1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኒዠር መፈንቅለ መንግስትና ማስጠንቀቂያዉ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 2015

ማስጠነቀቂያና ዛቻዉ ግን የወለፊንድ ባርቆ ለኒዠር ወታደራዊ ሁንታ ድጋፍ እያስገኘለት ነዉ።ማዕቀብና ማስጠንቀቂይው ግን በመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎቹ ላይ ተጽኖ የፈጠረ አይመስልም

https://p.dw.com/p/4UkbC
Niger Demonstration
ምስል DW

የኒጀር ወቅታዊ ሁኔታ

የኒዠር ወታደራዊ ሁንታ በመፈንቅለ መንግስት የያዘዉን ሥልጣን ከስልጣን ላስወገዳቸዉ ፕሬዝደንት መሐመድ ባዙም እንዲያስረክብ ከዉጪ የሚደረግበት ግፊት እንቀጠለ ነዉ።የምዕራባዉያን መንግስታት በመፈንቅለ መንግስቱ መሪና አስተባባሪዎች ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ እያዛቱ ነዉ።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) በበኩሉ በኒዠር ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን የጣለ ሲሆን ወታደራዊዉ ሁንታ ሥልጣኑን እስከመጪዉ ዕሁድ ደረስ ከስልጣን ለተወገዱት ለመሐመድ ባዙም ካላስረከበ የጦር ኃይል ርምጃ ጭምር እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።ማስጠነቀቂያና ዛቻዉ ግን የወለፊንድ ባርቆ ለኒዠር ወታደራዊ ሁንታ ድጋፍ እያስገኘለት ነዉ።ማዕቀብና ማስጠንቀቂይው ግን በመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎቹ ላይ ተጽኖ የፈጠረ አይመስልም። ይልቁንም የምራባውያን ማሳሰቢያም ሆነ የጎረቤት አገሮቹ ዛቻ  በርክታ ኒጀራውያን አደባባይ በመውጣት ለመፈንቅለ መንግስቱ ድጋፍ እንዲሰጡ እንዳደርጋቸው ነው የተስተዋለው። ቀደም ሲል በያገሮቻቸው ባካሂዷቸው መፈንቅለ መንግስቶች ወደ ስልጣን የመጡት የሚሊና ቡርኪና ፍሶ ወታደርዊ መሪዎችም፤ በኒጀር ላይ የሚደረግ የሀይል ጣልቃ ገብነት በየአገሮቻቸው ላይ የታወጀ ጦርነት ተደርጎ እንደሚወሰድ በመግለጽ፤ ከኒጀር ወታደራዊ መሪዎች ጎን የሚቆሙ መሆኑን  ግልጽ አድርገዋል። የመፈቅለ መግስቱ አስተባብሪና እራሳቸውን የአገሪቱ መሪ አድርገው የሾሙት ጀነራል አብዱርሃማኔ ትናንት በቴሊቬዥን በሰጡት መግለጫም፤ አገራቸው ለማናቸውም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማትንበረከክ በመግለጽ ኔጀራውያን ሊሰንዘር ከሚችል የውጭ ጥቃት አገራቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።  
በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የፕሪዘዳንት ባዙምን መንግስት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ ሊሆን እንድሚችል ነው ብዙዎች የሚናገሩት።  በመንግስትቱ ድርጅት የምራብ አፍርካና የሳህል አካባቢ ተወካይ ሚስተር ሊዎናርዶ ሳንቶስም ወደ ሀይል አማራጩ ፈጥኖ እንዳይገባ ነው ምክረ ሀሳብ የሚሰጡት፡ “ ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ የሀይል አማራጭ አስቸግሪ ነው የሚሆነው። በርግጥ አንዳንድ የምራብ አፍርካ የኢኮኖሚ ማህብረሰብ አባል አገሮች አስፈላጊ ከሆነ ሀይል ለመጠቀም እየተዘጋጁ እንደሆነ አውቃለሁ ። ግን ሁኔታው ተለዋዋጭና አስቸጋሪም በመሆኑ ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለጉ ነው ተመራጩ” በማለት አሳስበዋል። 
ከዚሁ ጋር ተያይዞና  መፈንቅለ መንግስቱን ተክትሎ፤ በማሊና ቡሪኪናፋሶ እንዳለ የሚነገረው ቫግነር የተሰኘው የሩሲያ የግል ወታደርዊ ቡድን ወደ ኒጀርም እንዳይገባና በዚህም ይህች ለአውሮፓውያን ከፍተኛ የኢኮኖሚና ወታደራዊ ስርትራቴጂክ ጥቅም ያላት አገር  ወደሩሲያ እንዳታዘነብል በተለይ በምራባውያኑ ዘንድ ስጋት ያጫረ መሆኑ እየተነገረ ነው። 
በአለማቀፉ የግጭቶች ተንታኝ ድርጅት ክራይሥ ግሩፕ፤ የሳህል ፕሮጀክት ዳይሪክተር ሚስተር ያን ሄርቬ ጃዝኩዌልም ይህ ሊሆን አይችልም የሚባል እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። “ አዲሱ ወታደራዊ መንግስት በስልጣን የሚቆይ ከሆነ አዳዲስ አጋሮችን መሻቱ አይቀርም። በዚህም ምክኒያት ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ለመጠር ፍላጎት ሊያሳድር ይችላል” በማለት ለዚህም ሩሲያ የቫግነር ወታደራዊ ቡድንን ልትጠቀም እንደምትችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 
በሌላ በኩል ደግሞ ሚስተር ባዙም ወደስልጣን መምጣታቸው ያበቃለት ጉዳይ እንድለሆነ የሚናገሩና ተስፋም የሚያደርጉ እንዳሉ ነው የሚታወቀው። የክራይሲስ ግሩፑ ሚስተር ያን ሄርቬያ እንደሚሉት ግን ፕሬዳንቱ ወደ ስልጣን ፈጽሞ ሊመለሱ አይችሉም ባይባልም አስቸጋሪነቱ ግን ግልጽ ነው፤ “ ፕሬዝዳንት ባዙም ወደ ስልጣን ሊመለሱ የሚቺሉበት ሁኒታ ሊኖር ይችላል፡፤ ግን የሚሆን አይመስልም። በዕርግጥ ሩሲያንም ጨምሮ ተመራጩ ፕሬዝድንት ወስልጣናቸው እንዲመለሱ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው።   ግን ይህ ውጫዊ ግፊት ከውስጣዊው ግፊት ጋር ካልተገናኘ የሚሰራ አይመስለኝም” በማለት ፕሬዝዳንቱ ዳግም በስልጣን መንበራቸው የመታየታቸው  ሁኒታ የደበዘዘ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኒጀር በሳህል አሸባሪዎችን ለመዋጋት፣ ስደተኖችንና ፈላስያንን ወደ አውሮፓ እንዳይተላለፉ ለመግታት የአውሮፓ ህብረት ዋና አጋር ሆና የቆየች ሲሆን፤ ይህ መፈነቅለ መንግስት፤ ወዳጅነቱንና አጋርነቱን  እንዳያደፈርሰውና በአካባቢውም ሌላ የህይል አሰላለፍ እንዳያስከትል ምራባውያኑ በተለይም አውሮፓ ሁኔታውን በጥንቃቄና በስጋት ጭምር እይተከታተሉት እንደሆነ በሰፊው ይነገር ይዟል።


ገበያው ንጉሴ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ