1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ለህጻናት ኦክስጅን መጥኖ የሚሰጥ መሳሪያ የሰሩ አሸንፈዋል

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2011

በአሜሪካ ኤምባሲ አዘጋጅነት ለወራት የዘለቀው አገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎቹ ታውቀው ባለፈው ቅዳሜ ተጠናቅቋል። በውድድሩ ወጣቶች በማኅበረሰባቸው ያስተዋሉትን ችግር ለመፍታት ያስችላል ያሏቸውን የፈጠራ ሥራዎች አቅርበዋል። ለመጨረሻው ውድድር ከቀረቡ 31 ፕሮጀክቶች ውስጥ ሦስቱ ተመርጠውም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

https://p.dw.com/p/35Wlt
Äthiopien nationaler Innovationswettbewerb SolveIT
ምስል US Embassy Addis Ababa

ለህጻናት ኦክስጅን መጥኖ የሚሰጥ መሳሪያ የሰሩ አሸንፈዋል

የጅማ ሆስፒታል በዓመት ወደ 4,500 ገደማ ለሚሆኑ እናቶች የማዋለድ አገልግሎት ይሰጣል። የሆስፒታሉ የጨቅላ ሕጻናት የጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግርም ሆነ በበሽታ ምክንያት ሕይወታቸው ለአደጋ ለተጋለጠ ሕጻናት ከፍተኛ ክትትል ያደርጋል። በ1930 ዓ. ም. የተመሰረተው ይህ ሆስፒታል እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሁሉ የህክምና መሳሪያዎች እጥረት አሉበት። ዘመናዊ የሚባሉ መሳሪያዎችም እንደልብ አይገኙም።

ሆስፒታሉን የሚረዱ በጎ ፍቃደኛ ኢትዮጵያውያን እና አሜሪካውያን የህክምና ባለሙያዎች የመሳሪያዎችን ችግር ልብ ብለዋል። ለዚህም ይመስላል የዛሬ አራት ዓመት ግድም ወደ ስፍራው ሲያቀኑ ጨቅላዎቹ ሕጻናት እንደልብ እንዲተንፍሱ የሚያግዙ መሳሪያዎችን ይዘው የሄዱት። ከሁለት ዓመት በኋላ የጨቅላዎቹን ማቆያ ክፍል የማየት ዕድል ያገኘው ነብዩ አህመድ የሕጻናቱን አተነፋፈስ ከሚያግዙ መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ አንድ ችግር ይመለከታል። ሆስፒታሉን በበላይነት በሚያስተዳድረው በጅማ ዩኒቨርስቲ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የነበረው ነብዩ ጥያቄ ይጠይቃል። “በዚያ ጊዜ ላይ አንድ ሕጻን ልጅ ኦክስጅን ከሲሊንደር ቀጥታ ሲሰጠው አየሁኝ። እና በዚያ አጋጣሚ አጠገቤ የነበረውን ነርስ ይሄ ነገር ጉዳት የለውም ወይ? ብዬ ጠየቅኩት። አይ ይጎዳል እንጂ አለኝ። እና ታዲያ ለምንድነው እንደዚህ የሚሰጠው ብዬ በምጠይቀበት ሰዓት ሌላ ምንም ዓይነት መሳሪያ የለንም ምን እናድርግ የሚል መልስ ሰጠኝ። ከዚያ በኋላ ነበር ጥናት ማድረግ የጀመርኩት። እና የዚያን ዕለት ማታ ገብቼ ኢንተርኔት ላይ የተጻፉ ጽሁፎች ሳይ ትክክለኛ ያልሆነ የኦክስጅን አሰጣጥ በጣም ጎጂ እንደሆነ አወቅሁኝ” ይላል ነቢዩ በወቅቱ የጠየቀውን እና ያገኘውን ምላሽ መለስ ብሎ ሲያስታውስ። 

Äthiopien nationaler Innovationswettbewerb SolveIT
ምስል iCog Labs, Solve IT

ከክሊንተን ፋውንዴሽን የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው በመላው ዓለም በኦክስጅን አቅርቦት እጦት ምክንያት በዓመት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 120 ሺህ ሕጻናት ሕይወታቸውን ያጣሉ። በኢትዮጵያም የመጀመሪያ ወራቸውን እንኳ ሳይደፍኑ በአጭሩ የሚቀጩ 60 ሺህ ሕጻናት ሞት ከዚሁ ከኦክስጅን እጦት ጋር የተያያዘ መሆኑን ድርጅቱ ያመለክታል። በጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ለሚደረጉ ጨቅላዎች ወሳኝ የሆነው ኦክስጅን ከመጠን በላይ ከተሰጠ ግን መዘዙ ብዙ ነው። የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የሕጻናት ሀኪም ዶ/ር ኤርሚያስ አበባው ጉዳቶቹን ይዘረዝራሉ።  

“አንደኛው እና ቶሎ የምናየው ውጤቱ ምንድነው? የማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ነው። እርሱ ላይ በአጭር ጊዜ የሚስተዋለው በማንቀጥቀጥ የሚታይ መቃወስን ሊፈጥር ይችላል። ከዚያ ባለፈ በረጅም ጊዜ የሳንባና የመተንፈሻ ቱቦዎች ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ይኖራል። ሳንባ ላይ በተለይ ይሄ ሳንባ ውስጥ ያሉ የአየር ከረጢቶች ላይ ጤናማ ሴሎች ያልተለመደ አይነት ለውጥ በማምጣት ወይም ጠባሳ በመፍጠር የአተነፋፈስ ስርዓቱን ያዛባል። እንደገና ከዚህ የተነሳ የአየር መተንፈሻ ቱቦዎች ብግነትን ሊያመጣ ይችላል። እንደገና ደግሞ በምንተንፍስበት ሰዓት የመተንፈሻ ዝለትን የማምጣት ተጽዕኖ ይኖረዋል። 

ሌላው ደግሞ ዓይን ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ነው። ዓይን ላይ የሚያመጣው አንደኛው ተጽዕኖ በምናይበት ሰዓት  ለዕይታ የሚጠቅመው retina የሚባል የመጨረሻው የዓይን ክፍል አለ። ይሄ retina ላይ ያሉ የደም ስሮች በተለይ ጨቅላ ሕጻናት ላይ ከ7 ወር በፊት እና ክብደታቸው ከ1.5 በታች የሆኑ ሕጻናት ላይ ዕድገቱ የሚቀጥል ነው የሚሆነው። ኦክስጅን ከመጠን በላይ በሚሰጥበት ሰዓት እነዚህ የደም ስሮች እንዲኮማተሩ  ያደርጋል። በዚያ ምክንያት ለአንድ ቀን ሁለት ቀን የበዛ ኦክስጅን፣ በተለይ ከ40 በመቶ በላይ በሚሰጥበት ሰዓት እና ቀጥሎም ይሄ ኦክስጅን በሚቋረጥበት ሰዓት በደም ስሮቹ ላይ ባለ በሚያስከትለው ችግር ምክንያት የደም ስሮች መፈንዳት ያመጣና የዓይን ውሃዎች ላይ ደም እንዲቋጥር በማድረግ ይሄ  retina የሚባለው ከዓይን ላይ እንዲላቀቅ እና በረጅም ጊዜ ደግሞ ዕይታን ሊያሳጣ የሚችል ጉዳት ይኖረዋል” ይላሉ ዶ/ር ኤርሚያስ።

Äthiopien nationaler Innovationswettbewerb SolveIT
ምስል iCog Labs, Solve IT

የኦክስጅን መጠን መብዛት በሕጻናት ላይ የሚያስከትለውን የጤና ጠንቅ ከንባቡ የተረዳው የጅማ ዩኒቨርስቲው ነቢዩ ችግሩን የሚፈታ መሳሪያ ለመስራት ያስባል። የመመረቂያ ፕሮጀክቱ ለማድረግ ከጓደኞቹ ጋር እየተማከረ ባለበት ወቅት ዩኒቨርስቲው ግቢ የተለጠፈ አንድ ማስታወቂያ ይመለከታል። ማስታወቂያው ወጣቶች የማኅበረሰባቸውን ችግር የሚፈታ የፈጠራ ሥራ ይዘው እንዲወዳደሩ ጥሪ የሚያቀርብ ነበር። በአሜሪካ ኤምባሲ ጠንሳሽነት እና አይኮግ ላብስ በተሰኘ የግል ድርጅት አስተባባሪነት የተዘጋጀው Solve IT የተሰኘው ይህ ውድድር ወጣቶች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በሶፍትዌርም ሆነ በሀርድዌር መፍትሄ እንዲያበጁ ይጠይቃል። 

የ23 ዓመቱ ነቢዩ ከሁለት የዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር በመሆን በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ይመዘገባል። እንደ እርሱ ሁሉ በጅማ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ፣ መቀሌ እና ሰመራ ከተሞች ያሉ 1,687 ወጣቶች በውድድሩ ለመሳተፍ መመዝገባቸውን አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ። ወጣቶቹ ያቀረቧቸው ሀሳቦች በክልላቸው እና ከተሞቻቸው ደረጃ እንዲመረጡ ሲደረግ የእነነቢዩ ለመጨረሻው ዙር ውድድር ካለፉት 31 የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል። 

ከጅማ ዩኒቨርስቲ በሰኔ ወር የተመረቁት ነቢዩ እና ጓደኞቹ ቀጣዩን ሁለት ወራት የፈጠራ ሥራቸው ለመጨረሻ ለውድድር ብቁ እንዲሆን ማሻሻያዎችን ሲያደርጉበት ከርሙ። የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ከሽልማት ስነ ስርዓቱ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ሲደረግ እነነቢዩም ሥራቸውን ይዘው ተገኙ። ተወዳዳሪዎቹ በአዲስ አበባ ቆይታቸው የአራት ቀናት ስልጠና እንደተሰጣቸው እና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በገንዘብ ሊደግፉ ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር እንደተገናኙ የውድድሩ አስተባባሪ ቤተልሔም ደሴ ትናገራለች። ወጣቶቹ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) አይነት ተቋማትን እንዲጎበኙ መደረጉንም ታስረዳለች። በስተመጨረሻም ሥራዎቻቸውን ዳኞች ፊት እንዲያቀርቡ ተደርጎ ሶስት አሸናፊ ሥራዎች መመረጣቸውን ታብራራለች።

Äthiopien nationaler Innovationswettbewerb SolveIT
ምስል iCog Labs, Solve IT

“ሶስቱ የተመረጡበት አንደኛ የገበያ አዋጭነታቸው ከ30 በመቶ ታየ። ከዚያ ደግሞ በገንዘብ አዋጭ ናቸው ወይ? ያስቀመጡት የገንዘብ መጠን እና ወደፊት ያስገኛል ብለው በሚያስቡት ገቢ መሰራት የሚችል ነው ወይ የሚለው ታየ። ከዚያ ደግሞ በቴክኒክ ደረጃ የሚጨበጥ ነው ወይ ? እነዚህ ልጆች በትክክል ያሉትን ነገር ሰርተዋል ወይ አሊያም ደግሞ መሰራት ይችላል ወይ የሚለው ታየ። በመቀጠል ደግሞ ሀሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ ዳኞቹ ዓውደ ርዕያቸው ጋር ሄደው የሙከራ ስራቸውን (prototype) አዩ። በዚህ ላይ ተመስርቶ የመጨረሻዎቹ ሶስት ተመርጠዋል” ትላለች ቤተልሔም።  

በመስፈርቶቹ መሰረት ዳኞቹ በሶስተኛነት የመረጡት በባህር ዳር ወጣቶች የተሰራን ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ቁስ ነው። ቁሱ በቦርሳ፣ በቁልፍ አሊያም በማንኛውም ውድ ዕቃ ላይ የሚያያዝ አሊያም የሚለጠፍ ነው። ቁሱ የተለጠፈበት ዕቃ ቢሰረቅ ወይ ቢወሰድ አሊያም ቢረሳ ከተወሰኑ ርቀቶች በኋላ ለባለቤቱ በተንቀሳቃሽ ስልኩ መተግበሪያ (አፕልኬሽን) አማካኝነት ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የተሰራው ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው የፈጠራ ሥራ የቤት ውስጥ ቆሻሻዎችን ተጠቅሞ የመብራት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል መሳሪያ ነው። አሸናፊነቱን የተቀዳጀው ደግሞ ነቢዩ እና ጓደኞቹ ለውድድር ይዘው የቀረቡት ለጨቅላ ሕጻናት ኦክሲጅንን መጥኖ መስጠት የሚያስችል መሳሪያ ነው። ነቢዩ ማብራሪያ አለው። 

“እኛ የሰራነው መሳሪያ ምንድነው ኦክስጅንን በዘፈቀደ ቀጥታ ከሲሊንደር ወይንም ደግሞ በግድግዳ በኩል ከሚመጣ ምንጭ ከመስጠት ይልቅ pulse oximetryን በመጠቀም ሕጻኑ ሰውነት ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን በመለካት፤ የWHO መመሪያ የሚፈቅደው አለ፤ ከ30 በመቶ ይጀምርና ቀስ እያለ የኦክስጅን መጠኑን እንደ ህጻኑ ሰውነት ፍላጎት፣ ራሱን በራሱ aoutomted እያስተካከለ የሚሰጥ ነው ማለት ነው። ይሄ ማለት ዶክተሩ ወይም ነርሷ የሕጻኑን የጤና ሁኔታ በማየት አማካይ መጠን ያስቀምጥለታል። ሕጻኑ ውስጥ ያለው የኦክስጅን መጠን ከዚህ መጠን እስከ እዚህ መጠን ቢሆን መልካም ነው ብሎ የሚስበውን ነገር ያስቀምጣል። ያንን ካስቀመጠ በኋላ ማሽኑ ስራውን ይጀምራል። ስለዚህ ማሽኑ ምንድነው የሚሰራው መቶ በመቶ ንጹህ ኦክስጅን በመስጠት ፋንታ 30 በመቶ [ይሰጣል]። ሌላውን ከአየር በመውሰድ 30 በመቶ፣ 40 በመቶ እያደረገ የሚሰጥ መሳሪያ ነው ማለት ነው” ሲል እነርሱ ስለሰሩት መሳሪያ ምንነት ያስረዳል።በዚህ መሳሪያ ፈጠራ ነቢዩ ከሁለት ጓደኞቹ ዮናስ ገብረወልድ እና ረድኤት ብርሃኑ ጋር የ75 ሺህ ብር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ የወጡ የፈጠራ ሥራዎችን ለሰሩ ወጣቶች ደግሞ የ50 ሺህ እና የ25ሺህ ብር ቼክ በሽልማቱ ስነ ስርዓቱ ላይ ተበርክቶላቸዋል። አሸናፊዎቹ ሙሉው ገንዘብ ወዲያውኑ በጥሬው የሚሰጣቸው ሳይሆን ያቀረቡትን የፈጠራ ሥራ ደረጃ በደረጃ ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እንዲያስችላቸው ተደርጎ የሚለቀቅላቸው እንደሆነ የውድድሩ አስተባባሪ ቤተልሔም ትገልጻለች።

Äthiopien nationaler Innovationswettbewerb SolveIT
ምስል iCog Labs, Solve IT

“ግብ (milestone) እናስቀምጥላቸዋለን። milestone ማለት ለምሳሌ በቴክኒክ ወይም በቢዝነስ ረገድ ግብ ታስቀምጥላቸዋለህ። ስለዚህ ይህን ግብ ካሳካችሁ ይህን ያህል በመቶ  የገንዘብ መጠን ይለቀቅላችኋል እያልን ነው የምንሄደው ማለት ነው።  ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ውድድሮች አይተህ ከሆነ ተወዳዳሪዎች ብር ይሸለማሉ፤ ከዚያ የተሸለሙትን ብር የፈለጉበትን ነገር ያደርጉበታል። የሚሰሩት ሥራ የት ደረሰ? የሚለው በደንብ ክትትል አይደረግበትም። ነገር ግን እኛ እንደዚያ እንዲሆን ስለማንፈልግ ያስቀመጥንላቸው ግቦች ባሳኩበት ልክ የሚያስፈልጋቸውን ብር እየለቀቅን እንሄዳለን ማለት ነው” ትላለች ቤተልሔም።  

ነቢዩም በውድድር ያገኙትን የገንዘብ ሽልማት የኦክስጅን መመጠኛ መሳሪያውን ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚያውሉት ይናገራል። “አሁን ዕቃው የተሰራው ከተለያዩ የህክምና ዕቃዎች ላይ መሳሪያዎችን በመውሰድ፣ እንደገና ደግሞ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በራሳችን በመግዛት ነው። ግን ይሄ የሕጻናት ላይ የሚሰራ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን በጣም ጥራት ባላቸው ዕቃዎች መስራት አለብን። ስለዚህ ገንዘቡን የምናውለው ዕቃውን ጥራት ባለ ሁኔታ ለመስራት ነው። ዕቃውን ደግሞ በምንሰራበት ጊዜ ብሩን ተጠቅመን የተሻለ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ፣ ብዙ መለያዎችን (features) ድጋሚ መጨመር ነው ያሰብነው” ይላል። 

አዲስ ተመራቂዎቹ እነ ነቢዩ ይህን የፈጠራ ስራቸውን ከማሳደግ ጎን ስራ እያፈላለጉ ይገኛሉ። በጅማ እና ወልቂጤ ከተማ ሆነው ሥራ ለመቀጠር በጥረት ላይ ካሉት ሁለቱ የተሻለ ዕድል ያገኘው ሶስተኛው ባልደረባቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሥራ ጀምሯል። የራሳቸውን ድርጅት መስርተው፣ በፈጠራ ስራቸው ከመቀጠል ይልቅ ሥራ መፈለጉ ላይ ያተኮሩት ከመደበኛ ሥራ የሚገኘውን ክህሎት እና ለመቅሰም እንደሆነ ነቢዩ ያስረዳል። “ከእኛ በሚበልጡ ሰዎች ስር ሆነን ዕውቀትን መጨመር ስለምንፈልግ ነው” ይላል።  

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ