1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የስኳር ፋብሪካዎቹን ማን ይገዛል?

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2011

ከ2003 -2010 ዓ.ም. 98 ቢሊዮን ብር  የወጣበትን የስኳር ማምረቻ ዘርፍ ወደ ግል ለማዘዋወር መንግሥት ፍላጎት ላላቸው ጥሪ አቅርቧል። በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ከሚገኙ 13 ፋብሪካዎች ስምንቱ ሥራ ላይ ቢሆኑም የገበያውን ፍላጎት መሙላት አልሆነላቸውም። ኢንዱስትሪውን በቅርብ የሚያውቁ ለግሉ ዘርፍ ሊዘዋወር ይገባል የሚል አቋም አላቸው

https://p.dw.com/p/3GzYt
Äthiopien Omo Kuraz III Sugar Factory
ምስል Ethiopian Sugar Corporation

ለስኳር ኢንደስትሪው ከ2003 -2010 ዓ.ም. 98 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል

የኢትዮጵያ መንግሥት በእጁ የሚገኙ 13 የስኳር ፋብሪካዎች እና ተያያዥ መሠረተ-ልማቶች ለመግዛት፣ ለማስተዳደር አሊያም በሽርክና ለመስራት የሚሹ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል። የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎች፤ የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች እና የኢታኖል ማምረቻዎች በተናጠል አሊያም በጠቅላላ መግዛት ያቀዱ ፍላጎታቸውን የሚያሳውቁበት ሰነድ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ይፋ ሆኗል። 

የገንዘብ ምኒስትር ድኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ቀደም ብለው ስለ መንግሥታቸው ውሳኔ በሰጡት ማብራሪያ ሰነዱ "በዚህ ዘርፍ ላይ ፍላጎት ያለው ማንኛውም የግሉ ዘርፍ አገር በቀሉም የውጪውም እንዲሁም ገና ፍላጎቱን ያልገለጸ ግን ፍላጎት እንዳለው የሚታሰበው ሁሉ በተቀናጀ መልኩ ፍላጎቱን የሚገልጽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 
ይኸ ሰነድ የስኳር አምራች ዘርፉን ወደ ግል ለማዛወር የመጀመሪያው ርምጃ ቢሆንም የመጨረሻው ውሳኔ ግን አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰነዱን ይፋ ከማድረጉ በፊት ከስኳር ፋብሪካዎቹ መካከል ያዋጣናል ያሉትን ለመግዛት ጥናት ያደረጉ ኩባንያዎች እንደነበሩ አቶ ለማ ጉሩሙ ይናገራሉ። 

የኢትዮጵያን የስኳር አምራች ዘርፍ በቅርብ የሚያውቁት እና መተሐራን ጨምሮ በተለያዩ ፋብሪካዎች በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ለማ በዓለም ገበያ ከፍ ያለ ስም ያላቸው ኩባንያዎች በመንግሥት ጥያቄ መሰረት ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው። 
 
ኢትዮጵያ ባላት የመሬት አቀማመጥ፤ የውኃ ሐብት እና የመሬት አቅርቦት በስኳር ማምረቻው ዘርፍ ስኬታማ ልትሆን እንደምትችል አቶ ለማ እምነታቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አገሪቱ አላት የሚባለውን እምቅ ሐብት ሥራ ላይ እናውላለን ብለው ተነሱ። የዛሬው የስኳር ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ በኋላ በሰኔ 2003 ዓ.ም. የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን አስር የስኳር ፋብሪካዎች ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል ፈረመ።

ይኸ ተቋም ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት ግን አልሆነለትም። ከሰም፣ ወልቃይት፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3 እና ኦሞ ኩራዝ 5 የስኳር ፋብሪካዎች ወዲያውኑ ከብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ተነጥቀው ለቻይና ኩባንያዎች ተሰጡ። የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም እንደሚሉት በሜቴክ እጅ የነበሩ ፋብሪካዎችን ግንባታ ለማጠናቀቅ 5.7 ቢሊዮን ብር አስፈልጓል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ