1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሿሚ ሴት ባለስልጣናት ፈተናዎች

ዓርብ፣ ጥቅምት 16 2011

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲስኩር ውስጥ የእኩልነት ጉዳይ ደጋግሞ የሚነሳ ቢሆንም፣ የፆታ እኩልነት ጉዳይ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ተደርጎ አይታይም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹ አዳዲስ ፖለቲካዊ ሹመቶች ግን ይህንን አጀንዳ ወደ ላይ ያመጣው ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራርም አዲስ ዘይቤ እየተከተለ እንደሆነ አሳይቶበታል፡፡ 

https://p.dw.com/p/37F4y
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ካቢኔ ቁጥሩ ወደ ሀያ ዝቅ ሲል የእያንዳንዱ ምኒስትር መሥሪያ ቤት ሥራ እና ኃላፊነት መጠን በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡ በአዲሱ ሹመት መሠረት የሚኒስትሮች ካቢኔው የፆታ እኩልነትን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑ፣ ይህንን የኃላፊነት መጠን መጨመር፣ ወንዶቹም ሴቶቹም ሚኒስትሮች በጋራ የሚሸከሙት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ጽሑፍ በተለይ የሚመለከተው ሴት ሚኒስትሮቹ በፆታቸው ብቻ ሊገጥማቸው የሚችለውን ፈተና ነው፡፡

ከፈተናዎች ሁሉ የሚከብደው የአንዳቸው ስኬታማ አለመሆን የሁሉም ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ ነው፡፡ ከሹመቱ በኋላ በብዙ ውይይቶች እየተደመጠ ያለው ስጋት ይኸው ነው፡፡ በፆታዊ ተዋረድ በተዋቀረ ስርዓተ ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የተቆጣጠረች አንዲት ሴት ሚኒስትር ስህተት ብትሠራ፣ በተመሳሳይ መንገድ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያለ ወንድ ባለሥልጣን ስህተት ሲሠራ እንደሚታየው ብቻ ተደርጎ የመወሰድ ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ስህተቱ ሴት ከመሆኗ ተነጥሎ የመታየት ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ 
ሴት ሚኒስትሮቹ እና ትዕምርታዊ ሹመታቸው ወይም ስኬታቸው ለታዳጊዎች ተምሳሌት ይሆናል ተብሎ እንደሚታሰበው ሁሉ፣ የሴቶቹ ስኬታማ አለመሆንም እንዲሁ አሉታዊ የተምሳሌትነት ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ሴቶቹ ላይ የእዚህ ስጋት ጫና እና ግፊት በሠራቸው ላይ ተደርቦ መቅረቡ አይቀርም፡፡ 

ሌላኛው ሴት ሚኒስትሮች የሚገጥማቸው ፈተና ከበታች ሠራተኞቻቸው እና ከማኅበረሰቡ ዘንድ፣ ለኮታ የተቀመጡ እንጂ እውነተኛ ሥልጣን ተቆጣጥረው ሕዝብ እንደሚያገለግሉ አለመታየታቸው ነው፡፡ ይህንን ስጋት በተመለከተ የቀድሞዋ ሚኒስትር ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ከልምዳቸው በመነሳት ደጋግመው ገልጸውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ የብሔር ውክልና እና ኮታ በሹመቶች መታየቱ ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ በሚቆጠርበት የአገራችን የፖለቲካ ዲስኩር ውስጥ የሴት ሚኒስትሮች ሹመት የሚወክለው ሴቶችን በጥቅሉ እንጂ የመጡበትን ብሔር ወይም የአካባቢ ማኅበረሰብ ተደርጎ አይደለም፡፡

ከዚህም በላይ በብሔር ኮታ የሚወከሉት ሹመኞች ላይ የሚጣለውን ያክል እምነት በሴቶቹ ላይ አይጣልባቸውም፡፡ አሁንም ይህ የፆታ እኩል ውክልናን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሹመት ከተነገረ ዕለት ጀምሮ የሚሰሙት ትችቶች ስጋቱን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉ አስተያየት ሰጪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በእጅ አዙር ለመጠቅለል የሴቶችን ሹመት የተጠቀሙ አድርገው ገልጸውታል፡፡ ሴቶቹ ሚኒስትሮቹ ይህንን እምነት መዋጋት ሌላኛው ፈተናቸው ነው፡፡ 

የስርዓተ ፆታ እኩልነት ጥያቄ
በመንግሥታዊ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የመወከል ጉዳይ አንዱ የሥርዓተ-ፆታ ማስተካከል ጉዳይ ቢሆንም፣ ብቸኛው ጥያቄ ግን አይደለም፡፡ የሴት ሚኒስትሮቹን ሹመት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደጉ የመጡ የሴቶች የእኩልነትና የመብቶች ጥያቄዎችን “አፍ ማዘጊያ”አድርገው የሚወስዱት ሰዎች አይጠፉም፡፡ የሚኒስትሮቹ ሹመት በተለይ ትዕምርታዊ መገለጫነቱ ከፍተኛ ይሁን እንጂ ዋናው ችግር የሚገኘው ብዙኃኑ የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ ባለው ስርዓተ ማኅበር ውስጥ ነው፡፡

የሴቶቹ ሹመት ታዳጊዎች ምሳሌ እንዲያገኙ ይሆናል እንጂ በየቤታቸው፣ በባሕሉ ውስጥ፣ በትምህርት ቤት እና በሌሎችም ቦታዎች የተጋረጡት የስርዓተ ፆታ ማኅበሩ ችግሮች አሁንም አሉ፡፡ ሚኒስትሮቹ ይህንን በማስተዋል ሹመታቸው የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ጥያቄዎችን ወይም ንቅናቄዎችን ማፈኛ እንዳይሆን፣ ይልቁንም ሴቶች ላይ የሚደርሰው ማኅበራዊ የፆታ መድልዕዎን ለመቅረፍ ብዙ መጓዝ እንደሚጠይቅ ደጋግመው መግለጥ እና ማጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡   

ተተኪ የማብቀል ፈተና
የሚኒስትሮቹ ሹመት ዜና በተሰማ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የ55 ሚኒስትር ዲኤታዎቻቸው ሹመት ፀድቋል፡፡ የሴት ሚኒስትር ዲኤታዎቹ ቁጥር ከጠቅላላው አንድ አምስተኛ እምብዛም አይበልጥም፡፡ ይህ ጉዳይ የሚያመለክተው የስርዓተ ፆታ ውክልና ጥያቄ በመንግሥት መዋቅር የታችኛው እርከን ውስጥ ገና ምኑም እንዳልተነካ ነው፡፡ ስለሆነም የአሁኑ የሚኒስትሮች ካቢኔ በቀጣዮቹ ግዜያትም የፆታ ውክልናውን ይዞ እንዲቀጥል እና ሴቶቹ ሚኒስትሮች በእንዲህ ዓይነቱ ካቢኔ ውስጥ የመጀመሪያዎቹም፣ የመጨረሻዎቹም እንዳይሆኑ ተተኪ የማብቀል ሥራ በሰፊው መሠራት አለበት፡፡ የእዚህ ኃላፊነት የሁሉም ሚኒስትሮች የጋራ ኃላፊነት ቢሆንም ሴቶቹ ላይ እንደሚበረታ መገመት ቀላል ነው፡፡  

ሴቶቹ ሚኒስትሮች ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎችንም ፈተናዎች መጋፈጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ሴት በመሆናቸው ብቻ ስለሴት ብቻ እንዲሠሩ የሚጠብቋቸው ሰዎችም ይኖራሉ፡፡ ሆኖም እነዚህን ሁሉ ስርዓተ ፆታ አመጣሽ ሸክሞች ብቻቸውን እንዲሸከሙ መጠበቅ አግባብ አይሆንም፡፡ እንደመፍትሔ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች እና ንቅናቄዎች የሴት ሚኒስትሮቹን ከወንዶቹ በተለየ ለመንታ ምዘና የሚዳርጋቸውን ሸክም የመጋራት እና ሕዝባዊ አመለካከቶቹን የማስተካከል ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።