1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር ቀጣይ ዕጣ-ፈንታ ምን ይሆን?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2012

አሜሪካ በኢትዮጵያ በኩል የነበራትን እምነት አጥታለች የሚሉት ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን የአፍሪካ ኅብረት ወይም ደቡብ አፍሪካ አደራዳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠብቃሉ። የሕግና ጸጥታ ተመራማሪው ማይክል ሐና «ግብፅ ያላት የመደራደሪያ መሳሪያ እንደ አሜሪካ፤ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያሉ ኃይለኛ አጋሮቿ ያላቸው ተሰሚነት ነው» ብለዋል

https://p.dw.com/p/3Z6ml
BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Premierminister Abiy Ahmed Ali mit dem ägyptischen Präsident Abdel-Fattah al-Sisi (2018)
ምስል Imago Images/Xinhua

ድርድሩ መቼ እና እንዴት እንደሚቀጥል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም

የግብፁ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሳሜሕ ሽኩሪ የአረብ ሊግ ስብሰባ እንደተጠናቀቀ በጀመሩት ጉዞ ከመሪዎች ሲገናኙ ከሚያነሷቸው አበይት ጉዳዮች አንዱ አገራቸው ከኢትዮጵያ የምትወዛገብበት የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ እና ድርድር ሆኗል። ሽኩሪ በባግዳድ ከፕሬዝዳንት ባርሐም ሳሊህ፤ በቤሩት ከንጉስ አብደላ ሁለተኛ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ተገናኝተው ኢራቅ እና ሊባኖስ በአረብ ሊግ ስብሰባ ግብፅን በመደገፋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሳሜህ ሽኩሪ የሚመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር የግብፅ ጥቅም እንዲከበር ኢራቅ እና ሊባኖስ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ጅቡቲ እና ሶማሊያን ጨምሮ 22 አባል አገራት ያሉት የአረብ ሊግ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኢትዮጵያ "ከታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር ሚዛናዊ ስምምነት ላይ ሳትደርስ ታላቁን የኅዳሴ ግድብ በውኃ ለመሙላትም ሆነ ሥራ ለማስጀመር በተናጠል የምትወስደውን እርምጃ" የሚቃወም የውሳኔ ሐሳብ አፅድቋል። በግብፅ የተረቀቀው እና ያለ አንዳች ማሻሻያ የጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ «ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ታሪካዊ መብት ሊሸራረፍ አይገባም» ብሏል።

ከ75 አመታት በፊት የተመሠረተው እና በግብፃዊው አሕመድ አቡ ጋይት ዋና ጸሐፊነት የሚመራው የአረብ ሊግ የያዘው አቋም ግን አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን መቃቃር ሲያካርር ከሱዳን ለሌላ አተካሮ ዳርጓታል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው የካቲት 27  ባወጣው መግለጫ «የውሳኔ ሐሳቡ በግድቡ ድርድር ቁልፍ የሆኑ ሐቆችን ከግምት ሳያስገባ ለግብፅ ጭፍን ድጋፍ ሰጥቷል» ሲል ነቅፏል። ሱዳን የውሳኔ ሐሳቡ ውዝግቡን ከማጦዝ ይልቅ ሶስቱ አገሮች ድርድራቸውን እንዲቀጥሉ በሚያበረታታ መንገድ እንዲሻሻል ሐሳብ ብታቀርብም ግብፅ ምንም አይነት ማሻሻያ እንዲደረግ ባለመፍቀዷ የውሳኔ ሐሳቡን እንዳልደገፈች የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

BG Grand Renaissance Dam | Verhandlungsrunde (2019)
አዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ ካይሮና ዋሽንግተን የተካሔደው ድርድር መቼና እንዴት እንደሚቀጥል አይታወቅምምስል AFP/A. Shazly

አሜሪካ «ሥምምነት ሳይፈረም የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጨረሻ ሙከራ እና የውኃ ሙሌት ሊከናወን አይገባም» የሚል መግለጫ በግምጃ ቤቷ በኩል ካወጣች በኋላ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ልዩነት እየተካረረ ሄዷል። ኢትዮጵያ የአሜሪካን ማሳሰቢያ የግብፅንም አቋም በመቃረን «የግድቡን [የውኃ] ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት» አከናውናለሁ ብላለች። 

ድርድሩ ወዴት ያመራል?

ሶስቱም አገራት ለድርድሩ ቁርጠኝነታቸውን ቢገልጹም የተካረረ አቋማቸው እንዴት ሊቀራረብ እንደሚችል ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም። በስዊድን ኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ግጭት ጥናት ፕሮፌሰሩ አሾክ ስዌይን «አሜሪካ ከአድሎ የጸዳ ድርድር ማካሔድ ትችላለች ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ እንደዚያ አልተመለከተችውም። ድርድሩ ሲቀጥል ኢትዮጵያ አልተገኘችም። ኢትዮጵያ በድርድሩ ሳትሳተፍ የቀረችበት ወይም ስምምነቱን ያልፈረመችበት ምክንያት አላት። ስለዚህ የዚህ ድርድር እጣ-ፈንታ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ፈታኝ  ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

«አሁን ድርድሩ ፈታኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል» የሚሉት ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን «በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ በፈለገችው መንገድ ግድቡን ውኃ መሙላት ትችላለች ወደሚል ስምምነት ይመጣሉ ብዬ እጠብቃለሁ። አሁን በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል በውኃ ሳቢያ ጦርነት ይቀሰቀሳል ብዬ አላስብም» ብለዋል። 

በአሜሪካው ሴንቸሪ ፋውንዴሽን የሕግ እና ጸጥታ ተመራማሪው ማይክል ሐና «ግብፅ በአሜሪካ በቀረበው ምክረ-ሐሳብ ተስማምታ ፈርማለች። ግብፅ ያላት ዋንኛ የመደራደሪያ መሳሪያ እንደ አሜሪካ፤ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያሉ ኃይለኛ አጋሮቿ ያላቸው ተሰሚነት ነው። ይኸ ጠንካራ የመደራደሪያ አቅም አይደለም» ብለዋል።

ማይክል «የአሜሪካን ምክረ-ሐሳብ ውድቅ ያደረገችው ኢትዮጵያ ምርጫ ከመካሔዱ በፊት በመጪው ሐምሌ ግድቡን በውኃ ለመሙላት በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ እንደምትጸና ገልጻለች። ስለዚህ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጭምር ነው። ሱዳን በዚህ ድርድር ለኢትዮጵያ ወግና አልፈረመችም። ኢትዮጵያ ብትፈርም ሱዳንም ትከተላለች ብዬ አስባለሁ። ለግብጽ ብቸኛው አማራጭ አሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ያለ ስምምነት ውኃ መሙላት እንዳትጀምር የሚያሳድሩት ጫና ነው» ሲሉ አስረድተዋል። 

Karte Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre EN
ግንባታው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካለፈው ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሆነበት የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል

የአሜሪካ ሚና ምንድነው?

ድርድሩን "በታዛቢነት" ተቀላቅላ ለሶስቱ አገሮች የስምምነት ምክረ-ሐሳብ ወደ ማዘጋጀት የተሻገረችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘንድ እንደ ገለልተኛ የመታየቷ ነገር ያበቃለት ይመስላል። ስቴቨን ምኑችን የሚመሩት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባለፈው ሳምንት ያወጣውን መግለጫ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው "ተቀባይነት የሌለው እና ለአንድ ወገን ያደላ ነው" ሲሉ አገራቸው በተቋሙ ገለልተኝነት ላይ ዕምነት ማጣቷን የሚጠቁም አስተያየት ሰንዝረዋል። ኢትዮጵያ «የታላቁ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውኃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ ነው» ስትል የአሜሪካ እና የዓለም ባንክን ሚና ማጠየቋ አይዘነጋም። 

በዋሽንግተን ዲሲ እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉት እና አሁን በኦሐዮ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት  መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ቀድሞም አሜሪካ በድርድሩ እጇን ማስገባቷ አይዋጥላቸውም።

ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ «አሁን ያለው [የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ] አስተዳደር ሁሉንም ነገር የሚያየው ከጥቅም አኳያ ነው። እኔ [ድርድሩን አሜሪካኖች] ከእስራኤል እና ከፍልስጤም ጉዳይ ጋር ያያዙት ይመስለኛል። በመካከለኛው ምሥራቅ ክብደት ያላቸው በመሆናቸው ግብፆችን ለማስደሰት የታሰበ ይመስለኛል። ሁለተኛ ግብፆች የራሳቸው የሆነ አላማ አላቸው። አሜሪካ ላይ ይኸ ነው የማይባል ሥራ በዋሽንግተን ዲሲ የሚያግባቡ ድርጅቶች በመጠቀም በኮንግረስ እና በሴናተሮች ላይ በሰፊው እንደሰሩ ነው። አሁን ደግሞ በተጠናከረ ሁኔታ ይሰራሉ» ሲሉ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሩ «በድርድሩ ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ [ማይክ ፖምፔዎ] ሁሉ አልተመደቡም። የተመደቡት በጅሮንዱ ናቸው። የብዙ አገሮችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ካየን አሁን ያለው የአሜሪካ መንግሥት ብዙ ነገሮችን በጥቅም መያዝ ላይ ትኩረት ይሰጣል። ኢትዮጵያንም ገንዘብ እና አማላይ ነገር ካቀረብንላቸው ለስለስ ሊሉ ይችላሉ በሚል ግብፆችን ለማስደሰት የተያዘ ስልት ነው» ሲሉ ምልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ግብፅ ከአሜሪካ ጋር ከኢትዮጵያ የተሻለ ጠንካራ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት የሚናገሩት ማይክል ሐና ይኸን ወዳጅነት በድርድሩ ልትጠቀምበት እንደምትችል ይናገራሉ። ባለሙያው እንደሚሉት የግድቡ ጉዳይ «በቀጣናው ጭምር ተፅዕኖ እንደሚኖረው ምን አልባትም ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል» የሚረዱት አሜሪካ እና ሌሎች ወገኖች ከስምምነት እንዲደረስ ግፊት ያሳድራሉ።    

ማይክል «ማበረታቻዎች ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶች የነበሩ ይመስለኛል። በኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብታዊ መዋዕለ-ንዋይ ባላት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኩል በሌላ የገንዘብ እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ኢትዮጵያ ስምምነት እንድትፈርም የመገፋፋት ሙከራ ወደፊት ልናይ እንችላለን። እንዲህ አይነት ሙከራዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። ይሁንና ይኸኛው ስልት የራሱ ውስንነቶች አሉበት። አሜሪካ ይኸ ጉዳይ በፍጥነት፤ በወዳጅነት እና በሰላም መፍትሔ እንዲበጅለት ትፈልጋለች ብዬ አስባለሁ» ሲሉ ልዕለ-ኃያሏ አሜሪካ ልትከተል ትችላለች ያሉትን ስልት ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የልማት ፈንድ ኮርፖሬሽን (International Development Finance Corporation) በተባለ ተቋም በኩል ከሶስት እስከ አምስት አመታት የ5 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካ መዋዕለ-ንዋይ በኢትዮጵያ እንደሚጠበቅ የፋይናንስ ምኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምኒስትሩ ለፋይናንሺያል ታይምስ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ይኸ መዋዕለ-ንዋይ በአገሪቱ ምጣኔ-ሐብት የግሉን ዘርፍ ማሻሻያ ለመደገፍ የታቀደ ነው። ከዚህ ባሻገር የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድዖ ድርጅት (USAID) ለመጪው ምርጫ የ30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በተለያዩ ተቋማት በኩል ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት ፈርሟል። እንዲህ አይነት የገንዘብ ድጋፎች አሜሪካ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ ኢትዮጵያን ለመጫን ትጠቀምበት ይሆን የሚል ሥጋት ያላቸው በርካታ ናቸው።

«አሜሪካ ወደ ድርድሩ የገባችው በግብፅ እንጂ በኢትዮጵያ ጥያቄ አይደለም። አሜሪካ ከግብፅ ባላት የጠበቀ ግንኙነት በድርድሩ ወደ ለግብፅ ጥቅም እንደማታደላ ኢትዮጵያ ተስፋ አድርጋ ነበር። ምክንያቱም አሜሪካ ከኢትዮጵያም ቢሆን ጥሩ ወዳጅነት አላት። ስለዚህ አሜሪካ በተወሰነ መንገድ ገለልተኛ አደራዳሪ ትሆናለች የሚል ተስፋ ኢትዮጵያ ነበራት። ያ ግን ተግባራዊ አልሆነም» የሚሉት ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን ኢትዮጵያ ሌላ አደራዳሪ ፍለጋ ልታማትር እንደምትችል ይገምታሉ። «ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካ አደራዳሪ እንድትሆን ጠይቃለች። ሌሎች ወገኖችም ወደ ድርድር ጠረጴዛው ሊመጡ ይችላሉ። ቻይና በድርድሩ እጇን ታስገባለች ብዬ አልጠብቅም። የአፍሪካ ኅብረት አሊያም ደቡብ አፍሪካ ወደ ድርድሩ ይመጣሉ ብዬ እጠብቃለሁ። አሜሪካ ግን ከዚህ በኋላ በአደራዳሪነት ለመቀጠል በኢትዮጵያ በኩል የነበራትን እምነት አጥታለች» ብለዋል።

BG Grand Renaissance Dam |  Treffen zwischen Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed Ali und Südafrikas Präsident Cyril Ramaphosa
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አሸማጋይ እንዲሆኑ ጠይቀዋልምስል AFP/P. Magakoe

ኢትዮጵያ በእነ አሜሪካ ከሚመራው ድርድር ገሸሽ የማለት አዝማሚያ ያሳየችው ባለፈው ጥር ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅን እንዲያሸማግሉ ሲጠይቁ ነበር። መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው የአፍሪካ ቀንድ ሥልታዊ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ሐሰን ኻኔንጃ (ዶ/ር) ከጉዳዩ ውስብስብነት አኳያ ይኸ ተመራጭ ነው የሚል ዕምነት አላቸው።

ሐሰን ኻኔንጃ  «ጠንካራ እና ያልተቻኮለ ድርድር መደረግ ይኖርበታል። ጉዳዩ በአህጉሩ ደህንነት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ስለሚኖር የአፍሪካ ኅብረት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ አለበት። ድርድሩን ለዋሽንግተን አሳልፈን ከሰጠን ችግር ይፈጠራል። እዚህ የምንኖረው እኛ ነን። የቪክቶሪያ ሐይቅ ከናይል ወንዝ መነሻዎች አንዱ ነው። ድርድሩ እነዚህ ላይ ሁሉ ተፅዕኖ አለው። ስለዚህ ድርድሩን ወደ አህጉሩ መመለስ አለብን» ብለዋል።

በአሜሪካ የገለልተኝነት ጉዳይም ይሁን ከአዲስ አበባ እስከ ካይሮ ከኻርቱም እስከ ዋኅንግተን ዲሲ በተካሔደው ድርድር እጣ-ፈንታ ተስፋ የቆረጡት ግን ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን ብቻ አይደሉም። የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ምኑቺን በአገራቸው ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት ስቲቨን ሖርስፎርድ የተባሉ የኮንግረስ አባል ስለ ሚዛናዊነት ደጋግመው ጠይቀዋል። በሖርስፎርድ «ሁሉም ወገኖች መደመጣቸውን፣ አሜሪካም ወገንተኛ አለመሆኗን ለማረጋገጥ ምን እያደረጋችሁ ነው?» ተብለው የተጠየቁት ምኑችን ጥያቄውን በቀጥታ ሳይመልሱ ቀርተዋል። ስቴቨን ሖርስፎርድ በበኩላቸው «ሚዛናዊ ብትሆኑ ኢትዮጵያ ወደ ድርድሩ ልትመለስ ትችላለች ብዬ አስባለሁ» ሲሉ ኮስተር ያለ ምላሽ ለምኑችን ሰጥተዋል።

ጆን ጋራሜንዲ የተባሉ ሌላ የኮንግረስ አባል ለምኑችን በፃፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅን ለማደራደር ያደረጋችሁት ጥረት ያበቃለት ይመስለኛል ሲሉ ተስፋ መቁረጣቸውን ጠቁመዋል። «አሜሪካ ገለልተኛ መሆን አለባት» ያሉት የምክር ቤቱ አባል በጉዳዩ ላይ የዘርፉን ባለሙያዎች እንዲያወያዩ ምክር ለግሰዋል። 

ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ኢትዮጵያ በድርድሩ አሜሪካ የሚኖራትን ሚና በቅጡ ልትለይ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። «አሁን ኳሱ በትራምፕ አስተዳደር ሜዳ ላይ ነው። ይኸን አቋም ማስተካከል አለባቸው። የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ማይክ ፖምፔዎን መያዝ አለባቸው። ወደ ተለመደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ዲፕሎማሲ አቅጣጫ መግባት አለባቸው» ብለዋል።

ድርድሩ መቼ እና እንዴት እንደሚቀጥል ባይታወቅም ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን ኢትዮጵያ እና ግብፅ ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል። ፕሮፌሰር አሾክ ስዌይን «ግብፅ ለበርካታ አመታት በወንዙ ተፋሰስ ላይ የነበራት ብቸኛ ባለቤትነት ከእንግዲህ እንደሌላት ግብፅ ልትገነዝብ ይገባል። ኢትዮጵያ ግድቡን ካቀደችው ረዘም ባለ ጊዜ ውኃ መሙላት አዋጪ ባይሆንም ካቀደችው ጊዜ በላይ ሊወስድ እንደሚችል መቀበል አለባት። ኢትዮጵያም ሆነች ግብፅ ሊረጋጉ ይገባል። መረጋጋትም አለባቸው። አለበለዚያ በድርድሩ መታረቂያ ሊያገኙ አይችሉም። ስምምነት ላይም አይደርሱም» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ