1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር ክልል መስተዳድርን ዳግም የማደራጀት ጅማሮ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2011

በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ አፈና የዲሞክራሲ እጦት እና የተደራጀ ሌብነት ሰፍኖ መቆየቱን የኢፌድሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ኤይሻ መሃመድ ገለጹ ::

https://p.dw.com/p/39t59
Gaas Ahmed
ምስል DW

«ስለክልሉ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተጠይቋል»

በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት አፈና የዲሞክራሲ እጦት እና የተደራጀ ሌብነት ሰፍኖ መቆየቱን የኢፌድሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ገለጹ ። በቅርቡ ርዕሰ መስተዳድሩን እና የክልሉን ገዥ ፓርቲ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ጨምሮ 72 የድርጅቱን ስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በክብር ያሰናበተው አብዴፓ 7ተኛ መደበኛ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ የክልሉን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እና አገራዊውን ለውጥ ለማሳካት ኢንጂነር አይሻን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። የመከላከያ ሚኒስትሯ በተለይም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ወንጀለኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ለ «DW» የገለጹ ሲሆን የአፋር ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ በአገር ውስጥም በውጭ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ፣ ድርጅት እና ቡድን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል። በቤልጅም ነዋሪ የሆኑት የአፋር የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ጋስ አህመድ በበኩላቸው በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተጀመረው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቅሰው ለለውጡ ሃይሎች ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ።  

የአፋር ኅብረተሰብ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በድህነት  በመልካም አስተዳደር ጉድለት ፍትሃዊ በሆነ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ችግር እና በልማት አገልግሎት ዘርፍ በተገቢው መንገድ ተደራሽ አለመሆኑ የአካባቢውን ሰላም እና ጸጥታ በእጅጉ አናግቶት እንደቆየ በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ሲገለጽ ቆይቷል ። ተፈጥሮ ከለገሰችው ሃብት እንኳ በአግባቡ እንዳይጠቀም ባይተዋር ሆኖ የቆየው የአፋር ሕዝብ በሰላማዊ ትግል መብት እና ነጻነቱን ለማስከበር ከፍተኛ ትግል እና መስዋዕትነት መክፈሉ ነው የሚነገረው። ለትግሉም ስኬት በርካቶች የሕይወት ዋጋ መክፈላቸውን ለአካል ጉዳት እና ለስደት መዳረጋቸውንም የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እና የክልሉ ተፎካካሪ ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ይፋ አድርገዋል። የአብዴፓ ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጋር ባካሄዱት ውይይት በአፋር ክልል መንግስት ፓርቲ አመራሮች መካከል ስር እየሰደደ የመጣውን አለመግባባት እና አለመተማመን ተከትሎ በአካባቢው እየተባባሰ የመጣውን ግጭት እና አለመረጋጋት ለመፍታት እንዲሁም አገራዊውን ለውጥ ይበልጥ ለማሳካት ነባር አመራሮችን በአዲስ የመተካት ጠቀሜታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። ከቀናት በፊት በክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ የተካሄደውን 7ተኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ ተከትሎም ለረጅም ዓመታት በፓርቲው እና በክልሉ መንግሥት አመራር የቆዩ 72 የአብዴፓ ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም መካከለኛ አመራሮችን በክብር እንዲሰናበቱ ተደርጓል። ከተሳናባቾቹም መካከል የፓርቲው ሊቀመንበር እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሃጂ ሥዩም አወል የሚገኙበት ሲሆን ፓርቲው አገራዊውን ለውጥ ለማሳካት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድን የአብዴፓ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል ። በአፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ እንስት የመከላከያ ሚኒስትር መሆናቸው የሚጠቀሰው ኢንጂነር አይሻ በተለይ ለ« DW» እንደገለጹት በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት አፈና የዲሞክራሲ እጦት እና የተደራጀ ሌብነት ተንሰራፍቶ መቆየቱን አስረድተዋል።

የአፋርን ክልል የሚመራው ፓርቲ ለውጥ አደናቃፊ ነው በሚል በክልሉ በአብዛኛው አከባቢ የተጀመረው ተቃውሞ ተጠናክሮ ቆይቷል ። በተለይም " ዱኩሂና " በሚል ስያሜ እራሳቸውን ያደራጁት የአፋር ወጣቶች አሁን ለተገኘው ለውጥ ከባድ መስዋትነት መክፈላቸውም ይነገራል ።የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በቅርቡ በማዕከላዊ ኮሚቴው ላይ ያካሄደውን ስር ነቀል ሹም ሽር ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት ሰሞኑን ስብሰባ በማካሄድ ካቢኔውም እንደሚመሰርት እና አዲስ ርዕሰ መስተዳድርም እንደሚሰይም ታውቋል። የኢፌድሪ የመከላከያ ሚኒስትር እና የአብዴፓ አዲሷ ሊቀመንበር ኢንጂነር አይሻ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ በማስፋት የዲሞክራሲያዊን ሥርዓት ከማጠናከር ጎን ለጎን በተለይም የለውጡ ኃይል የሆነው ወጣት በስራ እና በልማት ተጠቃሚ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ የክልሉ መንግሥት ጠንክሮ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት ።

ኢንጂነር አይሻ አገር አቀፉን የለውጥ ጅማሮ ለማሳካት ብሎም ክልሉን ለመገንባት በአፋር ሰላም ልማት እና እድገት ያገባኛል የሚል ማንኛውም አካል በግልም ይሁን በተናጥል በሙያውም ሆነ በሃብቱ እንዲያግዝ ጥሪ አስተላልፈዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የሚገኙት እና ነዋሪነታቸው በቤልጅየም ብራስልስ ከተማ የሆነው የአፋር የሰብ አዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ጋስ አህመድ በበኩላቸው ላለፉት ዓመታት በክልሉ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት ግፍ እና አፈና መፈጸሙን አስታውሰው የተፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ አዲሷ የአብዴፓ ሊቀመንበር ኢንጂነር አይሻ ቁርጠኛ አቋም ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው እና ድጋፋቸውንም እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።  አብዴፓ በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣውን ለውጥ የሚያሳካ ጠንካራ አመራር መምረጡን የገለጸ ሲሆን መጭው ዘመን የአፋር ሕዝብ ወደተሻለ እድገት የሚሸጋገርበት መልካም የአስተዳደር ሥርዓት የሚገነባበት የልማት እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችም አዎንታዊ ምላሽ የሚያገኙበት ብሩህ ጊዜ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።


እንዳልካቸው ፈቃደ


ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ