1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ ከንቲባ ንግግር የገጠመው ውግዘት

ሐሙስ፣ መጋቢት 7 2015

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ሰበብ እየተፈለገ ሲፈጸም የነበረው ማዋከብ፣ እንግልትና ማጉላላት መሻሻል ይታይበታል ተብሎ ተስፋ ሲደረግ "የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ፣ ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል የሆነ ንግግር ነው" ሲሉ እናት ፓርቲ ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/4Onc5
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በዚሁ ሳምንት ሲጀምር የመስተዳድሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዳርቻዎች ወደ ከተማዋ ይደረጋል ያሉት ፍልሰት የከተማዋ የፀጥታ ስጋትም ወደ መሆን መሸጋገሩን ለምክር ቤት አባላት ገልፀዋል።"ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግሥትን በመጣል በኃይል ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለመም ነው" ነው በሚል የክስተቱን አዝማሚያ አብራርተዋል። ይህንን የከንቲባዋን ንግግር ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) ከንቲባዋ "አደገኛ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ" ማድረጋቸውን በመግለጽ  "አገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው" ሲል ጉዳዩን ተቃውሞታል።
እነት፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ የተባሉ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ንግግር "የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ፣ በከፍተኛ ሴራና ፍረጃ ለበለጠው የዘር ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል ነው" በማለት አውግዞታል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማክሰኛ ዕለት ሲጀምር ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ከተማዋ ከፍተኛ "ፍልሰት" አለ በሚል መናገራቸው እና ይህም መንግሥትን የመቀየር ተልእኮ ጭምር ያለው እንቅስቃሴ መሆኑን መግለፃቸው ከተወሰኑ ፓርቲዎች ተቃውሞ አስነስቶበታል።
"ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ይህን መሰል አደገኛ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ማድረጋቸው አገረ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው" በማለት ሪፓርቱን ያጣጣለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ዜጎች በነፃነት ተዘዋውረው የመሥራት እና የመኖር ሰብዓዊ መብት ያላቸው መሆኑ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች ድንጋጌዎች እና በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት ጭምር የተረጋገጡ ተፈጥሯዊ መብቶች ሆነው ሳለ "እስካሁን ሲፈፀሙ ለነበሩ" ላላቸው በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ከለላ የሚሆን አደገኛ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው" ሲል ገልጾታል። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ሹምዬ ጉዳዩን አገር ወዳድ የሆነ ሁሉ እንዲያወግዝ ሲሉ ጠይቀዋል።
ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ሰበብ እየተፈለገ ሲፈጸም የነበረው ማዋከብ፣ እንግልትና ማጉላላት መሻሻል ይታይበታል ተብሎ ተስፋ ሲደረግ "የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ፣ በከፍተኛ ሴራና ፍረጃ ለዘር ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን የማሸማቀቅ አካል የሆነ ንግግር ነው" ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ እናት ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ የተባሉ ፓርቲዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልፀዋል። የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ነገሩ "ቁጣን የሚቀሰቅስ" ነው በማለት የፓርቲዎቹን አቋም ተናግረዋል።
መንግሥት እና ገዥው ፓርቲ "ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከሥልጣን እንዲያነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ" ሲል አብን ጠይቋል።
"የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፋፋይ ንግግሮችን ወደ ጎን ብሎ አንድነቱን እንዲያጸና" ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጥሪ አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጉባኤውን ባደረገበት ዕለት የከተማዋን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ የተባሉት አካላት ዋነኛ መነሻቸው አማራ ፣ ቀጥሎ ደቡብ ከዚያም ኦሮሚያ ክልሎች መሆናቸው ተገልጿል። ከሁሉም ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የተባሉት ኃይሎች በተለይ የበዓላት ጊዜን ተንተርሶ ሰላም ለማደፍረስ ወደ ከተማዋ እንደሚገቡ እና የሪፖርቱም መነሻም ይህ መሆኑ ተገልጿል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ