1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስመኘው ሞት፤ ሐሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛዎች

ዓርብ፣ ሐምሌ 20 2010

በኢትዮጵያ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በሳምንቱ ውስጥ በነበሩ የተለያዩ ክስተቶች ጎልቶ ተስተውሏል። ሀገሪቱ ባለችበት ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የእንዲህ አይነት መረጃዎች መብዛት እና በብዛት ተቀባይነት ማግኘት አሳሳቢ እና አደገኛ እንደሆነ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችም ሆነ ባለሙያዎች ሲገልጹ ሰንብተዋል።

https://p.dw.com/p/32DSL
Äthiopien | Semegnew Bekele | Manager von Mega-Staudamm erschossen
ምስል picture-alliance/AA/Minasse Wondimu Hailu

የስመኘው ሞት፤ ሐሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛዎች

ኢትዮጵያ ሳምንቱን ያሳለፈችው ሀዘንን የቀሰቀሱ ክስተቶች ተደራርበውባት ነው። በአስራዎች የሚቆጠሩ የሞቱበት የባሌ ግጭት፣ የነፍሰ ጡር ህይወት የተቀጠፈበት የደምቢዶሎ ግድያ፣ በተለያዩ እስር ቤቶች የነበረው አመጽ፣ ቃጠሎ እና ሞት፣ የደሴ መስጊድ ሁከት፣ በጅጅጋ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተከታትለዋል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችም ለየክስተቶቹ የተሰማቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ከእነዚህ ሁሉ በላቀ ብዙዎችን ድንጋጤ ውስጥ የከተተው እና ከዳር ዳር ያነጋገረው ግን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ነው።

አቶ ስመኘው ትላንት ሐሙስ ጠዋት በመሀል አዲስ አበባ ሊያውም በመስቀል አደባባይ በመኪናቸው ውስጥ እንዳሉ ሞተው ተገኙ የሚለው ዜና በማህበራዊ ድረገጾች በፍጥነት ለመሰራጨት አፍታም አልፈጀበት። በመስቀል አደባባይ የተገኙ ሰዎች በየገጾቻቸው ላይ የሚለጥፏቸው ፎቶዎችንም ብዙዎች ተቀባብለዋቸዋል። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ሀገር ኩራት የሚወሰደውን የህዳሴው ግድብን ከጅምሩ አንስቶ በስራ አስኪያጅነት የመሩት የአቶ ስመኘው ድንገተኛ ህልፈት በርካቶችን ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ከትቷቸዋል። 

Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል DW/T.Waldyes

የሞታቸው ወሬ እንደተሰማ ሀዘናቸውን በፌስ ቡክ ካካፈሉ ውስጥ አንዷ የሆኑት ገነት ጎይቶም በርሄ “ምን ብላችሁ መፃፍ፣ ስሜታችሁን መግለፅ፣ ማዘን እንደምትችሉ ቸግሯችሁ ያውቃል? ዝም ማለትም መፃፍም ቸገረኝ” ሲሉ ስሜታቸውን በቃላት ለማስረዳት መቸገራቸውን አጋርተዋል።  “ጌታ መድሃኒአለም.. .ምንድነው እየሆነ ያለው?” ስትል ድንጋጤዋን በፌስ ቡክ የገለጸችው እመቤት ላቀው “ኢንጂነር ስመኘው ለሀገር ስላደረጉት ሁሉ እናመሰግናለን። ከሴራ ትንተና እና ጣት መጠቋቆም ያልወጣው ፖለቲካችን አስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀለት ገና ብዙ ያስከፍለናል” ስትል ስጋቷን ገልጻለች።

ሃይላአብ ገብረመድህን በበኩሉ “በልቡ አገሩን ብቻ አንግቦ፣ ፖለቲካን ወግድ ብሎ፣ ስናስበው እንኳን የሚከብደንን አባይ ለህዝቧ ጥቅም ለማዋል በታላቅ አርበኝነት ብዙ መስእዋትነት የከፈለ የሃገር ልጅ” ሲል አቶ ስመኘውን ገልጿቸዋል። “ሁሉም ነገር ለፕሮፓጋንዳ በሚውልበት አገር ሰዉ የሱን ንጹህ ፍላጎት እና ቆራጥነት አይቶ የተሸነፈለት ጀግና። ለሃገራችን ልንሆን የምንገባው አይነት ሰው ነበርክ” ብሏል። 

ቤተልሄም ኒቆዲሞስ የእውቁን መሀንዲስ ሞት “ያማል” ብላለች። “ትህትናዎን እና በበረሀ ውስጥ ያሳዩንን ደግነት ሳስበው አመመኝ። ኢንጅነር ይሄ የምሁር ደም ያልጠገበ አዙሪት እርስዎን ይወስዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ያቃጥላል” ስትል በፌስ ቡክ ገጿ ጽፋለች። ሰይድ ከድር “ድንጋጤዬ ልክ አጣ። ከፊታችን ያለው ጊዜ አስፈሪ እየሆነብን ነው። ማነው ከዚህ ጊዜ መረር ብሎ የሚያስጥለን?” ሲል ጠይቋል። “እየነጋላት ይሁን እየመሸባት ያላታወቀላት፤ ሁሌም የሚጠቅማትን የምትቀብር ምስኪን ሀገር” ሲሉ ኢትዮጵያን የገለጿት ሃበሽ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም “የአፍሪካ ትልቁን ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ያለ ዉድ ሰዉ እንዴት አንድ ጠባቂ አጥቶ በአደባባይ ይገደላል?” ሲሉ ጥያቄቸውን አጋርተዋል። 

ሲራክ ተመስገን በብዙዎች ዘንድ በተለያየ መልክ የተንጸባረቀን ሀሳብ በፌስ ቡክ ገጹ በጥያቄ መልክ አቅርቧል። “አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ስራ አስኪያጅ እና ሰራተኞች በታጣቂዎች ተገደሉ። ተድበስብሶ አለፈ። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ። ተድበስብሶ አለፈ። የአባይ ግድብ ስራ አስኪያጅ ሞቶ ተገኘ። ቀጣዩ ማነው?” ብሏል። በፍቃዱ አባይ ደግሞ “ከኢንጂነር ስመኘው ሞት ባሻገር የመንግስት ቸልታ፣የበዛ ሆደ ሰፊነት፣ ያልተገባ እንክብካቤ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገም ያሳስበኛል። ስርአት አልበኝነት በአገሬ እንዲሰፍን፣ በፍርሀት እንድንሸበብ መንገዱ እየተጠረገ ነው” ሲል ጽፏል። ኢንጂነር ስመኘው “ተገድለዋል” ብለው ያመኑ በርካታ የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ድርጊቱን በፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መረር ባለ ቋንቋ ጠይቀዋል። "የዘገየ ፍትህ ከተነፈገ ይቆጠራል፤ ፍትህ የተበዳይን የተሰበረ ልብ ያክማል" የሚሉ አባባሎችን ለሀሳባቸው ማጠናከሪያነት የተጠቀሙት ቴስ ማሩታ በፌስ ቡክ ገጻቸው ይህን ብለዋል።

Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል DW/T.Waldyes

“ይቅርታ እና መደመር የሚሰራው ከለውጥ በፊት ለተፈጸሙ ጥፋቶች እንጂ ለውጥን በእንጭጩ ለማጨናገፍ እየተፈጸሙ ላሉ ግፍ ና በደሎች አይደለም። ይልቁንም ይህን ጅምር የለውጥ ተስፋ ለመቅጨት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሃገር ላይ ያነጣጠሩ ከባድ ወንጀሎች ናቸውና ከባድ ቅጣት ና አፋጣኝ የተግባር እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብም የሚደረገው ምርመራ ጥንቃቄ ቢፈልግም ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ሲሉ ቴስ ማሩታ አጽንኦት ሰጥተዋል ። 

ሰሚራ መሐመድም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሀሳብ በፌስ ቡክ ገጿ አንስታለች። “ያልታደልን ህዝቦች። እሱ አይደለም አሁንስ የሞተው። ተስፋችን እና ህልማችን ነው አብሮ የሞተው። የህዝብን ገንዘብ ዘርፈው ውሎና አዳራቸው መጠጥ እና ቁማር ቤት የሆኑ ስንት መሃይማን እያሉ ለእኛ ስትል በረሃ ላይ ለተንከራተትከው ሞት አይገባህም! በፍፁም። በጭራሽ! ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊገድሉ በሞከሩበት ቦታ ላይ ኢንጂነራችንን ገደሉብን። ህዝብ ነው የሞተው። አገር ነች በአደባባይ የተገደለችው! ይቅርታ አንፈልግም። ከዚህ በኋላ ፍትህ ነው የምንፈልገው ፍትህ!” ሲሉ ጽፈዋል። 

አቤኔዘር ቢ. ይስሐቅ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ከሰሞኑ ሁነቶች ጋር ተያይዞ ስጋት ገብቷቸዋል። “በዚህ አካሄዳችን የምፈራውና የምሰጋው ነገር ‘ዶ/ር አብይና አስተዳደሩ ወንጀለኞችን ሥርዓት ማሲያዝና ፍትህን ማስፈን አልቻሉም ’ብለው የሚያስቡና የሚያምኑ ወገኖች፣ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች በራሳቸው መንገድ ፍትህን ለማግኘት እርምጃ መውሰድ ጀምረው ሀገሪቱ ወደ ከፋ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ነው” ብለዋል። ይህ ስጋታቸው በተወሰነ መልኩ በጎንደር ተንጸባርቋል። የኢንጀነር ስመኘው ሞት ያስቆጣቸው የጎንደር ወጣቶች በከተማይቱ ቆሞ ያገኙትን የሰላም ባስ አውቶብስን አቃጥለዋል። የተቃጠለው አውቶብስ እና የወጣቶቹ የተቃውሞ ሰልፍ ፎቶዎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ሲሽከረከሩ ታይተዋል።

Symbolbild Facebook Social Media Fake News
ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner

ስሜታዊነት በሚያልበት በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ግብታዊ እርምጃዎችን ከሚያበረታቱ መረጃዎች እና ከሴራ ትንተናዎች መታቀብ እንዳለባቸው የሚመክሩ አሉ። ከእነርሱ መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ “ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በዚህ ሰአት ህዝብንና ሀገርን የማረጋጋት ስራ መስራት አለበት” ሲል ተከታዮን ምክር በፌስ ቡክ ገጹ ለግሷል። 

“የማህበራዊ ሚዲያው የኢንጅነሩ ሞት ያደናገጠውን ህዝብ ማረጋጋት አለበት። ይህም ብቻ አይደለም:- ለወራት የታቀደውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጲያውያን ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ተከትሎ የእሳቸውን ሀገር ውስጥ አለመኖር ሰበብ አድርገው ፍርሀት የሚነዙትን ማስቆም ግድ ነው። አሁን የፖለቲካ ጉዳይ የለም! አሁን የአመለካከት ልዩነት ምክንያት አይሆንም። ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ዘበኞቿ ነን። ሁላችንም ከሆዳቸው በላይ ማሰብ የማይችሉ ግለሰቦችን ባለን አቅም ሁሉ እየተቆጣጠርን ሰላምን መረጋጋትን ለማስፈን መጣር አለብን። እውቀት ችሎታ ታዋቂነት ሁሉ ከሀገር አይበልጥምና የሶሻል ሚዲያ ቆይታችንን በዚህ መልኩ ብናደርገው የተሻለ መስሎ ይሰማኛል” ብሏል።

“ከእርጋታ ወደቀውስ የሚደረጉ ጥሪዎችን እንጠንቀቅ” በሚል ርዕስ ይስሐቅ እሸቱም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጽሁፍ ባለፈው ማክሰኞ በፌስ ቡክ ገጹ አስነብቦ ነበር። ለይስሐቅ አስተያየት መነሻ የሆኑት በባሌ ጎባ እና ደሴ ባለፉት ቀናት የተከሰቱ ግጭቶች ናቸው። ሃይማኖታዊ ቅርጽ በተሰጠው የባሌ ጎባው ግጭት ሰዎች መሞታቸውን፣ በደሴ ሸዋበር መስጂድ በተፈጸመ ጥቃት ደግሞ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሷል። ሰሞኑን በየቦታው የሚታዩት ቀውስ የመፍጠር ጥረቶች ሰዎች ወደ ከፋ ነገር የሚሻገሩት “ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲሳተፉበት ነው” ይላል ይስሐቅ። ለዚህ ሁነኛ መፍትሄው “እሳት ሲመጣ ጭድ ሆኖ አለመገኘት” የሚለው ጸሀፊው “ስሜታዊነት ከተጫናቸው የችኮላ ቅስቀሳዎች እንጠንቀቅ” ሲል አሳስቧል። 

“ብዙ የአብይ አህመድ ተቃዋሚዎች አገሪቷ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደገባች፣ የፌዴራል መንግስት መቆጣጠር እንደተሳነው፣ ለማስተዳደር የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ወሬ እና ጭንቀት በመንዛት ላይ ይገኛሉ” የሚለው ሙሉአለም ጌታቸው “እኛም የዚህ ወጥመድ ሰለባ እየሆንን ነው” ሲል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስለሚተላለፉ መረጃዎች ረዘም ያለ አስተያየቱን አካፍሏል።“ሰዎች በፌስቡክ የሚያሰራጩት ዜናዎች እና ይሄን ተከትሎ ሚዲያዎች እያስተላለፉ ያሉት ዘገባዎች አገሪቷ በሙሉ ስጋት እና ሽብር ላይ የወደቀች እያስመሰላት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው አገሪቷ የዛሬ 6 ወር ወይም ዓመት በፊት ከነበረችበት ሁከት እና መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ፣ አሁን በአንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያለች ቢሆንም፣ ፌስቡክ እና ሚዲያዎችን ለሚከታተል ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ 

Facebook Logo auf Bildschirm mit Lupe
ምስል Reuters/D. Ruvic

ከዚህ በፊት ብጥብጥ እና ረብሻ የሚዘገበው ውጭ ሀገር ባሉ ሚዲያዎች አልያም በፌስቡክ ነበር፡፡ አሁን የመንግስት እና አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሚዲያዎች የዚህ ዓይነት ዘገባ አካል ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ማህበረሰብ ለእነዚህ ዓይነት ዜናዎች ተጋላጭ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን እንዴት ማብላላት እንዳለበት አቅሙን ገና አላዳበረም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እና የመጪው ጊዜ ብሩህነት ላይ አተኩረው የሚሰሩ የሚዲያ አውታሮች በቅርብ ይኖራሉ የሚል ተስፋ ባይኖረኝም ሕዝቡ ግን ዜናዎችን እና የፌስቡክ ወሬዎችን የመገምገም ብቃት (critical analysis) መገንባት መቻል አለበት፡፡ ይሄ ለውጥ የምንፈልገው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ እንዲያደርሰን የለውጡ ደጋፊዎች ግዙፍ ኃላፊነት እንዳለብን አንርሳ፡፡ በከፍተኛ የባለቤትነት እና የኃላፊነት ስሜት እንንቀሳቀስ” ሲል ሙሉአለም አስተያየቱን አስፍሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና የኮሚዩኒኬሽን መምህር አቶ ዳግም አፈወርቅ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ከሰሞኑ የሚስተዋሉ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸውን ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል። 

(ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ) 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ