1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት የአዳጊ አገሮች ስብሰባ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2015

«ቃል ሁልግዜም ይገባል ለምሳሌ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወይም ድህነትን ለማስወገድ፣ ክትባቶችን ለማምረት ሊሆን ይችላል። ግን ተግባራዊ ለማደረግ ቁርጠኘነት አይታይም።»

https://p.dw.com/p/4OMM3
Katar, Doha | UN LDC5 Konferenz
ምስል Amiri Diwan of the State of Qatar/Handout/AA/picture alliance

የተባበሩት መንግስታት የአዳጊ አገሮች ስብሰባ

ካለፈው እሑድ ጀምሮ እየተካሂደ ያለው ጉባኤ የድሆቹን አገሮች መሪዎች ጨምሮ የሌሌችንም  በርካታ አገሮች መሪዎች፤ አለማቀፍ ድርጅቶች፤ የግሉ ዘርፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ የተሳተፉበት ሲሆን፤ የስብሰባው አስተናጋጅ አገር ቀጠር  አሚር ሼይክ ታሚን ቢን ሃማድ አል ታኒ ስብሰባውን በንግግር ከፍተዋል። ሼክ ታሚን ቢን ሀማድ አል ታኒ በንግግራቸ፤ በሶሪያ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተስጠው ምላሽ መዘገየቱ ያስገረማቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለፖለቲካ አላማ ለማዋል መሞከር ተቀባይንት ሊኖረው እንደማይገባ አሳስበዋል።  
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር፤ የእነዚህን 46 አገሮች የችግር ስፋትና የድህነት መጠን እንዲሁም ከችግሮቻቸው ለመውጣት ማነቆ የሆኑባቸውን የዓለም የፋይናንስና ግብይት ስርአቶች ፣በመዘርዘር፤ የስርአት ለውጥ የሚያስፈግ መሆኑንና ያደጉ አገሮች ለበለጠ እርዳታ አዲስ ተሳነሽነት ሊያሳዩ የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል። ጉተሬዥ፤ የዓለም ፋይናንስ ስርዓት ለሀብታሞቹ አገሮች በሚጠቅም ሁኔታ እንጂ ለድሆቹ አገሮች በሚበጅ ሁኔታ የተቀየሰ አለመሆኑን ሲገልጹም፤ «ሁሉም የዓለም የፋይናንስ ስርአቶች በሀብታሞቹ አገሮች የተቀየሱና ለነሱ ጥቅም ብቻ የተዘጋጁ ብቻ ሲሆኑ ይልቁንም ድሀዎቹን አገሮች ከበለጸጉት አገሮች እስከ ስምንት እጥፍ ወለድ የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል። በዚህ የተዛባ የፋይናንስ ስርአትና ከፍተኛ የወለድ መጠን ምክኒያትም አገሮች ያላቸውን ሀብት ለልማት ሳይሆን ብድር ለመክፈል እንዲያውሉ መገደዳቸውንም ገልጸዋል። « ዛሬ 25 የሚሆኑ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ኢኮኖሚ  ብንወስድ 20 ከመቶ የሚሆነውን ኢኮኖሚያቸውን  ለብድር  ነው የሚከፍሉት» በማለት ያለው የፋይናንስ ስርዓትና የብድር ወለድ መጠን አገሮቹን በልማት እንዲለወጡ ሳይሆን ባሉበት እንዲቆዩ ወይም ከነበሩበት እንዲወርዱ ኣያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  
ዋና  ጸሐፊው ከእንግዲህ ከዚህ አዙሪት ለመላቀቅ ትኩረት ሊደረግባቸውና ሊተገበሩ ያሏቸውን ሀሳቦችንም ለጉባኤው አቅርበዋል ። 
ያደጉ አገሮች ድሀዎቹን ለመርዳት ምንም አይነት ምክንያት ማቅረብ እንደማይኖርባቸው በማሳሰብም አስፈላጊውን የልማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የዓለም አቀፍ የገንዘብና የብድር ስርአት እድገትን ለማፋጠንና ለማሳለጥ በሚበጅ ሁኔታ እንዲሻሻልና ለአየር ንብረት ለውጥ መቁቋሚያ ሀብታሞቹ አገሮች ሊሰጡት የሚገባውን ገንዘብ በወቅቱ እንዲከፍሉና ሀብታሞቹ አገሮች ለድሀዎቹ አገሮች ለመስጠት ቃል የገቡትን ማክበር የሚገባቸው ግዜም አሁን መሆኑን አስታውቀዋል። ያደጉ አገሮች ለታድጊ አገሮች ከጣቃላይ ገቢያቸው ከ0.15 እስከ  0.20 ከመቶ ለመርዳት የገቡትን ቃል ያለምንም ምክንያት ሊያከብሩ እንደሚገባ በማሳሰብ።  
የታዳጊ አገሮች መሪዎችና ተወካዮች በበኩላቸው በዓለም ላይ ያለው የተዘባ ስርዓትና የበለጸጉት አገሮች ስግብግብነት በሀብታቸው እንኳ እንዳያድጉና  ህዝባቸውን ከችግር እንዳያላቅቁ እንዳደረጋቸው አምርረው ሲናገሩ ተሰምቷል።  
ከዚህ ጉባኤ ብዙ ቢጠብቁም፤ የዋና ጸሐፊው ጥሪም ሆነ የታጊዎቹ አገሮች ጩኸት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ግን ብዙዎች ይጠራጠራሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት  ምዕራባውያኑ እራሳቸው በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በክፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ በመሆናቸው፤ ማናቸውንም የኢኮኖሚ እርዳታ ጥሪ መስማት አይፈልጉም ነው የሚባለው።
 የኢንቨስትመንትና የድርድር ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ጃን ናሉንጋ ይህንኑ አስተያየት ሲያጠናክሩ፤ ወትሮውንም ቢሆን ይላሉ፤« ቃል ሁልግዜም ይገባል ለምሳሌ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወይም ድህነትን ለማስወገድ፣ ክትባቶችን ለማምረት ሊሆን ይችላል። ግን ተግባራዊ ለማደረግ ቁርጠኘነት አይታይም» በማለት ይህ ጉባኤም እንደተለመደው ችግሮች የሚወሱበትና ቃል የሚገባበት ከመሆን አልፎ ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ መሆኑን እንድሚጣራጠሩ ገልጸዋል። 
ገበያው ንጉሤ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ

የተመድ ዋና ፀኃፊ በአዳጊ ሐገራት ስብሰባ ላይ
የተመድ ዋና ፀኃፊ በአዳጊ ሐገራት ስብሰባ ላይ ምስል Karim Jaafar/AFP/Getty Images
የአዳጊ አገሮች ስብሰባ
የአዳጊ አገሮች ስብሰባምስል Karim Jaafar/AFP/Getty Images