1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስማርት ስልክ ሱስ እና ማርከሻዎቹ

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2015

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የስማርት ስልክዎ አጠገበው ከሌለ የጠፉ ከመሰለዎ፣ስራ ላይ ማተኮር ከከበደዎ፣ ለመተኛት ከተቸገሩ፣ የባትሪው መቀነስስ የሚያስጨንቀዎ ከሆነ፣ ሳይጠራ ወይም መልዕክት ሳይላክ ስልከዎን ደጋግመው ከተመለከቱ ለስልከዎ ጥገኛ/ሱሰኛ/ ሆነዋል እና ከዚህ ለመውጣት መፍትሄ ያስፈልገዎታል።

https://p.dw.com/p/4NFcP
Einsamkeit
ምስል Thomas Trutschel/photothek/picture alliance

ቴከኖሎጅ ለወለደው ችግር መፍትሄ የሚሆኑ ቴከኖሎጅዎችም አሉ


ቴክኖሎጅ የዕለተ ዕለት ኑሮን ለማቅለል፣ መረጃ ለማግኘት፣ ለመዝናናት፣ ለተግባቦት፣ለትምህርት ከሰዎች ጋር ያለንን ግኑኙነት ስራን ውጤታማ ለማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ዓለው። በአንፃሩ ደግሞ አብዝቶ መጠቀም ይዞት የሚመጣ የራሱ መዘዝ ወይም አሉታዊ ጎን አለው። የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በተንቀሳቃሽ ስልኮች ሱስ እና መፍትሄዎች ላይ ያተኩራል።
.መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ  ተጠቃሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም የዓለም አቀፍ ስማርት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 6.8 ቢሊዮን ይገመታል ፣ ይህም የ 4.2% አመታዊ እድገት አሳይቷል።ለዚህም ዋናው ምክንያት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለአያያዝ እና ለአጠቃቀም ቀላል በመሆናቸው እና የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማቅለል ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው ነው። በአንፃሩ ሰዎች ከስልኮቻቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት በጨመረ ቁጥር በእነሱ ላይ ጥገኛ የመሆን ወይም በሱስ የመያዝ ሁኔታም  እየጨመረ  መሆኑን ፔው የሚባለው የአሜሪካ የጥናት ተቋም ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በ ፍሮንቲስ ሳይካትሪ /Fronntiers in Psychiatry/  ታትሞ የወጣ፤በእንቅልፍ እና በተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ  ላይ በቅርቡ በብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል 39% የሚሆኑት የስልክ ሱሰ ነበረባቸው ። በጎርጎሪያኑ ጥር  25 ቀን 2023 ዓ/ም ፕሎስ ዋን /plos One/በተባለ ድረ ገፅ  ላይ የታተመው  እና በቅርቡ  በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ በኢትዮጵያ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የኢንተርኔት እና የተንቀሳቃሽ ስልክ  ሱስ  ከፍተኛ ነው። ማለትም የስርጭት መጠኑ እስከ 85% እንደሚደርስ ያሳያል።
ለመሆኑ የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ለምን በሱስ እንድንያዝ ያደርጉናል? በስዊዘር ላንድ የሶፍትዌር መሀንዲስ የሆኑት አቶ ዳዊት ዓለሙ።አሰራራቸው በራሱ ሱስ ውስጥ የሚከት ነው ይላሉ።
ቴክኖሎጅ በተለይም የስማርት ስልኮች የሰውን ልጅ የዕለተ ዕለት ኑሮ ለማቅለል፣ መረጃ ለማግኘት፣ ለመዝናናት፣ ለተግባቦት፣ለትምህርት፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ግኑኙነት ለማሻሻል እና ስራን ውጤታማ ለማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ዓለው። በአንፃሩ እነሱን ከልክ በላይ መጠቀም ይዞት የሚመጣ የራሱ መዘዝ ወይም አሉታዊ ጎን አለው እና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የሰዎች አጠቃቀም ሱስ የሚባለው ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል ሀላፊ እና የሪኔሳንት/Renascent/ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራች  የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ።«ሱስ ባጭሩ አራት መገለጫዎች አሉት።አራቱ «ሲ»ዎች ይባላሉ። በእንግሊዥኛ በ«ሲ» የሚጀምሩ አራት ቃላት አሉ።እነዚህ መገለጫዎች ናቸው,»ካሉ በኋላ «አንደኛው «ኮንትሮል» ነው።ቁጥጥር ማለት ነው።ባለን ባህሪ ፣ሱስ በተያዝንበት ልምምድ ላይ ቁጥጥር ማጣት ነው።,ሁለተኛው «ክሬቪግ»ሰቅዞ የሚይዝ ፍላጎት ነው።ልምምዱን የመደጋገም ጉጉት እና ፍላጎት ማለት ነው።ሶስተኛው «ኮምፐልሽን»በዚያ ተግባር ውስጥ በፈቃደኝነት ሳይሆን በከፍተኛ በውስጣዊ ግፊት መሰማራት ማለት ነው።እሱን በማያደርጉ ጊዜ ከፍተኛ ጭንቀት መኖር።አራተኛው ደግሞ «ኮንሲኮንስ» ነው።አሉታዊ ውጤት ነው።» በማለት የሱስን መገለጫ ባህሪያት ገልፀዋል።   
ከዚህ አንፃር በ«ኮጄንት ሳይኮሎጂ» የታተመ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ስማርት ስልኮችን ከመጠን በላይ መጠቀም ጤናማ ያልሆነ ጥገኝነትን ይፈጥራል። ከነዚህም መካከል  ስልክ በአጠገብ ከሌለ ለመተኛት መቸገር፣ በባትሪው መቀነስስ መጨነቅ ፣ ስልክ ሳይጠራ ወይም መልዕክት ሳይላክ ደጋግሞ ማየት፣ ስራ ላይ ትኩረት ማጣት፣ ጥቂቶቹ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ስልክ በሌለበት ጊዜ የሚታይ ፍራቻ እና የመነጠል ስሜትን የሚያመላክቱ  ፎሞ /FOMO/እና ኖሞፎቢያ/ nomophobia/ እንዲሁም  ቴክስታፍሪኒያ /Textaphrenia/  መልዕክት ሳይገባገባ  እንዲሁ የማየት ልማድ እና ስልካችን  የነዘረን መስሎን አውጥተን የማየት ልማድ የሚያመለክተው ፋንተም ቫይብሬሽን /Phantom Vibration/ የመሳሰሉ አዳዲስ ቃላት ወደ ህክምና ሳይንሱ መዝገበ ቃላት ገብተዋል።ይህ ችግር ፕሮፌሰር ሰሎሞን እንሚገልፁት ከበይነመረብ ፍጥነት መጨመር ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ጨምሯል። የችግሩን ጥልቀትም በእርሳቸው የማገገሚያ ማዕከል በሚታከሙ አንዳንድ ታካሚዎች መመልከታቸውን ገልፅዋል።
በአጠቃላይ የስማርት ስልክ ሱስ  ምልክቶች እንደ  ቁማር ፣ መጠጥ እና አደንዛዥ እፅ ካሉ ሌሎች ሱሶች ጋር ተመሳሳይነት የሚታይባቸው ሲሆን፤ ይህም ጭንቀትን፣ ድብርትን፣ እንቅልፍ እጦት፣ የስራ መጥላት ባህሪ ከባሰም ከማህበራዊ ህይወት መራቅ እና ራስን ወደ ማጥፋት ሊያደርስ ይችላል። ከዚህ የተነሳ  በተጠቃሚው አዕምሮአዊ እና አካላዊ ጤና እንዲሁም በማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ይላሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን ።
የስማርት ስልክ ሱስ ሲባል በስልኩ አማካኝነት ያለገደብ የምንጠቀማቸው ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም ፣ቲውተር፣ ዩቱዩብ እና  ቲክ ቶክን የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገኛ ዘዴዎችን አብዝቶ መጠቀምን ያጠቃልላል። በመሆኑም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  አጠቃቀምን ማቆም ወይም መቀነስ ትልቅ መፍትሄ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ ።ስለሆነም በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ይህንን ያደረጉ አካላዊ እና አእምሯዊ ጤናቸውን ማሻሻል ፣ ምርታማነትን፣ ትኩረትን እና ደስታን መጨመር ችለዋል።ነገር ግን ራስን ከዚህ ማላቀቅ /ዲጂታል ዲቶክሲንግ/  ቀላል አይደለም። ምክንያቱም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከወዳጅ እና ዘመድ እንዲሁም ከጓደኞቻችን ጋር ለመገናኘት ፣ መረጃ ለማግኘት እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለመከታተል ምቹ መንገዶች ናቸው። ከዚህ ባሻገር ተጠቃሚዎች በመተግበሪያዎቻቸው ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመጨመር የተነደፉት መድረኮች እና ስልተ ቀመሮች ተጨማሪ የንግድ ወይም የመዝናኛ ምስሎችን እና  ቪዲዮዎችን የመመልከት አዙሪት ውስጥ የሚከቱ ናቸው። 
ነገር ግን እሾህን በእሾህ እንዲሉ ለዚህ ችግር ዲጅታል መፍትሄዎች መኖራቸውን አቶ ዳዊት ያስረዳሉ። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩን ለመቅረፍ የባለሙያ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰር ሰለሞን ገልፀዋል።

Facebook, Twitter, Instagram, TikTok
ምስል Hideki Yoshihara/AFLO/IMAGO
Äthiopien | Renaascant Zentrum für psychische Gesundheit in Addis Abeba
ሬኔሳንት የአዕምሮ ህክምና ተሃድሶ ማዕከልምስል privat
Professor Solomon Tefera
ፐሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት እና የሬኔሳንት የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራችምስል Privat
AfroRead- Bizuneh Birhan
አቶ ዳዊት ዓለሙ የሶፍትዌር መሀንዲስ ምስል Privat
Symbolbild | Doomscrolling
ምስል Thomas Trutschel/photothek/IMAGO

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
 

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ