1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤተ-እስራኤላዊያኑ አቤቱታ

ዓርብ፣ ኅዳር 14 2011

ለረጅም ዓመታት ከቤተሰብ ተለያይተናል ችግር ላይ ነን ያለነው ሲሉ አዲስ አበባና ጎንደር የሚኖሩ ቤተ እስራኤላዊያን ለ«DW »ገለጹ። ወደ እስራኤል ለመሄድ እንዳልቻሉ ከቤተሰቦቻችን ጋር በሁለት ሃገራት ተለያይተን መኖር ግድ ሆኖብናል ሲሉም ያማርራሉ።

https://p.dw.com/p/38oOA
Bete Israelis in Gondar
ምስል DW/G. Tedla

እስራኤል ያለዉ ኤምባሲ ቢያስመዘግበንም እስካሁን ያለዉ አንዳች ነገር የለም

ኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤሎች ከቤተሰብ ጋር ተለያይተናል ችግር ላይ ነው ያለነው ይላሉ። ከ20 ዓመታት በላይ ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል። ባል ከሚስቱ፣ ልጅ ከአባቱና ከእናቱ፤ ዘመድ ከዘመዱ ተለያይተናል የቤተ እስራኤላዊያኑ ቅሬታ። ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ወደ እስራኤል እንዳይሄዱ ተከልክለናል፤ እስራኤል ካሉ ቤተሰቦቻችን ጋር እንዳንገናኝ ተደርገናል፣ ችግር ላይም ወድቀናል ሲሉ ያማርራሉ። ያነጋገርናቸው ስማቸውን መግለጥ ያልፈለጉት ቅሬታ አቅራቢዎች የአዲስ አበባ እና የጎንደር ነዋሪ ናቸው።
አዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ከአባትዋ የተለያየችው ገና ሳትወለድ በፊት እንደሆነ ትናገራለች። አባቷ በተደጋጋሚም ቤተሰቡን ሊወስድ ቢሞክርም፤ ላለፉት 24 ዓመታት ግን አልተሳካለትም ትላለች። እስራኤል ላለው ኤምባሲ ቢያስመዘግበኝም እስካሁን አንዳችም ነገር የለም ስትልም ገልጻለች።  
“እዛ ያለው ኤምባሲ እንዳስመዘገበኝ ነው የነገረኝ፤ ግን ምንም ነገር የለም እስካሁን። በችግር ነው ያሳለፍነው። እኔና እናቴ ነን የምንኖረው። እናቴ ናት ያሳደገችኝ በብዙ ስቃይ።”
ሌላዋ ቤተ-እሥራኤላዊት ወጣት ላለፉት 21 ዓመታት እስራኤል የመሄድ ሙከራዋ አልተሳካም። ነዋሪነቷ ጎንደር ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦችዋ በሕይወት እንደሌሉ ትናገራለች። የቀሩት አክስትና አጎቶቿ እስራኤል አገር ናቸው እንደስዋ አባባል። ወሰ እሥራኤል የመሄዳቸው ጉዳይ ለግዜው እንደተዘጋ እዛ ያሉ ቤተሰቦችዋ ነግረዋታል። 
“ኤምባሲ ደውለው የተባለው ነገር ምንም አስተያየት ልንሰጥ አንችልም፤ ተዘግቷል ነው። ባለፈው ወደ እስራኤል አገር 1000 ሰዎች የሚሄዱ እንዳሉ ሀገር ዜና ላይ አይቻለሁ። ከነሱ መካከል እንኑር አንኑር ምንም የማቀው ነገር የለም።” 
እስራኤል ካሉ ወንድምና እህቶቻቸው ጋር መገናኘት ያልቻሉት ቤተ እስኤላዊ እናት በበኩላቸው ወደ እሥራኤል ተጉዘው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘቱን እንደናፈቁ ነው። ወደ ወገናችን መሄድ እንፈልጋለን ይላሉ።   
“ከወገናችን ጋር መጨመር ነው የምንፈልገው። ሁሉም ሰው ዘርና ሀረጉን ቆጥሮ ስለመጣ ከወገናችን መሄድ እንፈልጋለን።”
ያነጋገርናቸው ቤተ እስራኤላዊያኑ ለእስራኤል ኤምባሲ በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እንደተቸገሩ ይገልጣሉ። እዛ ያሉ ቤተሰቦቻቸውም እንዲወስዷቸው እየጠየቅን ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል። የጎንደሯ ወጣት ቤተ እሥራኤላዊት ጎንደር ላለው ኤምባሲ በግሏ በስልክ ለማነጋገር ጥረት አድርጋ ምንም የምናደርገው ነገር የለም የሚል መልስ ሰተውኛል ትላለች።
“ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት የሚጠባበቁ ከገጠር መተው ጎንደርና አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ብዙ ዓመት የሚጠብቁ ሰዎች አሉ እስራኤል አገር ለመሄድ። ለነሱ ከባድ ይሆንባቸዋል።”   
እኛም ጎንደር ላለው የእስራኤል ቆንስላ ጽ/ቤት ስልክ ደውለን ለማነጋገር ጥረት አድርገን ነበር። ምንም የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ገልጸዋል። አዲስ አበባ ላለው የእስራኤል ኤምባሲም ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪያችን ምላሽ አላገኘም።  
የ21 አመትዋ ወጣቷም ያለችው ይሄንኑ ነበር። የእስራኤል ጉዞ ህልሟ እስካሁን ሳይሳካ እናትና አባትዋ እንዲሁም አያትዋ ሀገረ-እስራኤል መግባት እንደናፈቁ በሞት ተለይተዋል።  
በአዲስ አበባና በጎንደር የሚገኙት ቤተ እስራኤላዊያን ከዛሬ ነገ ተሳክቶልን ወደ እሥራኤል እንሄዳለን በሚል ተስፋ ቢሞሉም፤ አንዳችም ለውጥ ሳይኖርው ዓመታት አስቆጥረዋል። ከሁሉም የከፋው ሳይገናኙ በሞት መቆራረጣቸው ሐዘናቸውን የከፋ እንዳደረገው ይናገራሉ። 

Bete Israelis in Gondar
ምስል DW/G. Tedla
Tausende Juden beten aus Protest gegen Nahostkonferenz in Annapolis
ምስል AP


ነጃት ኢብራሂም
ማንተጋፍቶት ስለሺ