1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሬግዚት ረቂቅ ውል እና ብሪታንያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2011

ሜይ በብሬግዚት ረቂቅ ውል ሰበብ ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚፈራ ሌላ ትልቅ ፈተናም አለ።በውሉ መሠረት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንድትወጣ ሜይ የብሪታንያ ፓርላማ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በፓርቲያቸው ውስጥ የሚገኙት ተቃዋሚዎቻቸው ቁጥር ከፍተኛ መሆን እና የአጋሮቻቸውም መቆጣት ረቂቅ ውሉ እንዳያልፍ እንቅፋት መሆኑ እንደማይቀር ተገምቷል።

https://p.dw.com/p/38b3i
England | PK Theresa May
ምስል Reuters/Pool/M. Dunham

 
የአውሮጳ ህብረት እና ብሪታንያ የተስማሙበት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት የምትወጣበት የብሬግዚት ረቂቅ ውል በብሪታንያ የፖለቲካ ቀውስ አስከትሏል። ከስምምነቱ በኋላ የሀገሪቱን የብሬግዚት ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሥራቸውን መልቀቃቸው ቀውሱን አባብሶታል። 
የብሪታንያ ህዝብ ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት«ትውጣ ወይም አትውጣ» ለሚለው ጥያቄ  ድምጽ ከመስጠቱ ከዛሬ ሁለት ዓመት ከ4 ወር በፊት ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ብዙም አከራካሪ አልነበረም። ዜጎችን ጨምሮ አብዛኛው ዓለም ህዝቡ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት ይወስናል የሚል ግምት አልነበረውም። ውሳኔው ከብዙሀኑ ግምት በተቃራኒ ከህብረቱ መውጣት መሆኑ ግን ያልተጠበቀ፣ያስደነገጠ እና ብዙም ያነጋገረ ነበር። ብሬግዚትን ሲደግፉ እና ህዝቡንም ሲቀሰቅሱ ለነበሩ ለሀገሪቱ ፖለቲከኞች ሳይቀር ውሳኔው ዱብ እዳ ነበረ የሆነው። ያኔ ድምጽ ከሰጠው ህዝብ 17.4 ሚሊዮኑ ወይም 52 በመቶው ብሬግዚትን ሲደግፍ 16.1 ሚሊዮኑ ወይም 48 በመቶው ከህብረቱ ጋር መቆየትን ነበር የመረጠው። ከተቀራራቢው የህዝበ ውሳኔ ውጤት በኋላም ብሪታንያ ብዙ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ሀገሪቱ ህብረቱን መልቀቅዋ ኪሳራው ያመዝናል በሚል  ውጤቱን እንደማይቀበል በማሳወቅ ወጣቱ ሌላ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ እስከመጠየቅ ደርሶ ነበር። ለብሬግዚት ህዝበ ውሳኔ የጠሩት ያያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ሥልጣናቸውን ሲለቁ ፤ ወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው ብሬግዚትን ሲቃወሙ የነበሩትን ቴሬሳ ሜይን ተካ። ሜይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ «ወደ ኋላ አንመለስም ብሬግዚት ብሬግዚት ነው»፣የህዝቡን ፍላጎትም ተግባራዊ እንዳርጋለን ብለው ነበር የተነሱት።  ያሉትን ተግባራዊ ማድረጉ ግን እንዲህ ቀላል አልሆነላቸውም። ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ያካሄደችው የፍቺ ድርድር ረቂቅ ውል ላይ ቢደርስም በሀገሪቱ ውዝግብ እና ክፍፍል አስከትሏል። ሂደቱም ከባድ እንደነበረ ነው ሜይ ካቢኔያቸው በረቂቅ ውሉ ላይ ከተስማማ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ያስረዱት። 
«ከፊታችን የተቀመጡ ምርጫዎች ለኛ አስቸጋሪ ነበሩ። በተለይ ከሰሜን አየርላንድ አማራጭ እቅድ ጋር የተያያዙት፤ ሆኖም የካቢኔው የጋራ ስምምነት «በአወጣጡ ረቂቅ ውል» እና በዝርዝር ጉዳዮች ላይ መንግሥት እንዲስማማ ነበር። ይህ በሚቀጥሉት ቀናት ወደፊት መራመድ የሚያስችለን እና ውሉንም ከፍጻሜ የሚያደርስልን ወሳኝ እርምጃ ነው። እኔም በዐዕምሮየ እና በልቤ ይህ ውሳኔ የኛን ብሪታንያ ጥቅም በደንብ የሚያስጠብቅ ነው ብዬ በጥብቅ አምናለሁ።»
የአውሮጳ ህብረት እና ብሪታንያ በተስማሙበት ረቂቅ የብሬግዚት ውል ውስጥ ከተካተቱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የአውሮጳ ህብረት አባል የአየርላንድ እና የብሪታንያ ግዛት የሰሜን አየርላንድ ድንበር እንዲሁም የዜጎች መብት አንዱ ነው። ከሽግግሩ ወቅት በኋላም ለጥንቃቄ ያስፈልጋል የተባለ አማራጭ ዕቅድም ተይዟል። ረቂቅ ውሉ ከዚህ ሌላ ብሪታንያ የሚኖሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአውሮጳ ህብረት ዜጎች እና በተለያዩ የአውሮጳ ህብረት ሀገራት ያሉ ብሪታንያውያንን መብቶችን እና ጥቅማ ጥቅሞችን ማስጠበቅንም አካቷል። ብሪታንያ ለህብረቱ መክፈል ያለበት ገንዘብ ጉዳይም እንዲሁ። የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ በረቂቅ ውሉ የተካተቱትን ዐበይት ጉዳዮች ይዘረዝርልናል 
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ብሪታንያ ከህብረቱ አባልነት የምትወጣው በጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2019 ነው። እስከ ታህሳስ 2020 ደግሞ የሽግግር ጊዜ ነው። የአውሮጳ ህብረት የብሬግዚት ተደራዳሪ ሚሼል ባርንየ ሁለቱ ወገኖች በዚህ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርጉ የተስማሙበትን አሰራር ገልጸዋል። 
«ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 30፣2019 እስከ እስከ ታህሳስ 2020 ለ21 ወራት፣ የውስጥ ገበያን የጉምሩክ ጉዳዮችን የአውሮጳ መርሆች እና አብረዋቸው የሚሄዱት መብቶች እና ግዴታዎችን አሁን ባለው ሁኔታ እንዳሉ ለመጠበቅ ተስማምተናል። ይህንንም በጋራ ስምምነቱ ለተወሰነ ጊዜ የማራዘም እድልም አለን።»
በረቂቅ ውሉ እነዚህን የመሳሰሉ ስምምነቶች ላይ ቢደረስም ከብሪታንያ ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች እንዲሁም ከዜጎች ልዩ ልዩ ተቃውሞ ተነስቷል። እስካሁን በብሬግዚት ድርድር ሂደት ሳይስማሙ ሥራቸውን የለቀቁ ባለሥልጣናት ቁጥር 11 ደርሷል።። ውሉን የብሪታንያ ካቢኔ ካጸደቀው በኋላም ከተሰናበቱት መካከል የብሬግዚት ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ አንዱ ናቸው። ከርሳቸው ሌላ አንድ የካቢኔ አባል ሁለት ምክትል ሚኒስትሮች እና ሁለት የፓርላማ አባላት ረዳቶችም  ባለፈው ሐሙስ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል። ገበያው እንደሚለው የአብዛኛዎቹ ሃላፊዎች ከስራ የመሰናበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። 
ሜይ በብሬግዚት ረቂቅ ውል ሰበብ ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚፈራ ሌላ ትልቅ ፈተናም አለ። በውሉ መሠረት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንድትወጣ ሜይ የብሪታንያ ፓርላማ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም  በወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው ውስጥ የሚገኙት ተቃዋሚዎቻቸው ቁጥር ከፍተኛ መሆን እና በሰሜን አየርላንድ ዴሞክራቲክ ዩንየኒስት ፓርቲ ውስጥ ያሉት አጋሮቻቸውም መቆጣታቸው ረቂቅ ውሉ እንዳያልፍ እንቅፋት መሆኑ እንደማይቀር ተገምቷል። ረቂቁ ተቀባይነት ካላገኘ የሚያስከትለው ችግር  ከባድ ይሆናል እንደገበያው።
ሜይ የፓርላማ አባላት ውሉን እንዳያግዱ ቢማጸኑም ሰሚ ያገኙ አይመስልም። ይህ ደግሞ የብሪታንያን የፖለቲካ ቀውስ ያባብሳል የሚል ስጋት አሳድሯል። ቀውሱን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ የመፍትሄ ሃሳቦችም እየተሰነዘሩ ነው። ከመካከላቸው ሁለተኛ ህዝበ ውሳኔ ይካሄድ የሚለው አንዱ ነው። ይህን ሃሳብ ካቀረቡት ውስጥ የቀድሞዎቹ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጆን ሜጀር፣ ቶኒ ብሌር እና ጎርደን ብራውን ይገኙበታል። ሌሎችም ሃሳቦች መሰንዘራቸው ቀጥሏል ፓርላማው ለሜይ ድጋፉን ካልሰጠ ተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ ብሔራዊ ምርጫ እንዲጠራ ይፈልጋል።ምርጫ እንዲካሄድ ደግሞ ከ650 የፓርላማ አባላት የሁለት ሦስተኛው ድምጽ መገኘት አለበት። ሜይ የመታመኛ ድምጽ ካላገኙ ሌላ ምርጫ መጥራት የሚቻልበት እድልም ይኖራል። እነዚህን የመሳሰሉ ሙከራዎች ከተደረጉ በኋላ ፓርላማው ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት አዲስ ህዝበ ውሳኔ ሊጠራ ይችላል። ህዝበ ውሳኔ ይጠራ ከተባለም ወራት ሊወስድ ስለሚችል ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት እንድትወጣ ከተያዘላት የጊዜ ገደብ ከመጋቢት 2019 በላይ እንዲራዘምላት መጠየቅ ይኖርባታል። ሆኖም ብሪታንያ እዚህ ሁሉ ውጥንቅጥቅ ውስጥ ሳትገባ ሌላ መፍትሄ ሊገኝ ይችልም ይሆናል። 

Symbolbild Brexit
ምስል picture-alliance/D. Kalker
Dominic Raab
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Dunham
Brexit-Chefunterhändler Michel Barnier
ምስል Reuters/E. Vidal
Theresa May
ምስል picture-alliance/empics

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ