1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ችግሮች

ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2011

መዲናይቱ አዲስ አበባን ሰንገው ካያዟት ችግሮች መካከል አንዱ የትራንስፖርት እጥረት አንዱ ነው። ይህን ችግር ይፈታል በሚል ከሦስት ዓመት በፊት ሥራ እንዲጀምሩ የተደረጉት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡሮች በየጊዜው በብልሽት እና በኃይል እጥረት መቆማቸው ደግሞ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/38gFC
Addis Abeba Äthiopien Bahn Straßenbahn Haltestelle
ምስል picture-alliance/dpaMarthe van der Wolf

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ችግሮች

ከሳምንታት በፊት በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተለቀቀ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ በሩ የተከፈተ አንድ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ይታያል። ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ባለው ባቡር ተጨማሪ ሰዎች ለመግባት ይተናነቃሉ። ቀጥሎ ባለው በርም ያለው የባሰ እንጂ ከዚህኛው የተሻለ አይደለም። በሁለተኛው በር ለመግባት የሚታገሉትን ጭርሱኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ አባላት ሲያግባቧቸው እና ስርዓት ለማስያዝ  ሲጥሩ ይስተዋላል። 

ከዚህ ቀደም በአንበሳ አውቶብስ ይታይ የነበረው መሰል የመጨናነቅ እና የመጓጓዣ እጥረት ችግር የባቡር አገልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎችም አዘውትሮ እያጋጠማቸው መሆኑን ሲያማርሩ መስማት እየተለመደ መጥቷል። የዛሬ ሦስት ዓመት አገልግሎት የጀመረ ሰሞን በየፌርማታው በየ10 ደቂቃው ይደርሳል የተባለለት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አሁን እንኳን በተባለበት ሰዓት ሊመጣ ተሳፋሪ እየጠበቀው ዘግቶ ሁሉ ያልፋል እያሉ ተጠቃሚዎች ያማርሩታል።

እንዲህ አይነት ነገር ከታዘቡት ውስጥ ባሳዝነው ደሳለኝ አንዱ ነው። በሳምንት ከሶስት እስከ አራቴ ባቡር እንደሚጠቀም የሚናገረው ባሳዝነው በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ላይ የታዘባቸውን ችግሮች  ይዘረዝራቸዋል። የባሳዝነው አይነት የተጠቃሚዎች እሮሮ የሚደመጥበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት 475 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጥቶበታል። ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ እንደሚመለክተው የአዲስ አበባ ባቡሮች በቀን ከ110 ሺህ እስከ 120 ሺህ ለሚሆን ህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

Addis Abeba Äthiopien Bahn Straßenbahn Haltestelle
ምስል picture-alliance/dpaMarthe van der Wolf

ከቻይና ሀገር በተገዙ 41 ባቡሮች ስራውን የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንደማይሰጥ ትችት ይቀርብባታል። ለዚህም በብልሽት ምክንያት መስራት ያቆሙ ባቡሮችን በማሳያነት የሚጠቅሱ ታዛቢዎች አሉ። በጉዞ ላይ እያሉ በየጊዜው ወገቤን የሚሉ ባቡሮች መበራከትም በፕሮጀክቱ ላይ ጥያቄ ማስነሳታቸው አልቀረም። የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ላይ ችግሮች እንደሚታዩ ይቀበላሉ። የችግሮቹ መንስኤዎች የኃይል መቆራረጥ እና የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ነው ይላሉ። 

በየቀኑ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጓጓዙበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በዋነኛነት የሚጠቀመውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከፋፍልበት የራሱ ጣቢያዎች እንዳሉት አቶ ደረጀ ይናገራሉ። በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ በእነርሱ ላይም ተጽዕኖ እንደሚያመጣ እና ባቡሮችን ድንገት በየቦታው እንዲቆሙ እንደሚያስገድዳቸው ያስረዳሉ።

ለአዲስ አበባ ባቡሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆን ሌላው በምክንያትነት የሚነሳው የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ነው። በዚህም ምክንያት አገልግሎት ሊሰጡ ይገባቸው ከነበሩት 41 ባቡሮች ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንደማይሰሩ የቅርብ ጊዜ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር በበኩላቸው አሁን በስራ ላይ ያሉት ከ22 እስከ 26 የሚሆኑ ባቡሮች ናቸው ይላሉ። ስማቸው እንዳይገለጽ የሚሹ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የጥገና ባለሙያ በከተማይቱ በሁለት አቅጣጫዎች ከተዘረጋው የባቡር መስመር ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው ባቡሮች ያሉት በአንደኛው እንደሆነ ያስረዳሉ። 

እንደጥገና ባለሙያው ከሆነ ከወራት በፊት ለማግኘት አስቸጋሪ የነበሩ ጥቃቅን የባቡር መለዋወጫዎች አሁን በመገዛታቸው ችግሩ ተቃልሏል። ሆኖም አሁንም ትልቅ ችግር የሆነው ባቡሩ በሐዲዱ ላይ የሚሽከረከርበት ክፍል (wheel) በጥገና ማዕከላቸው አለመኖር እንደሆነ ይገልጻሉ። የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ግን በባለሙያው ገለጻ አይስማሙም። ችግሩ ያለው ሌሎች መለዋወጫዎች ላይ ነው ባይ ናቸው። ይህን ያህል ትልቅ ፕሮጀክት ሲታሰብ እንዴት መለዋወጫ ላይ ቅደመ ዝግጅት አልተደረገም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። 

Addi Abeba Straßenbahn
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

አቶ ደረጀ የገንዘብ ጥያቄ ቀረበ ያሉት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ያቀረበውን የድጎማ በጀት ነው። ፕሮጀክቱ ለባቡር መለዋወጫ ዕቃዎች ግዢ እና ለሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎች የሚውል የ1.5 ቢሊዮን ብር ድጎማ የጠየቀው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር። መስሪያ ቤታቸው ይህን ድጎማ እስካሁን እንዳላገኘ አቶ ደረጀ ገልጸዋል። ባቡሮቹ የገጠማቸውን የመለዋወጫ ችግር ለመፍታት “ፍላጎት እና ሀገራዊ አቅምን በማጣጣም የውጭ ምንዛሬን በማፈላለግ” ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነም ያስረዳሉ። 

ከአዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት ጋር ሌላው ተያይዞ የሚነሳው ችግር የመረጃ መለዋወጫ መስመሮች ማለትም የኮሚዩኒኬሽን እና ሲግናል ገመዶች ብልሽት ነው። እነዚህ ገመዶች የተዘረጉት በአንድ የቱርክ ኩባንያ እና በሀገር በቀሉ የብረታ ብረት እና ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አማካኝነት ነበር። አሁን ችግር እየታየባቸው ናቸው የሚባሉት በሜቴክ የተመረቱት ገመዶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በገመዶቹ ላይ ብልሽት መታየቱን የሚቀበሉት አቶ ደረጀ ጉዳዩ ግን ከእርሳቸው መስሪያ ቤት ይልቅ የሚመለከተው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ነው ይላሉ። 

የአዲስ አበባ ባቡር ቀላል ፕሮጀክት የገጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ገቢውን የሚያሳድግበት አዲስ ጥናት እያስጠና እንደሆነ አቶ ደረጀ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የባቡር አገልግሎትን የሚጠቀሙ ሰዎች እንደየርቀቱ ሁለት፣ አራት እና ስድስት ብር የሚከፍሉ ሲሆን በአዲሱ ጥናት ይህን ለማስቀረት መታሰቡን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በሁሉም መስመሮች ወጥ የሆነ ክፍያን በማስከፈል አሁን የሚታዩ ማጭበርበሮችን ለመግታት መታቀዱን ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት ከሚያጓጉዛቸው መንገደኞች በቀን ከ300 እስከ 350 ሺህ ብር እንደሚያስገባ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ተስፋለም ወልደየስ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ