1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ የካቲት 16 2011

የሲዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ደግሞ የ51 ዓመቱ ጎልማሳ የሚደላቀቁባቸዉ 25 ቅንጡ መኪኖቻቸዉ ተሸጠዉ ገንዘቡ ለኤኳተርያል ጊኒ ሕዝብ አገልግሎት እንዲዉል ወስኗል።በልዩ ትዕዛዝ የሚሰሩት ቡጋቲ ቬይሮን የመሳሰሉት መኪኖች እያንዳዳቸዉ 2 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣሉ።አንድ መቶ ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ዘመናይ ጀልባቸዉን ግን ፍርድ ቤቱ እንዳይነካ በይኖላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3DtRu
Kenia Afrika Proteste gegen Korruption
ምስል Getty Images/S. Maina

የአፍሪቃ ሙስና፣ ሴኔጋል ምርጫና ሥጋት

 

አፍሪቃ ከነፃነት ጀምሮ ከምዕራባዉያን መንግስታት የሚሰጣት ብርድርና ርዳታ የሕዝቧን ኑሮ አለማሻሻሉን የሚያረጋግጡ ጥናቶችና ትችቶች ደገምገም፣ጎላ ጠንከር እያሉ የወጡት ከ2005 ጀምሮ (ዘመኑ በሙ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነዉ።የምዕራብ ፖለቲከኞችና የርዳታ ድርጅቶች የየጥናቱን ዉጤት ለማስተባበል ያላደረጉት ሙከራ የለም።የተሳካ የመሰለዉ ግን ርዳታዉ የሕዝቡን ኑሮ ያልወጠዉ አፍሪቃዉያን መሪዎች ወይም ፖለቲከኞች የርዳታዉን ገንዘብ ለየግል ጥቅማቸዉ ስለሚያዉሉት ነዉ የሚለዉ ሳይሆን አልቀረም።የምዕራባዉያን ርዕሠ-ከተሞች ሥለአፍሪቃ ሙስና ሲያወሩ፣የአፍሪቃን አብያተ መንግስታት የተቆጣጠሩት ፖለቲከኞች ፀረ-ሙስናን ጧት ማታ ይዘምሩ ገቡ።

ከ2006 ወዲሕ አፍሪቃ ከአዲስ አበባ እስከ ሌጎስ፣ከዳካር እስከ ጁሐንስበርግ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ኮሚቴ ወይም መስሪያ ቤት ተጥለቀለቀች።መሪዎችዋ የሙስኛን ጣት-መላስ ለመቁረጥ በየፓርላማዉ ያቅራሩ ያዙም።የዋሽግተን፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ዤኔቭ ፖለቲከኞች ምናልባት የትኩረት አቅጣጫ በማሳት ክክሒላቸዉ ርካታሲዝናኑ ባንኮቻቸዉ የአፍሪቃ መሪዎች ካፍሪቃ የሚዘርፉትን ገንዘብ ከበፊቱ በረቀቀ ሥልትና በከፋ መጠን ማከማቸቱን ቀጠሉ።

ዦን ዣኩስ ሉሙምባ የአፍሪቃና የአዉሮጳ ፖለቲከኞች በፀረ-ሙስና ትግል ሥም ሊደብቁ የሚሞክሩትን ቅጥ ያጣ ሙስና ካጋለጡ ምናልባትም ካደጋ ካመለጡ ጥቂት አፍሪቃዊ አንዱ ናቸዉ።ኮንጎዊ ናቸዉ።ኪንሻሳ የሚገኘዉ የጋቦን ባንክ የብድር አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ነበሩ።አንድ ቀን አጠራጣሪ ገንዘብ እንዲያዘዋዉሩ ታዘዙ።

ሰዉዬዉ የፍትሕን መዛባት መቃወምን በደም ሳይወርሱት አልቀረም።የቤተ-ሰብ ስማቸዉን ያስታዉሱ።ሉሙምባ ነዉ።እና አለቆቻቸዉን ጠየቁ።«አርፈሕ ሥራ» ዓይነት ተባሉ።እንዲዛወር የተፈለገዉ ገንዘብ በተጭበረበረ መንገድ የተገኘ 40 ሚሊዮን ዩሮ ነበር።«እንቢኝ» አሉ።ከዚያ በኋላ በጠመንጃ ይታደኑ ያዙ።ኮበለሉ። ወደ ፈረንሳይ።
                              
«ያን ገንዘብ የሚያዘዋዉሩት ከቀድሞዉ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸዉ ኩባንዮች ነበሩ።የባንኩ ገዢም የካቢላ የቅርብ ታማኝ ነበሩ።ችግሬ ገንዘቡ መተላለፉን መቃወሜ ነዉ።ብዙ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስኝ ለመሰደድ ተገደድኩ።»

Infografik Corruption Perceptioin Index 2018 EN

ሉሙምባ አልተገደሉም።ፈረንሳይም ፈጥና ጥገኝነት ሰጠቻቸዉ- እድሜ ላጎታቸዉ ሥም።የፓትሪስ ሉሙምባ እሕት ወይም ወድም ልጅ ናቸዉ።ፓትሪስ ሉሙምባ። የጎንጎ የነፃነት ታጋይ፣ የመጀመሪያዉ ጠቅላይ ሚንስትርም ነበሩ።በቤልጂግ ቅኝ ገዢዎች የተገዙ የገዛ ወገኖቻቸዉ አሰቃይተዉ ገደሏቸዉ።1961።

ዦን ዣኩስ ሉሙምባ ፈረንሳይ ፍርድ ቤት ክሰዋል።አርባ ሚሊዮን ዩሮ።ስንቱን ኮንጓዊ ለስንት ቀን ይቀልብ ነበር።ጠበቃቸዉ ሔንሪ ቱሊስ ግን «ዳዊት ከጉሊያድ ጋር የሚያደርገዉ ትግል» ይሉታል።ክሱን።ዳዊት ያሸንፋል የሚል ተስፋ ግን አላቸዉ።

አፍሪቃ የሚፈፀም ምናልባትም ከአፍሪቃ ተዘርፎ አዉሮጳ የገባ ገንዘብን በተመለከተ የአዉሮጳ ፍርድ ቤቶች ብዙ ክስ አስተናግደዉ አያዉቁም።በቅርብ ዘመኑ ታሪክ የሚጠቀሰዉ አንድ ነዉ።የኤኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝደንት ልጅና ምክትል ፕሬዝደንት የቴዎዶሪን ኦቢያንግ ቅሌት።

በ2017 ያስቻለዉ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ቀበጡን ጎልማሳ የሕዝብ ገንዘብ በማባከንና የተጭበረበረ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀል በሌሉበት የ3ዓመት እስራት በይኖባቸዋል።ፈረንሳይ የሚገኘዉ  ቪላቸዉ እንዲወረስ ወስኗል።ቤቱ 100 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣል።

የሲዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ደግሞ የ51 ዓመቱ ጎልማሳ የሚደላቀቁባቸዉ 25 ቅንጡ መኪኖቻቸዉ ተሸጠዉ ገንዘቡ ለኤኳተርያል ጊኒ ሕዝብ አገልግሎት እንዲዉል ወስኗል።በልዩ ትዕዛዝ በዕዉቅ የሚሰሩትን ቡጋቲ ቬይሮን የመሳሰሉት መኪኖች እያንዳዳቸዉ 2 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ያወጣሉ።አንድ መቶ ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ዘመናይ ጀልባቸዉን ግን ፍርድ ቤቱ እንዳይነካ በይኖላቸዋል።

ኤኳቶሪያል ጊኒ ትንሽ ናት።ግን በ1990ዎቹ የፈለቀባት ነዳጅ ዘይት በሐብት አበሻብሿታል።ሐብቱ ግን  የሑዩማን ራትስ ዋች ባልደረባ ሳራሕ ሰዓዱን እንደሚሉት ለሕዝቡ የፈየደዉ የለም።
                                    
«በሐገሪቱ የተንሰራፋዉ ሙስና፣ መንግሥት የሕዝቡን ጤናና ትምሕርት ከመዘንጋቱ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነዉ።ሐገሪቱ ከፍተኛ የነብስ ወከፍ ገቢ ካላቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ብትሆንም፣የትምሕርትና የጤና አገልግሎት ከአማካዩ የአፍሪቃ ደረጃ በጣም የወረደ ነዉ።»

ሙሰኞችን፣ የሙስናን ጉዳትና ደረጃን የሚከታተለዉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘዉ ድርጅት ከአፍሪቃ የሚዘረፈዉ፣የሚባክነዉና የሚጭበረበረዉ ገንዘብ፣ ተጭበርብሮ ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጠዉ (ታጠበ ይሉታል እንግሊዘኛ ለበስ አማርኛ ተናጋሪዎች) ገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነዉ ባይ ነዉ።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በሌለኛዋ ትንሽ፣ ሐብታም ግን የደሐ ሕዝብ አፍሪቃዉት ሐገር በጋቦን መሪ ዓሊ ቦንጎ ላይ በ2017 ፈረንሳይ ዉስጥ መስርቶት የነበረዉ ክስ በመረጃ እጦት ዉድቅ ሆኖበታል።የድርጅቱ ባልደረባ ጂሊያን ዴል እንደሚሉት ሙስናን መከላከሉም መዋጋቱም በጣም አዝጋሚ ነዉ።
                              
«ሒደቱ አዝጋሚ ነዉ።አስቀድሞ የመከላከሉም ሆነ ወንጀለኞችን የመቅጣቱ ሒደት ሊፋጠን ይገባል።መከላከል ስንል በተለይ የተጭበረበረ ገንዘብን ሕጋዊ ሽፋን የመስጠቱ ሒደት መገታት አለበት።ኩባንዮች የባለቤቶቹና የየባለድርሻዎችን ገቢ፤መጠንና ማንነት በግልፅ እንዲያሳዉቁ መደረግ አለበት።»
ሙስና በየስፍራዉ አለ።የአፍሪቃ ግን የከፋ ነዉ።በሁለት ምክንያት።ገንዘቡ የሚላስ የሚቀመስ ከሌለዉ ሕዝብ ጉሮሮ የሚነጠቅ ነዉ።-አንድ።የተዘረፈዉ ገንዘብ የሚዉለዉ ለአዉሮጳ፣አሜሪካና እስያ ባንኮች ወይም ሸቀጦችና አገልግሎቶች መግዢያ ነዉ-ሁለት።ሙስናን መዋጋት ደግሞ መሪዎችን፣ የጦር ጄኔራሎችን፣ ቱጃሮችን፣ቢሮክራቶችን መዋጋት በመሆኑ ፈተናዉ ከባድ ነዉ።አንገትን ሊያበጥስ ይችላል።ዦን ዣኩስ ሉሙምባ ግን አልፈራም ይላሉ።
                            
«አልፈራም።እዉነት ሹመትና ሽልማት እንደማትፈልቅ አዉቃለሁ።እኔ ባልፍ እንኳን ትግል ይቀጥላል።ትግሌ ለኔ ብቻ ሳይሆን  ለብዙ ኮንጎዎችም ነዉና።ሥለ ገንዘብ መጠን መናገር አልፈልግም።ይሁንና ለደረሰዉ ጥፋት ካሳ ሊከፈል ይገባል።»
«ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል------» ዓይነት ነገር።ያጎቱ ልጅ።

Kenia Afrika Proteste gegen Korruption
ምስል Getty Images/S. Maina

 

II. የሴኔጋል የምርጫ ዝግጅትና ዉዝግብ

በማያባራ ግጭት፣ ዉዝግብ፣ ትርምሷ-ደግሞ ሰከን ሲል-በቅምጥ ሐብቷ ብዛት፣ በመልከዓ ምድር ትልቅነቷ የመገናኛ ዘዴዎች «ቋሚ» ደንበኛ የሆነችዉ፣ ዛሬም በሙስናዋ የጠቃቀስናት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባለፈዉ ታሕሳስ አጠቃላይ ምርጫ አድርጋለች።ያቺ ሰፊ፤ ሐብታም፣የድሆች ሐገር ባንድ ጊዜ ፕሬዝደንታዊ፤ ምክር ቤታዊና አካባቢያዊ ምርጫ ስታደርግ የታሕሳሱ የመጀመሪያዋ ነዉ።

እርሟን ያደረገችዉ ምርጫ ዉጤት ጥር መጀመሪያ ላይ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ግን እስካሁን በሚንጣት ሁከት-ግጭት ላይ ፖለቲከኞቿ አዲስ ዉዝግብ ገጥመዉ እየተናቆሩ፣ ሕዝቡን እያደናቆሩት ነዉ።ከኮንጎ ቀድማ የረጅም ጊዜ መሪዋን አሰናብታ ምርጫ ያስተናገደችዉ ዚምባቡዌም የግጭት፣ዉዝግብ፣ምድር፣ የኪሳራ ድሕነት አብነት ሐገር እንደሆነች ክፉ ቀን ሸኝታ ክፉ ቀን ታስተናግዳለች።

ባለፈዉ ሳምንት ከአቡጃ የሰማነዉ ግን ከማንም አይገጥምም።የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታት፣ ማሕበራትና ድርጅቶች ታዛቢዎች፣ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ተንታኞች ለቅዳሜ ተይዞ የነበረዉን ምርጫ ለመከታትል በናጄሪያ ከተሞች ሲተረማመሱ፣ መራጭ-ተፎካካሪዎች ሰዐታት ሲያሰሉ የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ድምፅ መስጪያዉ ጊዜ መራዘሙን አስታወቀ።አምስት ሰዓት ነበር የቀረዉ።
የአትላንቲክ ባሕርን የተንተርሳቸዉ ሴኔጋል የናጄሪያን ግራ አጋቢ የምርጫ ታሪክ ምናልባትም የኮንጎ፣ የዜምባቡዊና የሌሎችንም የምርጫ ማግስት ምስቅልቅል በአርምሞ ቁል ቁል ትመለከት ይሆናል።ባገባደድነዉ ሳምንት ግን የራስዋ-እራስዋን ስለያዛት ሌሎችን የምትታዘብበት ጊዜ ያገኘች አይመስልም።

Senegal Wahl | Wahlkampf von Ousmane Sonko in Pikine, Unterstützer
ምስል Reuters/Z. Bensemra

መጋቢት ማብቂያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይደረግባታል።አምስት ዕጩዎች ይወዳደራሉ።በሴናጋል የ21 ዓመት ታሪክ ትንሽ ቁጥር ያላቸዉ ዕጩዎች ሲመዘገቡ የዘንድሮዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።የምዕራብ አፍሪቃ የሰለምና መረጋጋት አምባ ናት።ሴኔጋል።ዘንድሮ ግን እንጃ።

የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የአብዱላዬ ዋዴ ልጅ ከሪም ዋዴ ለመወዳደር ያቀረቡትን ጥያቄ ምርጫዉን የሚመራዉ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ዉድቅ አድርጎባቸዋል።በዚሕ የተናደዱት ጡረተኛዉ ፖለቲከኛ (አባት ዋዴ) ደጋፊዎቻቸዉ የድምፅ መስጪያ ጣቢያዎችን እንዲጋዩ ጠይቀዋል።

ዋዴ ብዙ ደጋፊ-አድናቂም አላቸዉ።ያቺ የሠላም አምባ ዘንድሮን እንደ እስከዘንድሮዉ በሰላም ማለፏ ካጠራጠረበት ምክንያት አንዱ-የዋዴ ጥሪ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ታምባዱድ በተባለዉ ግዛት በተደረገ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ደጋፊዎች ተጋጭተዉ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።ግጭት ግድያዉ፣ ሠላማዊቱ ሐገር እንደነበረች ያለመቀጥሏዋ፣- ምልክት ሁለት እንበለዉ።

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ፀሐፊት ዕጩዎች የቴሌቪዥን ክርክር እንዲያደርጉ እየጠየቁ ነዉ።አራቱ «እሺ» ብለዋል።በስልጣን ላይ ያሉት ማኬይ ሳል ግን አልፈቀዱም።ሳልን ከሚፎካከሩት ዕቹዎች በሳል ልምድ ያላቸዉ ኢድሪሳ ሴክ ናቸዉ።59ኝ ዓመታቸዉ ነዉ።ድሮ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።ከተመረጡ በ45ቱም የሴኔጋል አዉራጃዎች አንዳድ ዘመናይ ሆስፒታልና ዩኒቨርስቲ ለመገንባት ቃል ገብተዋል።

ከዚሕ ቀደም ትልቁን ስልጣን ለመያዝ ሁለቴ ሞክረዉ አልተሳካላቸዉም።ተስፋ አልቆረጡም።ጎላ፣ደመቅ እያሉ የመጡት ግን የ44ት ዓመቱ የተቃዋሚዎች ዕጩ ዑስማኔ ሶንኮ ናቸዉ።ከተመረጡ እስካሁን የተደረጉ የጋስና የማዕድን ስምምነቶችን በሙሉ ለመከለስ ቃል ገብተዋል።

አንጋፋዉ ማዴኬ ንያንግ ናቸዉ።65 ዓመታቸዉ ነዉ።ጠበቃ ናቸዉ።የፍትሕ ስርዓቱን ዳግም ለማዋቀር ቃል ገብተዋል።ከንያንግ በሁለት ዓመት የሚያንሱት ኢሳ ሳል አደገኛ ያሏቸዉን መንደሮች እና አሮጌ የአሳ ማሸጊያ ፋብሪካዎችን ለማፅዳት ቃል ገብተዋል።ዋቲ ተብሎ የሚጠራዉ ጥናት ተቋም ኃላፊ ዶክተር ጊለስ ያቢ የዕጩዎቹ የምረጫ ዘመቻ ቃልን «ጥሩ» ይሉታል።በአፍሪቃ ያልተለመደ።
                                      
«እንደሚመስለኝ ይሕ፣ መራጩ ሕዝብ አንዱ ከሌላዉ ለይቶ እንዲያዉቅ ይረዳዋል።በሁሉም የፖለቲካ መርሐ-ግብር ዉስጥ የፍትሕ ስርዓቱን የሚለከቱ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል። ስለ እስር ቤቶች ግንባታ፤ እስረኞች ከእስር ቤት ሲወጡ ከሕብረተሰቡ የሚቀየጡበት መርሐ-ግብር፣ሌላዉ ቀርቶ አካል ጉዳተኞችን ለሚቀጥሩ ኩባንዮች ስለሚደረግ ድጋፍ የሚዘረዝር መርሐ ግብር ሁሉ አለ።ወጥ መርሐ ግብር ለማቅረብ ሙከራ ተደርጓል።»
የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር አሌይ ንጎዩሌ ንዳዬ ምርጫዉ ነፃና ፍትሐዊ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል።ድምፅ ማጭበርበር አይቻልም ባይ ናቸዉ-ሚንስትሩ።የዳካሩ ነዋሪ ግን የመራጭነት መታወቂያ እንኳ እንዲሰጠን ከጠየቅን ሁለት ዓመታችን ይላሉ።«የመራጭነት መታወቂያ እንዲሰጠን ካመለከትን አንዳዶቻችን 2 ዓመታችን ነዉ።እስካሁን አልተሰጠንም።» አስመራጮቹ እንዳሉት የምርጫዉን ሒደት ከአዉሮጳ ሕብረትና ከካናዳ የተወከሉ 100 ታዛቢዎች ይከታተሉታል።

Senegal Wahl | Wahlkampf von Ousmane Sonko in Pikine, Unterstützer
ምስል Reuters/Z. Bensemra

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ

እሸቴ በቀለ