1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ ውሳኔ፤ የጠ/ሚሩ ጉብኝት፤ አዲሱ ፓርቲ

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ሰኔ 8 2010

ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መስማማቷን ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/2zeLL
EPRDF Logo

የኢህአዴግ ውሳኔና የህወሓት መግለጫ እና ጠ/ሚሩ

ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መስማማቷን ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ይህ ስምምነት የሁለቱን ሃገራት ግኑኝነት የሚያሻሻልና ሰላምን የሚያወርድ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ዉሳኔ የተደሰቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በርካቶች ቢሆኑም ጥቂት የማይባሉም ተቃዉሟቸዉን ማሰማት ቀጥለዋል።

ኤፍሬም ተክሌ ኢህአዴግን ውሳኔ አስመልክቶ በፌስቡክ ገፁ ላይ «መቼም ሁለቱ ሐገሮች ለምን እንደተዋጉ፣ ውግያውንም ሲመሩ የነበሩ ግለሰቦች ጭምር አንድ አይነት ነገር ሲናገሩ ሰምቼ አላውቅም» ሲል ፅሁፉን ይጀምራል። ያኔ ልጅ እንደነበረ በመጠቆምም ትዉስታዉን በመቀጠል እንዲህ አጋርቷል፤ «ባልገባን ምክንያት በልጅነታችን አብሮ አደጎቻችን ካደጉበትና በብቸኝንት ከሚያቋት ሐገር ሲባረሩ ትዝ ይለኛል። ያደኩበት ሰፈር የድሐ ሰፈር እንደመሆኑ የሰፈሬ ልጆች ወደ ጦርነት በመሔድ አልቀዋል። ዛሬ ላይ በልጆቻቸው ትዝታ የሚቆዝሙ ወላጆች የትየለሌ ናቸው። የደነ-ደነ ልብ በማናቸውም ነገር ይደራደራል። ያኔ የሆነውም ይሔ ነው። የደነ-ደነ ልብ በብዙ ደሐ ነብስ ተደራድሮል»። የኢትዮጵያ መንግሥት ለቀረበዉ የሰላምና የእርቅ ጥያቄ ኤርትራም አወንታዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ተስፋ እንደምያደርግም ኤፍሬም በአስተያየቱ ገልፀዋል።

ቦንሳ ኡ እራና የተባሉ ደግሞ የኢህአዴግ ውሳኔ ጥሩ ቢሆንም ትልቅ ተቃውሞ ሊገጥመዉ እንደሚችል በፌስቡክ አሳስቧል። የቦንሳን ማሳሰቢያ ተመልክተው በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ዉሳኔዉን በተመለከተ የታየውን ተቃዉሞ ልብ ይሏል። ዳንኤል ብራሃኔ ሰኞ እለት በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረዉ ጥቆማ በትግራይ ክልል የባድሜና የኢሮብ ነዋሪዎች ዉሳኔዉን በተመለከተ ተቃዉሞ እያደረጉ መሆናቸዉን ገልጿል። በትናንትናዉ ዕለትም በአዲግራት ተመሳሳይ ተቃዉም እንደተደረገ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ተቃዉሞዉ በዚህ አልተገታም። የኢህአዴግ መሥራች እና አባል የሆነዉ ህወሓት ሰሞኑን ያካሄደውን አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ያወጣዉ መግለጫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ሞቃ ያለ ዉይይት ቀስቅሷል። የህወሓት ማዕከላዊ ኮምቴ የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰደዉን ዉሳኔ እንደሚደግፍ ይገልጻል። ይሁን እንጅ ውሳኔዉ ወደ ኢህአዴግ ምክር ቤት ሳይቀርብ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያዩበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉን አንደ ጉድለት ጠቅሷል።

ተስፋኪሮስ ሳህለ በፌስቡክ ገፁ ላይ «የኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ግን ምንድን ነው ያስቸኮለው እና ኣቋራጭ መንገድ ሊመርጥ ያስቻለው? ኢህኣዴግ ከራሱ እና ከማህበራዊ መሰረቱ በላይ የሆነ የኢህኣዴግ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ኣሰራሮች የማያውቅ (ወይም ግድ የማይሰጠው) ኃይል ይኖር ይሆን?» ስል ጠይቀዋል። በመዘርዘርም ኢህኣዴግ አንድ «ስብሰባው ሳይጠናቀቅ የመግለጫ ናዳ ኣወረደብን»፣ ሁለተኛ «የኢህኣዴግ ምክር ቤት ተወያይቶ ሳያፀድቀው የድርጅቱ/የግንባሩ ውሳኔ ሆነ» ሦስተኛ «መንግስት ሳይወያይበት የመንግስት ፖሊሲ ሆነ» ብሏል። መሃመድ አደሞ መግለጫዉን «ግራ የተጋባ እና ተስፋ ቢስ» ስል በፌስቡክ ገፁ ላይ ተችቷል። ምክንያቱንም ሲያስቀምጥ «በኢህኣዴግ ስራ ኣስፈፃሚ ኮሚቴ ዉስጥ ያሉት የህወሓት አባላት አገሪቱ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግኑኝነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ባለፈዉ ሳምንት ድምጻቸዉን ሰጥተዋል። ይሄን ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ ተቃዉሞዉን አሰማ። አሁን ህወሓት ይህንን እድል በመጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይን ለማዳከም እየሞከረ ነው፤»የሚል አስተያየቱን አስፍረዋል።

ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ የመወያያ ርዕስ የሆነዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉብኝታቸዉ ወቅት በአማርኛ ቋንቋ ንግግር ማድረጋቸዉ አንዱ መወያያ ነበር። ኢትዮጵያን ወክለው በዉጭ አገር ያሉት ባለስልጣናት ንግግር ሲያደርጉ በደንብ በማይችሉት እንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ የሙጥኝ ብለዉ ነዉ፤ ስለዚህ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ በአማርኛ ንግግር ማድረጋቸዉን «ትልቅ ነገር ነዉ» ሲል አህመድ ጊሼ በፌስቡክ ገፁ ጠቅሷል። ዲ ጀ ፋት ሱ ደግሞ ይህንኑ አስመልክቶ በፌስቡክ ገፁ ላይ፤ «ስሜታዊ በሉኝ፤ የፈለጋችሁትን በሉ፤ ግን ዶክተር ዐብይ ኢትዮጵያን እንዲያድናት ከእግዚአብሔር የተላከ ነዉ። ንግግሩን ባየሁት ግዜ እንባ በእንባ ሆንኩ» ብሏል።

ቡሎ ኢራና በበኩሉ ጠ/ም በአማርኛ ንግግር ማድረጋቸዉ ብዙ ሰዎችን እንደተደሰቱ እና «ከምን ግዜም በላይ አርበኛ» በማለት እንደጠሯቸው መታዘቡን ገልፀዋል። ቡሎ ይህ ጥሩ ነዉ ካለ በኋላ ተመሳሳይ ሰዎች ጠ/ም በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ንግግር ሲያደርጉ ሕገ-መንግስቱን ጥሰዋል በማለት  ሲከሱ ነበር በማለት ይህም ያልተለመደ ነዉ ሲል አስተያየቱን ደምድሟል። ሽመልስ ስለሺ በበኩሉ «ሀገሪቱ በብሄር ግጭት ናላዋ ዞሮ መግባባት ጠፍቶ እያለ፤ ጉጂ ኦሮሞና ጌዴኦ በየቀኑ እየተጨፋጨፉ፤ ዐብይ በአማርኛ ግብፅ ላይ ንግግር አደረገ ብለን እንጨፍር ሲሉህ ነውኮ ላጥ ማለት ያለብህ!» የሚል አስተያየቱን በፌስቡክ አስነብቧል።

Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ የግብፅ ጉብኝታቸዉን ካጠናቀቁ በኋላም እዚያ በተለያዩ ምክንያቶች እስር ቤት ዉስጥ የነበሩትን 32 ዜጎች ከእስር አስፈትተው አብረው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸዉ ተነግሯል። ይህንን በተመለከተ የጠቅላይ ምስንስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ፊፁም አረጋ  የተፈቱት ሰዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ርምጃ በጣም እንደተደሰቱና ስሜታቸዉን ለመግለፅም ቃላት እንዳጠራቸዉ በትዊተር ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ በትጥቅ ትግል ተሰልፈው የነበሩት ቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/ ኮማንደር የሆኑት ኮሎኔል አበበ ገረሱ እና የቀድሞ የኦነግ የፖለቲካ አመራር አቶ ዮናታን ዱቢሳ ኤርትራ የሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያቸውን በመተዉ በጠ/ምሩ ይቅር ባይነት ወደ አገር መመለሳቸዉንም አቶ ፊፁም በትዊተር ገፃቸዉ አመልክተዋል።

ድባቤ ድጋፌ በትዊትር ዶክተር ዐብይ ትልቅ የመሪነት ብቃት እንዳላቸዉ ፤ ሁሉም መሪዎች ይህን አረአያ መከተል አለባቸዉ ብላለች። ሞሃመድ ኦላድ በበኩሉ በጠ/ምሩ ርምጃ መደሰቱን ከገለፀ በኋል አሁንም ግን በኢትዮጵያ ዉስጥ በእስር የሚማቅቁ እንዲፈቱ አሳስበዋል።

Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

ሌላኛው የሰሞኑ መወያያ ርዕስ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ላይ አዲስ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ መቋቋሙ ነዉ። የሺወርቅ ጋቤሻት አማራ፤ በፌስቡክ ይህ አዲሱ ፓርቲ «አንድ አማራ ለሁሉም አማራ! ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!» በሚል አላማ መቋቋሙ እንዳስደሰታት ገልጻለች። ሞሃመድ አብደላ ደግሞ ፓርቲዉ ብሔር ተኮር ሆኖ መቋቋሙን በበጎ እመለከታለሁ ካለ በኋላ፤ ግን ደግሞ የፖለቲካ ፕሮግራማቸዉንና በብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ላይ ያላቸዉን አቋም ለማወቅ እንደሚፈልግ ገልጿል። ቄሮ ኦሮሚያ በበኩሉ፤ በፌስቡክ አዲሱ ፓርቲ የተደበቀ እና ግልጽ የሆነ አካሄድ አለዉ ይላል፤ «ግልፁ  ክልሉን አሁን እያስተዳደረ ያለዉን የአማራ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለማዳከም ነዉ፤ ድብቁ ግን አሁን ያለዉ የፖለቲካ ስልጣን ጉዳይ ስላሳሰባቸዉ ነዉ» በማለት አስተያየቱን አስፍሯል። አሉላ ሶሎሞን «ለኢትዮጵያ ቀጠዩ ነገር ምንድ ነዉ?» ስል ይጠይቃል። አዲስ የተቋቋመው የአማራ ፓርቲ ሃሳብም አሁን ያለዉን የፌዴራል ስረዓትና ሕገ-መንግስቱን ለማፍረስ ነዉ» ይላል። ደመላሽ ወንድም በበኩሉ «አዲስ የተቋቋመው ፓርቲ ለአማራ እታገላለሁ ማለቱን የህወሓት ሰዎች ማጣጣል ጀምረዋል።» ሲል በፌስኩብ ላይ አስተያየቱን አስነብቧል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ