንቅቀዉ እንዲያቁና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚችሉ  በየቀኑ ይሰራል።  ሚዛን የጠበቁ ዘገባዎችን እያሰራጨን፤ ፕሮፖጋንዳ ከተጨባጭ ዜና እንዴት መለየት እንደሚቻል እናሳያለን። ማኅበረሰብ በዴሞክራሲ ስር ነዉ ስንል ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃን ሲያገኝ እና በእድገት እና ልማት ተካፋይ መሆን ሲችል ብቻ ነዉ። በዚህም ምክንያት የዓለም የሚገኝ ማኅበረሰብ  የተመ አንቀጽ 19 ተግባራዊ ማድረግ እዲችል ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።»         

የ« DW» ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ 70ኛ ዓመትን በተመለከተ በ«DW» አንቀጽ 19 በሚል ማኅበራዊ መገናኛ ልዩ ዝግጅቱ ላይ ያስተላለፉት መልክት ነበር።  የሰዉ ልጅ ከተፈጠረ ከመጀመርያዋ ደቂቃ ጀምሮ ነጻና እኩል ክብር የሚሰጠዉ ነጻ ነዉ፤ የሚለዉ ቀላል አርፍተ ነገር ቢመስልም ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ ድንጋጌ ነዉ። በጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር ታህሳስ 10 ፤ 1948 ዓ,ም ፓሪስ ላይ የፀደቀዉ የተመድ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ፤ በዓለም ዙርያ በሚገኙ የዓለም ሃገራት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮና ታስቦ ዉሎአል።

Symbolbild Pressefreiheit
ምስል picture alliance/dpa/N. Khawer

የዛሬ 70 ዓመት የፀደቀዉና 217 የዓለም ሃገራት የተስማሙበት የሰዉ ልጆች እኩል መሆንን የሚደነግገዉ ሕግ ለአብዛኞች ነጻነትን እና እኩልነትን ያመጣ ቢሆንም አሁንም ግን በዓለም ዙርያ የመብት ጥሰት የመናገር ነፃነት እየተደፈጠጠ መሆኑ ገሃድ ነዉ። የሰዉ ልጅ የሰብዓዊ መብትን ከፅሑፍ ባለፈ መሪት ላይ ማዉረዱን ትናንትም ዛሬም እንተሳነዉ ይታያል ያሉት ጀርመን በርሊን ከተማ ሲኖሩ ከ 25 ዓመት በላይ የሆናቸዉ አቶ መስፍን አማረ ጉዳዩ አንገብጋቢ መሆኑን ተናግረዋል።       

«ይህ ነገር ከ 70 ዓመታት በፊት የተደረገ ነዉ። እንዳነበብኩት ከሆነ ለመጀመርያ ጊዜ በዉሉ ላይ የተፈራረሙት 48 ሃገራት ነበሩ። የሰዉ ልጅ በሰዉነቱ በስብዕናዉ መከበር እንዳለበት እና ነጻነቱን ማግኘት እንዳለበት የዝያን ጊዜ የተስማሙት ሃገሮች ያኔንም ያምኑ ነበር። ይሄ ቲዮሪዉ ነዉ፤ በስራ ላይ ዉሎ ሲታይ ግን በሕዝቡ ዘንድ ያለዉ ነገር ያኔም የተለየ ነበር ዛሬም የተለየ ነገር ነዉ ያለዉ። ዩናይትድ ስቴትስን ብንወስድ በ 1948 በጎርጎረሳዉያኑ ዓመት ይህን ዉል ፈርመዉ ፤ ነገር ግን የነጭ እና የጥቁር ሊዩነት በ 1960 ዎቹ ዓመተምህረት ነዉ ከዉሉ በኋላ መፍትሄ ያገኘዉ። ጥቁሮች እና ነጮች አንድ ትምህርት ቤት መማር አይችሉም ነበር፤ አንድ አዉቶቡስ ላይ ተሳፍረዉ መሄድ አይችሉም ነበር። ለዚህ ምክንያታቸዉ ደግሞ የነበረዉ ነጭ ሰዉ የተለየ ነዉ ብለዉ በማሰባቸዉ ነዉ። ወደ አዉሮጳ bveንመጣ ብዙዎቹ ሃገራት ይህንንም የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን ከፈረሙትም ሃገሮች ዲሞክራስያዊ የሚባሉትም ሃገሮች እራሳቸዉ ብዙ የአፍሪቃ ቅኝ ግዛት የነበራቸዉ እና ሲጨቁኑ የነበሩ ናቸዉ። እንደ ስዊዘርላን ያሉ ትልልቅ የዴሞክራሲ ሃገሮች ሴቶች እንዲመርጡና እንዲመረጡ የፈቀዱት በ ጎርጎረሳዉያኑ 1971 ዓመት ነዉ።»   

ኢትዮጵያ በጎርጎረሳዊዉ 1948 የፀደቀውንና በዚህ ሳምንት መጀመርያ 70ኛ ዓመቱን ያከበረዉን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ከአፍሪካ አገሮች በቀደምትነት የፈረመችና ያፀደቀች አገር መሆንዋ ይታወቃል። በኢትዮጵያ እንኳን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ሊጤን ይቅርና በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የሚታየዉ የኢትዮጵያዊ  ጨዋነት፤ እንግዳ ተቃባይነት፤ ሰዉ አክባሪነት ፤ የመሳሰሉት ባህላዊ ክንዉኖች እየተሸረሸሩ መሆናቸዉን የሚናገሩ ዜጎች ጥቂት አይደሉም። በርግጥ የሰዉ ልጅ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ባህሉ ማድረግ አይችል ይሆን? ካልሆነስ ለምን? አቶ መስፍን አማረ 

DW-Intendant Peter Limbourg begrüßt die Mitglieder des Wirtschaftsrats der CDU e.V.
ምስል DW/P. Böll

«ባህል ከሆነ ሊወራረስ የሚችል ነገር ነዉ የሚሆነዉ በማንኛዉም ሃይማኖት ቤቶች የሚስተምሩት ነገር አለ። ሰዉን ከልጅነቱ ጀምሮ ስብዕናዉን መቀበልን ካስተማሩ ፖለቲከኞች መለያየትን ትተዉ ወደ አንድነት የሚያመጡ ከሆነ ሰዉ በማንነቱ የሚከበር ከሆነ ወደ ባህል ማምጣት ይቻላል። ዋናዉ ነገር ጨቋኞች እስካሉ ድረስ ሰዉ የራሱን ፍላጎት፤ መብቱን ለማስጠበቅ መታገሉ አይቀርም። የራሱን ነፃነት ሲያስጠብቅ ደግሞ አደጋ ሊኖረዉ ይችላል። ምክንያቱም የሌሎችን ሊነካ ይችላል ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ባህል ለማድረግ ብዙ ሥራ ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ከትምህርት ቤት ከሃይማኖት ተቋማት ሁሉ አንድ ላይ ከሰሩና ይህ እየዳበረ ከሄደ ሕዝብ ባህሉ ሊያደርገዉ ይችላል። አፍሪቃ ዉስጥ የምንወያየባቸዉና የምንወዛገብባቸዉ አንዳንድ ነገሮች በአዉሮጳ እንደ አርስት እንደመነጋገርያ ነጥብ አይቀርብም ። ምክንያቱም ከብዙ ዘመናት ዲሞክራስያዊ ልምድ የተነሳ ተለማምደዉት ባህላቸዉ አድርገዉታል። ስለዚህ ይህ የነፃነት ጉዳይ ባህል ሊሆን ይችላል። ባህል ማድረግ ይፈጃል ነገርግን ጊዜ ይፈጃል ብዜ ሰዎች አብረዉ መስራት አለባቸዉ። »      

የሰዉ ልጅ ነጻነቱ ስብዕናዉ መከበር እንዳለበት በሕግ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሃይማኖቶች እና አስተሞሮዎችም በመጀመርያ ደረጃ ተጽፎ ያለ ነገር ነዉ። በርግጥ የሰዉ ልጅ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ባህሉ ማድረግ አይችል ይሆን? ለምን? በጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ ለሆኑት ለፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና ለሕግ ባለሞያው ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ያቀረብነዉ ጥያቄ ነዉ። ዶክተር ለማ እንደሚሉት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ባህል ማድረግ ከፈለግን ከፍተኛ የባህል አብዮት ማካሄድ ይኖርብናል፤ ይላሉ።   

«ሰብዓዊ መብትን ባህል ለማድረግ የባህል አብዮት ያስፈልጋል ። የሰዉ ልጅ ስብዕናን እንደ ባህል አድርገን ፤የሰብዓዊ መብቶችን እንደ ባህል አድርገን ለምን አናከብረዉም ለምን አንጠቀምበትም ለሚለዉ ይሄ የሰዉ ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሃሳብ ደረጃ ያለ ነዉ ነገር ግን የሰዉ ልጅ አስቸጋሪ ስለሆነ ፤ የሰዉ ልጅ በፈቃዱ የሌላዉን ሰዉ መብት ስለማያከብር ፤ በዚች ምድር ላይ የአንዱ ሰዉ መብት መረገጥ ለሌላዉ ጥቅም እስካስገኘ ድረስ ይህን ነገር ለማስቀረት በሰብዓዊ መብት ሕግ መኖሩ አግባብ ነዉ። ነገር ግን የሰዉ ልጅ ባህሉ ማድረግ ያለበት ለምሳሌ ልጅ አይመታም ፤ ወይም መንገድ ላይ እየሄዱ አይተፋም፤ ወይም አፍንጫዉ የተጠረገበት ወረቀት አይጣልም። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በሕግ አያስቀጣም ግን በኅብረተሰብ ደረጃ ስለሚስንቅ በግድ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማክበር አስፈላጊ ይሆናል ባህልም ማድረግ ያሻል።»      

በጀርመን በተለያዩ መስርያ ቤቶችና ተቋት የተመድ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ 70ኛ ዓመት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታስቦና ተከብሮ ዉሎአል። የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ከፈረንሳዩ አቻቸዉ ጋር በመሆን ለሰብዓዊ መብት መከበር ለታገሉና ለተመረጡ ዜጎች የጀርመን-ፈረንሳይ የሰብዓዊ መብት ሽልማትን አበርክተዋል። ይህንኑ ተከትሎ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ መልዕክት አስተላልፈዉ ነበር።

Artikelbild Weltzeit 1-2019: Meinung braucht Freiheit/Die Handlanger der Despoten (Fotolia/SripFOTO [M])
ምስል Fotolia/SripFOTO [M]

«የሰዉን ልጆች መብት እንዲጠበቅ የተደነገግበት ሕግ ዛሬ 70ኛ ዓመት ሞላዉ። ይህ ሕግ የሰዉ ልጅ መብት እንዲከበር የወጣ የመጀመርያ ድንጋጌ ነዉ። ድንጋጌዉ ከወጣ በኋላ በዓለም ዙርያ የሚገኙ ሰዎች፤ በኑሮ፤ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ እንዲሁም  በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ድጋፍ መስጠት መቻላቸዉን በሕግ መረጋገጡን አዉቀዋል። ይህን ነፃነት የሚደነግገዉን ሕግ ዛሬም ድረስ ለማስፈፀም በተለያዩ አጋጣሚዎች እየታገልን ነዉ። አሁንም ቢሆን ይህ ሕግ ለእያንዳንዱ የሰዉ ልጅ ፤ ማለትም ሴት ይሁን ወንድ የተለያየ የቆዳ ቀለም እንዲሁም የተለያየ ሃይማኖት ይኑረዉ አይኑረዉ ሕጉ እኩል መስራቱ ተቀባይነት ያላገኘበት ቦታ ይታያል።  እንድያም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰዎች መብት እንዲከበር የተደነገገ ሕግ አለን። እንደመታደል ሆኖ  በዓለም ዙርያ ይህ ሕግ እንዳይጣስ የሚታገሉ ሰዎች አሉ። እነዚህን ሰዎች መደገፍ እንፈልጋለን። »

ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ከአፍሪካ አገሮች በቀደምትነት የፈረመችና ያፀደቀች አገር ኢትዮጵያ ሕጉን ከማፅደቅና ዓመታትን ከማስቆጠር ባለፈ ወደ ትግበራ ተቀይሮ የድንጋጌውን ዓላማ ከመፈጸም አኳያ ግንዛቤ ሊካሄድ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ መስፍን አማረ፤ በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወቅት በሂትለር የተገደለችና በተለይ በሃሳብ ነፃነት ረገድ በጀርመን ስምዋ ጎልቶ የሚነሳዉ ሮዛ ሉግዘምበርግ የተባለች ሴት "Freiheit, ist Immer die Freiheit des Andersdenkenden" «ነፃነት ማለት ከኔ የተለየ ሃሳብ ላላቸዉ ሰዎች የምሰጠዉ ነፃነት ነዉ» ስትል መናገርዋን በምሳሌነት የሚጠቅሱት አቶ መስፍን አማረ፤ ነጻነት ሲታስብ የሌላዉን ነፃነት ከማክበር መጀመር እንዳለበት ተናግረዋል።

አቶ መስፍን እዚህ ላይ የጀርመንን ጉዳይ ካነሱልኝ ዘንዳ የጀርመን ሕገ መንግሥት የመጀመርያዉ አንቀጽ ስለ ሰዉ ልጅ መብት ነዉ አይደል?

ሰብዓዊ መብትን እንደ ግብረገብ ማወቅ እና መማር ቢቻልም ለራስ ብቻ በሚደረግ ትግል እንዲሁም ጨቋኝ ሥርዓትም ሆነ መሪ አልያም ራስ ወዳድ በመኖሩ ሰብዓዊ መብትን ባህላችን ለማድረግ ከፍተኛ የባህል አብዮት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ደግመዉ የተናገሩት ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ፤

Bangladesch Dhaka - DW Diskussion zu Migration "Challenges and Approaches in the East and the West"
ምስል DW/M. M. Rahman

ጀርመናዊትዋ የ «DW» ዋና አዘጋጅ ኢነስ ፖል በመጨረሻ አድማጮች በመናገር ነፃነት በሰብዓዊ መብት ጉዳይ አድማጮች ያላቸዉን ሃሳብ እንዲኣካፍሉን መልክትዋን ታስተላልፋለች።

« የተመድ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ 70ኛ ዓመትን በማክበር ላይ እንገኛለን። በዚህ ድንጋጌ ለኛ ለ«DW» ዎች  ሃሳብን የመናገር ነፃነት ዋንኛ ነጥብ  ነዉ። ይህ ድንጋጌ  በዓለም ዙርያ ሃሳብን በነፃነት የመናገር መብትን የሚደነግገዉ ሕግ አንቀጽ 19ኝ ነዉ። ስለዚህም ሃሳብን በነፃነት የመናገር መብት አስፈላጊነትን በተመለከተ በ«DW» የማኅበራዊ መገናኛ ፕሮጄ ላይ ሃሳባችሁን ስሜታችሁን እንድታካፍሉን እንፈልጋለን»  

የሰብዓዊ መብትን የመናገር ነጻነትን እንደ ባህል ተግባራዊ እንዳድርግ በሚለዉ በእለቱ እንግዶች አስተያየት በመደምደም ሙሉዉን ስርጭት እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ