1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የቸገራቸው ተፈናቃዮች-በሸዋሮቢት እና በሰንበቴ

ረቡዕ፣ ሰኔ 23 2013

ከሶስት ወራት ገደማ በፊት በተቀሰቀሰ ብርቱ ግጭት ተፈናቅለው በሸዋሮቢት የወጣቶች ማዕከል እና በሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርካታ የተጠለሉ በርካታ ሰዎች ለለት ጉርስ የሚሆን በቂ ዕርዳታ እስከማጣት መድረሳቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "የፍትኃዊነት ችግር" መኖሩን ያረጋገጡ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዕርዳታ እየተሰጠ ነው ብለዋል

https://p.dw.com/p/3vpq3
Äthiopien Stadt Shewa Robit
ምስል Eshete Bekele/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የቸገራቸው ተፈናቃዮች-በሸዋሮቢት እና በሰንበቴ

ግድግዳዎቻቸው ተፋፍቀው በቆሸሹ የሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች ወደ አንድ ጎን ተሰብስበው ለመኝታ የሚያገለግሉ ፕላስቲኮች ተነጥፈዋል። ፍራሾችም በመማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ይታያሉ። በየጥጋጥጉ ጀሪካኖች፣ ብረት ምጣድ እና ማብሰያዎች፣ የተለያዩ አልባሳት፣ በማዳበሪያ ቋጠሮዎች ተደርድረዋል። ቀኑ እሁድ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ ዋዜማ ነው።

ከ62 አመታት በፊት የተቋቋመው ትምህርት ቤት በሩን በተማሪዎቹ ላይ ዘግቶ ላለፉት ሶስት ገደማ ወራት የተፈናቃዮች መጠለያ ሆኗል። የታጠቡ አልባሳት በቅጥር ግቢ ግቢው በተዘረጋ ሽቦ ላይ ተሰቅለው ይታያሉ። ትካዜ የተጫናቸው ጎልማሶች በየትምህርት ክፍሎቹ ዳጃፎች ቁጭ ብለዋል። እናቶች መሬት ይጭራሉ። አቀማመጣቸው፣ ፊታቸው እና አጠቃላይ ሁኔታቸው ባለፉት ሶስት ወራት ኑሮ እንደጨከነባቸው ይመሰክራሉ። ከሶስት ወራት ገደማ በፊት በአካባቢው በተቀሰቀሰ ግጭት ከአጣዬ ከተማ ተፈናቅሎ በሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠለለው ጀማል ዲሲር ኑሮ ከከፋባቸው አንዱ ነው።

"ውኃ እዚህ ግቢ አንዲት ቧንቧ አለች። ያቺ በሳምንት አንዳንዴ ትመጣለች። አለ አይባልም። አልባሳት ምንም ነገር የለንም። መኝታም ያው ካርቶን ነው። ካርቶን የሌለውም ሽርጡንም ምኑንም አንጥፎ ነው የሚተኛው። ሕክምና የሚባል ነገር ምንም ነገር የለም" ይላል ጀማል ያሉበትን ሁኔታ ለዶይቼ ቬለ ሲያስረዳ። እንደ ጀማል ከሆነ ብርቱው ፈተና ግን በቀዝቃዛው የስሜንቶ ወለል ላይ መተኛት አይደለም። የሚበላ ምግብ እጦት እንጂ። "ዛሬ ዛሬ በአሁኑ ሰዓት የምንበላው ያስፈልገናል። መኝታው ምኑ ምኑ ችግር የለውም። ዋናው ለሰው ልጅ [አስፈላጊው] ምግብ ነው። የመኝታውን ችግር መላመድ ይቻላል። እዚህም አፈሩ ላይ መተኛት እችላለሁ። የምግብ እና የውኃ [እጦትን] ግን መላመድ አይቻልም" ይላል ጀማል።

Äthiopien Grundschule Sanbatee
በሩን በተማሪዎቹ ላይ ዘግቶ የተፈናቃዮች መጠለያ የሆነው የሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትምስል Eshete Bekele/DW

ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ 400 ገደማ አባወራዎች በዚሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ቁጥራቸው መቀነሱን ዕርዳታ በማቅረብ ከተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለመረዳት ተችሏል። እንደ ወጣቶቹ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በቅጥር ግቢው 160 አባወራዎች ወይም ከ1000 ሺሕ በላይ ሰዎች ይገኛሉ።

ጀማል እና ሌሎች ተፈናቃዮች እንደሚሉት በረመዳን የፆም ወቅት የሰንበቴ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች እገዛ ሲያደርጉላቸው ቆይተዋል። ይሁንና የፆሙ ወቅት ሲያበቃ እርዳታው እንዳልቀጠለ ከተፈናቃዮቹ አንዱ የሆነው መሐመድ አማን ያስረዳል። "ረመዳን ከወጣ ወር ሆኗል። በዚህ ወር ውስጥ ማንም ሰው የሚበላው ነገር የለም። ግማሹ እየለመነ እየበላ ነው። ያን አጥቶ ደግሞ በባዶ ሆዱ የሚተኛ አለ" የሚለው መሐመድ በቂ እርዳታ አለማግኘታቸውን ገልጿል።

"በአጣዬ በኩል እኛን የሚረዳ አንድ ኃላፊ አለ። እሱ ሔዶ አስተዳዳሪውን ጠየቀልን። ´እዚህ ይግቡ፣ እንሰጣቸዋለን፣ እርዳታ መጥተው ይውሰዱ` ምናምን ተባለ። ስንሔድ እርዳታ ዛሬ ይገባል ነገ ተሰርቋል። ከዚህ የምንሔደው እንዲያውም እንደ አጣዬ ዜጋ አልሆንም። እሱ ግቡ ያለበት ቦታ ሕዝቡ ለመግባት ለነፍሳችን እንፈራለን ብሎ እምቢ አለ። በዚህ ምክንያት አልሰጣችሁም የለም ብሎ ዘጋበት። ከዛ መጥቶ እኛን `ወንድሞቼ ከዚህ ወረዳም ከዚያ ወረዳም አጥቼላችኋለሁ። ምንም ነገር የለም። ተስፋችሁን ቆርጣችሁ ከለመናችሁ ለምናችሁ ኑሩ እኔ ምንም የማደርግላችሁ ነገር የለም` ብሎ አቆመው" ይላል መሐመድ።

Äthiopien Grundschule Sanbatee
ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ 400 ገደማ አባወራዎች በዚሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ቁጥራቸው መቀነሱን ዕርዳታ በማቅረብ ከተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለመረዳት ተችሏል።ምስል Eshete Bekele/DW

መሐመድ አማን እና ጀማል ዲሲርን ጨምሮ በሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ዘንድ ´ሊሰጠን ይገባ የነበረ ዕርዳታ ተዘርፏል´ የሚል ተደጋጋሚ ክስ ይደመጣል። ዶይቼ ቬለ በእርግጥ ለተፈናቃዮች የተመደበ እርዳታ ለሌላ መሰጠቱን አሊያም መዘረፉን አላረጋገጠም።

የዕርዳታ እጦት የሚፈትናቸው ግን በሰንበቴ የሚገኙትን ብቻ አይደለም። በሸዋሮቢት ከተማ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል የተጠለሉ ተፈናቃዮች ተመሳሳይ ፈተና ውስጥ ናቸው። እንደ ሰንበቴ ሁሉ ዕድሜያቸው የገፋ፣ ህመም የተጫናቸው ለወጣቶች መዝናኛ ተብሎ በተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ ተጠልለዋል። ሕፃናት ውር ውር ይላሉ። በአዳራሹ  የቆሸሹ ፍራሾች በብዛት ይታያሉ። ሞፈር አገላብጠው ያርሱ የነበሩ ገበሬዎች ቀለስ ባደረጓቸው መጠለያዎች ዕቃ ያጣጥባሉ። ጀውሃ ከተባለችው አነስተኛ ከተማ የተፈናቀሉት የ40 አመቷ ወይዘሮ ዓለም አድማሱ አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ዓለም "ከእኛ የተሻሉ ሰዎች ከሕዝቡም መታፈግ ሁኔታ፣ ከበሽታውም ሁኔታ ትንሽ እኛ እንኳ እንውጣ ብለው ወደ ውጪ ተከራይተው የወጡ አሉ። ከጀውሃ የተፈናቀለው ወደ 3900 ሰው ነው። ለተጠየቀው ወደ ኋላ የማይል አርሶ አደር፣ በዚህ ቦታ ና ቶሎ ቢሉት ፊቱን የማያጠቁር ሕዝብ ነበር። የጀውሃ ሕዝብ ዕርዳታም ከመንግሥት የማይፈልግ ነበረ። የሰላም ሁኔታ ግን ንብረቱንም እሱንም አሳጥቶ ራቁቱን አስወጥቶታል" ሲሉ ግጭቱ የአካባቢውን ሕዝብ አኗኗር ማናጋቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

አብዱ ዳውድ አዲስ ዓለም ነጌሶ ከተባለ ቦታ በግጭቱ ሳቢያ ተፈናቅሎ ሸዋሮቢት ከተማ በሚገኘው መጠለያ ያለፉትን ሶስት ወራት የተጠለለ የ28 አመት ወጣት ነው። "እስከ ዛሬ የሸዋሮቢት ከተማ መስተዳድር ዕርዳታ እያሰባሰበ ነው እየመገበን ያለው። አንድ ጊዜ ብቻ መንግሥት ዕርዳታ ሰጥቶናል። የሰጠን ዱቄት ብቻ ስለነበረ በሶ አይደለም በጥብጠን አንጠጣውም፣ በሶም ልጠጣ ብትል ስኳር ያስፈልገዋል። ተጓዳኝ ምግቦች የሉም። ያንን ሸጠን ሩዝ እየገዛን፣ ዘይት እና አሸቦ (ጨው) እያቻቻልን ተጠቅመንበታል። የከተማ መስተዳድሩ እስከ ዛሬ እየለመነ አብልቶናል። አሁን ግን ወደ መሰላቸቱ ላይ ደርሷል። መንግሥትም ዞር ብሎ ሊያየን አልቻለም" ሲል ችግር እንደገጠማቸው አብዱ ያብራራል።

ራሳቸው ተፈናቃይ ሆነው ተፈናቃዮችን የመመገብ ኃላፊነት የተጣለባቸው ወይዘሮ ዓለም "ይኸንን ሶስት ሺሕ ምናምን ሕዝብ ስንመግበው የከተማ አስተዳደሩ የሚያመጣልንን ነገር ጠዋት ቁርስ ካበላን ምሳ እየዋለ፤ ምሳ ካበላን እራት እየዋለ ነው። እንጨት ይቸግራል፤ ዘይት ይቸግራል፤ ብዙ እዚህ የሚጎድሉ ነገሮች አሉ። አሁን የከተማ አስተዳደሩ በመሸነፍ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ከሚገባው በላይ ታገለ። አሁን ከአቅሙ በላይ ነው። መንግሥት ተደራሽነቱን ለሕዝቡ ማሳየት አለበት" ሲሉ ይወተውታሉ።  

ወይዘሮ ዓለም "ከተማ የምታብበው ገበሬ ሲኖር ነው፤ ደሞዝተኛ የሚከፈለው ገበሬ ሲኖር ነው። እኛ በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት የለመድን ሰዎች ነን። አሁን ግን እጃችን ታስሮ፤ ገበሬው አንገቱን ቀልሶ መሬት እየጫረ ነው" ሲሉ የሚገኙበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ላለፉት ሶስት ወራት ኑሯቸውን በሸዋሮቢት ከተማ ለወጣቶች መዝናኛ በተዘጋጀ አዳራሽ ያደረጉ ወይም በሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠለሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ሁሉም ተፈናቃይ ለመሆን የተገደዱት በተመሳሳይ ደም አፋሳሽ ግጭት ነው። ቤተሰባቸውን፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን አሊያም ጎረቤቶቻቸውን ተነጥቀዋል፤ ያፈሩት ጥሪት ወድሟል፤ በተጠለሉበት እርዳታ ቢቀርብላቸውም በቂ ሳይሆን ቀርቶ እየተራቡ ነው።

Äthiopien Shewa Robit IDP
ራሳቸው ተፈናቃይ ሆነው ተፈናቃዮችን የመመገብ ኃላፊነት የተጣለባቸው ወይዘሮ ዓለም "እኛ በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት የለመድን ሰዎች ነን። አሁን ግን እጃችን ታስሮ፤ ገበሬው አንገቱን ቀልሶ መሬት እየጫረ ነው" ሲሉ የሚገኙበትን ሁኔታ አስረድተዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ግን በአካባቢው "253 ሺሕ አካባቢ ተፈናቃዮች አሉ። ለእነሱ የሚሆን ድጋፍ ካሁን በፊት ልከናል። አሁንም እየተጓጓዘላቸው ነው የሚገኘው። የአሁኑ ወር እንደ አገርም የተፈጠረ ችግር ስላለ፤ የእኛም ሰፊ ቁጥር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሁሉም ቦታ ትንሽ መዘግየት አለ። ከዚያ ውጪ ግን ባለፈው ወር ግጭቱ እንደተፈጠረ በሰሜን ሸዋ እና አካባቢው ለግንቦት ወር የሚሆን 34 ሺሕ ኩንታል እህል አሰራጭተናል። አሁንም የሰኔ ወር እየተጓጓዘላቸው ነው። ምን ያህል በቂ ነው? እንደ ቤት ሊሆን አይችልም። እኛ በዓለም የምግብ ድርጅት መስፈርት መሰረት ለአንድ ግለሰብ 15 ኪሎ ግራም ለወር ይሰጣል" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በዕርዳታ ሥርጭት ረገድ ችግር መኖሩ ወደ አካባቢው ከተላከ ቡድን የክልሉ መንግሥት መረጃ እንዳገኘ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። "እነዚህን ነገሮች ማስተካከል እንዳለብን ተነጋግረናል" የሚሉት ኮሚሽነር ዘላለም ከተፈናቃዮቹ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች የማይቀበሏቸው አሉ።

"የተሰጠው ሐብት በትክክል ጥቅም ላይ ውሏል አልዋለም የሚለውን የሚያጣራ አንድ ቡድን ልከን እዛ የፍትኃዊነት ችግር አለ፤ የተላከው ድጋፍ በአግባቡ እየደረሰ አይደለም የሚል ምላሽ አምጥቷል። ግጭቱ የተፈጠረው መጋቢት መጨረሻ አካባቢ ስለሆነ የመጀመሪያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚያዝያ ወር ላይ እንዲህ አይነት ነገር ሊፈጠር ይችላል። እነዚህን ነገሮች ማስተካከል እንዳለብን ተነጋግረናል። እኛ የምንልከው ለዞን እና ለወረዳ ነው። እዚያ አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ ተብሏል። ነገር ግን የግንቦትን ወር 34 ሺሕ ኩንታል እህል ልከናል። የአሁኑ ትንሽ ዘግይቶባቸዋል። ይኸ ከመንግሥት የሚላከውን ነው እንጂ የምናነሳ ህብረተሰቡ እየደገፈ ነው ያለው። ይኸን ያህል ተርበን በጣም ጠቅላላ ረሐብ ውስጥ ነው ያለንው የሚለውን ግን ለመቀበል እቸገራለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዓለም፣ መሐመድ፣ ጀማል እና ዳውድን የመሳሰሉ ተፈናቃዮች የሚሉት ግን ከኃላፊው አስተያየት የተቃረነ ነው። በሸዋሮቢት የወጣቶች ማዕከል ከቀኑ 7 ሰዓት ገደማ ደካክመው የተኙ ተፈናቃዮችን እያሳየ አብዱ "ይኸ የምታየው ሰው ቁርስ ሳይበላ ቀርቶ የተኛ ነው። ምክንያቱም የከተማ አስተዳደሩም በጣም ደከመው" በማለት ችግሩ ብርቱ መሆኑን አስረድቷል።

ጥያቄው አንገብጋቢው የለት ጉርስ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአካባቢው ከተካሔደው እርቅ በኋላ ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገ ነው። ባለ40 ቆርቆሮ የመኖሪያ ቤቱ የተቃጠለበት አብዱ ዳውድ "ብመለስ የት እወድቃለሁ?" የሚል ሥጋት አለው።

Äthiopien Shewa Robit IDP
በሸዋሮቢት ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃይምስል Eshete Bekele/DW

ጀማል ዲሲር ወደ ቀየው ተመልሶ ኑሮውን ማስተካከልን ቢመኝም እንዴት እና መቼ ለሚሉ ጥያቄዎች ግን መልስ ማግኘት ይቸግረዋል። የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ፣ ማረፊያ እና መቋቋሚያን የመሳሰሉ ሳንካዎች ጀማል እና መሐመድ አማንን ከመሳሰሉ ተፈናቃዮች ፊት የተጋረጡ ፈተናዎች ናቸው። "ከዚህ ውጡ ከተባለ የት ነው የምንሔደው? ኪስ የለም ምን የለም። ቤት ነው ኪራይ ላይ ነበርን ቤቱ ተቃጥሏል። መከራያስ ቤት ኪራይ ካገኘን በምን እንከራያለን?" እያለ የሚጠይቀው ጀማል መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ተናግሯል።

በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት በሁለቱም ወገን ተፈጽመዋል የሚባሉ ወንጀሎች ዘግናኝ ናቸው። የማምለኪያ ሥፍራዎች፣ የሕክምና እና የትምህርት አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ወድመዋል። ግጭቱን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፌድራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው በስፋት ተሰማርተው ይታያሉ። የጸጥታ አስከባሪዎቹ ቁጥጥር በተለይ ከሸዋሮቢት እስከ ሰንበቴ ባለው መንገድ ላይ ጥብቅ ነው። ለደም አፋሳሹ ግጭት መፍትሔ ለማበጀት በአካባቢው ዕርቅ እየተካሔደ ቢሆንም በእርግጥ ቀውሱ ዳግም ላለመቀስቀሱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ማረጋገጫ የላቸውም። ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በአካባቢው ባለሥልጣናት የቀረበላቸውን ጥሪ የተቀበሉ የመኖራቸውን ያክል በጥርጣሬ የሚመለከቱት ጥቂት አይደሉም። 

የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ኑሯቸው ለመመለስ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ የተካተቱበት ኮሚቴ አቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በግጭቱ የፈረሱ ቤቶች እና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ወደ 1,5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ