1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት እና «አይ ሲ ሲ»

ቅዳሜ፣ ጥር 27 2009

በአዲስ አበባ 28ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባዔ የተሳተፉት መሪዎች ዓ/አቀፍ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍ/ቤት፣ አይ ሲ ሲን በጋራ ለቀው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ስልት ደገፉ።   በኬንያ እና ሱዳን የተመሩ ብዙ አፍሪቃውያት ሃገራት መንበሩን በዘ ሄግ፣ ኔዘርላንድስ ያደረገው ዓ/አቀፉ ፍርድ ቤት በአፍሪቃ አኳያ አድሏዊ አሠራር ይከተላል በሚል ይወቅሳሉ።

https://p.dw.com/p/2WsY6
Niederlande Den Haag Internationaler Gerichtshof
ምስል picture-alliance/AP Images/J. Lampen

icc afrika for soa cms - MP3-Stereo

ይኸው አፍሪቃውያንን ብቻ ዒላማ አድርጓል በሚል የሚወቀሰው ፍርድ ቤት በተቀረው የዓለም አካባቢ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንዳላየ እንደሚያልፍ ነው መሪዎቹ ያመለከቱት። ተሰናባቹ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ኤራስተስ ምዌንቻ እንዳሉት፣ አፍሪቃውያት ሃገራት የሚፈልጉት «አይ ሲ ሲ» በሁሉም ሃገራት አኳያ የሚከተለው አሰራር አንድ ዓይነት እንዲሆን ነው።  አፍሪቃውያቱ ሃገራት መሪዎች በዝግ በተካሄደ ስብሰባ ላይ በተነደፈው ስልት ላይ የሰፈሩትን ሀሳቦች ቢቀበሉም፣ ብዙዎች ተጨባጭ ርምጃዎችን ያልያዙ በመሆናቸው ፣ ስልቱ ለጊዜው ብዙም የሚለውጠው ጉዳይ አይኖርም በሚል ቅሬታቸውን ገልጸዋል። 
አፍሪቃውያት ሃገራት «አይ ሲ ሲ»ን ለቀው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ስልት መደገፋቸውን የተመለከተው ዜና በአፍሪቃ ህብረት ዓቢይ ጉባዔ የእንደ ተራ ተጨማሪ መረጃ ብቻ ነበር የታየው። 
«አይ ሲ ሲ»ን በተመለከተ መሪዎቹ በዝግ ስብሰባ መምከራቸውም ሆነ በዚያ የደረሱት ስምምነት በጉባዔው ላይ አልተገለጸም። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣን ነበሩ መሪዎቹ ይህንን ውሳኔ መደገፋቸውን ለዜና ምንጮች የገለጹት። በፕሪቶርያ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ውስጥ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ጉዳይ ላይ የሚሰሩት 

Internationaler Strafgerichtshof mit Logo

አላን ንጋሪ እንዳስረዱት፣ አፍሪቃውያኑ መሪዎች የደገፉትን ስልት በቅርብ ሲመለከቱት ግን ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት እና ፍርድ ቤቱ የተቋቋመበትን የሮምን ውል ለቆ ለመውጣት የተደረሰ ውሳኔ አለመሆኑን ማየት ይቻላል።  ስምምነት ባገኘው ስልት ላይ የሰፈረው ውሳኔ አሳሪ ባህርይ የሌለው ሲሆን፣ የዘ ሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትን ለቆ የመውጣት አለመውጣት ውሳኔ የያንዳንዷ ሃገር ፈንታ ነው።  አሁን ተዘጋጀ በሚባለው ስልት አኳያ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ታንዛንያን የመሳሰሉ በርካታ ሃገራት ጥርጣሬ አላቸው፣  ሌሎችም በስልቱ የሰፈሩትን ሀሳቦች ለማጥናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀዋል። ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ለቆ የመውጣቱ ስልት የተዘጋጀው ደቡብ አፍሪቃን፣ ቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኬንያን በመሳሰሉ ሃገራት ግፊት ነው።  እነዚህ ሃገራት «አይ ሲ ሲ»ን ለቆ የመውጣቱን ጥያቄ ሲያቀርቡ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። 

እንደሚታወቀው፣ የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ነበሩ ይህን ሀሳብ ከአንድ ዓመት በፊት ያቀረቡት። ፕሬዚደንት ኬንያታ እና ምክትላቸው ዊልያም ሩቶ ራሳቸው በኬንያ እጎአ ከ2007ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ በሀገሪቱ የተካሄደውን ግጭት እና ሁከት ቀስቅሳችኋላ በሚል እስከ 2014 ዓም ድረስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው ነበር የቆዩት። «አይ ሲ ሲ» አፍሪቃውያንን ብቻ ዒላማ አድርጓል ያሉትን አሰራር ጉዳይ ለተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ለማቅረብ አስበው የነበሩ የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከአንድ ዓመት በፊት በቀረበው ስልት ላይ በሰፊው መወያየታቸው ይታወሳል።  አፍሪቃውያን በአህጉሩ የሚፈጸም ወንጀልን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመዳኘት የውጭ ፍርድ ቤት ሳይሆን የሚያስፈልጋቸው የተጠናከረ የራሳቸው የፍትህ  ስርዓት መሆኑን የሱዳን ኤኮኖሚያዊ እና ልማት ጉዳዮች ተመልካች መስሪያ ቤት ዋና ጸሓፊ ዶክተር ሁሴይን ኻርሹም አስረድተዋል።
«የህብረቱን «አፍሪካን ኮርት ኦፍ ጃስቲስ» ወይም የአፍሪቃ የፍትህ ፍርድ ቤትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው። ለእያንዳንዱ የአፍሪቃ መንግሥትም የፍርድ ቤቱን ኅልውና እንዲያፀድቅ ጥሪ ማስተላለፍ ተገቢ ይሆናል። ሁለተኛው እያንዳንዱ መንግሥት የሃገሩን የፍትህ ስርዓት ማጠናከር ይኖርበታል። ምክንያቱም «አይ ሲሲ» መውሰድ ያለበትን ርምጃ ሁሉ እየወሰደ አይደለም።»

Äthiopien, Präsident von Kap Verde Jorge Carlos Fonseca
የ«አይ ሲ ሲ» አባልነቷን መቀጠል የምትፈልገው ኬፕ ቬርዴ ዲፕሎማትምስል Regierung von Kap Verde

ይሁንና፣ «አይ ሲ ሲ»ን እና የሮሙን ውል ለቀው ለመውጣት እንደሚፈልጉ የሚናገሩ ሃገራት በዚሁ ረገድ ተጨባጭ ርምጃ ሲወስዱ አለመታየቱን የፕሪቶርያ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ አላን ንጋሪ ተናግረዋል። ኬንያ ከሮሙ ውል መውጣት የሚያስችላትን ረቂቅ ሕግ ብታዘጋጅም፣ ለፅድቂያ ሳይበቃ መቅረቱን ንጋሪ አስታውሰዋል። ደቡብ አፍሪቃም በሮሙ ውል ላይ ይደረጉ ያለቻቸውን ማሻሻያዎች አቅረባ ነበር። እንደሚታወሰው፣ ደቡብ አፍሪቃ አፍሪቃን እጎአ በ2015 ዓም ለአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ወደ ሃገሯ የሄዱትን በ«አይ ሲ ሲ» ክስ የተመሰረተባቸውን የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺርን ለፍርድ ቤቱ ባለማስረከቧ ብርቱ ወቀሳ ነበር የተፈራረቀባት። 
አንዳንድ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክን የመሳሰሉ ሃገራት ዓለም አቀፉን የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤትን አሁንም ይደግፋሉ። ይሁን እንጂ፣ ፍርድ ቤቱን ለቃ የመውጣት ፍላጎቷን በተለያዩ አጋጣሚዎች ያጎላችው ዩጋንዳ «አይ ሲ ሲ» ተሃድሶ የማያደርግ ከሆነ አባልነቷን እንደምታበቃ አሁን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ሳም ኩቴሳ አማካኝነት በይፋ ዛቻ አሰምታለች።  

Omar Hassan Ahmad al-Bashir Präsident Sudan Internationalen Strafgerichtshof Logo
ምስል picture-alliance/dpa/Montage DW

« ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ካለፉት አስራ ሁለት ዓመታት የተከተለውን አሰራር ማሻሻል ይኖርበታል። እንደታየው፣ እስካሁን ሁለት ወይም ሶስት ብይኖችን ብቻ ነው ያሳለፈው።  በያመቱ 180 ሚልዮን ዶላር  የሚያወጣው ፍርድ ቤት ስራውን እንደሚገባ እያከናወነ አይደለም የሚል አስተሳሰብ ነው ያለን። »
አፍሪቃውያን መሪዎች በ28ኛው የህብረቱ ጉባዔ ወቅት ከተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተወካዮች ጋር ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውስጥ እንዲደረጉ ባሰቧቸው ለውጦች ላይ ለመምከር አቅደው ነበር፣ ይሁንና፣ ወደ አዲስ አበባ የተላኩት የምክር ቤቱ ተወካዮች በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙት ስለነበሩ ህብረቱ እቅዱን ሰርዞዋል። ሆን ብሎ አፍሪቃውያንን  ዒላማ  አድርጓል በሚል በአህጉሩ ብርቱ ወቀሳ ከሚሰነዘርበት ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት 124 አባል ሃገራት መካከል አንድ ሶስተኛው አፍሪቃውያት  ናቸው።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ