1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሪዎች ዉዝግብ

ሰኞ፣ መስከረም 21 2011

የሰባ አንድ ዓመቱ አዛዉንት አምና ይሕን ጊዜ የሰሜን ኮሪያዉን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ለመስደብ የሐገር መሪነት ሞገስ፤ የዲፕሎማሲ ክብር እና የሚያዉቁ አልመሰሉም። «አጭሩ የሮኬት ሰዉዬ እራሱ እና ሥርዓቱን የማጥፋት ተልዕኮ ይዟል።» ዘንድሮ«ትናንት ዛሬ አይደለም» አሉ ሰዉዬዉ።

https://p.dw.com/p/35pd4
UN-Vollversammlung verurteilt Israel für Gewalt im Gazastreifen
ምስል picture-alliance/Xinhua/Li Muzi

የተመድ ጠ/ጉባዔ ዋና ጉዳዮች

 

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለት ዓመት የሠሩት ሁለት መቶ ዓመት ከተፈራረቁት የሐገራቸዉ መሪዎች ሁሉ እንደሚበልጥ ተናገሩ።ተሳቀባቸዉ።ሳቁ።አምና የዛቱበትን አመስግነዉ ዘንድሮ ኢራን ላይ ዛቱ።የኢራኑ ፕሬዝደንት በትራምፕ ላይ ተሳለቁ።የሩሲያ፤የቻይና፤ የፈረንሳይ፤ የፍልስጤም፤ የሶሪያ እና የሌሎችም ሐገራት ተወካዮች የትራምፕን መርሕ ነቀፉ፤ ያወገዙም አሉ።የእስራኤል እና የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ግን ኢራንን አዉግዘዉ ትራምፕን አወደሱ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአፍሪቃ ቀንድ ለዉጥን «የተስፋ ነፋስ» በማለት ሲያደንቁ ዓለምን ግን ከመተማመን ይልቅ መጠራጠር ከሰላም ይብስ ጠብ እንደነገሰባት አስጠነቀቁ።ትንሺቱ ሐገር ኒዊ ዚላንድ ትንሽ ሕፃኗን ከትልቁ ጉባኤ በማሳተፍ ታሪክ ሰራች።73ኛዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ።

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 193 አባል ሐገራትን የሚያስተናብር ለሁሉም ሐገራት የሚደርስ  የድፍን ዓለም ማሕበር ነዉ።በየዓመቱ ብዙ ጊዜ መስከረም  ግን አንዴ የሚያደርገዉ ጠቅላላ ጉባኤም የአባል ሐገራት ተወካዮች በሙሉ በየተራ የሚናገሩበት ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ ስብሰባ ነዉ።ሁሌም ግን ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለመሪዋ ቅድሚያ ይሰጣል።በብዙ ምክንያት።

Generalversammlung der Vereinten Nationen | Flagge Iran
ምስል picture-alliance/newscom/UPI Photo/J. Angelillo

ድርጅቱ ራሱ እንዲመሠረት ሐሳብ ያቀረቡት፤ አባል ሐገራትን ያሰባሰቡ፤ መተዳደሪያ ደንብ ወይም ቻርተሩን ያረቀቁ፤ ለድርጅቱ መስሪያ ቦታ የፈቀዱ፤ ከፍተኛዉን በጀት የሚሰጡትም አሜሪካኖች ናቸዉ።ዘንድሮም እንደ እስከ ዘንድሮዉ ሁሉ ከሐገራት መሪዎች ሁሉ የመጀመሪያዉ ተናጋሪ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ነበሩ።

«አስተዳድሬ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ በሐገራችን ታሪክ የነበሩ ሁሉም ያክል አስተዳደሮች ካከናወነቱ የበለጠ ሠርቷል።»

አዳራሹ መጀመሪያ በጉባኤተኖች ፈገግታ ወዲያዉ በሳቅ ተነቃነቀ።የሚሳቃብቸዉም ሳቁ።----መልሱን አልጠበቅሁም ነበር።ግን ይሁን» እያሉ።

                                   

የሰባ አንድ ዓመቱ አዛዉንት አምና ይሕን ጊዜ የሰሜን ኮሪያዉን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ለመስደብ የሐገር መሪነት ሞገስ፤ የዲፕሎማሲ ክብር እና የሚያዉቁ አልመሰሉም። «አጭሩ የሮኬት ሰዉዬ እራሱ እና ሥርዓቱን የማጥፋት ተልዕኮ ይዟል።»

ዘንድሮ ትናንት ዛሬ አይደለም አሉ ሰዉዬዉ።«ሊቀመንበር ኪም ለሳዩት ድፍረት እና ለወሰዷቸዉ እርምጃዎች ማመስገን እወዳለሁ።»

በ1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ወይም ቻርተር ሲፀድቅ የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ቱሩማን ያስተላለፉት መልዕክት የድርጅቱ መርሕ ዋልታና ማገር መስሎ ነበር።እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያሉት እዉነት ቢሆን የጆርጅ ዋሽግተን ይሁን፤ የአብራሐም ሊንከን፤ የሩዘቬልት ይሁን የትሩማን ወይም የአርባ አራት ቀዳሚዎቻቸዉ አስተዳደር የትራምፕን አያክልም።ትሩማን ከሰባ-ሰወስት ዓመት በፊት ያስተላለፉት መልዕክት ግን ዛሬም ሰሚ እንጂ አክባሪ አላገኘም።

UN Generalversammlung in New York | Donald Trump, Präsident USA
ምስል Getty Images/S. Platt

                                  

«እነዚሕ በዘር፤ በኃይማኖት፤ በቋንቋ እና በባሕል በጣም የተለያዩ 50 ሐገራት ይሕን ስምምነት ማድረጋቸዉን የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ።ይሁንና እነዚሕ ልዩነቶች በአንድ የማይናወጥ ዉሳኔ ተረሱ።ጦርነትን በማሰወገድ የጋራ ፅኑ ዉሳኔ።»

ያኔ ሐምሳ ነበሩ።ዘንድሮ 193።በ73 ዓመት ጉዞ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች በየዓመቱ የሚያወግዙት፤ የሚወቅሱት መንግስት፤ድርጅት ወይም ተቋም አጥተዉ አያዉቁም።ትራምፕ ግን እንደመሪ አያወግዙም  አንድም ይሳደባሉ ወይም ይፎክራሉ አለይማ ይዝታሉ እንጂ።በስድብ መዘርዝራቸዉ አምና ሁለተኛ የነበረችዉ ኢራን ዘንድሮ አንደኛ ሆናለች።

«የሶሪያን ሰብአዊ ቀዉስ ለማስወገድ የሚነደፈዉ ስልት በሙሉ፤ ቀዉሱን ያቀጣጠለዉ እና እንዲባባስ ገንዘብ የሚመድበዉ የኢራንን አረመኔያዊ ሥርዓትን የሚመለከት መሆን አለበት።በሙስና የተዘፈቀዉ የኢራን አምባገነን፤ የኢራን መሪዎች ብጥብጥ፤ሞት እና ጥፋትን ዘርተዋል።»

ትራምፕ እንዳሉት ለሶሪያዉ ጦርነት ተጠያቂዋ ኢራን ናት።የየመንን ሕዝብ የሚፈጀዉ ጦርነት አራማጅ ኢራን ናት።ለእስራኤል ፀጥታ የምታሰጋዉ ኢራን ናት።የኒክሌር ቦምብ ለመስራት የምታደባዉ ኢራን ናት።አሸባሪነትን የምደግፍ፤የምታሰራጭ፤ የምታስፋፋዉ ኢራን ናት።

Syriens Außenminister Walid al-Muallimn fordert in UN-Generaldebatte sofortigen Abzug der US-Armee
ምስል imago/UPI Photo/J. Angelillo

የኢራኑ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩኻኒ ለትራምፕ ዉንጀላ ዝርዝር መልስ አልሰጡም።አንድ ሁለት መንግሥታ ቢፈግፏቸዉ እንጂ ትራምፕ ብቻቸዉን ናቸዉ።ተነጥለዋል አሉ።ሩሐኒ።

                                   

«ከአንድ እና ሁለት ሐገራት በስተቀር ዩናይትድ ስቴትስን የደገፈ ሐገር የለም።ይሕ አሜሪካንን ልዩ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ መነጠል እንዲደርስባት አድርጓል።»

እኒያ ሁለት ሐገራት እስራኤል እና ሳዑዲ አረቢያ መሆን አለመሆናቸዉን ሩሐኒ በስም  አልጠቀሱም።ኢራንን ለማዉገዝ የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናት የትራም ታማኝ፤ታዛዥ መሆናቸዉን አረጋግጠዋል።  የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደ ጥሩ አስተማሪ የኢራንን ሚስጥር ያጋልጣል ያሉትን በቀለም የተዥጎረጎረ ካርታ ይዘዉ ጠቅላላ ጉባኤዉ ፊት ቀረቡ።

                                             

«ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራን ቴሕራን ዉስጥ ሌላ የሚስጥር ሥፍራ እንዳላት አጋልጣለሁ።የኢራን ሚስጥር የኑክሌር መርሕ ግብር አካል የሆኑ በርካታ መሥሪያዎች እና ቁሳቁሶች የሚከችበት ትልቅ የአዉቶሚክ መጋዘን ( አለ)»

የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብድል አልጀቢር እንደ አባት፤አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ የፍስጤሞች የመኖር ሕልዉና ይከበር አላሉም።እስራኤል የአረቦችን መግደል፤ማሰደዷ መሬታቸዉን መቀማትዋን ታቁም አላሉም።የመን፤ሊቢያ፤ ሶሪያ ላይ የሚረግፉ ወገኖቻቸዉን ከቁብ አልቆጠሩትም። ትራምፕ እና ኔታንያሁን  ደገፉ።ኢራን ወነጀሉ።

«ኢራን የአሸባሪነት እንቅስቃሴዋን እና ጠብ ጫሪ ባሕሪዋን እንደቀጠለች ነዉ።የኢራን የኑክሌር ፤ የሚሳዬል መርሐ ግብር እና ለአሸባሪዎች የምትሰጠዉን ድጋፍ ጨምሮ አሜሪካ በኢራን ላይ ልትወስድ ያሰበችዉን አዲስ እርምጃ እና ስልት ንጉሳዊ መንግስትን እንደሚደግፍ እገልፃለሁ።»

የእስራኤል እና የሳዑዲ አረቢያ መሪዎች የደገፉት የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ ሥልት የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብርን ለማስቆም የተፈረመዉን ዓለም አቀፍ ስምምነት ትራምፕ ማፍረሳቸዉን ነዉ።ትራምፕ ያፈረሱትን ስምምነት  ሩሲያ፤ቻይና፤ ብሪታንያ፤ፈረንሳይ፤ ጀርመን እና የአዉሮጳ ሕብረት መከበር አለበት እንዳሉ ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለጉባኤዉ እንደነገሩት ትራምፕ የጣሱትን JCPOA የተባለዉን ስምምነት ብቻ አይደለም አሜሪካ የመሠረተች፤የምትመራ እና የምትደግፈዉ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ ጭምር እንጂ።

UN-Generalversammlung in New York | Jacinda Ardern, Premierministerin Neuseeland
ምስል Reuters/C. Allegri

  «ኢራን የገባችዉን ግዴታ ብታሟላም፤ ዩናይትድ ስቴት፤ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ቁጥር 2231ን ጥሳ፤ የJCOPA ስምምነትን በተናጥል ማፍረሷ አጠቃላይ የኑክሌር ሙከራን ለማገድ እንዳይፀድቅ እና መካከለኛዉ ምሥራቅን ከአዉዳሚ ጦር መሳሪያዎች ለማፅዳት የተደረገዉ ስምምነት እንዳይፀድቅ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የፀደቀዉ ስምምነት እንዲፀና የምንችለዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

የሶሪያ ጦርነት ለኢራን-ዩናይትድ ስቴትስ፤ ለዩናይትድ ስቴትስ-ሩሲያ እና ለየተባባሪዎቻቸዉ ዉዝግብ ሌላዉ ሰበብ ነበር።የሶሪያዉ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ወሊድ አል ሙአሊም ለጉባኤዉ እንደነገሩት ግን መንግሥታቸዉ ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ ከመጨረሻዉ መጀመሪያው  ላይ ይገኛል።የመንግስታቸዉ ድል እዚሕ አዳራሽ ዉስጥ ያላችሁ ያሏቸዉን መንግሥታት እንደሚያበሳጭ አስታዉቀዋልም።በዩናይትድ ስቴትስ የሚመሩ መንግስታትን ተቃራኒ አቋምንም ወርፈዋል።

                                             

«በዓለም አቀፍ ሕግ የተከበረልንን እና አሸባሪነትን የመዋጋት ብሔራዊ ኃላፊነታችን በገዛ ሐገራችን እንዳንወጣ እና ሕዝባችንን ከጥቃት እንዳንከላከል የአንዳድ ሐገራት መንግሥታት አግደዉናል።እነዚሁ መንግሥታት በዩናይትድ ስቴትስ መሪነት ሶሪያ ዉስጥ አሸባሪነትን እንዋጋለን የሚል ሕገ-ወጥ ማሕበር መስርተዋል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተመሠረተ በጥቂት አመታት ዉስጥ ካሳላፈቸዉ ዉሳኔዎች ትልቁ ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት ለሁለት እንዲገመስ መወሰኑ ነበር።1947።በዉሳኔዉ መሠረት በአንደኛዉ ገሚስ እስራኤል በተቀረዉ ፍልስጤም የየራሳቸዉ መንግስት መመስረት ነበረባቸዉ።ፍልስጤሞች ዛሬም ነፃነት ይላሉ።71ኛ ዓመታቸዉ።

Benjamin Netanjahu UN Vollversammlung
ምስል Getty Images

                               

«እየሩሳሌም አትሸጥም።የፍልስጤም ሕዝብ መብት ለድርድር አይቀርብም።እስራኤል እና ፍልስጤምን ለማደራደር አዉሮጳ፤አሜሪካ፤አፍሪቃ፤የአረብ ሐገራት ሌሎችም ሐገራት የአራትዮሽ (ቡድንን) መቀየጥ ይችላሉ።ዩናይትድ ስቴትስ ግን አትሆንም።አትሆንም።ምክንያቱም ለእስራኤል በጣም ያዳላሉ።»

የፍልስጤም ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ።አባስ ለፍልስጤሞች ነፃነት ላነሱት ጥያቄ የእስራኤሌ ጠቅላይ ሚንስትር የሰጡት መልስ አባስ ለዶክትሬት ዲግሪያቸዉ ማሟያ ባዘጋጁት ፅሁፍ ሆሎኮስትን ክደዋል የሚል ነበር።

ሶሪያ፤የመን፤ ሊቢያ፤ ፍልስጤም-እስራኤል፤ ምያንማር-ሮሂንጂያ ሠላም የለም። ዩናይትድ ስቴትስ-ቻይና፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን-፤ ሩሲያ-ዩናይትድ ስቴትስ፤ ዩናይትድ ስቴትስ አዉሮጳ፤ አዉሮጳ-ሩሲያ  የጋራ መርሕ የለም። ዋና ፀሐፊ  አንቶኒዮ ጉተሬሽ በጉባኤዉ መክፈቻ እንዳሉት ዓለም መተማመን የጠፋባት፤መደማመጥ የከሰመባት፤ ሥጋት እና ጥርጣሬ የሰፈነባት ሆናለች።

                                           

«ዓለማችን ከፍተኛ በሆነ የመተማመን እጥረት እየተሰቃየች ነዉ።ሕዝቦች በመኖር ዋስትና እጦት ሥጋት ይሰቃያሉ።ደሕንነት እይሰማቸዉም።መተማመን ጨርሶ ከሚጠፋበት ደረጃ ላይ ነዉ።በብሔራዊ ተቋማት፤በመንግሥታት መካከል፤ በዓለም ዓቀፍ የሕግ ሥርዓት ላይ እምነት የለም።»

ግን ጉተረሽ እንዳሉት በምሥቅል፤ ሥጋት ጥርጣሬዉ መሐል ከወደ አፍሪቃ ቀንድ የተስፋ ጭላንጭል በርቋል።የተስፋ ነፋስ ብለዉታል እሳቸዉ።

«በዓለማችን ትምርምስ እና መሳከር ቢያይልባትም፤የተስፋ ብርሐን ሲነፍስ ይታየኛል።ከጥቂት ቀናት በፊት ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታሪካዊ ሥምምነት ሲፈራረሙ አይቻለሁ።ከዚያ በኋላ የኤርትራ እና የጅቡቱ ፕሬዝደንቶች የሠላም ድርድር ለመጀመር ጄዳ-ዉስጥ ተስማምተዋል።ኤርትራ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል።እዚያዉ አካባቢ የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት በኢጋድ አማካይነት የሰላም ዉል ተፈራርመዋል።»

USA Rohani vor der UN-Vollversammlung
ምስል Reuters/E. Munoz

ተስፋ ነዉ።በጉባኤዉ ላይ ከመቶ የሚበልጡ ሐገራት በነግስታት፤ በርዕሠ-ብሔራት ወይም በመራሔ መንግሥታት ተወክለዋል።ትኒሺቱ ሐገር ኒዉዚላንድ ግን በጠቅላይ ሚንስትሯ ብቻ አይደለም የተወከለችዉ።በሰወስት ወር ሕፃኗም ጭምር እንጂ።ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርደረም ወደ ኒዮርክ የሔዱትን የ3 ወር ሕፃን ልጃቸዉን አቅፈዉ፤ የልጅቱን አባት ወይም ፍቅረኛቸዉን አስከትለዉ ነዉ።የጉባኤዉ አስተናጋጆች ለሰወስት ወሯ ሕፃን «የኒዉዚላንድ ቀዳማዊት ሕፃን» የሚል መታወቂያ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ