1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ እና የኮንጎ ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 7 2010

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ በዚህ ሳምንት በዚችው አፍሪቃዊት ሀገር  ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረት ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/31QZM
Kongo DRK UN-Soldaten der Mission MONUSCO
ምስል DW/Flávio Forner

የተወሳሰበው የተመድ እና የኮንጎ ግንኙነት

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ በዚህ ሳምንት በዚችው አፍሪቃዊት ሀገር  ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረት ፈጥሯል። ጉተረሽ ከአፍሪቃ ህብረት ሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽን  ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ባንድነት በመሆን ከኮንጎ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ከብዙ ጊዜ ጀምረው ፍላጎት ቢያሳዩም እና እቅድ ቢይዙም ፕሬዚደንት ካቢላ በተለያዩ ምክንያቶች ሰሞኑን እንዳደረጉት የከፍተኞቹን ዲፕሎማቶች ጉብኝት ለሌላ ጊዜ ገፍተዋል። ካቢላ በውጭ ጉዳዮች አማካሪ ኪካያ ቢን ካሩቢ አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ጉብኝቱ የተሰረዘው የሀገሪቱ ከፍተኛ  ባለስልጣናት በጠቅላላ የፊታችን ታህሳስ ወር የሚካሄደውን ምርጫ በማዘጋጀት ላይ በመሆናቸው ነው።
የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚገምቱት፣ ሁለተኛው እና የመጨረሻው የስልጣን ዘመናቸው ባለፈው ታህሳስ 20፣ 2016 ዓም በይፋ ያበቃው ፕሬዚደንት ካቢላ የሳቸው ተተኪ ይመረጥበታል ተብሎ ስለታቀደው መጻዒ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከጉተረሽምም ሆነ ከማሃማት የሚነሳ ጥያቄን ለማስወገድ ነው የሞከሩት።  ምክንያቱም፣ ጉተረሽ እና ማሀማት ካቢላ በቀጣዩ ምርጫ እንደማይወዳደሩ በይፋ ቃላቸውን እንዲሰጡ መጠየቅ አይፈልጧቸው ሊጠይቋቸው ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።  
 የኮንጎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚሉት፣ ካቢላ፣  ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ ባይፈቅድም፣ እንደገና በዕጩነት የመቅረብ ሀሳብ አላቸው  ።  የኮንጎን ፖለቲካ የሚከታተሉት የማዕከላይ አፍሪቃ አኩሜኒካል መረብ ባልደረባ ጌዚኔ አመስም ካቢላ ስልጣን የመልቀቅ ሀሳብ የላቸውም ባይ ናቸው። 
« ካቢላ የውጭ ዲፕሎማቶችን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው  እና ስለመጪው ምርጫ ለመነጋገር አለመፈለጋቸው  በጣም አሳሳቢ ነው። መልስ ያላገኘው ጥያቄ ካቢላ ለድጋሚ ምርጫ በተወዳዳሪነት ይቀርባሉ ወይ የሚለው ነው። »
የለንደን ዓለም አቀፍ ስልታዊ ጥናት ተቋም ተንታኝ ያኖሽ ኩልንበርግ ይህን የጌዚኔ አስተያየት ይጋራሉ።
«   ካቢላ ስልጣን እንደያዙ መቆየት ይፈልጋሉ። ይህን እንዴት እውን እንደሚያደርጉ ገና አይታወቅም። በዚህም የተነሳ የውጭ፣ ብሎም፣ የአፍሪቃ ህብረትንም ሆነ የተመድን ጣልቃ ገብነት ለማሳነስ ነው የሚጥሩት። ከተመድ ወይም ከአፍሪቃ ህብረት ጋር የተያዙ ቀጠሮዎችን መሰረዝም ይህን ጥረታቸውን ለማሳካት ያስችሏቸዋል።»
የተመድ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ በቀጣይነት ያቀረበው ወቀሳ  ካቢላ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ ጉብኝትን የሰረዙበት ሌላው ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል።
« የተመድ በሀገሪቱ የሚታየውን የጦር ወንጀል በቅርብ  እንዲቆጣጠር አይፈልጉም። ምክንያቱም ብዙውን የመብት ጥሰት  የሚፈጽመው  ራሱ የኮንጎ  ጦር  ነው። ይህ እንዳይጋለጥ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ ይፈልጋሉ። » 
የተመድ ጠበብት ከጥቂት ጊዜ በፊት ያወጡት 126 ገጾች ያሉት ዘገባ በኮንጎ የካዛይ ግዛት ከ2016 ዓም ወዲህ በካሙዊና ምሳፑ ዓማፅያን   ለመንግሥት ቅርብ ከሆነው የባና ሙራ ሚሊሺያ ቡድን እና ከኮንጎ ጦር  ጋር በሚያካሂዱት ውጊያ   ከባድ የመብት ጥሰት  መፈጸሙን አጋልጧል። በዚሁ የመብት ጥሰትም ላይ ሁሉም ተቀናቃኞቹ ወገኖች፣ የመንግሥት ወታደሮች ጭምር ተጠያቂ መሆናቸውንም ነው ዘገባ ው ያመለከተው።
የኮንጎ መንግሥት እና ፖሊስ ዘገባውን ሀሰት በሚል አስተባብለዋል። በአንጻራቸው  ጌዚኔ አመስ የተመድ ጠበብት ያካሄዱትን ምርምር የሚታመን  ብለውታል። ይሁንና፣ የጠበብቱ ቡድን ዘገባ ሳይወጣ በፊትም ቢሆን የተመድ እና የኮንጎ መንግሥት ግንኙነት ውጥረት እንደታየበት ያኖሽ ኩልንበርግ ገልጸዋል። ካቢላ ባለፈው ጥር ወር በሰጡት አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ  ወቅት በሀገራቸው በተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ቡድን ፣ በምህጻሩ ሞኑስኮ ላይ ጠንካራ ወቀሳ በመሰንዘር ፣ ጓዱ ቢዘገይ እስከ 2020 ዓም ድረስ ኮንጎን ለቆ እንዲወጣ መጠየቃቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባት ማስከተሉ ቢታወስም፣ እንደ ያኖሽ  ኩልንበርግ አስተያየት፣  የኮንጎው ፕሬዚደንትና መንግሥታቸው ከተመድ ተልዕኮ ተጠቃሚ  ናቸው።
« ካቢላ እና አማካሪዎቻቸው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ስምሪትን ለራሳቸው ጥቅም እንደሚያውሉት አውቀውበታል። ከጥቅሞቹ የ2006 እና የ2011  ምርጫዎችን ማዘጋጀት እና በገንዘብ መርዳት   ይጠቀሳል። የኮንጎ መንግሥት መስጠት ያለበትን  አገልግሎት የተመድ  ከብዙ አሰርተ ዓመት ወዲህ በመሸፈን ላይ ይገኛል። የተመድ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ፣ ሞኑስኮም ካቢላን በምሥራቃዊ ኮንጎ ከሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን የመከላከል ስራ እንደሚሰራ ተጨማሪ ጦር ያገለግላል። በርግጥም፣ ካቢላ የተመድን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላቱ ተግባር መጠቀሙተሳክቶላቸዋል። »
17,000 ወታደሮችን የያዘው ሞኑስኮ 1,15 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር ዓመታዊ በጀት የተመደበለት በዓለም ትልቁ የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ነው፣ በመሆኑም፣ የተመድ  ከኮንጎ መንግሥት ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መድረስ አይፈልግም። እንደሚታወሰው፣ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ የጓዱን ተልዕኮው ባለፈው መጋቢት ወር በአንድ ዓመት አራዝሞታል። 
የተመድ ጓድም የኮንጎን ሲብል ህዝብ ደህንነት ማስጠበቅ እና የታህሳሱ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መካሄድን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ማድረጉን የሞኑስኮ ቃል አቀባይ ፍሎረንስ ማርሻል አስታውቀዋል። 
« የኮንጎ መንግሥትን የመደገፍ ስራችንን እንቀጥላለን። ሞኑስኮ ከብዙ ዓመታት ወዲህ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በመዲናይቱ ኪንሻሳ ከሚገኘው  መንግሥት ጋር ያለን መደበኛ ግንኙነት አለው። »
ከተመድ ጋር የተፈጠረው ዲፕሎማቲካዊ ውዝግብ እንዳይባባስ  ፍላጎት መኖሩን ነው የፕሬዚደንት የቅርብ አማካሪ ዦን ፒየር ካምኒላ ለዶይቸ ቤለ የገለጹት።
« የተመድ አባል ሀገር ነን። በሀገራችን ትልቁ የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተሰማርቷል። እና እንዴት ነው የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊን ወደ ሀገራችን እንዳይገቡ የታገዱ ሰው ናቸው ልንል  የምንችለው? » በማለት አንቶንዮ ጉተረሽ እና ሙሳ ፋኪ ማሀማት ወደ ኮንጎ ቢሄዱ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በደስታ እንደሚቀበሏቸው አስታውቀዋል። 

Angola Flüchtlingslager nahe Kakanda
ምስል DW/N. Sul d'Angola
Schweiz - UN-Generalsekretär in Genf
ምስል picture-alliance/Keystone/C. Zingaro
Joseph Kabila Präsident der Demokratischen Republik Kongo
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

አርያም ተክሌ/አንቶንዮ ካሽካሽ

ማንተጋፍቶት  ስለሺ