1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታንዛንያ የወርቅ ማዕድን

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2005

ታንዛንያ የተፈጥሮ ማዕድን ባለ ሃብት ናት። በምስራቅ አፍሪቃዊትዋ ሀገር ታንዛንያ 36 ሚሊዮን አዉንስ ወርቅ፤ ማለት ወደ አንድ ሚሊዮን ኪሎ ግራም የወርቅ ክምችት እንዳላት ይገመታል። በዚህም ታንዛንያ በአፍሪቃ አህጉር በወርቅ ሃብት ክምችት ከደቡብ አፍሪቃ እና ጋና ቀጥላ ሶስተኛ ደረጃን እንድትይዝ ያደርጋታል።

https://p.dw.com/p/17R3Z
ምስል DW/J. Hahn

ህዝቧ ግን የዚህ ሃብት ተጠቃሚ አይደለም። የማዕድን ማዉጫ ቦታዎችም በዉጭ ሃገር ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ነዉ የሚገኙት። በ1990 ዎቹ ዓመታት መጨረሻ የማዕድን ማዉጫ ቦታዎችን መንግስት በቅናሽ ቀረጥ እና በአነስተኛ ክፍያ የስራ ፈቃድ የማግኘት ዕድልን ለዉጭ ሀገር ኩባንያዎች ዕድልን ከሰጠ በኋላ በበርካታ የማዕድን ማዉጫ ቦታዎች፤ በአካባቢዉ ነዋሪዎች እና ድርጅቱን በሚያንቀሳቅሱት አካላት መካከል ዉጥረት ተቀሰቀሰ። በተለይ በኬንያ አዋሳኝ በሚገኘዉ ሰሜናዊ ምዕራብ ታንዛንያ ዳርቻ በሰሜናዊ ማራ አካባቢ  ግጭቱ ጠንክሮ ይታያል።በዚህ አካባቢ ያለ ወርቅ ሌላ የሚንቀሳቀስ ነገር የለም፤ ስለዚህም  በርካቶች ጥቂት ግራም ወርቅን ለማግኘት ሲሉ ብቻ ህይወታቸዉን አደገኛ ሁኔታ ላይ ሲጥሉ ይታያል። ግዜ ወርቅ ነዉ፤ የሚል አነጋገር አለ- ኬዋንጃ ከተማ ከኬንያ ድንበር በመኪና የግማሽ ሰዓት መንገድ እንኳ አይርቅም። ታንዛንያዊዉ ጁማኔ ቁመቱ ረጅም ከሆነዉ ቁልል አፈር ላይ ሁለት ሜትር ሽቅብ እየቧጠጠ ወጣ። በጁ በያዘዉ ጠርሙስ የቀዳዉን ጭቃ የቀላቀለ ዉሃ ጎንጨት አድርጎ አንድ ግራጫማ ከሆነ የሚያንጸባርቅ ድንጋይ ላይ ረጭቶ በአዉራ ጣቱ ፋቅ ፋቅ እንዳደረገዉ ወርቅማ መልክን በማየቱ ፊቱ በፈገግታ ተሞላ። ከዝያም በፍጥነትያገኘዉን ድንጋይ  እሱሪዉ ኪስ ከተተ፤ « የምንሰራዉ እዚህ ነዉ። የማዕድን ማዉጫዉም የኛ ነዉ! ግን ነጮች አላስቀምጥ ብለዉናል ፤ ያሳስሩናል። እዚህ በመጣን ግዜ ፖሊስ ያባርረናል። ሁሉ ነገር ነዉ የከበደብን፤ እዚህ ችግር ብቻ ነዉ ያለዉ» ጁማነ እራሱን የሚጠራዉ «ያለፈቃድ የሚገባ» ሲል ነዉ። ይህ ማለት ማዕድን ማዉጫ ቅጽር ግቢ ያለፈቃድ በመግባት ከአፈር ቁልሉ የሚገኝ ስብርባሪ ማዕድን የሚለቅሙ ሰዎች መጠርያ ነዉ። በዓለም ግዜፉ የወርቅ አምራች ኩባንያ በእንግሊዘኛ ምህፃሩ (ABC)የተሰኘዉ ሲሆን፤ የዚህ ኩባንያ ቅርንጫፍ የሆነዉ ባሪክ ካናዳ የተሰኘዉ ኩባንያ ነዉ። ጁማነ ቅጥር ግቢዉ በመግባት የሚለቅመዉ ኩባንያዉ የማይፈለግ ብሎ ከጣለዉ አፈር ቁልል ዉስጥ በመምረጥ ነዉ። ቢሆንም ኩባንያዉ ይህንን የማይፈለግ ብሎ የቆለለዉን አፈር ማንም እንዳይነካ በዘበኛ ያስጠብቀዋል። ግን ከማዕድን ማዉጫዉ ከሚወጣዉ የአፈር ቁልል ላይ ያለፈ ትንሽ የወርቅ ማዕድን ይኖራል ብለዉ ተደብቀዉ ገብተዉ የሚፈልጉ በርካቶች ናቸዉ። እዚህ ከሶስት አንዱ ነዋሪ አፈር  ቁልሉ ላይ እየወጣ የወርቅ ማዕድን በመፈልግ የሚተዳደር ነዉ። አብዛኛዉ ደግሞ ወጣት ነዉ፤ ህፃናትም ይገኙበታል። ጁማነ 20 ዓመቱ እንደሆነ ይናገራል። እዚህ አፈር ቁልል ላይ የሚያገኘዉን የወርቅ ስብርባሪ የሚሸጠዉ በዚሁ በገጠር ባለ ገባያ ዉስጥ ነዉ። በወር ወደ 200,000 ሺሊንግ እንደሚያገኝ  ይናገራል፤ ወደ አንድ መቶ ይሮ መሆኑ ነዉ። በዚህም ጁማነ በአካባቢዉ ከፍተኛ መተዳደርያን ከሚያገኑት ነዋሪዎች ይመደባል። በድንገት በዚሁ አፈር ቁልል አካባቢ ፀጥታዉ ደፈረሰ፤ ጁማነ በእጁ እያመላከተ አንድ ጥቁር አረንጓዴ መለዮ የለበሰ ፖሊስ ከሩቅ መምጣቱን ያሳያል።  «ተመልከት! ፖሊስ ሰዎችን እያባረረ ነዉ። ሁሌም በዉጥረት ዉስጥ እያደረገን ነዉ። እዛ ጋ ያለዉም የታጠቀ ፖሊስ ነዉ። ዝም ብለዉ ነዉ ሰዉ ላይ የሚተኩሱት ሰዎች ይሞታሉ! ብዙ ግፍ እየደረሰብን ነዉ» የማዕድን ማዉጫ ኩባንያዉ አካባቢዉን፤ በታጣቂዉች እንዲሁም በብሄራዊ ፖሊሶች  በጥብቅ ያስጠብቃል። ጠባቂዎቹ አስለቃሽ ጋዝ፤ የጎማ ጥይት እንዲሁም ሽጉጥ የታጠቁ ናቸዉ። በአካባቢዉ ላይ ብዙን ግዜ የቆሰለ ወይም የሚሞት አይጠፋም። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ብቻ እንደ መንግስት መገኛኛ ብዙሃን የማዕድን ማዉጫ ኩባንያዉ አካባቢ ስምንት ሰዎች ተገለዉ ተገኝተዋል። በዚህም ያለፈቃድ ግቢ ዉስጥ እየገቡ አፈር ቁልሉ ላይ የወርቅ  ስብርባሪ በሚፈልጉ ሰዎች የሚያሰሙት ቁጣ በጣም በርትቶአል። «Baraki ዉስጥ ያሉ ሰዎች ስለሰዉ ግድ የሌላቸዉ ብቻ ናቸዉ። ለዚህ ነዉ እኛ ላይ ልክ ዉሻ እንደሆን ሁሉ አነጣጥረዉ የሚተኩሱብን። ፖሊሶቹም ኩባንያዉ የሚላቸዉን  ነገር ብቻ ነዉ የሚያደርጉት። እንደ አሻንጉሊት ኩባንያዉ የፈለገዉን ነገር ነዉ የሚታዘዙት»  ከዚህ ማዕድን ማዉጫዉ ከሚያወጣዉ የአፈር ቁልል በስተጀርባ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ይሰራል። በሰሜናዊ ማራ በሚገኘዉ የማዕድን ማዉጫ ፤ ለብዙ ግዜ ድርጅቱን የሚያስተዳድሩት ኩባንያዎች ተቀያይረዋል። ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም ጀምሮ ABG የተሰኘዉ ኩባንያ ማዕድን ማዉጫዉን በማስተዳደር ላይ ይገኛል። ይህ ኩባንያ በታንዛንያ ከአስር ዓመታት በላይ የተንቀሳቀስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በታንዛንያ የሚገኙ አራት የወርቅ ማዕድን ማዉጫ ቦታዎችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል። እንደ ኩባንያዉ ገለፃ በሰሜናዊ ማራ የማዕድን ማዉጫ ቦታ በአካባቢዉ ከሚኖሩ 360 ሰራተኞች ተቀጥረዋል። ሌሎች 1500 ሰራተኞች ደግሞ በሌላ አስቀጣሪ ድርጅት በኩል ተቀጥረዉ ኩባንያ ዉስጥ በማገልገል ላይ ናቸዉ። ይህ ኩባንያ ለአካባቢዉ ነዋሪዎች ጥሩ ስራ ፈጣሪ ግን አልሆነም። የማዕድን ማዉጫ ኩባንያዉ በአካባቢዉ ላይ ለሚኖሩት በግምት 70,000 ነዋሪዎች  በጣም ጥቂት ሰራተኞችን ነዉ የቀጠረዉ። ጥቂት ተቀጣሪ ግን ለድርጅቱ በርካታ ገቢን ያስገኛል። እንዲህ አይነቱ የአሰራር ችግር  በጥሪ ሃብት ምርቱ ዘርፍ የተለመደ መሆኑ የማይታበል ነዉ። በሰሜናዊ ማራ የሚገኘዉ የማዕድን ማዉጫ ቦታ፤ አንድ ትልቅ የማዕድን ማዉጫ ቦታን ያስታዉሳል። መጀመርያ ማዕድኑ የሚገኝበትን አካባቢ በድማሚት በማንጎድ እና አፈሩ ተዝቆ ይወጣል። ወርቅ የያዘዉ ድንጋይ ደግሞ በቀጣይ ይጣራል። ታድያ የሰሜናዊ ማራ የሚገኘዉ የወርቅ ማዉጫ ኩባንያ ABG በ ጎ,አ 2011 ዓ,ም  200 ሚሊዮን ይሮ ገቢን አግኝቶአል። የኩባንያዉ አስተዳዳሪ Garya Chapman, ኩባንያዉ ስለ አካባቢዉ ማህበረሰብ ሃላፊነት እንደሚሰማዉ እንዲህ ይናገራሉ። «ከግዜ ጋር ቀጣይነት እና በእኛ እና ማህበረሰቡ ዘንድ እምነትን ለማግኘት በመስራት ላይ ነን ይህንንም ከዳር እናደርሳለን፤ ቢያንስ ከማህበሩ ክብር እናገኛለን። እንድንወደድም እንፈልጋለን፤ ግን መከባበር እና የጋራ ስራ አይነተኛዉ እና ተፈላጊዉ መንገድ ነዉ።» ይህን ለማግኘት በሰሜናዊ ማራ የሚገኘዉ የማዕድን ማዉጫ ኩባንያ «የማህበረሰብ ግንኙነት» በሚል አንድ ማህበር አቋቁሞአል። ይህ 17 ወንዶችና ሴቶችን ያቀፈዉ ማህበር በአካባቢዉ በሚኖሩ ሰዎች ቤት በመዘዋወር የገጠር ተጠሪዎች እና የአካባቢ አዛዉንቶችን በማነጋገር ግንኙነትን ይመሰርታል ሃሳብ ይቀያየራል። በዚህም ኩባንያዉ ለህብረተሰቡ የሚሰራቸዉን ፕሮጄዎች ይቆጣጠራል። የአፍሪቃዉ ባሪክ የተሰኘዉ የወርቅ ማዕድን ማዉጫ ኩባንያ አንዳንድ በሰራቸዉ ስራዎች ኩራትም አለዉ። ለምሳሉ ከማዕድን ማዉጫዉ ቦታ እንብዛም የማይርቀዉ (INGWE SECONDARZ SCHOOL) ኢንግቬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነዉ። በ 2012 ዓ,ም ABG የፈራረሱትን የመማርያ ክፍሎች አድስዋል፤ በመቀጠል የመመገብያ ክፍልና አንድ የመማርያ ህንጻን ገንብቶአል። ታድያ ይህ ሁሉ ሲያደረግ ኩባንያዉ ለአካባቢዉ ነዋሪዎች የስራ እድልን ፈጥሮአል ነዉ። ፈዘዝ ያለ ቡናማ ልብስ ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር Joash Mageka የማዕድን ኩባንያዉ አደረገ የተባለዉን ስራ ደመቅ አድርገዉ ያሞግሳሉ። «ብዙ ነገር ነዉ የተቀየረዉ! ትምህርት ቤቱ በርግጥ አሁን ጥሩ ሆንዋል። ለዚህም በጣም ኮርቻለሁ። ከዚህ በፊት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ ያለፈቃድ በማዕድን ማዉጫዉ እየገቡ ሌላ ስራን ይሰሩ ነበር ። አሁን ግን ይህ ነገር እምብዛም አይታይም። መማራቸዉ አሳዉቆአቸዋል።» ትምህርት ቤቱ የሚታይ አስደሳቹ ፕሮጄ ነዉ። ለማዕድን አዉጭ ኩባንያዉም አካባቢዉን ማሳደጉን የሚያሳይበት በምሳሌ የሚያቀርበዉ ስራዉ ነዉ። ABG የወርቅ ማዉጫ ኩባንያ ታንዛንያ ዉስጥ ከጎ 2010 ዓ,ም ጀምሮ 20,6 ሚሊዮን ዶላር ለማህበረሰባዊ መረኃ-ግብሮች ወጭ ማድረጉን ይገልፃል። ይህ ደግሞ ሲሰላ ኩባንያዉ ካስገኘዉ ገቢ ዉስጥ አንድ በመቶ ያነሰ ይሆናል። እንደ ኩባንያዉ ቃል አቀባይ ገለፃ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት አብዛኛዉ ወጭ የፈሰሰዉ በሰሜናዊ ማራ ለሚገኙ ነዋሪዎች ነዉ። ግን ይህ ቀደም ሲል አልተደረገም? መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነዉ። Zakayo Kalebo በማህበረሰብ ግንኙነት ማህበር የኩባንያዉ ወገን ተጠሪ እንዲህ ይገልጻሉ፤«ሰዎች ይህ የማዕድን ማዉጫ በመኖሩ እና በአካባቢዉ ላይ እድገት በመታየቱ እጅግ ደስተኛ ናቸዉ። በፊት ይህ የማዕድን ማዉጫ ባልነበረበት ወቅት ሁኔታዉ እንዲህ እንደ አሁኑ አልነበረም» የዉጭ ኩባንያ በቦታዉ ላይ ሳይመጣ የአካባቢዉ ነዋሪዎች በራሳቸዉ መንግድ በጥቂቱም ቢሆን  ወርቅ እያወጡ ይተዳደሩ ነበር። በሚያገኙትም ገቢ ኑሮአቸዉን ይገፉ ነበር። በ1990 ዎቹ መጨረሻ አለማቀፎቹ የማዕድን አዉጭ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላ ትናንሾቹ ማዕድን ቆፋሪዎች ስራ ቦታቸዉን አጡ።  በሰሜናዊ ማራ ስለ ኤኮኖሚ እድገት እና ብልፅግና ማዉራቱ በርግጥ ነገሩን እጅግ ከማጋነን በቀር በሌላ ሁኔታ መግለፅ አይቻልም። የአካባቢዉ የወርቅ ንግድ በዉጭ ያሉትን ነዋሪዎችንም ወደቦታዉ እንዲመጡ ሳይጋብዝ አልቀረም። ለምሳሌ በጎረቤት ኬንያ ነዋሪ የነበረዉ ዴቪድ አሩምባ ከአንድ አመት በፊት ወደ ሰሜን ማራ በዚሁ በወርቅ ንግድ ለመተዳደር መጣ። የ 25 ዓመቱ ማራ ከቤተሰቡ መካከል ብቸኛዉ ትምህርትን ያገኘ ነበር፤ ማራ በህገ-ወጥ በማዕድን ማዉጫ ቅጽር ግቢ እየገባ በቁልሉ አፈር ላይ የወርቅ ስብርባሪን የመፈለጉ ስራን መተግበር እንደማይፈልግ እንዲህ ይናገራል፤ « ሌላ ሥራን ለመስራት ወስኛለሁ። አብዛኞች ይገደላሉ ወይም ይቆስላሉ። እኔ ሁልግዜ ፖሊስ መጣብኝ አልመጣብኝ እያልኩ በፍርሃት መኖርና መስራትን፤ ወይም ስህተተኛ ሆኜ መገኘትን አልፈልግም። ስለዚህም አንድ ትንሽ ድርጅት አቋቁሜያለሁ። በዚህ ደግሞ ነፃ የሆነ ዉስጣዊ ስሜት አለኝ» ዴቪድ በካዊንጃ አንድ የመኪና ማጠብያ ሳሎን ከፍቶአል፤ ባለቤቱ ደግሞ ሙዝ እና በላስቲክ ጠርሙስ ቤንዚን እየሞላች ትሸጣለች። ዴቪድ በከፈተዉ የመኪና ማጠብያ ድርጅት የአካባቢዉ ነዋሪዎችን ሞተር ብስክሌት ያጥባል። አብዛኞቹ ደንበኞቹ ታድያ በማዕድን ማዉጫ ኩባንያዉ አካባቢ በሚገኘዉ የአፈር ቁልል ላይ የወርቅ ማዕድንን በመፈለግ በወርቅ ማዕድን ሽያጭ የሚተዳደሩት ናቸዉ። በአካባቢዉ ላይ ሞተር ሳይክል ያለዉ ጥሩ መኖሩን ሃብት እንዳለዉ ማሳያ ምልክትም ነዉ። አብዛኛዉ የአካባቢዉ ነዋሪ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ ነዉ፤ ኑሮዉን የሚመራዉ። ዉሃና እና የኤሌክትሪክን የሚጠቀም ደግሞ በጣም የተንደላቀቀ ኑሮን የሚመራ ከሆነ ነዉ። በሰሜናዊ ማራ ነገሮች ትክክል ያልሆኑበት ጉዳይ ምን ይሆን? ይህ ጥያቄ በዳሪሰላም ለሚገኘዉ የታንዛንያ መንግስት የቀረበ ጥያቄ ነበር። በታንዛንያ የማዕድን ሚንስትር Sospeter Muhongo ራሳቸዉ የመጡት ከሰሜናዊ ማራ አካባቢ ነዉ። የስነ ምድር ትምህርትን የተከታተሉት የታንዛንያዉ የማዕድንን ሚኒስትር፤ ይህንን ስልጣን የያዙት በቅርብ ግዜ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎች የበለጠ ቀረጥ እንዲከፍሉና ማህበረሰቡ የሚያስፈልገዉን ነገር እንዲያሟላ የበለጠ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ግን ሚንስትሩ ከመሾማቸዉ በፊት ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ ፖለቲካ ስላሳደረዉ እንቅፋት እና ለመሻሻል ማወቅም ሆነ መናገር አይሹም፤ « ሁሉንም ነገር ለማድረግ እየሞከርን ነዉ፤ ወደፊትምበዚህ አካባቢ ሰላም እና የፀጥታዉን ሁኔታ ለማስጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እንጥራለን። ይህን ለማደርግ ከሁሉ በፊት የትምህርት ስልጠና ላይ መዋለ ንዋይን ማፍሰስ ይኖርብናል። ሰዎች በደንብ ስልጠናን ከወሰዱ እና ከተማሩ አስተሳሰባቸዉም ይቀየራል»በኩዋንጃና አካባቢዋ ግን እስካሁን የተቀየረ ነገር የለም። በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ ላይ ያለዉ ወርቅ ግን ጥቅምን እያስገኘ ነዉ። በገጠር መንደሩ ዳርቻ ላይ በአንድ ሰዋራ ስፍራ ከወርቅ ማዉጫ ኩባንያዉ ቅፅር ግቢ በመግባት አፈር ቁልሉ ላይ ከድንጋይ ጋር ያለዉን የወርቅ ስባሪን በመሰብሰብ ትንሽ ግራም የምትመዝን ድብልብል ወርቅ ያወጣሉ። ከለቀሙት ድንጋይ ዉስጥ ወርቁን እየለቀሙ የሚያወጡትም እዝያዉ ነዉ። በመጀመርያ ወርቅ የያዘዉን ድንጋይ እስኪልም ከፈጩ በኋላ በተቋጠረ ዉሃ ዉስጥ ከተዉ ሜርኩሪ በመጨመር ለጤንነት አደገኛ በሆነ ሁኔታ ወርቁን ከድንጋይ በመለየት በአንድ ላይ ይሰበስቡታል።በዚሁ ቦታ ላይ የሚሰራ እንድ ማንነቱን መናገር ያልፈለገ ሰዉ የአሰራሩ ዘዴ እጅግ ለጤና ጎጂ መሆኑን እና ስለጤንነቱም በጣም እንደሚጨነቅ ይናገራል። «እያንዳንዱ ሰዉ ቤተሰቡን ለመመገብ በቂ ገንዘብ ማግኘትን ይፈልጋል። እኔ ቀደም ሲል በግብርና ስራ እተዳደር ነበር፤ በግብርና አንድ ዓመት ሰርቼ የማገኘዉ ነዉ፤ አሁን በምሰራዉ በዚህ ስራ በአንድ ቀን የማገኘዉ» ወጣቱ በእጁ ላይ አንዲት ትንሽ ድብልብል ምናልባትም ከአንድ ግራም ያነሰች አስቀምጦ ያሳያል። ይህችን ቅንጣት ወርቅ ሲሸጠጥ ምናልባት ወደ ሃያ ይሮ ግድም ነዉ የሚያገኘዉ። ታንዛንያ ካላት የጥሪ ሃብት አንድ ኢምንት የምትሆን ቅንጣት፤ ግን ለደሃይቱ ሰሜናዊ ታንዛንያ ነዋሪ ይህ ገንዘብ መተዳደርያ ነዉ።

North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania Schuldirektor Joash Mageka
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
Infografik Afrikas Rohstoffe Tansania Gold Amharisch
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn
North Mara Gold Mine in Tansania
ምስል DW/J. Hahn

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ     

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ ዘገባዎች አሳይ