1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የብሔራዊ ባንኩ ሹም ሽር

ረቡዕ፣ ሰኔ 13 2010

የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ተስኖታል፤ የግልና የመንግሥት ባንኮችን በእኩል አይን አያይም እየተባለ የሚወቀሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሹም ሽር ተካሒዶበታል። ዶ/ር ይናገር ደሴ ለረዥም አመታት ያገለገሉትን አቶ ተክለወልድ አጥናፉን ተክተው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነዋል። ብሔራዊ ባንክ ያሻዋል የሚባልለትን ገለተኝነትና ነፃነት በሹም ሽር ያገኝ ይሆን?

https://p.dw.com/p/2zxVA
Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar
ምስል picture-alliance/M.Kamaci

የብሔራዊ ባንክ ሹም ሽር

የውጭ ብድር የተጫናት ኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ገዢዎቿን ሽራ በአዲስ ተክታለች። የብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ተነስተው በዶክተር ይናገር ደሴ ተተክተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ የብሔራዊው ባንክ ምክትል ገዢ ሆነው ተሾመዋል። በዋና ገዢነት የተሾሙት አቶ ይናገር የኢንቫሮመንታል ኤኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። ሹመታቸው እስከ ተሰማበት ዕለት ድረስ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለረዥም ዓመታት በብሔራዊ ባንክ ገዢነት ያገለገሉትን አቶ ተክለወልድ አጥናፉንም ሆነ ምክትል ገዢው ዶክተር ዮሐንስ አያሌውን የሻረበትን ምክንያት በይፋ አላስታወቀም። የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት በቅርበት የሚከታተሉ እና በባንክ አገልግሎት ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ግን ሹም ሽሩ አስፈላጊ እንደነበር ያምናሉ።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም እንደሚሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአቶ ተክለወልድ አጥናፉ እየተመራ "ከበጀት ፖሊሲ በተለየ መልኩ ነፃነቱን አረጋግጦ መሥራት የሚችል የገንዘብ ፖሊሲ ማረጋገጥ አለመቻሉ" ዋንኛ ችግሩ ሆኖ ቆይቷል። አቶ ተክለወልድ ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው አመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ የኤኮኖሚውን እንቅስቃሴ ማፋጠን፣ የሥራ ቅጥርን እና ለግሉ ዘርፍ የብድር አቅርቦትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ አለመሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ። አቶ ጌታቸው ብሔራዊ ባንኩ የመንግሥት እና የግል የገንዘብ ተቋማትን በእኩል አለማየቱ ሌላው ጉድለቱ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

የሕብረት ባንክ እና ሕብረት ኢንሹራንስ መሥራቹ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉም ከአቶ ጌታቸው የሚገጥም ሐሳብ አላቸው። እየሱስወርቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "የባንክ አገልግሎት ዘርፉን ብዙ የማያወያይ እንደ ፖለቲካው አመራር እኔ አውቅልሀለሁ የሚል ሆኖ ቆይቷል" ሲሉ ይተቻሉ። "ከዚህ ቀደም ከዘርፉ ጋራ ተቀራርቦ መወያየት ያልነበረበት፤የንግድ ሕጉ በስራ ላይ ያልዋለበት በይበልጥ ብሔራዊ ባንኩ ከቁጥጥር ኃላፊነት አልፎ የግል ባንኮቹ አስተዳዳሪ ወደ መሆን በጣም ያቀረበ ሰፍኖ ቆይቷል" የሚሉት አቶ እየሱስወርቅ ቁጥጥሩም ቢሆን ፖለቲካዊ ጫና የነበረበት እንደሆነ ይገልጻሉ። አቶ እየሱስወርቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "አዳማጭ የሆነ በባንክ ዘርፉ ላይ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ቁጥጥር የሚያደርግ አመራር ይኖራል" የሚል ተስፋ አላቸው። ይኸ ተስፋቸው አዲስ በተሾሙት ዶክተር ይናገር ደሴ ትከሻ ላይ ይወድቃል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም "ይናገር ደሴ ምን አይነት የገንዘብ ፖሊሲ ፍልስፍና አላቸው የሚለውን አናውቅም። ምክንያቱም በአካዳሚክ ከባቢው ውስጥ አልነበሩም። ከፖሊሲ አንፃር የሰሩት ጥናት ኖሮ፤ ያሳተሙት ሕትመት ኖሮ ይኼ ይኼ ነው ፍልስፍናቸው፤ ስለዚህ የገንዘብ ፖሊሲ በዚህ አቅጣጫ ይመራል የምንልበት ነገር የለም" ሲሉ ይናገራሉ።  

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

"የሰዎች መለዋወጥ ለውጥ ያስከትላል ምንም ጥያቄ የለውም" የሚሉት የኢትዮጵያ የባንክ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ አዲሱ ሐባም ቢሆኑ በተጨባጭ ምን እንደሚለወጥ መናገር እንደሚቸግር ያስረዳሉ።

አቶ ይናገር የተሾሙበት ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ የማስፈፀም ኃላፊነት አለበት። ብሔራዊው ባንክ በገበያው የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን የመቆጣጠር፤ የወለድ ምጣኔንም የመወሰን ሥልጣንም አለው። የኢትዮጵያ የባንክ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አዲሱ ሐባ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች ባንኮች እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመቆጣጠር ሥልጣንም በብሔራዊ ባንክ እጅ ነው።

አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የብሔራዊ ባንክ ገዢ በነበሩባቸው ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት አሁን ወዳለበት የዕድገት ንቅናቄ የገባበት እንደሆነ ይነገርለታል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው እንደሚሉት አቶ ተክለወልድ ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት በአንፃራዊነት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ነበር። ብር ከሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሪ ምጣኔ እየጨመረ ቢመጣም ለውጡ ግን ከብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት አገሪቱ በምትከተለው ፖሊሲ ምክንያት ውድድር ባይኖርበትም አቶ ተክለወልድ ብሔራዊው ባንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በተሻለ ደረጃ እንዲጠቀም፤ ተደራሽነቱንም እንዲያሰፋ በማድረጉ ረገድ አዎንታዊ ሚና እንደነበራቸው አቶ ጌታቸው ያምናሉ። 

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዢ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባል ናቸው። አዲሱ ዶክተር ይናገርም ቢሆኑ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባል እና ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከልም ይገኙበታል። አቶ ጌታቸው የባንኩ አሰራር እና አደረጃጀት እንዲሁም ከሥራ አስፈፃሚው ጋር ያለው የቀረበ ቁርኝት ሚናውን በአግባቡ እንዳይወጣ ጋሬጣ ሆኖበታል ሲሉ ይናገራሉ።

"ብሔራዊ ባንክ በጀቱን እና በጀት የሚፈጸምበትን ሁኔታ በኤኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን አስተዋፅዖ በነፃነት ገምግሞ መንግሥትን መደገፍ በሚኖርበት ሰዓት መደገፍ እንዲችል፤ በመንግሥት ላይ ገደብ ማድረግ በሚኖርበት ሰዓት ገደብ የሚያደርግ" ሊሆን እንደሚገባው አቶ ጌታቸው ይናገራሉ። ባለሙያው "ሁለቱንም በሚያደርግበት ሰዓት ዋና ዓላማው የዋጋ ግሽበትን ዝቅተኛው መጠን ላይ ማስቀመጥ፤ በኤኮኖሚው ውስጥ ያለውን የቅጥር መጠን ማይክሮ ኤኮኖሚው በሚችለው መጠን ማድረግን እንደ አላማው ወስዶ ሁለቱንም የሚያደርግ በአስተሳሰብም፤ በፍልስፍናም፤ ፖሊሲ በማውጣትም፤ በመተግበርም ረገድ ከፊስካል ፖሊሲው ወይንም ከሥራ አስፈፃሚው በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችል ብሔራዊ ባንክ ያስፈልጋል" ሲሉ ይሞግታሉ። አቶ ጌታቸው "የብሔራዊ ባንክ ገዢው የኢሕአዴግ አባል እንደመሆናቸው መጠን በተለያዩ የመንግሥት ሹመቶች ውስጥ የቆዩ እና በአመራር ረገድ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር እሱ ነፃነት ይመጣል ወይ የሚለው በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚቀመጥ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ