1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2010

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሊቀ-መንበሩ ልሳን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት «እኛ ነን አሸባሪ» ብሎ ሲናገር የተቃዋሚ ድርጅቶች ትግል እና ጩኸት ፍሬ አፍርቶ መንግሥታዊ ዕውቅና ማግኘቱን ስለሚያበስር ድርጅቶቹ እና አባሎቻቸው በድላቸው መደሰት ይገባቸዋል።

https://p.dw.com/p/30yJa
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

ከአንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ጋር በወቅታዊ የፖለቲካ ሒደቶች ጉዳይ እየተወያየን ነበር። ድንገት በቁጭት እንዲህ አለኝ «አሁንማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኛን ድምፅ ቀምተው የራሳቸው አስመስለውታል»። ይህንኑ ሲያስረዳኝ እንዲህ አለ «ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቀድሞ ተቃዋሚ (እርሳቸው ‘ተፎካካሪ’ ነው የሚሏቸው) የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ የነበሩትን በሙሉ በማንገብ በፖለቲካ አመለካካት ልዩነት የሚፈፀም እስርን፣ ሙስናን፣ አፋኝ አዋጆችን፣ ወዘተ በመቃወማቸው ምክንያት የተቃዋሚውን ድምፅ የራሳቸው አስመስለዋል።» ይህ አረዳድ የብዙ የተቃዋሚ ድርጅቶች ግንዛቤ እንደሆነ አስተውያለሁ። እንደ እውነቱ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ የተቃዋሚ ድርጅቶች ድል ተደርጎ ነበር መወሰድ ያለበት።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ «የፖለቲካ እስረኛ የለኝም፤ የማሰቃየት ተግባር ፈፅሜ አላውቅም» ይል የነበረው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሊቀ-መንበሩ ልሳን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት «እኛ ነን አሸባሪ» ብሎ ሲናገር የተቃዋሚ ድርጅቶች ትግል እና ጩኸት ፍሬ አፍርቶ መንግሥታዊ ዕውቅና ማግኘቱን ስለሚያበስር ድርጅቶቹ እና አባሎቻቸው በድላቸው መደሰት ይገባቸዋል። ነገር ግን እነርሱ በዚያ መንገድ የተረዱት አይመስልም። የቀድሞ ጩኸቶቻቸው የፖለቲካ እና ሲቪክ ምኅዳሩ በመጥበቡ ምክንያት የመጡ እንደመሆናቸው፣ በትግላቸው የመንግሥት አካል ‹ድክመቶቼ ናቸው› በሚል ከተቀበላቸው በኋላ ይህንን እንደድል በመቁጠር ፈንታ፣ «ድምፃችንን ተቀማን»፣ «የድል ባለቤትነታችን አልታወቀልንም» በሚል እየተብሰለሰሉ ኃይላቸውን ማባከን የለባቸውም፡፡ ይልቁንም አማራጮቻቸውን ይዘው በመቅረብ የወቅቱ ፖለቲካ የሚጠይቀውን ጨዋታ መጫወት ይጠበቅባቸዋል። ያለፈውን የፖለቲካ-ተከላካይነት የትግል ምዕራፍ ተሻግሮ ወደፊት ለመራመድ አለመቻል፣ ከፊታቸው የተጋረጠ የመጀመሪያው ፈተናቸው ነው።

 

የተሻለ አማራጭ የመስጠት ፈተና

ገዢው ፓርቲ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታዊ ተቋማትን በመቆጣጠሩ፣ የገንዘብ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ እንዲሁም ከዚህ በፊት የመደራጀት ፈተና ስላልነበረበት፣ በመዋቅርም በተዳራሽነትም ከተቃዋሚ ድርጅቶች የበለጠ አደረጃጀት ከላይ እስከ ታች አለው። ኢሕአዴግ ከአባላቱ ውጪ  የደጋፊ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ነጋዴዎች ወዘተ ሊጎች አሉት። በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ እና አልፎ አልፎም በራሳቸው ድክመት የጠራ ርዕዮተ ዓለም፣ ጥሩ መዋቅር እና ብዙ አባላት የላቸውም።

ስለሆነም፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከዚህ በፊት “በፖለቲካ ልዩነት መግደል፣ ማሰር እና ማሳደድ ይቅር” በሚል ሲሟገቱ ያገኙ የነበረውን ያክል ድጋፍ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ሲቀሩ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። ይልቁንም ለአገሪቱ መልከ-ብዙ ችግሮች አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔዎችን በማቅረብ ራሳቸውን መሸጥ አለባቸው። ይህ ዓይነቱን አካሔድ ለመቀበል በመንፈስም፣ በኢኮኖሚያዊ አቅምም ሳይዘጋጁ ነገሮች በፍጥነት መለዋወጣቸው ግራ ያጋባቸው ይመስላል። በአሁኑ ወቅት፣ በተለይ ክልላዊ የተቃዋሚ ድርጅት ሰዎች ከክልላቸው ገዢ ፓርቲ የበለጠ ብሔርተኛ እና ለክልላቸው ሕዝብ ከሌላው የበለጠ አድሎኛ በመምሰል ደጋፊ ለማፍራት ወይም የተወሰዱባቸውን ለማስመለስ እየተፍጨረጨሩ ነው። ይህ አካሔድ ከዚህ በፊት አረና ትግራይ ከሕወሓት የበለጠ መሆኑን ለማሳየት የተጠቀመበት የትርክት አካሔድ ሲሆን፣ አሁን የኦፌኮ (ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ) አመራሮችም በዚሁ አካሔድ የተጠመዱ ይመስላል። በቅርቡ የተቋቋመው አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) ከብአዴን ለመብለጥ ተመሳሳይ አካሔድ መርጧል።

 

ክልላዊ ትብብሮች እና የኅብረ-ብሔር ድርጅቶች ፍጥጫ

የወቅቱ ፖለቲካ መለዋወጥ ከተለመደው ውጪ ክልላዊ ድርጅቶች ልል ትብብር እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። በተለይ ኦሕዴድ ከኦፌኮ እንዲሁም በቅርቡ ወደ አገር ቤት የገባው ኦዴግ (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) የትርክት መግባባት እያሳዩ ነው። የፌዴራል መንግሥቱን የሚመለከቱበት መንገድ እና የወቅቱ ፖለቲካ ፈተና ነው ብለው የሚያምኑት ጉዳይ ላይ የጎላ ልዩነት የላቸውም። በሕዝቡ በኩልም ተባበሩ የሚል ግፊት አለባቸው። በተመሳሳይ መንገድ አረና ትግራይ እና ሕወሓት ታይቶ የማይታወቅ ሐሳባዊ ምስስሎሽ እያሳዩ ነው። ይህ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ከዋና ከተማዋ ተሻግረው በክልሎች ለማግኘት ለሚፈልጉት ድጋፍ ፈተናውን ከበፊቱ የበለጠ ያከብድባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ይህ አዝማሚያ ቀደም ሲል በተፈጠረው የብሔርተኛ ድርጅቶች ስብስብ፣ መድረክ  አባላት መካከል የፉክክር ስሜት መጨመሩ አይቀርም።

 

የድምፆች መከፋፈል

ተቃዋሚዎች የተጋረጡባቸውን ፈተናዎች በድል ተወጥተው ለሚቀጥለው አገር ዐቀፍ ምርጫ ከደረሱ የድምፅ መሰንጠቅ ፈተና ይገጥማቸዋል። ኅብረ-ብሔር የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በብሔር ከተደራጁት ተቃዋሚዎች እና ከክልላዊ ገዢ ፓርቲዎች ጋር ለፉክክር ይቀርባሉ። ክልላዊ ገዢ ፓርቲዎች የተቀባይነታቸው ደረጃ ከበፊቱ የጨመረ ከመሆኑም በላይ፣ ከገዢው ፓርቲ የሚተርፈው እና ለተቃዋሚ ድርጀቶች የሚደርሰው ድምፅ በብሔርተኞቹ እና በኅብረ-ብሔርተኞቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ይሰነጠቃል። ይህም ከወዲሁ የሚቀጥለው ምርጫ ነጻ እና ፍትሐዊ ቢሆን እንኳ አሸናፊ ማን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ እየሰጠ ነው።

በተጨማሪም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተደራሽነት ከዋና ከተማይቱ ውጪ በአራቱ ክልሎች ማለትም - ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች የተወሰነ ነው። በቀሪዎቹ ክልሎች ውስጥ ያላቸው ሕዝባዊ መሠረትም ይሁን መዋቅር እዚህ ግባ የማይባል ነው። ኢሕአዴግ ግን ከአራቱ ክልል ውጪ ያሉትን ክልሎች ገዢ ፓርቲዎች በአጋርነት ይዟል። በቀጣዩ ምርጫ ራሱን በማደስ አጋር ድርጅቶቹን አባል ሊያደርጋቸው እንደሚችል ከዚህ በፊት የድርጅቱ አመራሮች ፍንጭ ሰጥተዋል። ይህ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ፈተና ያበረታዋል። ይሁን እንጂ ተቃዋሚ ድርጅቶቹ ለዚህ የተዘጋጁ አይመስልም።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃዋሚዎች በአጭር ጊዜ ዝግጅት ገዢውን ፓርቲ የሚነቀንቁበት አጋጣሚ የተከሰተው በምርጫ 1997 ነው። ብዙ ተቃዋሚዎች ለ2012ቱ ምርጫ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ቅድመ ምርጫ 1997ን ያክል ከሆነ በቂ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ በነጻ እና ርትዓዊ ሁኔታም ቢወዳደሩ እንኳን ገዢው ፓርቲ በውስጡ ያለውን መከፋፈል ካላባባሰው በቀር፣ በውድድሩ ቀድሞ የጀመረ ሯጭ ዓይነት ያሸናፊነት ዕድል አለው።

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ