1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ሰሞነኛ የጸጥታ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 3 2011

ተደጋጋሚ ግጭቶችን ሲያስተናግድ በከረመው የአማራ ክልል ይስተዋል የነበረው የጸጥታ መደፍረስ እየተሻሻለ መምጣቱን የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና የክልሉ ባለስልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ለ100 ሺህ ሰዎች ገደማ መፈናቀል ምክንያት ለሆኑት ለእነዚህ ግጭቶች መፍትሄ ለማበጀት ከየአካባቢው ማህብረሰብ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/3ILrh
Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

የአማራ ክልል ሰሞነኛ የጸጥታ ሁኔታ

ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች የተፈጠሩ ሲሆን ክልሉም በእነዚህ ቦታዎች ሰላም ማስፈን ተስኖት ቆይቷል፡፡ ከወራት በፊት በክልሉ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ዞኖች በሚኖሩ በአማራና በቅማንት ማሕበረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ጉዳት ደርሷል። በቅርቡ ደግሞ በክልሉ በአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች መካከል በከሚሴና አጣዬ አካባቢዎች እንደዚሁም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በአማራ እና ጉሙዝ ብሔር ተወላጆች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። 

ዶይቼ ቬለ (DW) ያነጋገራቸው የምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪዎች እንደዚሁም የአማራ ክልል ባለስልጣናት ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል። አካባቢዎች ወደ መረጋጋት የተመለሱት በክልሉ አመራር አካላት፣ በህዝቡ እንዲሁም የፀጥታ አካሉ ባደረጉት ጥረት መሆኑንም ገልጸዋል። 

ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮባቸው ከነበሩት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አካባቢዎች አንዱ በሆነው በቆላ ድባ የሚኖሩ ግለሰብ አካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እየሰፈነበት ነው ብለዋል። 
የተፈናቀሉ የመንግስት ሰራተኞችም ወደ ሥራ ገበታቸው በመመለስ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር የመተማ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ መንገድ ላይ መኪና እያስቆሙ ከሚዘርፉ አንዳንድ የሽፍትነት ባህሪይ ካላቸው ሰዎች በስተቀር በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ወደነበረበት እየተመለሰ ነው፡፡

በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በተለይም መተከል በተባለው የሁለቱም ከልል ህዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት በተቀሰቀሰ ግጭት ህፃናትን ጨምሮ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ስጋቱ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ያልተወገደ ቢሆንም የተሻለ ነገር እየታየ መሆኑን የDW ዘጋቢ ከአሶሳ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪ ገልፀዋል፡፡

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በቅርቡ በከሚሴ እና አጣዬ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ግጭቶች ተፈጥረው ህይወት አልፏል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሐሰን እንደሚሉት "በሁለቱም ህዝቦች በኩል ችግር የለም። በርካታ የህዝብ ውይቶች ተደርገዋል። ህብረተሰቡ ወደ ሰላሙ ተመልሷል" ብለዋል፡፡

አጠቃላይ ህብረተሰቡ፣ አመራሩና የአገር መከላከያ ሰራዊት እደረጉ ባለው ከፍተኛ ጥረት የክልሉ ሰላም እየተሻሸለ መሆኑን ደግሞ የአማራ ክልል የሰላም ግንባታና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴየር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ተናግረዋል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል አካባቢ ከነበረው ግጭት አስከፊነት አንፃር በአንዳንድ አካባቢዎች ከስጋት ያልወጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ግን አልደበቁም፡፡

ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ አማራ ክልል ከክልሉ ውጭም ሆነ በክልሉ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ብዙዎቹ ለሞትና ለአካል ጉዳት የተጋለጡ ሲሁን ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ተገኘው መረጃ እንደሚያሳው በምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች በተፈጠረው ግጭት ብቻ ከ6000 በላይ ቤቶች በእሳት ጋይተዋል። 

በአጠቃላይ በሁሉም አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ደግሞ ከ107 ሺህ በላይ የአማራ ክልል ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ቤቶች እየተገነቡና ተፈናቃዮችም በመመለስ ላይ መሆናቸውን ኤጀንሲው አመልክቷል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ