1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ የግማሽ ዘመን ምርጫ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥቅምት 26 2011

«የግማሽ ዘመን ምርጫ» በሥልጣን ላይ ላለዉ ፕሬዝደንት እና ፓርቲ እንደ ሕዝበ-ዉሳኔ የሚቆጠር ነዉ።ከ1932 (እ.ጎ.አ) ወዲሕ በተደረጉ ምርጫዎች በስልጣን ላይ ያለዉ ፕሬዝደንት የሚወክለዉ ፓርቲ በምክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫ ያገኘዉ አምስቴ ብቻ ነዉ።የነገዉ ስድስተኛ ይሆን ይሆን?

https://p.dw.com/p/37hF5
USA Präsidentschaftswahlen 2016 Wähler
ምስል picture-alliance/AP Images/J. Taylor

የአሜሪካ ምርጫ እና እድምታዉ

                    

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ምጣኔ ኃብት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ማሳደጋቸዉን በኩራት ይናገራሉ።የአሜሪካ ሕዝብ እሳቸዉ ያበሻበሹትን ሐብቱን «ጥፋተኞች» ከሚሏቸዉ ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲከላከል አስጠንቅቀዋልም።ዴሞክራቶቹን የወከሉት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ባንፃሩ «ምጣኔ ኃብቱ ካደገ፣ ጀማሪዉ ማነዉ?» እያሉ ይጠይቃሉ።ትራምፕ ፣ አሜሪካ ድንበር አጠገብ የተኮለኮሉ ስደተኞች የብቸኛዋ ልዕለ ኃያል ሐገር «ወራሪ» በማለታቸዉ ኦባማ ይሳለቃሉ።የአሜሪካ ሕዝብ የትኛዉን እንደሚመረጥ ነገ ይወስናል።ተንታኞች፣ በምርጫዉ አንዱ ሌላዉን በግልፅ ማሸነፍ አለማሸነፉን ከወዲሁ በትክክል መተንበይ አልቻሉም።ባንድ ነገር ግን ትራምፕ፤ ኦባማ፤ ተንታኞችም አንድ ናቸዉ።የነገዉ ምርጫ ለአሜሪካ ለዓለምም ወሳኝ ነዉ።ላፍታ እንቃኘዉ።

  የአሜሪካ ሕዝብ ነገ በሚሰጠዉ ድምፅ አንድ መቶ አባላት ካሉት ሴኔት (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት) 35ቱን ይመርጣል።የተወካዮች (ሕግ መምሪያ) ምክር ቤት አባላትን በሙሉ ይመርጣል።435 እንደራሴዎች። የ39 ግዛቶች አገረ-ገዢዎችን ይመርጣልም።በልማዱ «የግማሽ ዘመነ-ሥልጣን» የተባለዉ ምርጫ ብዙም ትኩረት የሚሰጠዉ አልነበረም።የዘንድሮዉ ግን ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሕይወት ዘመናቸዉ ካዩአቸዉ ልዩ ምርጫዎች አንዱ ነዉ።

«ይሕ በሕይወት ዘመናችን ካየናቸዉ በጣም አስፈላጊ ምርጫዎች አንዱ ነዉ።በጣም አስፈላጊ ምርጫ ነዉ።እንደ 2016ቱ በጣም አስፈላጊ ነዉ አልልም።ግን ልዩ ነዉ።በርግጥም በጣም አስፈላጊ ነዉ።እኛ ሁላችንም ታላቅ ድል ከተጎናፀፍንበት ከ2016ቱ ምርጫ ወዲሕ እጅግ ከፍተኛ ጉጉት የተንፀባረቀበት፤ አይቼዉ የማላቀዉ የኤሌክትሪክ ኃይል  አየር ላይ የናኘበት (ምርጫ) ነዉ።»

DW Dokumentationen USA - das Phänomen Trump
ምስል ORF

ትራምፕ ከተቃዋሚነት ይልቅ እንደ ግል ባላንጣ ለሚዩዋቸዉ ለቀድሞዉ ፕሬዝደንት ለባራክ ኦባማም ልክ እንደ ትራምፕ ሁሉ በሕይወት ዘመናቸዉ ካዩት ምርጫ ሁሉ በጣም አስፈላጊዉ ምርጫ ነዉ።ልዩ የመሆኑ ምክንያት ግን ኦባማ ለኢንዲያና ግዛት መራጮች እንዳሉት እንደ ትራምፕ ዓየር ላይ ኤሌክትሪክ መናኘቱን ሥላዩ አይደለም።አሜሪካ «መንታ መንገድ» ላይ በመሆንዋ እንጂ።

 «ከሁለት ቀናት በኋላ፤ ኢንዲያናዎች! ከሁለት ቀናት በኋላ፤ በሕይወት ዘመናችን በጣም አስፈላጊ በምለዉ ምርጫ ድምፅ ትሰጣላችሁ።ፖለቲከኞች ሁል ጊዜ እንደዚሕ እንደሚሉ አዉቃለሁ።ባሁኑ ወቅት ግን በእርግጥም እዉነት ነዉ።ምክንያቱም አሜሪካ መንታ መንገድ ላይ ናት።የሚሊዮኖች የጤና ጥበቃ (መርሕ) በምርጫዉ የሚበየን ነዉ።ለሰራተኛ ቤተሰቦች ፍትሐዊ (መርሕ) በምርጫዉ የሚወሰን ነዉ።ከሁሉም በላይ የሐገራችን ባሕሪ ወይም ሥርዓት የሚወሰነዉ በዚሕ ምርጫ ነዉ።»

USA Obama in Chicago
ምስል picture-alliance/newscom/K. Krzaczynski

የዩናይትድ ስቴትስ ባሕሪ ወይም ሥርዓት በምርጫዉ ይወሳናል ማለት፣ ቱጃሩ ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራም ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ የወለፊንድ የሚያስኬዱት የትልቅ ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መርሕ ይበየናል ማለት ነዉ።ኦባማ እንዳሉት አነስተኛ ገቢ ላለዉ አሜሪካዊ ይጠቅማል የተባለዉን የጤና መርሕ ለመሻር ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያላደረጉት ጥረት የለም።ለሐብታሞች የቀረጥ ቅናሽ በማድረጋቸዉ የመንግሥትን ገቢ ቀንሰዋል።

ስደተኞች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ከማገድ አልፈዉ የሐገሪቱን ድንበር በግንብ ለማሳጠር ወስነዋል።ትራምፕ ለነገዉ ምርጫ በከፈቱት ዘመቻም ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለሚወለዱ ልጆች ዜግነት የሚያሰጠዉን የአሜሪካን የሕገ-መንግሥት አንቀፅ ለመሻር ቃል ገብተዋል።ሰሞኑን ሜክሲኮ ድንበር ላይ የሠፈሩ የደቡብ አሜሪካ ሐገራት ስደተኞችን የሚያግድ ጦር ሠራዊት አዝምተዋል።ስደተኞቹ ለትራምፕ ልዕለ ኃያሉትን ሐገር የሚወሩ ናቸዉ።

                                                 

«ባለፈዉ ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ ጦርን አዝዣለሁ።ሕዝቦች ሆይ! ጨዋታ አይደለም የያዝነዉ።የሚተመዉን (ሕዝብ) እያያችሁ ነዉ።ወረራ ነዉ።አይደለም? ወረራ ነዉ።ብዙ ነገር እየተደረገ ነዉ።እራሳችሁን ጠይቁ።እንዴት ይሕ ሊሆን ቻለ? ሁለተኛዉን ቅፍለት አይታችኋል?በነገራችን ላይ  ለሁንዱራስ፣ለኤልሳልቫዶር፤ ለነዚሕ ሐገራት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንከፍላለን።በነገራችን ላይ በቅርቡ ይሕን ክፍያ እናቆማለን።ምንም አላደረጉም።ለኛ ምንም አላደረጉልንም።»

የችግረኛ ስደተኞቹን ፍልሰት ዶናልድ ትራምፕ «ወረራ» ማለታቸዉን፤ ጦር ማዝመታቸዉንም ባራክ ኦባማ ይሳለቁበታል።

                           

USA Präsidentschaftswahlen 2016 Wähler
ምስል picture-alliance/AP Images/H. Rousseau

«ለምርጫዉ ሁለት ሳምንት ሲቀረን አሁን፤ ለአሜሪካ እጅግ አስጊዉ ነገር፤ የተጎሳቆሉት ደሐ፤ረሐብተኛ ስደተኞች ከአሜሪካ ድንበር ብዙ ማይል ርቀት ላይ መስፈራቸዉ ነዉ።-----ተጨማሪ የሥራ ዕድል ማጣት፤ልጆቻችንን እንዴት እንደምናስተምር? ከገዳዮች እጅ ጠመጃ ማስፈታት (ለነሱ) የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም።አስጊዉ ነገር በብዙ ሺሕ ማይል ርቀት ላይ የሚገኙት ሰዎች ናቸዉ።በነገራችን ላይ ጀግኖች ወታደሮቻችንን ለፖለቲካ ዓለማ ማስፈፀሚያ ሊጠቀሙባቸዉ እያዘመቷቸዉ ነዉ።የጦር ሠራዊቱ ወንድ እና ሴት አባላት ከዚሕ የተሻለ ተልዕኮ በተገባቸዉ ነበር።»

ምርጫዉ፤ የምርጫ ዘመቻዉ በመጋጋሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ብዙ ምክንያቶችም ልዩ ነዉ።ለልዩዉ ምርጫ እስከ ትናንት ለተደረገዉ ዘመቻ ለማስታወቂያ የወጣዉ ገንዘብም ብዙ ነዉ።ተፎካካሪዎች የስደተኞችን ጉዳይን ለሚመለከቱ ማስታወቂያዎች ብቻ 124 ሚሊዮን ዶላር ከስክሰዋል።የዛሬ አራት ዓመት በተደረገዉ ምርጫ ስደተኞችን ለሚመለከት የምርጫ ማስታወቂያ የወጣዉ 24 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር።  

የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ለፕሬዝደንታዊ ይሁን ለምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ ድምፅ የሚሰጠዉ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ሥለ ዉጪ በሚያራምዱት መርሕ ላይ ተመስርቶ ዓይደለም።አብዛኛዉ መራጭ ድምፅ የሚሰጠዉ፤ ተመራጮችም በምርጫ ዘመቻቸዉ የሚያነሱት ጉዳይም በአብዛኛዉ በሐገር ዉስጥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸዉ።የሁሉም ምርጫዎች ዉጤት ግን የዩናይትድ ስቴትስን የዉስጥም የዉጪም መርሕ በዉጤቱም የዓለምን ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ  ሒደት መበየኑ አያጠያይቅም።የዘንድሮዉ ምርጫ ልዩ የሚሆነዉም ዶናልድ ትራም ገና ሁለት ዓመት ባልሞላ ዘመነ ሥልጣናቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ የመሠረተች እና የምትመራዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዉሳኔ ሳይቀር እየሻሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማፍረሳቸዉ ጭምር ነዉ።

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ወዲሕ በዩናይትድ ስቴትስ፤ በቻይና እና በሩሲያ መካከል የተፈጠረዉ መቀራረብ የዓለምን ሠላም በጋራ ለማስከበር ይረዳል የሚል እምነት በማሳደሩ ብዙ ሲደነቅ፤ ሲወደስ ነበር።ትራምፕ ግን ሰሜን ኮሪያን የኒክሌር ቦምብ (ትጥቅን) ለማስፈታት ቆርጠዉ መነሳታቸዉን እየተናገሩ፣ ሰሜን ኮሪያን ለማግባባት ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍ የምትችለዉን ቻይናን በቀረጥ ጭምሪ፤በደሴቶች ግዛት እና በንግድ ሰበብ ይቆነጥጣሉ። የሶሪያዉን ጦርነት ለማስቆም እንደሚሹ ይናገራሉ።የጦርነቱን ሚዛን ባሻት የምትዘዉረዉን ሩሲያን ሲፈልጋቸዉ በማዕቀብ፤ ሲሻቸዉ በቀረጥ ጭማሪ ይቀጣሉ።ደግሞ በተቃራኒዉ የሩሲያዉን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን ሥራ እና ችሎታ ያደንቃሉ።

እስራኤል እና ፍልስጤምን ማስታራቅ እንደሚፈልጉ አስታዉቀዋል።ግን በተቃራኒዉ ፍልስጤሞች እንደ ርዕሠ-ከተማቸዉ፤የድፍን ዓለም ሙስሊም፤ ክርስቲያን እና የሁዲ እንደ ቅዱስ ከተማዉ የሚቆጥራትን እየሩሳሌም የእስራኤል ግማደ ግዛት ናት ብለዉ አፀድቀዋል ።

ትራምፕ ዛሬ ለሕዝባቸዉ ያቀረቡት «የምርጫ ዋዜማ ስጦታም» ዓለም አቀፍ ሕግ እና ስምምነትን ጥሰዉ በኢራን ላይ የጣሉትን ተጨማሪ ማዕቀብ ነዉ።

«ዩናይትድ ስቴትስን ለአንድ ወገን ካዳላዉ አሳፋሪ የኢራን ሥምምነት አዉጥቻታለሁ።እና ኢራን በጣም የተለየች ሐገር ሆናለች።ኢራን ባለፉት ስድት ወራት የተለየች ሐገር አልሆነችም።ይሕ ይታመናል?ሥልጣን ስይዝ ፣ ጥያቄዉ (ኢራኖች) መላዉን መካከለኛዉ ምሥራቅን ለመቆጣጠር ምንያ ጊዜ ይፈጅባቸዋል የሚል ነበር።ወደ ሜድትራኒያን እያማተሩ ነበር።አሁን ግን ወደ ሜድትራኒያን ማየት አይችሉም።»

USA Präsidentschaftswahlen 2016 Wähler
ምስል picture-alliance/dpa/E. S. Lesser

ሌላዉ ቀርቶ  ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ፤ተባባሪ እና ተሻራኪ ከነበሩት ከምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት ጋር በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ፤ በዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ዉል፤ በኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር በሽቀጦች ቀረጥ ሰበብ የገጠሙት አተካራ ዓለምን የምታስተባብረዉን ሐገር ከቅርብ ታማኞችዋ ሳይቀር እየነጠላት ነዉ።ከትራምፕ ጋር በየሰበብ አስባቡ መነታረክ የሠለቻቸዉ አዉሮጶች ከሰባ ዘመን በላይ በጥብቅ ያስተሳሰራቸዉን መርሕ በሌላ የሚቀይሩበትን ብልሐት እያሰላሰሉ ነዉ።

በዉጪ መርሕ የጀርመን ማሕበረሰብ የዩናይትድ ስቴትስ ጉዳይ አጥኚ ዮሴፍ ብራሜል እንደሚሉትም የአሜሪካ መሪ፤ መርሕ፤ የምርጫ ዉጤት ማንም ሆነ ምን አዉሮጳ ለራስዋ በራስዋ መቆም አለበት።

«ብዙ አትጠብቁ፤ እርምጃ ዉሰዱ፤የአሜሪካ ቁጥጥር እና ምዘና ለኛ ችግር መፍትሔ አይሆንም።ለእራሳችን እራሳችን ማሰብ አለብን።እንደ አዉሮጳዊ በራሳችን መተማመንን እና በነፃነት ማሰብን መማር አለብን።»

ለአሜሪካም ቢሆን ያሁኑ ምርጫ ዉጤት ምንም ሆነ ምን የትራምፕን መርሕ ብዙ ያስለዉጣል ተብሎ ዓይታመንም።ይሁንና በምርጫዉ ተቃዋሚዎቹ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች ሲሆን በሁለቱ ካልሆነ በአንዱ ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫዎች ካገኙ ትራምፕ፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴዎችን አብላጫ ድምፅ ይዘዉ በአሜሪካ ሕግ ላይ እንዳሻቸዉ «እንዳይጋልቡ ልጓም» ሊያበጁላቸዉ ይችላሉ ነዉ ተስፋ-እምነቱ።

የቅድመ ምርጫ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት የዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች የህዝብ ተወካዮችን፣ ሪፐብሊካኖች ደግሞ የሕግ መወሰኛ ወይም የሴኔቱን አብላጫ መቀመጫዎች ይይዛሉ።እስካሁን በትክክል የሚታወቀዉ ግን ዉጤቱ እስከ ነገ ማታ አለመታወቁ ነዉ። «የግማሽ ዘመን ምርጫ» በሥልጣን ላይ ላለዉ ፕሬዝደንት እና ፓርቲ እንደ ሕዝበ-ዉሳኔ የሚቆጠር ነዉ።ከ1932 (እ.ጎ.አ) ወዲሕ በተደረጉ ምርጫዎች በስልጣን ላይ ያለዉ ፕሬዝደንት የሚወክለዉ ፓርቲ በምክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫ ያገኘዉ አምስቴ ብቻ ነዉ።የነገዉ ስድስተኛ ይሆን ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋዓለም ወልደየስ