1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ አንዳርጋቸው መፈታትና የመረጃ መጣረሶች

ዓርብ፣ ግንቦት 24 2010

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ጥንቅራችን ማጠንጠኛ ነው። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ይለቀቃሉ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ብተለያዩ ሰዎች የተለያዩ መረጃዎች ሲተላለፉ ነበር። መረጃዎቹ መጣረስ ተስተውሎባቸዋል። ​​​​​​​አሸባሪ ተብለው የነበሩ አንዳንድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ክስ በኢትዮጵያ ተቋርጧል።

https://p.dw.com/p/2yfwF
Äthiopien Oppositioneller Andargachew Tsige  begnadigt
ምስል DW/Yohannes Gebreegziabher

ከእስር የተፈቱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

የመረጃ ፍሰት ዝግ አለያም እጅግ ጠባብ በሆነባቸው  ሥፍራዎች ነዋሪዎች የመረጃ ፍሰት ክፍተትን ለማጥበብ ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። በተለይ ደግሞ የመብት ተቆርቋሪዎች እና ጋዜጠኞች ያለ መታከት ክፍተቱን ለመሙላት ሲጣጣሩ ይታያል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሊፈቱ ነው ከተባለበት ቀን አንስቶ እስከተፈቱበት ድረስ የታየው ውዥንብር ግን እጅግ የጎላ ነበር። ከታዋቂ ሰዎች አንስቶ ተነባቢ እስከኾኑ የመገናኛ ዘርፎች ድረስ ስህተቱ ተስተጋብቷል። በኬንት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎች መምህር የኾኑ ኢትዮጵያዊ ረዳት ፕሮፌሰረን አነጋግረናል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችንም አሰባስበናል።  

ከተጨባጭ መረጃዎች እና እውነቶች ይልቅ ስሜት የሚነዳቸው አስተያየቶች እና መላ ምቶች ፈረንጆቹ (Post-truth world) የሚሉት ለብዙ ስህተት ይዳርጋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን፣ 2010 ዓም ከእስር ከመፈታታቸው በፊት የኾነውም ይኸው ነው። ከአራት ዓመት ግድም እስር በኋላ የመፈታታቸው ዜና ዕውን ከመኾኑ ቀደም ብሎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በርካታ በብዥታ የተዋጡ መረጃዎችን ሲያስተላልፉ  ነበር።

ይኽን በመታዘብ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መረጃ አለን የሚሉ ሰዎች በተለይ ታዋቂ የኾኑት ሰከን ሊሉ ይገባል ብለዋል። ብዙዎች የየራሳቸውን መላ ምት እየሰጡ ለስህተት የተዳረጉበት ክስተት ለትችት እና ስላቅ ዳርጓቸዋል። 

Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

አቶ አንዳርጋቸው ከመፈታታቸው በፊት ተፈቱ የሚለው የተሳሳተ መረጃ ያታከተው ናዝራዊ በትዊተር ገጹ የሚከተለውን ብሏል። «ተፈታ ተፈታ ተፈታ ከሚል ውጪ ማስረጃ ይዞ ትልቁን እስር ቤት ተቀላቀለ የሚል ዜና ያለው ይቀስቅሰኝ። ካላየሁ አላምንም» በሚል በተሳሳተ መረጃ መሰላቸቱን ቅዳሜ እለት ጽፏል። አቶ አንዳርጋቸው ማክሰኞ መፈታታቸው እርግጥ እስኪሆን ድረስም የተሳሳቱ መረጃዎች መፍሰሳቸውን አላቋረጡም ነበር። 

«ሰዉ ሁሉ ባለምንጭ ሆኖ የለ እንዴ? ይህን ሁሉ ምንጭ ይዘን፥ መጠማታችን ግን እሚገርም ነው። በዚህ አያያዛችን ግን ምንጭና ተንታኝም ለጅቡቲ የምንልክበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም» ሲል የተሳለቀው ደግሞ ደራሲ ዮሐንስ ሞላ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ ኬንት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ጥናቶች መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ወርቃለማሁ ወርቅነህን በአቶ አንዳርጋቸው የመፈታት ዜና ስለነበረው ውዥንብር አንስተው ሲናገሩ መረጃዎችን የማጣራት ጥንቃቄ መደረጉ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

Äthiopien Oppositioneller Andargachew Tsige  begnadigt
ምስል DW/Yohannes Gebreegziabher

አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የእስረኞች መፈታት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር መልካም ጅምር ነው ሲሉ ብዙዎች አወድሰዋል። መልካም ፍሬ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፌስቡክ ላይ ካሰፈራቸው አምስት ነጥቦች በአንደኛው የሚከተለውን ብሏል። «ብዙ ታሳሪዎች እየተፈቱ ፤ ዘግናኝ ክሶችም ከዜጎች ላይ እየተነሱ ነው። አገራችንም ሙሉ ለሙሉ እንድትፈታልን እንፈልጋለን። ሁሉም ነጻ ሆኖ የሚኖርባት እና ያቅሙንም ሳይሰስት የሚያበረክትላት አገር እንድትኖረን እንመኛለን። እስካሁንም በተደረገው ደስተኞች ነን» ብሏል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዓመታዊ የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ጠቀዋል የሚል መልእክት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተንሸራሽሯል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ በዝግጅቱ ላይ መሳተልፍ አለባቸው ወይንስ የለባቸውም በሚልም ብዙዎች የየራሳቸውን የአምደ መረብ መጠይቅ ሲያደርጉም ታይቷል።

በሌላ መልኩ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በነዶክተር መረራ ጉዲና መዝገብ ተከሰዉ የነበሩት ኢሳት ቴሌቪዢን ጣቢያ፤ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) የዶክተር ብርሐኑ ነጋ እና የአቶ ጀዋር መሐመድን ክስ ማንሳቱም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ኾኖ ዘልቋል።

ሙሉ ዘገባው ከታች የድምጽ ማገናኛው ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ