1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አሜሪካ ጠየቀች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2011

አሜሪካ 100 ተቃዋሚዎች ገደማ የተገደሉበት እና የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የወሰዱት እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ጠየቀች። ወደ ኻርቱም አቅንተው የነበሩት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ምኒስትሩ ቲቦር ናዥ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3KWaE
Äthiopien Stellv. US-Außenminister für afrikanische Angelegenheiten Tibor P. Nagy
ምስል DW/S. Muchie

አሜሪካ የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የወሰዱት እርምጃ እንዲጣራ ጠየቀች

አሜሪካ በሱዳን እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2 ቀን 2019 ዓ.ም. የተከሰተው ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎች ምንጩ ምን እንደሆነ ለጊዜያዊ ወታደራዊ ምክር ቤቱ በትክክል የተከሰተው ምን እንደሆነ ፣ ለምን እንደተከሰተ ፣ ትዕዛዙን የሰጠው ምን እንደሆነና ምን ያህል የጉዳቱ ሰለባዎች እንዳሉ ለመለየት ነጻ እና ተአማኒነት ያለው ምርመራ እንዲደረግ ማሳወቋን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጊይ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በሱዳን የተወሰኑ የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዳነጋገሩ የገለጹት ባለስልጣኑ ሰዎች ከመገደላቸው በላይ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ብዙዎች ተደብድበዋል ለሌሎች አስደንጋጭ ጥቃቶችም ተጋልጠዋል ብለዋል።በመሆኑም የሚደረገው ገለልተኛ ምርመራ በድርጊቱ የተሳተፉት ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። ከሰኔ 2 2019 በፊት ሱዳናውያኑ በመጨረሻም ከ35 አመታት በኋላ ነገሮች በጎ መስመር ያዙ የሚል ተስፋአድሮባቸው እንደነበር አውስተው ሆኖም ይህ ተስፋ በነጋታው ተንኖ እንደጠፋ እና ወደ እልቂት መሻገሩን አመልክተዋል።

ይህ ይሆናል የሚል ምንም ምክንያትም ሆነ መነሻ እንዳልነበረም ተናግረዋል። ከጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፤ አለም በችግር እና ፈተና ውስጥ መሆኑ እየታወቀ ሱዳን ላይ ለምን ይህን ያህል ትኩረት ተደረገ የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ጠቅሰው ይህ ሁኔታ ነገሩን በተለየ መልኩ እንዲያስቡ እንዳደረጋቸውም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቲቦር ናጊይ አክለውም በሌሎች ሃገሮች እንደሚስተዋለው ወታደሮች በንጹሃን ላይ ጥፋት አድርሰው ነጻ መሆናቸውና ሟቾችም ደመ ከልብ ሆነው መቅረታቸው ሀቅ በመሆኑ ይህ ነገር በሱዳን በተከሰተው ግድያ እንደማይታይ እና አጥፊዎች ከምርመራ ውጤት በኋላ ተጠያቂ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን እለለብን ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ